የሒስ እና ሃያሲ ጉዳይ

Wednesday, 15 February 2017 13:16

 

“የሒስ ጥበብ ሂደት በኢትዮጵያ” በሚል አብይ ርዕሰ ጉዳይ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ባሳለፍነው ቅዳሜ (የካቲት 4 ቀን 2009 ዓ.ም) በኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተመፅሐፍት ኤጀንሲ (ወመዘክር) አዳራሽ ጉባኤ አካሂዶ ነበር። በስፍራው በርካታ የስነ-ፅሁፍ ባለሙያዎችና ደራሲያን ይገኛሉ ተብሎ ቢጠበቅም፣ አልተገኙም። ከተመደበለት ሰዓት በእጅጉ ዘግይቶ በተጀመረው በዚህ ፕሮግራም ላይ የተገኘው ታዳሚም ቢሆን ከተጠበቀው በታች ነበር።

በዕለቱ በአብይ ጉዳይነት ውይይት ስለተካሄደበት፣ “የሒስ ጥበብ ሂደት በኢትዮጵያ” ዙሪያ በመድረኩ ተገኝተው በወፍ በረር ቅኝት ላይ የተመሰረተ ጥናታቸውን ያቀረቡት ፀሐፊ ተውኔትና ገጣሚ አያልነህ ሙላቱ ናቸው። “በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ሃያሲና ሂስ መኖር አለበት” የሚሉት ፀሐፊ ተውኔትና ገጣሚ አያልነህ፤ በተለይም የፈጠራ ስራን በሚመለከት ሲናገሩ “አንድ የፈጠራ ስራ የጥልቅ ስሜትና አመለካከት ውጤት ነው” ብለዋል። እናም የፈጠራ ስራዎችን ጥልቀትና ርቀት ገላልጦ ለማሳየት፣ በዕውቀት የዳበሩና በንባብ የበለፀጉ ሃያሲያን ያስፈልጉናል ባይም ናቸው።

አንድን የፈጠራ ስራ ተመልክቶ መልዕክቱን ወዲያውና በቀጥታ ለማግኘት የማይቻልበት ጊዜ መኖሩን ያስታወሱት ሃሳብ አቅራቢው፤ ለዚህም ሃያሲያን የሚያስፈልጉበትን ምክንያት በዝርዝር አስረድተዋል። የአንድን ፈጠራ ፅሁፍ በቀላሉ ለመረዳት ከሚያስቸግርበት ዋነኛ ምክንያት ብለው ሲያስረዱም፣ ፀሐፊያኑ የሚከተሉት የጋራ የሆነ የፈጠራ ሂደት ባለመኖሩ እና በባህሪውም ስነ-ፅሁፍ ግላዊ ስለሆነ ለመረዳት ጊዜ ይወስዳል ያሉ ሲሆን፤ ለዚህም ድልድይ በመሆን እና የፈጠራ ስራውን በማፍታታት አንባቢያንን የሚረዳ ስልጡን ሃያሲ ሊኖር ይገባል” ይላሉ። በሁለተኛ ደረጃ ለሃያሲ አስፈላጊነት የሚጠቀሰው፣ ፈጣሪው (ፀሐፊው) ያተኮረበት ጉዳይ በጠባይ ከባድና ውስብስብ በመሆኑ ልዩ ማብራሪ የሚጠይቅ ይሆናል የሚል ነው። ሌላው የፈጠራ ስራው ተምሳሌታዊ (symbolic) የሚታይበት ከሆነ ለመተንተን ሃያሲ አስፈላጊ ነው። አራተኛውና የመጨረሻው ደግሞ፣ ስራው ልዩና ማብራሪያን የሚጠይቅ ሆኖ ሲገኝ ሃያሲያን ያስፈልጉናል ሲሉ አስረድተዋል።

ማንም ሰው አንድን የፈጠራ ስራ አንብቦ መጥፎ ነው አልያም ጥሩ ነው ማለት ይችላል ያሉት የውይይት ሃሳብ አቅራቢው፤ ሃያሲያን ከተራ አንባቢ የሚለየው ነገር ቢኖር፤ ለውዴታውም ሆነ ለጥላቻው ምክንያት አዘልና ተጨባጭ ማስረጃ ማቅረብ መቻሉ ነው ተብሏል። ለዚህም አንድ ሀያሲ በፀሐፊውና በአንባቢው መካከል የበለጠ መግባባት እንዲኖር ይሰራል ሲሉ ተደምጧል።

