የህፃናትን ዓለም ማሳያ “ነፃና ንፁህ” ሥዕሎች

Wednesday, 01 February 2017 13:27

“የኔ ልጅነት በበርካታ ጨዋታዎች መካከል ያለፈ ነው። በርግጥ ስራዎቼ የኔን ልጅነት ብቻ ማዕከል አድርጌ የሰራሁዋቸው አይደሉም። ህፃናትን ሳስተምር ያገኘዋቸውን ሀሳቦች ነው አሁን ላይ በስዕል ስራዎቼ የምገልፃቸው ማለት እችላለሁ።” ይላል፤ ወጣቱ ሰዓሊ ይስሃቅ ሣህሌ። እናም መምህር ሆኖ በሚያስተምራት ህሊና አለማየሁ የተባለች ህፃን ሳቢያ የአሳሳል ፍልስፍናው የተቀየረው ይህ ሰዓሊ የተመረጡ ስራዎቹን በ22ኛው የጋለሪያ ቶሞካ የሥዕል አውደ-ርዕይ ላይ አቅርቧቸዋል። ስራዎቹም ካለፈው ሳምንት መጨረሻ አንስቶ ለቀጣዮቹ ሁለት ወራት በዕይታ ላይ ይቆያሉ።

 

ስለ ስዓሊ ይስሃቅ ሣህሌ የሚከተለውን የከተበው አንጋፋው ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ እንዲህ ያስነብበናል፤ “የሠዓሊ ይስሃቅ ሣህሌ ኪነ-ቅቦች የህፃናት ዓለምን ህይወት፤ በቅርበት በእነርሱ ስዕላዊ ቋንቋና ምስላዊ አገላለፅ ጣዕምና ለዛ፣ ታስበውና ተጠንተው የተሳሉና የተቀቡ ናቸው። እንደ ህፃናቱ አሳሳል በወፍራም መስመራት የተሰመሩ፣ ሰፋፊ ዝርግና ደማቅ ኅብረ-ቀለማት የተቀቡ ነፃ፣ ንፁህና የዋህ ኪነ-ቅቦች ናቸው። ሁሉም ኪነ-ቅቦች በህፃናት ዓለም ህይወት፣ በእነሱ ለእነሱ የተሰሩ የሚመስሉ ናቸው። ጥያቄው የህፃናትን ስዕላዊ ጣዕምና ለዛ ጠብቆ መሳልና መቀባት ሰዓሊ የሆነ ሁሉ ይችላል ወይ ነው? መልሱ፤ ለህፃናት ህይወት ፍቅርና ክብር ያለው ከሆነ አዎ ይቻላል የሚል ይሆናል። ሰዓሊ ይስሃቅ ሣህሌም እዚህ በቀረቡት ኪነ-ቅቦቹ ይህንኑ በሚገባ ገልጾልናል፤ አሳይቶናልም። ህፃናት ሁሉ እነዚህን ኪነ-ቅቦች አይተው እንደሚደሰቱና እንደሚዝናኑ እሙን ነው። ምክንያቱም ለእነሱ ነገረ-ልቦና የቀረቡ ኪነ-ቅቦች ናቸውና።” ብሏል።

 

እንደ ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ አገላለፅ ሁሉ በጋለሪያ ቶሞካ ለዕይታ የቀረቡት ስራዎቹን ስንመለከት በቀለማት ያሸበረቁና ለመስመሮቻቸውም የማይጨነቁ የሚመስሉ አመራማሪ ስራዎቹን እንመለከታለን። ለመሆኑ ለሰዓሊ ይስሃቅ ቀለምና መስመር ምን ትርጉም ይሰጡታል? “ራሴን ልክ እንደህፃናት በመቁጠር ነፃና ቀጥተኛ የሆኑ ያልተደባለቁ ቀለማትን እጠቀማለሁ። ስሰራ ራሴን በህፃናቱ ልብ ስለማስበው ቀለማት አያስጨንቁኝም። እኔ በመሰረታዊ ቀለማትም አልጠቀምም። ስራዬን ስሰራ ህፃናቱ ቢስሉ እንዴት እንደሚስሉ እያሰብኩ ነው የምሰራው” ባይ ነው።

 

“ነፃና ንፁህ” የተሠኘ አብይ ርዕስ የተሰጠው ይህ የስዕል አውደ-ርዕይ ከ43 ያላነሱ ስራዎችን በጋለሪያ ቶሞካ ለተመልካች አቅርቧል። “በህፃናት ዓለም ውስጥ መገኘት፣ ያንን ዓለም መተንተን፣ በህፃናት ህሊና ውስጥ የሚፈሱ ቀለማትን ማጫወት ደስ ይለኛል!” የሚለው ወጣቱ ሰዓሊ፤ በእርሱ አተያይ የህፃናት አዕምሮ ሲገለፅ፣ “ከልጆች ነገረ ስራ ሁሉ ነፃነታቸው ይማርከኛል። መናገር የሚፈልጉትን ነገር በግልፅ መናገራቸው። መውደድና መጥላታቸውን አለመደበቃቸውና አለማስመሰላቸው በጣም ይማርከኛል ይህ ይመስለኛል ህፃናትን ነፃና ንፁህ የሚያሰኛቸው” ይላል።

