የኢዮብ መኮንን አሻራዎች በ“እሮጣለሁ” አልበም

Wednesday, 11 January 2017 14:17

የፍቅር፣ የነፃነት፣ የእምነትና የሃሳብ ልዕልናን ማስተላለፊያ መሳሪያ  ነው፤ የሬጌ የሙዚቃ ስልት። .. . ይህንን ደግሞ ኢዮብ መኮንን በሚገባ እንደተረዳው ለማወቅ “እንደቃል” የተሰኘ የመጀመሪያ አልበሙን ማድመጥ ይበቃል። እርሱም ቢሆን በተደጋጋሚ ስለፍቅር፣ ተስፋ እና  ነፃነት ደጋግሞ በመናገርና በማቀንቀኑ ብዛት በበርካቶች ልብ ውስጥ በተለየ ስፍራ ነበረው።

እነሆ በሞት ከተለየን በሶስት ዓመቱ በተለያዩ የሙዚቃ ባሙያዎች (አቀናባሪዎች) ዘንድ ሲሰራቸው የነበሩ ስራዎቹን በአንድ ያጣመረ “እሮጣለሁ” የተሰኘ አልበሙን አገኘን። ኢዮብ መኮንን አሁንም በሬጌ ስልት ውስጥ በፍቅር፣ በእምነት፣ በፅናትና በተስፋ መካከል በዜማ ሲመላለስ እንሰማዋን። ይህ “እሮጣለሁ” የተሰኘ አልበሙ በውስጡ አስራ አራት ስራዎች ተካተውበታል። ከሙዚቃው ይልቅ ያነሳቸውን ሃሳቦች ተንተርሰን እስቲ ስራዎቹን በጥቂቱ ለመዳሰስ እንሞክር።

የአልበሙ መጠሪያ ሆኖ በአስራ አራተኛው “ትራክ” ላይ የሚገኘው “እሮጣለሁ” የተሰኘው ስራ ግጥምና ዜማው የዚህ ዜማ ደራሲ ኃይሉ አመርጋ ሲሆን፤ ግጥሙ ደግሞ የኤርሚያስ ታደሰ ነው። በዚህ ስራው ኢዮብ ስለራሱ ያዜመ ይመስላል። ህይወቱን በተቻለ መጠን ለዓላማ እንዳሮጣት ይተርክልናል።

የኔነቴን አሻራ በምድሪቷ ሳልጥል

በዕውቀቴ ሳልሰራ ለመኖር ሳልታገል

ለሞት ሙት ሆኜለት መቼ እቀመጣለሁ

እሮጣለሁ - ሮጣለሁ (2)

በስራዎቹ በፍቅር፣ በፅናት፣ በተስፋና በእምነት እንደሚሮጥና በህያው ስራዎቹ ዘመን ተሻጋሪ አሻራውን ማስቀረት የቻለ ባለተሰጥኦ መሆኑን መመስከር ይቻላል። እንዳገኘሁለት ማን በነገረው? . . . እስቲ ደግሞ የፍቅር ብርታትና ሃሳብ በሁለተኛው የኢዮብ መኮንን አልበም ውስጥ እንዴት እንደተገለፀ እንመልከት። ስለፍቅር ያዜማቸው ስራዎቹ በአንደኛ፣ በአራተኛ፣ በስምንተኛና አስራ አንደኛ “ትራኮች” ላይ በጉልህ ይደመጣሉ።

በሃሳብ ከቀዳሚ አልበሙ ስራ ጋር የሚቀራረበውና በሙዚቃ ስልቱም ለስላሳ የሬጌ ስልትን ማዕከል ያደረገው “ተውያልሽኝን” የተሰኘው ስራ ይጠቀሳል። ይህ ስራው ግጥም ካህኑ ሞገስ ሲሆን፤ ዜማው ደግሞ የሙሉቀን ዳዊት ነው። “መታዘዝ ከመስዋእት ይበልጣል” እንዲል ቃሉ ኢዮብም ስለወደዳት ልጅ ሲል ሌሎች ሲመክሩት ያልሰማውን ሁሉ ሲተው እንመለከታለን።

