ፍቅር ያደራበት “ሦስት ማዕዘን-፪”

Wednesday, 25 January 2017 12:58

 

የፊልሙ ርዕስ፡      “ሦስት ማዕዘን - ፪”

ደራሲ፡             ቴዎድሮስ ተሾመ

ዳይሬክተር፡         ቴዎድሮስ ተሾመ

ፕሮዳክሽን፡         ሴባስቶፖል ፕሮዳክሽን

ኤዲተር፡           ስንታየሁ ሲርጋጋ፣ የምስራች ግርማና መጂድ አሊ

ካሜራ፡            ማቲያስ ሹበርት

ተዋንያን፡          አበበ ባልቻ፣ ሰለሞን ቦጋለ፣ ሰላም ተስፋዬ፣ ማህደር አሰፋ፣ ሙሉቀን ተሾመ፣ ጌታሁን ሰለሞን እና ሌሎችም

 

“ሰው ማለት ሰው የሚሆን ነው ሰው የጠፋ ዕለት” ይላል አንድ ለጊዜው የማላስታውሰው ቴአትር ውስጥ የታነፀ ገፀ-ባህሪይ። ይህንን የሚያሳይ ፊልም ነው በደራሲና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ተሾመ የተሰራው “ሦስት ማዕዘን - ፪” ፊልም። ዘሩን በመጀመሪያው የሦስት ማዕዘን ፊልም ላይ የዘራው ይህ ፊልም የአብሮነትን ጥቅም፤ እንደ እሣት በሚለበልብ ፈተና፤ እንደ ክህደት በሚያንገበግብ ገጠመኝ፤ እንደመስጠት በማይነጥፍ መስዋዕትነት፤ እንደዜጋ በማይለዋወጥ ፍቅር መካከል እያገላበጠ ያሳየናል።

በቅርቡ ለዕይታ የበቃው ይህ ፊልም በበርካቶች ዘንድ ተወዳጅ ሆኗል። ለተወዳጅነቱ አብይ ምክንያቶች ሆነው የሚጠቀሱት ጉዳዮች፤ የተዋንያኑ ውህደትና አንጋፋነት፣ የካሜራው ጥራትና የኤዲቲንግ መሳለጡ፤ የድምፁ ጥራትና የሲኒማቶግራፊው ከፍታ ሊሆን ቢችልም፤ ከዚህ ሁሉ በላይ ግን የፊልሙን ምርጥ ታሪክ ጽፎ ያዘጋጀው የቴዎድሮስ ተሾመ ነው።

 

የሰሀራ እና የሜክሲኮ በረኻዎችን ተቋቁመው ሰሜን አሜሪካ የገቡት ባለታሪኮቹ በደስታም በሐዘንም መለስ ብለው የሚያሳዩን እውነት አላቸው። ከእነርሱ ባልተናነሰ በዚህ ፊልም ውስጥ ጐልቶ የሚታየው ሶማሊያዊው ዶ/ር አብዱራሂም (አበበ ባልቻ) የስደተኞችን ልፋትና የውጤታቸውንም ከፍታ እንደማሳያ ሆኖ መቅረብ ይችላል።

የበረኻ ጓደኛቸውን በሞት የተነጠቁት አራቱ ነፍሳት ዘር እና ድንበር ሳያግዳቸው በፍቅር ተሳስረው እናያለን። ቃልአብ (ሰለሞን ቦጋለ) ፍፁም ልብን እስከመስጠት በደረሰ ፍቅር፤ ከድንበር ባሻገር ነው ሲል ዊንታን (ማህደር አሰፋ) ሲንከባከብ፤ በአንፃሩ ደግሞ ስደት ሰውነቱን በልቶ አካላቱን ከእንቅስቃሴ ውጪ ያደረገበት ትልቁ፤ ጀማል (ሙሉቀን ተሾመ) ከዘርና ከሃይማኖት በላይ በሆነ ጽኑ ፍቅር በወደደችው እልፍ (ሰላም ተስፋዬ) እጅ ላይ ወድቆ ማየት ለበርካቶች የፍቅርን ጥልቀት (ጥግ) የምናይበት እንዲሆን ተደርጐ ተሰርቷል ለማለት ያስደፍራል።

 

በፍቅር ስም፣ በጓደኝነት ስም፣ በባልደረባነት ስም፣ ሰው-ሰውን ሲጐዳና ሲጠቅም የምናይበት ፊልም ነው። ከሁሉም - ከሁሉም ግን መውደዷን ያለገደብ የሰጠችው እልፍ (ሰላም ተስፋዬ) የልጅ ፍላጐቷን ለማሟላትና ዕምነቷን ለመጠበቅ የሄደችበት መንገድ በፊልሙ ውስጥ የአብሮነትን ጥግ ለማሳየት ከበቂ በላይ ነው።

በአንፃሩ ደግሞ በሚያምነው የስራ ባልደረባው በሀሰት ተወንጅሎ ለስድስት ዓመታት በእስር ቤት ያሳለፈው ዶ/ር አብዱራሂም (አበበ ባልቻ) በፍጥነት ወደነበረበት ከመመለስ ይልቅ ሰዎችን ለመርዳት በሚል የጎዳና ህይወትን መጀመሩ ከባድ ግን የአብሮነትን ጥግ ለማሳየት የቆመ ባለታሪክ ሆኗል። ይህም ሆኖ በሀሰት የወነጀለውን ዶ/ር ለመበቀል የተጠቀመው መንገድ አንጀት አርስ ሆኗል።