ታዲያ ይህንን የመሰለ ማህበራዊ መግባባትና ከፍታን ለመፍጠር የሚሰሩ ሃያሲያን እዚህ ደረጃ እንዲረሱ የሚያስፈልጋቸው ልዩ ጠባይ ምን እንደሆነ ጥናት አቅራቢው ሲዘረዝሩ የሚከተሉትን ሃሳቦች አስቀምጠዋል። የመጀመሪያው በሙያው የሰለጠኑ ይኖርባቸዋል። ሲቀጥል በትምህርት ያገኙትን እውቀት በስራው ላይ ለብዙ ጊዜ በመቆየት ማዳበር ይጠበቅባቸዋል። ሶስተኛው ምዕራፍ ደግሞ ሃያሲያን ወደዘርፉ ሲመጡ በትምህርታቸው ብቻ ሳይሆን ከዝንባሌያቸው የመነጨ ቢሆን ይመረጣል የሚል ሃሳብ ቀርቧል። ጥናት አቅራቢው በዚህ አጋጣሚ አንዲት ሃሳብ አንስተዋል “ደራሲ ይወለዳል፤ እንደሚባው ሁሉ ሃያሲም ይወለዳል” ለዚህም አመክኒዮ የቀረበው ሃሳብ፤ የሃያሲነት ሙያም ልክ እንደደራሲነት ሁሉ ልዩ ዝንባሌንና ተሰጥኦን የሚጠይቅ እንደሆነ ተብራርቷል።

አቅም ያላቸው ሃያሲያን መፈጠር አንድን ማህበረሰብ (አንባቢ) ወደላቀ ዕውቀት ከማሸጋገራቸውም ባሻገር ለፀሐፊያኑም የተሻለ ስራ ድጋፍ መሆን ይችላሉ ተብሏል። እናም አንድ ሃያሲ የተሻለ ማህበረተሰብ እንዲፈጠር የራሱን ሚና የመጫወቱን ያህል፤ በሃያሲ የተገራ ማህበረሰብ ደግሞ ከደረጃው የወረደን የፈጠራ ስራ ለመቀበል መፀየፉ እንደማይቀር ተወስቷል።

በታሪክ ሂስ ጎልቶ የወጣባቸውና ያለፈባቸው ዘመናት የትኞቹ እንደሆኑም ፀሐፊ ተውኔትና ገጣሚ አያልነህ ሙላቱ ያስረዳሉ። በጥንታዊ ዘመን ሂስ በእነፕሌቶና አርስቶትል ጫንቃ ላይ አርፎ ይሰራበት እንደነበር ተወስቷል። በመካከለኛው ዘመን ደግሚ ሂስ የሮማ ቤተ ክርስትያን ፍልስፍና ላይ የተመሰረተ ነው። ዳግማዊ ልደት በምንለው ዘመን ደግሞ የኤፒኮ ስራ የተፍረከረበበት ጊዜ ሲሆን፤ ሮማንቴክ ዘመን ተብሎ የሚጠራው ደግሞ ካፒታሊዝም የገነነበት ወቅት እንደሆነ ጠቃቅሰው አልፈዋል።

በመድረኩ ለውይይት የሚሆን ሀሳብ በቅኝት ጥናት መልክ ያቀረቡት ፀሀፊ ተውኔት አያልነህ፤ ስለሂስ ዓይነቶችም እንደሚከተለው አስቀምጠዋል። አንድ ሀያሲ አንድን የፈጠራ ስራ አንብቦ ስሜቱ እንደመራው የሚሰጠው ሂሳዊ አስተያየት “ተራ ሂስ” ተብሎ ይጠራል። ሌላው በተለያዩ አገራት በብዛት የሚሰራበት “ጋዜጣዊ ሂስ” ይጠቀሳል። ይህ አይነቱ የሂስ መንገድ በሀገራችን ደካማ እንደሆነ ቢገለፅም፤ በተቀረው አለም ግን አንድ ታዋቂ ሃያሲ በጋዜጣ ላይ ስለአንድ መፅሀፍ (የፈጠራ ስራ) የሚሰጠው ሂስ የፈጠራውን ዋጋና ተፈላጊነት ከፍ እንደሚያደርገው ተገልጿል። ሌላው የሂስ አይነት በዩኒቨርስቲዎችና በኮሌጂች የሚቀርቡት የማሰልጠኛ/ የማስተማሪያ ሂሶች ሲሆኑ በስተመጨረሻ የሚጠቀሰው ግን ምሁራዊ ሂስ የሚባለው እንደሆነ የዘርፉ ተመራማሪዎች ይስማሙበታል። 

