የፖፕ ሙዚቃው ኮከብ፤ ጆርጅ ማይክል

Wednesday, 28 December 2016 13:57

 

በበርካቶች ዘንድ የፖፕ ሙዚቃ ኮከብ እንደሆነ የሚነገርለት እንግሊዛዊው ጆርጅ ማይክል በተወለደ በ53 ዓመቱ እሁድ ሌሊት (ለሰኞ አጥቢያ) በመኖሪያ ቤቱ ባጋጠመው ድንገተኛ የልብ ድካም ህይወቱ ማለፉ ተሰምቷል። በተስረቅራቂና ጆሮ ገብ ድምፁ ተወዳጅ የሆነው ይህ አርቲስት አቀንቃኝ ብቻ ሳይሆን የሙዚቃ ደራሲና ፕሮዲዩሰርም እንደነበር ስራዎቹ ይናገራሉ።

 

በ1980ዎቹ የሙዚቃውን ዓለም በይፋ የተቀላቀለው ጆርጅ ማይክል፤ ስኬትን ያገኘበትና ከዋም (WHAM) ባንድ ጋር ሰርቶ ለህዝብ ያቀረበው የመጀመሪያ ተወዳጅ ስራው “ፓስድ አዌይ ፒስፉሊ” (Passed away peacefully) ሲሆን፤ ይህም ስራው በወቅቱ በእጅጉ ተወዳጅና ከአድናቂዎቹም ጋር የታወቀበት እንደሆነ ይነገራል። የአርቲስቱን ዜና እረፍት የተናገረው ቢቢሲ የቀድሞው የዋም ባንድ ጓደኛውን አንድሬው ዲግሌይ እና የሰር ኢልተን ጆንን የትዊተር ገጾች ዋቢ አድርጐ የሐዘን ስሜቶቻቸውን አስነብቧል። የቀድሞው ጓደኛው “ጆርጅ ማይክልን በሞት በመነጠቃችን ልቤ ተሰብሯል” ያለ ሲሆን፤ ሰር ኢልተን ጆን በበኩሉ፤ “በጥልቅ ድንጋጤ ውስጥ ነኝ። ተወዳጁን ጓደኛዬን ነው ያጣሁት፣ ደግ፣ ግልፅና ብሩህ አዕምሮ የነበረው አርቲስት ነበር። ለቤተሰቦቹና ለአድናቂዎቹም መፅናናትን እመኛለሁ” ብሏል።

 

ይህ አርቲስት በተለይ ለኛ (ለኢትዮጵያውያን) የክፉ ቀን ደራሻችን ነው። በ1977 ዓ.ም ተከስቶ የበረውን ድርቅ ተከትሎ፤ በርካታ የዓለማችን አርቲስቶች በተሳተፉበት “Do they know it’s Christmas?” በተሠኘውና ለገቢ ማሰባሰቢያነት በተሰናዳው የሙዚቃ ድግስ (ኮንሰርት) ላይ በወጣትነቱ ስራውን ማቅረብ የቻለ ሰው ነበር።

 

አብረውት በማኔጀርነት የሚሰሩት ሚስተር ማይክል ሊፕማን የድንገተኛ አሟሟቱ ምክንያት፣ የልብ ድካም እንደሆነ ቢናገሩም፤ በሐዘን ላይ የወደቁት ቤተሰቦቹ ግን ስለአሟሟቱ መንስኤ ምንም አይነት አስተያየት ከመስጠት መቆጠባቸውን የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ዘግበዋል።

ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ በቆየበት የሙዚቃ ዓለም ከዘጠኝ በላይ አልበሞችን ለአድማጮቹ አቅርቧል። ከስራዎቹ መካከልም በ1984 (እ.ኤ.አ.) “ኬርለስ ዊስፐር” (Careless Whisper) ለጆርጅ ማይክል የመጀመሪያው በሶል ስልት የተቀነቀነና ከዋም የባንድ ቡድን አባላት ጋር የሰራው ሙዚቃ ነው። በዚህም ስራው በሙዚቃው ዓለም ጥንካሬውንና ብስለቱን እንዳሳየበት የሙዚቃ ሃያሲያን ይስማሙበታል። በተለይ ይህ “ኬርለስ ዊስፐር” የተፃፈው በ17 ዓመቱ እንደነበር ይታወቃል። በ1986 (እ.ኤ.አ.) ደግሞ በአልበሙ ሽፋን ላይ እንደገለፀው ላለፉት ምርጥ ትዝታዎች መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ሰርቼዋለሁ ሲል፣ “ኤ.ዲፍረንት ኮርነር” (A different Corner) ለአድማጭ አደረሰ። ስለሁለተኛ ስራው ሲናገርም፣ “ይህ በህይወቴ ውስጥ በትክክል የወቅቱን ስሜቴን የገለፅኩበት ስራ ነው። በጥቂቱም ቢሆን የህይወቴን ውጣ ውረድ በዚህ ሙዚቃ በኩል ገልጫለሁ” ይላል።

 

በበርካቶች ዘንድ ተወዳጅና በተመሳሳይም አወዛጋቢነት የታየበት ሦስተኛ አልበሙ በ1987 (እ.ኤ.አ.) “አይ ዋንት ዩር ሴክስ” (I want your sex) በሚል መጠሪያ ወጣ። ምንም እንኳን በሚዲያው ዓለም በቢቢሲ ለበርካታ ጊዜያት ተደማጭ ቢሆንም፤ የኤም ቲቪ ሰዎች ግን በአርትኦት ካልሆነ በስተቀር ለአድማጭ ተመልካቹ ለማድረስ ፈተና ሆኖባቸው ነበር። በመቀጠል በ1990 (እ.ኤ.አ.) የወጣው “ፕሬይንግ ፎር ታይም” (Praying for time) ይገኛል። ይህ ዘፈኑ በገንዘብና ሃይማኖት መካከል ስለሚፈጠር የሞራል ፈተና የሚያትት አነጋጋሪ ስራው ነበር። ከእነዚህ አነጋጋሪ ስራዎቹ በተጨማሪ በአልበም ደረጃ የሚጠቀሱት Older, Patience, Faith, Song from Last Century, Listen without prejudice እና ሌሎችም ይገኙበታል።

 

ከ35 ዓመታት በላይ በሙዚቃው ዓለም ያሳለፈው፤ ጆርጅ ማይክል 100 ሚሊየን ቅጂዎችን በመሸጥም ይታወቃል። የመጨረሻ አልበሙን በ2014 “ሲምፎኒካ” (Symphonica) በሚል መጠሪያ መልቀቁ ይታወሳል። እሁድ ሌሊት ኦክስፎርድ ሳይድ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ህልፈተ ህይወቱ የተሰማው አርቲስቱ፤ በበርካታ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ፖለቲከኞች፣ የሙዚቃ ባለሙያዎችና አድናቂዎች ዘንድ ድንጋጤን ፈጥሯል።

 

አስቀድመው ወዳጆቹ ስር ኤልተን ጆን እና የቀድሞ ባንድ ጓደኛው አንድሬው ሪዲግሊይን ጨምሮ በርካቶች የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን በትዊተር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል። ታዋቂዋ ድምፃዊት ማዶና በትዊተር ገጿ ላይ “ሌላ ታላቅ አርቲስት አጣን” ብላለች። ታዋቂዋ የጊታር ተጫዋች ብሬያን ማይ በበኩሏ፤ “የጆርጅ ማይክል ሞት ከአስደንጋጭ አጋጣሚም በላይ ነው” ስትል ተደምጣለች። የኤ.ቢ.ሲው መሪ ድምፃዊና የሙዚቃ ደራሲው ማርቲን ፍሬይ፤ “የጆርጅ ማይክል ሞት ከባድ ውድመት ነው” ሲል በትዊተር ገፁ ላይ ገልጿል።

 

