“በሥዕል ስራዎቼ የሴትን ጥንካሬ ማጉላት እፈልጋለሁ”

Wednesday, 04 January 2017 14:22

 

 

                                                                                                      ሰዓሊ ሜሮን ኤርሚያስ    

 

“በሥዕል ስራዎቼ ውስጥ የሴትን ልጅ ብርታት ማሳየት በጣም ያስደስተኛል” ትላለች የዛሬዋ የመዝናኛ አምድ እንግዳችን ሰዓሊ ሜሮን ኤርሚያስ። አዲስ አበባ ተወልዳ ያደገችው ይህቺ ሰዓሊ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሥነ-ጥበባት ትምህርት ቤት፤ “በፋይን አርት ኤንድ ዲዛይን” በማታው መርሃ -ግብር በመማር የመጀመሪያ ዲግሪዋን 1997 ዓ.ም አግኝታለች።

የቅርቤ ነው በምትለው ወንድሟ የስዕል ተፅዕኖ ስር የወደቀችው ገና በልጅነቷ የምትናገረው ሰዓሊ ሜሮን፤ በልጅነቷ የወንድሟ የአማረ ኤርሚያስን የስዕል ስራዎች አዘውትራ በመመልከት፤ ከልቧ መመሰጥ ስለመጀመሯ ታስታውሳለች። “ወንድሜ በስዕል ስራው ቢቀጥል ትልቅ ደረጃ መድረስ የሚችል ነበር። በሰራቸውም ስራዎች እስከ ሃያ ሁለት የሚደርሱ የምስክር ወረቀቶችን ማግኘት የቻለ ሰው ነው። ነገር ግን የስዕል አቅሙን በደንብ መጠቀም ሳይችል ዲቪ ደርሶት ወደአሜሪካ በመሄድ ኑሮውን እዛ አድርጓል” ስትል ስለወንድሟ ታብራራለች።

ሙሉ ትኩረቷን ወደስዕል ስራዋ በማድረግ መስራት መጀመሯን ተከትሎ በሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤት የነበራትን ቆይታ አጠናቃ በርካታ አውደ-ርዕይዎችን በተለያዩ ቦታዎች ማሳየት መጀመሯንም ትገልጻለች። ነገር ግን የእርሷን ብርቱ አቅም ከእሷ በላይ መመስከር የቻለው መምህሯ ሰዓሊ ዮሴፍ ሃ/ማርያም እንደሆነ ታስታውሳለች። “የሰራውን ስዕል የተመለከተው ሰዓሊ ዮሴፍ ከጠበቀው በላይ እንደሆንኩበት ነግሮኛል” ትላለች። የስራዋን ጥሩነትና በሳልነት ከመምህሯ ምስክርነት ያገኘችው ሰዓሊ ሜሮን፤ “አይዞሽ” ባዮቼ በዝተው እዚህ ደርሻለሁ ትላለች። ከባለሙያዎች መካከል የአባቷ ወዳጅ እንደነበረ የምትገልፀው በሰዓሊና መምህሩ እሸቱ ጥሩነህ ብርታት እንደሆናት ትናገራለች። ይህም ሆኖ የቀሩኝን ነገሮች የሞሉልኝም ባለሙያዎች በመሆናቸው ምስጋና ይገባቸዋልም ባይ ነች።

በተለያዩ ስፍራዎች (በሀገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ) የስዕል አውደ-ርዕይዎችን ስለማሳየቷ የምታስታውሰው ሰዓሊ ሜሮን፤ ከተመልካቹ የምታገኘው አስተያየት የበለጠ የሚያተጋትም እንደሆነ ታስረዳለች። በሸራተን አዲስ፣ በሂልተን ሆቴል እና በተለያዩ ቦታዎች በግልና በጋራ ስራዎቿን ለተመልካች አድርሳለች። “እውነቱን ለመናገር ኢትዮጵያ ውስጥ ስዕል አዋቂ ትንሽ ቢሆንም ስዕልን አድናቂ ግን ብዙ ነው ብዬ አምናለሁ” የምትለው ሜሮን፤ እነዚህ ተመልካቾች የሚሰጡት አስተያየት ብርታት እንደሚሆናትም ትናገራለች።