ተው ያልሽኝን ተውኩት - እታዘዝሻለሁ

ሌላም ካለ በይኝ - እተውልሻለሁ

አንቺ ካልወደድሺው ኧረ ሲቀር ይቅር

የማልተወው የለኝ - ካንድ አንቺ በስተቀር።

ስለፍቅር ሲል ዝቅ በማለቱ ምክንያት በሰዎች አፍ ስለመግባቱ የሚነግረን ደግሞ “ሰማኋቸው” በተሰኘ ስራው ነው። የዘፈኑ ዜማና ግጥም የተሰራው በምዕራፍ አሰፋ ነው። በዚህ ስራው ውስጥ ጥልቅ የፍቅር ፍልስፍናም እናገኛለን። ሰው ፍቅር ሳይኖረው ለሰዎች ዘንድ ከፍ ቢል ምን ዋጋ አለው ሲልም ይጠይቀናል።

ልሁን ሞኝ የምወደውን ካገኘው

ፍቅርን ያጣ ብልጥ እስቲ ደስታው ምንድነው?

ዝቅ ልበል ከግምታቸው በብዙ

ምን ጥቅም አለው ከፍታ ፍቅርን ካልያዙ።

በእውነት ልቡ በተሸነፈ ልቡ ያሰበው ስላለ

ከተመቸው ጋር አብሮ ከዋለ

እንዴት አፍቃሪ ልበቢስ ተባለ? (ሲል ይጠይቃል)

በአራተኛ “ትራክ” የተቀመጠው “የጋበዝኳቸው”  የሚለው ስራው፤ ግጥምና ዜማ የአለማየሁ ደመቀ ነው። በዚህ ስራ ውስጥ ክስተት ስለሆነበት ድንቅ ፍቅር ይተርካል። በርካቶች በልቡ ያለውን የፍቅር ግብዣ እንደታደሙ ቢጠብቅም፤ እየመጡ ከመሄድ ውቺ በምንም  መልኩ የፍቅር ግንኙነት ሳይሰምርለት የቀረው ይህ ሰው ድንገት ግን አንዲት ሴት ያገኛል፤ ፍቅርም ይሰምርለታል፤ እናም እንዲህ ይገልጻታል።

ከጥሪው መዝገብ ስምሽ ሳይሰፍር

በሌሎች ግብዣ አመጣሽ ፍቅር።

አክባሪ ያጣው ደጋሽ እልፍኜ

ያልታለምሽውን አንቺን አገኜ

ከምድር ይሁን ወይ ከሰማይ

ከየት መምጣትሽን ባይኔ ሳላይ

ድንገት ፊቴ ተከሰትሽ

አስደነቅሽኝ ልቤን ገዝተሽ

አሃሃሃ ሃይ ሎጋ - ካንቺ'ጋ (3)

እምነትና ፍቅር የማይፈፅሙት ተዓምር እንደሌለ የሚያወሳው ዜማ በቁጥር አስራ አንድ ላይ ይገኛል። የግጥምና የዜማ ደራሲው ኤርሚያስ ታደሰ ሲሆን ግጥሙን ኤርሚያስ ታደሰና ዳግማዊ አሊ ሰርተውታል። በእምነት ፍቅር ስለወደቀች ነፍስ እንደሚከተለው ያዜማል።

ዓይኔ መስሎ ፈሪ

ልቤ ነው ደፋሪ

ቅንጣት እምነት ይዞ

ፅልመትን ሰባሪ

አይበግረው ከቶ ውሃጥም ንዳዱ

ተስፋ መቁረጥ የለም

መውደድ ነው መንገዱ።

ኢዮብ መኮንን ከፍቅር ባሻገር ስለተስፋና ስለአንድነት፤ ስለይቅርታና ስለቻይነት በሚከተለው መንገድ አቀንቅኗል። የሰው ልጅ አሁን ካለበት ክፉ ቀን ይልቅ ያሳለፈውን ደግ ዘመን ቢያስታውስ ምንኛ ደስ እንደሚል የሚተርከው እንዲህ ሲል ነው።