 

በመነሻው እንደብዙ ተርታ ሰዓሊያን ደስ ያለውን ነገር ይስል የነበረው ይስሃቅ፤ ብዙ ጊዜ በመልከዓ-ምድር አቀማመጥ እንደሚመሰጥም ይናገራል። ዳሩ ምን ያደርጋል ህሊና አለማየሁ የተባለች ህፃን ተማሪው፤ የመምህሯን የይስሃቅን የአሳሳል ፍልስፍና እስከወዲያኛው የቀየረችው ይመስላል። የህፃን ባልሆነ ህሊናው የህፃናትን ዓለም ሲያስብ ቆይቷል። እናም ዛሬ ላይ በህፃናት ላይ በሚሰራቸው ስራዎቹ ተለይቶ ለመታወቅ ችሏል።

 

ሰዓሊ ይስሃቅ ስራዎቹን በማንኛውም ሰዓት ሀሳብ ከመጣለት መስራት እንደሚችልም ይናገራል። ለመሆኑ ለስራዎቹ መነሻ ሀሳቦችን እንዴት ያገኛል? “ሁልጊዜ ሀሳብ ፍለጋ ላይ ነኝ። ድንገት በመንገድ ስሄድ እንኳን ሀሳብ ከመጣልኝ ንድፉን በማስታወሻዬ እይዛለሁ። በንድፍ ደረጃ የያዝኩትን ስራ በቀለም ማሳመሩ ለኔ በጣም ቀላል ነው” ባይ ነው።

 

ለአንድ ሰዓሊ ቀለምና መስመር ብዙ ትርጉም እንዳላቸው የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ። ለመሆኑ ለሰዓሊ ይስሃቅ ቀለምና መስመር የሚሰጡት ትርጉም ምንድነው? “ብዙ ጊዜ በኔ ስራዎች ውስጥ ደማቅ ቀለማት ይንፀባረቃሉ፤ ይህ ማለት ግን እይታን የሚረብሽ አይነት እንዳልሆኑ ይታወቅልኝ። ስራዎቼ የህፃናትን መንፈስ የተላበሱ በመሆናቸው የቀለምና የመስመር አጠቃቀሜም እንደነሱ ነው። ቀለሞቼ ልክ እንደ ህፃናቱ ቀጥተኛ ናቸው። ቀይ ካስፈለገ ቀይ፣ ቢጫ ካስፈለገ ደግሞ ቢጫ እንጂ መደባለቅ ብሎ ነገር የለም። ለምን ህፃናት የሥነ-ጥበብ ት/ቤትን ሕግ ስለማያውቁና በነፃነት ስለሚስሉ ማለት ነው” ይላል።

 

በስዕል መስክ በጐ ተስዕኖ ካሳረፉበት ባለሙያዎች መካከል ቀድሞ የሚጠራው ሰዓሊ በኃይሉ በዛብህን እንደሆነ ይናገራል። “ከህፃናት ስራዎች ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያለው ይህ ሰዓሊ እኔንም ወደዚያ የሳበኝ እርሱ ሳይሆን አይቀርም” ይላል። ገና ከመነሻው ህፃናት ላይ አተኩሮ በሚስላቸው ስዕሎች ውስጥ ቀለሞቹ ይመስጡኝ ነበርም ሲል-ትኩረቱ የተሳበበትን ወቅት ያስታውሳል።

 

አሁን ላይ በርካታ የኪነ-ጥበብ ስራዎችን ከካሜራ ጀርባ በመሆን እየሰራ የሚገኘው ሰዓሊ ይስሃቅ ሣህሌ፤ በተለያዩ የስዕል አውደ-ርዕይዎች ላይ በግልና በቡድን በመስራት (በማሳየት) ይታወቃል። በፈረንሳይ ባህል ማዕከል፣ በብሔራዊ ሙዚየም፣ በብሔራዊ ቴአትርና በአስኒ በተ-ስዕል ስራዎቹን ለተመልካች እይታ አብቅቷል።

 

ሙሉ ለሙሉ ትኩረቱን በህፃናት አሳሳል ላይ አድርጐ የሚሰራው ይስሃቅ - በቀጣይም ለህፃናት የሚሆን መፅሐፍ በማዘጋጀት ላይ እነደሚገኝ ይገልፃል። ከዚህ በተጨማሪ በሳምንት አንድ ቀን ህፃናትን ያስተምራል። ይህም ከህፃናቱ ላለመራቅ የፈጠረው ዘዴ እንደሆነ ይናገራል። “ከስራዬ ውጪም ቢሆን እንደመሳል የሚያዝናናኝ ነገር የለም” የሚለው ይስሃቅ፣ ከልጆችና ከስዕል ጋር ስሆን በጣም እዝናናለሁ ባይ ነው። 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
15127 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 472 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us