“በስራዎቼ ውስጥ ብዙውን ጊዜ ለማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት የሴትን ልጅ ጥንካሬ የሚያሳይ ነው። ምናልባት እኔም ሴት ስለሆንኩ ሊሆን ይችላል። በተጎሳቆለ ህይወት ውስጥ ኖረው እንኳን ጎልተው መታየት የሚችሉ ሴቶችን መሳል ደስ ይሉኛል” የምትለው ሰዓሊ ሜሮን፤ አንዲት ሴት መንገድ እየጠረገች ብስላት ራሱ አንዳች የምትጎላበትን ነገር እፈልጋለሁ፤ ምክንያቱም ያ ቦታና ሁኔታ በትክክል ሴቷን የሚገልጻት አይደለም፤ ምናልባት ከጀርባዋ ያሉ ብሩህ ቤተሰቦቿን ለመሸፈን ያደረገችው ሊሆን ይችላል የሚል እምነት እንዳላት ትናገራለች።

ለአንድ ሰዓሊ ቀለማት፣ መስመሮችና ቅርጾች ብዙ ትርጉም እንዳላቸው የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ። ለመሆኑ ሰዓሊ ሜሮን በስራዎቿ ውስጥ በአጋጣሚም ይሁን አስባና ፈቅዳ በተደጋጋሚ የምትጠቀመው የቀለም ዓይነት ምንድነው? “ እኔ ብዙ ጊዜ ለአይን የማይከብድና ደማቅ የሆነ ቀለምን እመርጣለሁ። መስመሮችና ቅርፆችም እንዲሁ ለስራዬ ትርጉም በሚሰጥ ሁኔታ የምጠቀምባቸው የጥበቡ ማሳያዎች ናቸው” ትላለች። ደማቅና ብሩህ ቀለምን እወዳለሁ የምትለው ሰዓሊ ሜሮን፤ እንደባህሪዬ ደስ የሚለኝ ቀለም ነው የምትለው ብርቱካናማን ነው። እንደሰዓሊ ሜሮን አገላለፅ ብርቱካናማ ቀለም ሰውን የሚስብና ሞቅ ያለ የደስታ ስሜት የሚፈጥር ነው ባይ ናት። ይህም በመሆኑ በስዕል ስራዎቿ ውስጥ በብዛት ደስታ፣ ተስፋና ህይወት በስፋት ይንጸባረቃሉ።

በተረጋጋ መንፈስ ውስጥ ስትሆን የመሳል ስሜቱ እንደሚመጣላት የምትናገረው ሜሮን፤ ትንሽም እንኳን የድብርት ስሜት ከተሰማት ስቱዲዮ ከመግባት ፊልም ማየትን እንደምትመርጥ ትናገራለች። “አንድን ስዕል ለመሳል አካባቢዬ የግድ ጭር ማለት የለባትም” የምትለው ሰዓሊዋ፤ የምስልበት ሃሳብ ውስጤ ካለ ሰዎችም ተቀምጠው፤ ቡና እየተጠጣ ቢሆን መሳል እችላለሁ ባይ ናት። “የስቱዲዮ በር ዘግቼ ስዕል ስዬ አላውቅም። አሁን - አሁን ግን ልጆቼ ቀለም እንዳይነካኩብኝ በሚል ፍራቻ እዘጋለሁ እንጂ መዝጋትን ምርጫዬ አላደርግም” ትላለች። እናም አንድን ስዕል በመሳል መነሻ ምክንያት ስለሚሆኗት ነገሮች ስትገልጽ፣ “ትንሽ ነገር ይበቃኛል። በተለይ ደስ ሲለኝ መሳል ምርጫዬ ነው” የምትለው ሜሮን፤ ነገር ግን በክረምት መሳል በፍጹም እንደማትወድ ትናገራለች። ሞቅ ባለ ወቅትና ስሜት ላይ ከተገኘው ሁሌም ቢሆን መሳል እችላለሁ ባይ ነች።