 

የዊንታ (ማህደር አሰፋ) ድንገት የልብ ድካም ህመምተኛ መሆን፤ የፍቅሯን ከፍታ ለመቀነስ የሄደችበት አሳዛኝ ምክንያት “ከፍ እያልክ በሄድክ ቁጥር መውደቂያህ እየራቀህ ይመጣል” የሚለውን የፈረንጅ አባባል፤ በፍቅረኛዋ ህይወት ውስጥ የፍቅር ከፍታው ጉዳት እንዳይፈጥርበት ያመጣችው ምክንያት እንደሆነ ተመልካች ይረዳል። “ነፍሴን አትርፈህልኛልና ከዚህ በኋላ የኔ አይደለችም” ያለችው ዊንታ፤ የሆዷን በሆዷ ይዛ በፍቅርና በነፍስ ውሳኔ መካከል ስታምጥ እንመለከታለን።

 

በፊልሙ ውስጥ እንደትልቅ የሞራል ፈተና የቀረበው የልብ ንቅለ-ተከላ ሂደት ነው። በድብቅ የሰዎችን ልብ እየገዛ የሚሸጠው ዶክተር የዊንታን ጤንነት ለመመለስ የህፃን ልጅን ህይወት ለመቅጠፍ የተደረገውን ድርድር ስንመለከት፤ “አይ ሰው” ያሰኛል። “የመጣው መፍትሄ ከችግሩ የባሰ ነው” የሚለውን ቃለ-ተውኔት እዚህ’ጋ እናስታውሳለን።

በፍቅር፣ በሞራል፣ በፅናትና በእምነት የሚፈተኑት “የሦስት ማዕዘን - ፪” ባለታሪኮች በአገሮቻቸው መካከል ከተሰበረው ድንበር ይልቅ፤ የልባቸው በፍቅርና በሰብዓዊነት የተሰበረው ልባቸው ይበልጥ አብሮነታቸውን አጥብቆታል። እናም የግለሰቦች መጥበብ አገራችንን ብሎም ዓለማችንን በክፉ መንገድ እንዳያጠባትም እንሰጋለን። “ይህቺን የምታክል ምድር ይዘን እንደገናም ከዚህም ለማነስ እንጨቃጨቃለን” ይለናል ዶ/ር አብዱራሂም።

 

በተንኮል፣ በግፍ፣ በማን አለብኝነት፣ ባለማስተዋል ያጣናቸውን የሰውነት ሃብቶች፤ ማለትም ፍቅርን፣ መቻቻልን፣ ድንበር አልባነትን፣ ሰብዓዊነትንና ፅናትን የምንመለከትበት የልበ-ሰፊዎች ፊልም ነው - “ሦስት ማዕዘን - ፪”…. እናም በድንበር የተራራቁ፣ በጦር የሚፈላለጉ ሰዎች ከጠባብ አስተሳሰብና ድንበር ወጥተው በፍቅር ታሪክ ውስጥ የዓለም ዜጐች ሲሆኑም እንመለከታለን።

 

በዚህ ፊልም ውስጥ እንደስህተት የሚጠቀስ ነገር ብዙም የለም። ነገር ግን ፍፁም ከስህተት የፀዳ ነው ለማለትም አያስደፍርም። ለምሳሌ በበርካታ ፊልሞች ውስጥ ተደጋግሞ እንደቀላል ስህተት የሚቆጠረው የኮንቲኒቲ ችግር አለ። “ሦስት ማዕዘን - ፪” ፊልም የኮንቲኒቲ ችግር ከታየባቸው ትዕይንቶች መካከል ለመጥቀስ ያህል፤ የመጀመሪያው ጀማል (ሙሉቀን ተሾመ) ለግብዣ በሚጠራበት ወቅት ከመኝታ ቤት ልብስ ለብሶ (ቀይሮ) ከመውጣቱ በፊት የነበረው የዊልቸር አቀማመጡና፤ የአንገት አስተጣጠፉ በኋላ ላይ ሊቀጥል አለመቻሉ በጉልህ ይታያል።

 

ሁለተኛው የኮንቲኒቲ ችግር ደግሞ ቃልአብ (ሰለሞን ቦጋለ) በሆስፒታል ውስጥ በነበረበት ቆይታና መፀዳጃ ክፍል ደርሶ ሲወጣ በሚያሳየው ትዕይንት መካከል ጉልህ ልዩነት ታይቶበታል። ከዚህ ሁሉ በላይ ግን በፊልሙ ውስጥ “የተኮረጀ ትዕይንት” መስሎ የቀረበው የገንዳ ውስጥ ትዕይንት ነው። ይህ ዊንታ (ማህደር አሰፋ) እና ቃልአብ (ሰለሞን ቦጋለ) በዋና ገንዳ አካባቢ የተሰራው ትዕይንት ከዚህ ቀደም በውሃ ማስታወቂያ ላይ የታየን ትዕይንት በእጅጉ የሚያስታውስ ወይም የሚመሳሰል ነው ማለት ያስችላል። በተረፈ “ሦስት ማዕዘን - ፪” ባለታሪኰቹን በደራ ፍቅር ያስተሳሰረና ከድንበርና ከዜግነት መለያየት በላይ አንድ ያደረገ የአብሮነትን ጥግ ያሳየን ፊልም ነው።¾   

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
14823 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 233 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us