የደፈረሰው “የዘመን አሻራ”

Wednesday, 18 January 2017 09:59

 

የመፅሐፉ ርዕስ  - “የዘመን አሻራ”

ደራሲው       - ፋንታዬ እሸቱ ወ/ሥላሴ

የመፅሐፉ አይነት - ልብ -ወለድ

የገጽ ብዛት     - 333

የታተመበት ጊዜ  - 2008 ዓ.ም

ዋጋ           - 90 ብር ከ95 ሳንቲም

 

ኢትዮጵያ ካሳለፈቻቸውና በታሪክም አሻራቸውን ጥለው ካለፉት የቅርብ ጊዜያቶች መካከል አንዱ የኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ተጠቃሽ ነው። ደራሲ ፋንታዬ እሸቱ ወ/ስላሴም ይህን የዘመናችንን ክስተት የልቦለድ ቅመሞችን ተጠቅሞ፤ የፈጠረ ገፀባህሪያትንና ታሪካቸውን እያስታከከ አንዳች አሻራ ሊያሳየን ይሞክራል።

“የዘመን አሻራ” መፅሐፍ ውስብስብ ታሪኮችን፣ በርካታ ገፀባህሪያትን፣ ልል ሴራዎችንና ጠባብ መቼትን ተጠቅሞ ዘመኑን ሊያሳየን ይሞክራል። በሁለቱ አገራት (ኢትዮጵያና ኤርትራ) የውስጥ ትርምስና የድህነት ፍትጊያ፤ ያልጠራ መጨረሻና ምክንያት አልባ ውጤቶችን ጭምር በ “የዘመን አሻራ” መፅሐፍ ውስጥ እናነባለን።

የ1990ዎቹን መጀመሪያ ተንተርሶ የሚተርከው ይህ መፅሐፍ፣ በሁለቱ ወንድማማች አገሮች መካከል የተጠላለፈውን የተንኮል ሴራ ልብ በሚያንጠለጥል መልኩ ያሳያል። ይህም በመሆኑ በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ኤርትራዊያን እንዴት እንደወጡና እነሱን ተከትሎ ጎራቸው በውል ያለየ የሻዕቢያ መልዕክተኞች ከተማን የማተራመስ (በተለይም የተመረጡ ባስልጣናትን በኤች.አይ.ቪ /ኤድስ ቫይረስ) በማጥቃት እና የቦምብ ፍንዳታ ጥቃት በመፈፀም በስውር የበቀል አጀንዳ ይዘው እናያቸዋለን። የሁለቱ አገራተ የድንበር ጦርነት አቅጣጫ ለማስቀየስ የተቀመጠው ይህ ሴራ እንዲህ የሚል ነው፤ “ጥሩ ዕቅድ ነው ባድመና ሽራሮ ላይ ሕዝብ ከማጨራረስ በአቋራጭ ጦርነቱን ለመጨረስ አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ለመግባት የሚያስችል ፕላን ነው ሌሊቱን ሲያነብ ነው ያደረው”  (ገፅ ÷118)

በመፅሐፍ ውስጥ ውስብስብ ታሪኮች ተገናኝተዋል። በጌቱና በፅዮን መካከል በተፈጠረው ፍቅር ላይ የሚያጋጥመው መሰናክል፤ በዘውዱና በሂሩት መካከል የተፈጠረው ጥላቻ፤ ለ10 ዓመታት ባሏን የምትጠብቀው ሲስተር አዳነችና በዶ/ር ሙሴ መካከል የተለያዩ ታሪኮች ተፈጥረዋል። በአንፃሩ ደግሞ የኤርትራውን ተልዕኮ ለሚሰፈርም መንታ ገፅ የተላበሰው ያዕቆብ፣ ዘረዕዝጊ፣ ሙሉ፣ ክብሮምና ጥበቃው ሄኖክ በአንድ በኩል ተሰልፈው ይፋለማሉ።

ፍፃሜውን በአንባቢ የምናብ አቅም መልስ እንዲያገኝ አድርጎ በእንጥልጥል የተወው ይህ ልቦለድ በርካታ ድፍርስርስ የታሪክ መንስኤ አልባ ውጤቶችን እንድናነብ አስገድዶናል። ይህን ዳሰሳ ለመፃፍ ከተነሳሁበት ዋነኛው ሃሳብ ሌሎች ፀሀፍትም እንዳይደግሟቸውና ልብ ሊባሉ የሚገባቸውን ሃሳቦች በመጠቆም የተሻለ ስራ እንዲመጣ ለማበረታታት ጭምር ነው።