በተለያዩ ሰዓሊያን ስራዎች ከመመሰጥ አልፋ እራሷን በሰዓሊነት ሙያ ውስጥ ያገኘችው ሜሮን ኤርሚያስ፤ ምናልባት ሰዓሊ ባትሆን ኖሮ ምን ትሰሪ ነበር? በሚል ላቀረብንላት ጥያቄ ስትመለስ በፈገግታ ተሞልታ ነበር። “በርግጠኝነት ጠበቃ እሆን ነበር ምክንያቱ ደግሞ ተማሪ እያለሁ ቦሌ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ክርክር እናደርግ ነበር፤ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ክፍለ ጊዜያት በምናደርገው ክርክር ብዙ ጊዜ አሸናፊ ነበርኩ” ስትል ከሰዓሊነቱ ብትቀር ወደህግ ባለሙያነት የሚወስዳት አቅም እንደነበራት ትናገራለች።

ከታላቅ ወንድሟ ባለፈ በስዕል ህይወቷ የምትሳብባቸውና የምታደንቃቸው ሰዓሊያንን በተመለከተ ሜሮን ስትናገር፤ “ለኔ እንደመጀመሪያ መጠራት ካለበት የማደንቃቸው እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ  ናቸው” ትላለች። ከእኚህ አንጋፋ የጥበብ ሰው ጋርም የስዕል አውደ-ርዕይ አዘጋጅታ እንደነበር በማስታወስ፤ መልካም ሰው እንደነበሩም ትመሰክራለች። ቀጥሎ በስዕል ስራዋ ውስጥ በጎ ተፅዕኖ ካሳረፉባት ሰዓሊያን መካከል መምህሯ ዮሴፍ ኃ/ማርያምን በመጥቀስ እንደምታደንቀውም ጭምር ትገልጻለች። ከሀገራችን ወጣ ብላ ደግሞ ከዓለም አቀፍ አርቲስቶች መካከል በግንባር ቀደምትነት የምትጠራው ሰው ሊዮናርዶ ዲያቪንቺን ነው” “ዲያቪንቺ በጣም ምርጥ-ምርጥ ስራዎችን ከመስራቱም ባሻገር በአለማችን ላይ በርካታ የፈጠራ ውጤቶችን ያበረከተ ሰው ስለሆነ በጣም አደንቀዋለሁ” ባይ ናት።   

በበርካቶች ዘንድ ታይቶ የተወደደላትን “የቅዱስ ያሬድ” ስዕል የኔ አብይ የፈጠራ ስራ (Masterpiece) ስራዬ ነው የምትለው ሰዓሊ ሜሮን፤ ይህን ስራ መቼም ደግሜ የምሰራው አይደለም ትላለች። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ውስጥ በመንፈሳዊ ዝማሬ አጀማመሩ በጉልህ የሚነሳው “ቅዱስ ያሬድ”፤ ከሰዓሊ ሜሮን ስራዎች ውስጥ በጉልህ የሚጠቀስ ነው። ይህ ስራዋ ከሀገር አልፎ በተለያዩ አገራት ባሳየቻቸው አውደ-ርዕይዎች ሁሉ አብሯት የቆየና ስለመሸጥም አስባው የማታውቀው ስራ እንደነበር ትናገራለች። “ስራውን የገዛችው ከኤ.ዊ.ብ መስራቾች አንዷ የሆነችው ወ/ሮ ናሁስናይ ግርማ በጣም ስወደደችው ወስዳዋለች። ስዕሉ በሸራተን አዲስ ሆቴል በተካሄደ ጨረታ ወደሌላ ሰው እጅ ገብቷል። ስራውን የሸጥኩት ብርን ፈልጌ አይደለም። ይልቅስ ቅዱስ ያሬድን ብዙ ሰው እንዲያውቀው ለማድረግ እኔ'ጋ ከማቆይ ይልቅ የወሰደው ሰው ጋር ሲቆይ ይበልጥ የመታወቅ እድልን ያገኛል፤ መነጋገሪያም ይሆናል ብዬ ስላመንኩ ነው” ትላለች። ይህንንም በማድረጓ ስለቅዱስ ያሬድ ብዙ መፃፉንና እንዲተዋወቅ መደረጉን እንደመልካም አጋጣሚ ትጠቅሳለች። “ቅዱስ ያሬድ” በተሰኘው የስዕል ስራ ውስጥ በተለይ የሚጠቀሱት ከበሮ በገናና ፅናፅን ጎልተው እንደሚታዩ ሰዓሊዋ ትገልጻለች።