ዛሬ አንዳችን ብንሆን በዳይ ጥፋተኛ

መልካማ ጣፋጭ ህይወት ቆይተናል እኛ

ከውብ ቀኖቻችን ብርሃን ከተሞሉ

ጭለማን አንምዘዝ ለጊዜያችን ሁሉ

ሰው አንድ ላይ ሲኖር በፍቅር በውዴታ

በሁሉም መስማማት የለበት ግዴታ

ባንድ መንታ መንገድ ምንጫችን ቢለያይ

ብዙ እንዳልተጓዝን ለምን እንተያይ።

ያለፈን ፍቅር ስለማደስ የሚያትተው “ተጠርቼ” ስራው ሶስተኛው “ትራክ” የካሙዙ ካሳ ግጥም ሲሆን ዜማ ደራሲዎቹ ልዑልና ኢዮብ ናቸው። እናም በዚህ ስራ ውስጥ “ስለይቅር” መባባል ያትታል። ይቅርታ በህይወት ውስጥ ሰላምን አምጪ እንደሆነም ይነግረናል።

­

ቅያሜያችን እጅግ በዝቶ ነበረ

በፅናት መካረሩ በረረ

ህይወት ነው ይቅርታ

ከሰጠነው ቦታ

ሰላማችን ይብዛ

በፍቅር ይገዛ።

ስለስደት የዘፈነበት “ወደ እናቴ ቤት እመለሳለሁ” ሲሆን፤ በግጥም ሃይሉ አበጋዝ በዜማ ደግሞ ኤርሚያስ ታደሰ ተሳትፈዋል። ከስደት መልስ ዞሮ - ዞሮ ወደናት ሀገር ስለመመለስ ያትታል። እናም እኛም አለን በተሳሳተ ተስፋ ተይዘን ነው የምንጓዘው ሲል ይሞግታል።

እንደው ሙሉ ሆኜ ተፈጥሬ

በቀቢፀ ተስፋ ታጥሬ

ያጣው የሌለኝ ደርሶ ቢመስለኝ

አወይ እግሬ (2)

ወስዶ አወጠኝ ካገሬ

ወደናቴ ቤት እመለሳለሁ

ከሞቀ እቅፏ ልኑር ብያለሁ።

ስለዓለም ሁኔታ በመደነቅ የሚነግረን፤ ለታላቅ ሰው ትንሽ ነገር ሲከብደው፤ ጋን በጠጠር ይደገፋልን የሚያስታውስ ስራው ደግሞ ቁጥር 7 ነው። ይህ ስራ “ማን ያውቃል” የሚል ሲሆን፤ ግጥምና ዜማው የሰራው ኤርሚያስ ታደሰ ነው። በዚህ ስራው ውስጥ መገረሙን የሚገልጸው እንዲህ ሲል ነው።

­­

ስንቱን ትልቅ ችግር ሲፈታ የኖረ

ከሱ አልፎ ለሌሎች ዘዴን የቀመረ

ቀላል ነገር ገጥሞት ሲከዳው ብላቱ

በታናሹ ምክር ካሳብ ከጭንቀቱ

ሲወጣ  ማየቱ (ኦ! ይገርማል!)

ሰነፉ ብርቱ ነው (ኦ! ይደንቃል!)

በሚያውቀው ሲገኝ (ኦ! ይገርማል!)

ካለ ቦታው ገብቶ (ኦ! ይደንቃል!)

አዋቂው ሲሞኝ (ኦ! ይገርማል!)

ይህም ብቻ አይደለም፤ እውነትን ስለመናገር ያለውን ድፍረት፣ ስለማስመሰል ከንቱነት፤ እራስን መሆን ስላለው ብርታት እና ስለውዳሴ ከንቱ በጆሮ ገብ ዜማዎቹ ተጫውቶልን አልፏል። በቀዳሚ አልበሙ በኦሮምኛ ስራው የምናውቀው ኢዮብ፤ በዚህ ስራው ደግሞ በቃሲም ሙህፀዲን ዜማ የተደረሰለትና ግጥሙን አብደላ ቃሲም የፃፈውን የሱማልኛ ዜማ በድንቅ ሁኔታ ተጫውቶታል። እናም የኢዮብ ከሞት ጋር ግብ - ግብ ውጤት ያለውና አሻራውን ለኛ የተወበት ነውና መቼም አንረሳውም!

ይምረጡ
(5 ሰዎች መርጠዋል)
15213 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 258 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us