ገና በትምህርት ቤት ሳለ ወደሙዚቃው ዓለም የተሳበው ጆርጅ ማይክል፤ ከጓደኛው አንድሬው ሪድጌሊይ በፖፕ ስልት በሚታወቀው ዋም ባንድ ውስጥ ሰርቷል። ከዚያም በ1986 (እ.ኤ.አ.) ተገንጥሎ በመውጣት ከሰር ኤልተን ጆን፣ ከአሬታ ፍራንክሊን እና ከኩዊን ጋር በተለይ በ“ሶሎ” ስልት መታወቅ ችሏል። አሁን ላይ በልብ ድካም ህይወቱ እንዳለፈ ይነገር እንጂ፤ በ2011 (እ.ኤ.አ.) በሳምባ ምች በሽታ ሆስፒታል ገብቶ መውጣቱንም መረጃዎች ይጠቁማሉ። በ2013 ደግሞ ከመዟዟሪያ ተሽከርካሪው ላይ ወድቆ የጭንቅላት ጉዳት ስላጋጠመው ሆስፒታል ገብቶ ነበር። ከዚህ ሁሉ ምስቅልቅል ህይወቱ ጋር የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን በተመለከተ አጥብቆ ተከራካሪነቱ ከአወዛጋቢነቱ ባለፈ በአፈንጋጭ ባህሪው ምክንያት በበርካቶች ዘንድ የሚተችም አይነት ሰው ነበር።

 

ጆርጅ ማይክል የዘር ግንዳቸው ከግሪክ ከሆኑት ቤተሰቦቹ በለንደን ተወልዶ ያደገ ሲሆን፤ በእነዚህ ሦስት አስርት ዓመታት ውስጥም አምስት የስቱዲዮ አልበሞችን፣ ሁለት የጋራ አልበሞችን፣ 40 ነጠላ ስራዎችን፣ 16 የሙዚቃ ቪዲዮዎችን፣ 4 ቪዲዮ አልበሞችን በመስራት ይታወቃል። በእነዚህ ስራዎቹም ታላላቅ ከበሬታን ያገኘባቸውን እውቅናና ሽልማቶች አግኝቷል።

 

በዕጩነት ቀርቦባቸው ከተሸለመባቸው ስራዎቹ መካከል በተለያዩ ጊዜያት ሽልማቶችን አግኝቷል። ለምሳሌም በአሜካን ሚውዚክ አዋርድ በአምስቱ ዘርፎች ታጭቶ፤ በሦስቱ አሸናፊ ሆኗል። በግራሚ አዋርድ በስምንት ዘርፎች ታጭቶ፤ በሁለት አሸናፊ ሆኗል። በብሪት አዋርድ በአምስት ዘርፎች ታጭቶ በሦስቱ አሸንፏል። በጆን አዋርድ ሦስት ጊዜ በዕጩነት ቀርቧል። በኤምቲቪ አውሮፓ ሚውዚክ በአራት ዘርፎች በዕጩነት ቀርቦ በአንዱ አሸናፊ ሆኗል። በኤም ቲቪ ቪዲዮ አዋርድ ላይ በአስራ አምስት ዘርፎች በዕጩነት ቀርቦ በአራቱ አሸናፊ መሆን ችሏል። ለአይቮር ኖቬሎ አዋርድ በአራት ዘርፎች ታጭቶ በአራቱም አሸናፊ መሆን የቻለ ሲሆን፤ በጂ.ኤል.ኤ.ኤ.ዲ. ሚዲያ አዋርድ ደግሞ የዕጩነት ማዕረጉ አልቀረበትም።

 

በበርካቶች ልብ ውስጥ በሙዚቃ ስራዎቹና በሚያነሳቸው ሃሳቦቹ ቦታን ያገኘው የሶል ሙዚቃ ኮከቡ ጆርጅ ማይክል በ1963 ተወልዶ በ2016 ማብቂያ (በገና ሰሞን) ላይ የህይወቱ ፍፃሜ ሆኗል። እናም ሁሌም የፈረንጆቹ ገና በመጣ ቁጥር የሚደመጥለት “The Last Christmas” ሙዚቃው ዘንድሮ በተለየ መልኩ በብዙዎች ይደመጥ ዘንድ ጊዜው ሆኗል። በበርካቶች ልብ ውስጥ የነገሰው ጆርጅ ማይክል እንዲህ ባለ መልኩ በድንገት ተሰናብቶናል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
14579 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 258 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us