“የዘመን አሻራ” ልቦለድ በእጅጉ የደፈረሰ መሆኑን ከላየ ጠቅሻለሁ። መደፍረሱ የሚጀምረው ደግሞ ከፊደል ግድፈት ብዛት ነው። በርካታና ተደጋጋሚ የፊደል ግድፈቶች ታይተውበታል። ይህም አንባቢን የሚጎረብጥ ንባብን የሚያስተጓጉል ከመሆኑም በላይ መፅሐፉ አርትኦት አልተሰራለትም እንድንል ያስገድደናል። በሌላ በኩል የዐረፍተ ነገሮች መደራረብ (ውስብስብ ዐረፍተ ነገሮችን መጠቀም) የመፅሐፉን ውበት ከቀነሱት ነገሮች መካከል ይጠቀሳል።

በመጽሐፉ ውስጥ ያሉ ገፀባህሪያት ከምክንያት ይልቅ በተደጋጋሚ በስሜት የሚገፉ መሆናቸው እንዴት ነው ነገሩ ያስብለናል?. . . ምሳሌ በመጥቀስ ሲስተር አዳነችን ማየት እንችላለን። ከአስር ዓመት በላይ ባለቤቷን (ሻምበል ከፈለኝን) ከኤርትራ ይመለሳል ብላ ስትጠብቅ ፅናቷ የሚገርም ነው። ነገር ግን ከዚህ ፅናቷ ፍፁም ተቃራኒ በሆነ መልኩ በወሲብ ወላፈን ስትግል መመልከትና ሀሳቧ ሁሉ ሲጠብ እንታዘባለን። ይህ የገፀ ባህሪዋን አሳሳል ወጥነት ጥያቄ ውስጥ የሚጥል ሆኖ እናገኘዋለን። ሌላው የገፀባህሪይ አሳሳል ላይ ወጥነት የሚጎለው ደህንነቱ ያዕቆብ ነው። መነጋገር ባለመቻሉ ብቻ አብረውት የቆሙትን ጓደኞቹን በሞት ይቀጣል። ምክንያት ሁሉ ሰንካላ ነው። ለምሳሌም ዘረዕዝጊን ከገደለው በኋላ የሚያስቀምጠው ሃሳብ፣ “ነገሮች እንዳይበላሹ ሲል ያደረገው እንጂ ዘረዕዝጊ ለሀገሩ ያለው ፍቅር ከእሱ እንደሚበልጥ ያውቃል” (ገፅ- 302) ሲል ይነግረናል።

ይህው የያዕቆብ እምነት አልባነት በብዙ መልኩ ይገለፃል። በሌላም በኩል አብሯት እየኖረ መረጃ የሚቀባበልበት ሙሉ የኢትዮጵያ ጦር ባሬንቱ ድረስ መግባቱን ስትነግረው እንዳላመናት ይገልፅና “ዜናውን ከኢትዮጵያ ሬዲዮ ሲሰማ ግን አመነ” (ገፅ÷312) ይለናል። የተልዕኮ አንድነታቸው እና መተማመናቸው ምን ያህል እንደሆነም ግራ የሚያጋባ ነው።

“የዘመን አሻራ” ውስጥ የሚያስቀና ፍቅር ተደርጎ የተሳለ የጽዮን እና የጌቱ ግንኙነት በርካታ መሰናክሎችን ሲያልፍ እናነባለን። ነገር ግን የሚወዳት ልጅ በተሳሳተ መረጃ ወደኤርትራ ተባራ ስትሄድ የመንገብገቡን ያህል፤ ወደሀገር ውስጥ በምኮር ስትመለስ የጌቱ መንፈስ መቀዛቀዝ ለምን ያስብላል።  ወደምርኮኞች መጠለያ መሄድ ባይችል እንኳን ፍርድ ቤት በምትቀርብባቸው ቀጠሮዎች እንዴት ሳይገኝ ይቀራል የሚል ጥያቄን ያጭራል። እዚህ'ጋ የፍቅርን ጠንካራነት ለማሳየት ደራሲው ቢችልም ፅዮንም፣ ጌቱ በቤተሰቡ ግፊት ከአይኗ ሲርቅ ባልተጨበጠ ምክንያት ሌላ ሴት ወዶ ነው ብላ መቀየሟ፤ የፍቅራቸውን ጥልቀት ጥያቄ ውስጥ ይጥለዋል።

ሌላው በመፅሀፍ ውስጥ ተደጋግሞ የተገለፀውና እንደድክመት የሚጠቀሰው የወንጀል ህግ አንቀፆች መዘለላቸው ነው። ለምሳሌ እንጥቀስ ከተባለ “የአእምሮ ህመምተኛ የሆነ ሰው በወንጀል መከሰስ እንደሌለበት የሚያዘውን የወንጀለኛ መቅጫ ቁጥር ----- ሽፋን በማድረግና ከህግ ፊት ለማምለጥ ሞክረዋል።” (ገፅ ÷ 226) ይላል። ይህን መሰል የህግ ክርክሮች በልቦለዱ ውስት ሲካሄዱ ደራሲው በሙሉ በክፍት ቦታ አልፎታል። ይህም ፀሐፊው በበቂ ምርምርና ዕውቀት እንዳልፃፈው የሚጠቁም ተግባር ነው። ወይም የህግ አማካሪዎችን ቢጠይቅ የተሻለ መስራት ይችል ነበር ለማለት ያስደፍራል።