ከሌሎች ዓለም ሰዓሊያን አንፃር ምን ይጎድለናል? ስንል ላቀረብንለት ጥያቄ፣ “የመጀመሪያውና ዋነኛው ነገር እኛ ሀገር የስዕል ስራዎችን የማሳያ ቦታ እጥረት አለ። ይህ ደግሞ ሰዓሊያን ስራዎቻቸውን በደንብ ሰርተው እንዳያሳዩ እንቅፋት ሆኗል። ይህ ከሄድኩባቸው ያደጉ አገሮች (ህንድ እና ሲውዘርላንድ) አንፃር ወደታች የምንጎተትበት ምክንያት ነው” የምትለው ሜሮን፤ ሁለተኛውና ሌላኛው ከሌሎች አገራት ጋር ስንነፃፀር ቢኖረን የሚያስብለው “በሄድኩባቸው አገሮች ለስዕሉና ለሰዓሊው የሚሰጠው ክብር ላቅ ያለ ነው” ትላለች። እኛ ሀገር ለፊልም እይታ የሚደረገውን ሰልፍ የምታስታውሰው ሜሮን፤ ሌሎች አገራት የስዕል አውደ-ርዕይዎችን ለማየትም እንደዛው ሰልፍ አለ ትለናለች። በአገራችን የቱንም ያህል በርካታ ተመልካች አለ ብንልም ስዕሎችን የመግዛት አቅሙ ግን የለም የምትለው ሜሮን፤ በውጪ ሀገር ግን የአርቲስቱን “ኦርጂናል” ስራ ቀርቶ የህትመቱንም ቢሆን ለመግዛት ሰው ያለው ተነሳሽነት እንደሚያስገርማት ትናገራለች። ይህም ለጥበቡ የምናሳየውን ክብር በልዩነት የሚያሳይ እንደሆነ ታሰምርበታለች።

ብዙ ጊዜዋን በስራ የምታሳልፈው ሰዓሊ ሜሮን፤ የመዝናኛ ጊዜ ካገኘች ፊልም ማየቱን እንደምትመርጥ ትናገራለች። “የሀገር ውስጥም ሆነ የውጪ ፊልሞችን ማየት ደስ ይለኛል። በተረፈ ግን ሙዚቃ መስማትንም እንደመዝናኛ መውሰድ እችላለሁ” ትላለች። “በህይወቴ በጣም እድለኛ ሴት ነኝ” የምትለው ሰዓሊ ሜሮን፤ ልጅ እያለች ቤተሰቦቿ በተለይም አባቷ በምታደርገው ነገር ሁሉ ያግዛት እንደነበር ታስታውሳለች። አሁን ላይ የሁለት ልጆች እናት የሆነችው ሜሮን፤ ባለቤቷ እና እናቷ ስራዎቿን በትጋት ትሰራ ዘንድ ድርሻቸው ከፍተኛ መሆኑን በመግለፅ ሁልጊዜም እንደምታመሰግናቸው ትናገራለች።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
14649 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 258 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us