“የዘመን አሻራ” ድንገቴ ድርጊቶችና ታሪኮችንም አብዝቶ ይተርካል። ከነዚህ መካከል ሊጠቀስ የሚገባው የሂሩት በዲቪ ሎተሪ ከሀገር መውጣት ነው። በምን ሰዓት ዲቪ እንደሞላች አንድም ቦታ ሳይጠቁመን ቆይቶ፤ ድንገት ዲቪ ደርሷት ሲለን ድንቃይ ይመስልብናል።

ሌላኛው የምክንያትና ውጤት መላላት የሚታይበት ወይም “የተዓማኒነት ጥያቄ” የሚነሳበት የመፅሐፉ ታሪክ የጌቱ ቤተሰብ ጉዳይ ነው። ጌቱ አባቱ ያዘጋጀለትን ሴት አላገባም በማለቱ እና ፅዮንን አግብቼ እኖራለሁ በሚል አቋሙ ምክንያት ቤተሰቡ ሁሉ የአእምሮ በሽተኛ ነው ብሎ መደምደሙ በእጅጉ የማይታመን ነው። አንድም ሰው ከቤተሰቡ አባላት (ምናልባትም ከወንድሙ ሚስት ትርንጎ እና ከአባቱ ሁለተኛ ሚስት እርጎዬ በስተቀር) እንዴት ሰው በጅምላ ያስባል? ያስብላል። ይህንን የጅምላ ውሳኔ ፅዮን፣ “ቤተሰቦቹ እንዲህ ካደረጉ ጤነኞች አይደሉም” (የገፅ ÷106) ስትል ትገልጸዋለች።

በ“የዘመን አሻራ” ልቦለድ ታሪክ ውስጥ ያለ ምክንያትና ውጤት ማሳያ ተደርጎ ከሚጠቀሰው ጉዳይ መካከል ሌላው ዘውዱ ለፅዮን ያለው ፍቅርና የወሰደባት እርምጃ ግራ አጋቢነት ነው። እንደዚያ ለፍቅሯ አበድኩ ከነፍኩ ያለው ሰው በሀሰተኛ መረጃ ወደኤርትራ እንድትገባ ማድረጉን ስንመለከት ስራው ሁሉ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” አይነት ነገር ነው።

የመፅሐፉን ውስብስብ ታሪክ በሚገባ ለመረዳትና ፋታም ለማግኘት እንዲረዳ ሲባል፤ አንባቢን ለማገዝም ሆነ የተወሰነ ሂደት እንዲጓዝ፣ በክፍሎች ወይም በምዕራፋት ቢከፋፈል ጥሩ ይሆን ነበር። ዳሩ ግን ይህ በቁርጥራጭ ትዕይንቶች ብልጭ ድርግም ማለቱ አሰልቺ ሆኗል።

በስተመጨረሻም በእውነት የሀገር ደህንነትን በሚያምስ መልኩ አራት ኪሎ የሚገኘው ቤተመንግስት ድረስ በስውር ዋሻ በኩል የተደረገው ጉዞ ውጤቱ አወዛጋቢ ሆኗል። በዋሻው ውስጥ የተጠመዱት ፈንጂዎች መጨረሻ ግልፅ አይደለም። ልክ እንደ መቶ አለቃና እንደመርማሪው አረጋዊ አንባቢም ከያዕቆብ ጀርባ ያለውን “ጡንቸኛ ሰው” ማወቅ ይፈልጋል። “ሁሉም ከያዕቆብ በስተጀርባ ያለውን ሰው ማወቅ ስላልቻሉ ፍርሃት አደረባቸውና ጉዳዩን ችላ አሉት” (ገፅ ÷ 303) ይለናል። እውነት የሀገር ደህንነት ነገር እንዲህ በቀላሉ ችላ የሚባል ነውን?

እንዲሁም በሲስተር አዳነች ህፃን ልጅ አዜብ ሞክሼ ስም ያላት ሴት ጋር አገናኝቶን፤ ከታሪኩ በስተጀርባ ያለችውን የቤተመንግስቷን ሴት በቅጡ አንባቢ እንዳይረዳ አደፋፍኖና አደፈራርሶ በማለፉ “የዘመን አሻራ” ድፍርስ ታሪክ እንጂ የጠራ ነገር ሳያሳየን አልፏል ማለት ይቻላል።   

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
14672 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 189 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us