ከአራቱ የሂስ አይነቶች በተለየ የሚጠቀሰው ምሁራዊ ሂስ ባለሙያው በሂስ ሙያ የሰለጠነ ወይም ባይሰለጥንም እንኳን በኪነ-ጥበብና በተለያዩ ዘርፎች ሰፊ ዕውቀት ያለው እንደሆነ ይጠበቃል። ምንም እንኳን የሁሉም የሂስ ስራ በተመሳሳይ የተሻለ የፈጠራ ስራ እንደስራ ለማስቻል የሚተጋ ነው ቢባልም፤ ሂስ እንደሚሰጥበት የፈጠራ ስራ አይነት፣ ባህሪና አላማ የሃያሲያን ሂስ ሊለያይ ይችላል። ነገር ግን የሁሉም ጠቅላይ ዝንባሌ፤ ስሜታዊ፣ ታሪካዊ፣ ቅርጻዊ፣ ይዞታዊ፣ ስነልቦናዊ፣ ማህበራዊ ወይም ስነ-ውበታዊ ሊሆን ይችላል።

የቱንም አይነት ሂስ ቢሆን ሃያሲው ስለፈጠራ ስራው ትንታኔ ሲሰጥ የሚጠቀመው ቋንቋ የሰለጠነና ውበት ያለው እንደሆነ ይጠበቃል። በዚህም ምክንያት ከተራው ስሜታዊ “ተቺ” ይለያል። ሃያሲ ስለአንድ ፈጠራ የሚያቀርበው የጥላቻም ሆነ የውዴታ ትንታኔ “ለምን?” የሚለውን የአመክኒዮ (የምክንያታዊነት) ምላሽ የሚሰጥ መሆን ይኖርበታል። ለምሳሌም ከስሜት አንፃር ሂስ ሲሰጥ የማህበረሰቡን ስሜትና የፀሐፊውን ስሜት ለማግባባት ይሞክራል። ቅርፃዊ ሂስ ሲሰጥ የፈጠራ ስራውን የቋንቋ አጠቃቀምና ቅርፅ ይተነትናል። ይዞታዊ ሂስ ሲሰጥ ደግሞ ደራሲው ለማለት የፈለገውን መልዕክት ፈልቅቆና ቀምሮ በግልፅ ያሳያል። ታሪካዊ ሂስ የሚሰጥ ሃያሲ የታሪክ ዕውቀት ሊኖረወ ይገባል። በሌላው ዘርፍም ቢሆን እንዲሁ ነው በሚል ተቀምጧል። ይህም የሃያሲን ተሽሎ መገኘት ምን ጊዜም በተለያዩ መስኮች ለሚደረግ የዕድገት ጉዞ ወሳኝ መሆኑን ያመለክታል።

በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ሂስ ግላዊ ሊሆን እንደሚችልና በአንድ ጉዳይ ላይ የተለያየ አረዳድ ሊፈጠር እንደሚችል ሃሳብ አቅራቢው አስረድተዋል። በአንድ የፈጠራ ድርሰት ላይ እያንዳንዱ ሰው የራሱ የሆነ ግላዊ አስተሳሰብ ይኖረዋል። ለአንዱ ቆንጆ መስሎ የሚታየው የፈጠራ ስራ፤ ለሌላው ቆንጆ ሆኖ ላይታይ ይችላል። የፈጠራ ስራው ውብ መሆን ወይም ሰለመሆንን ለመግለፅ ስምምነት ላይ ለመድረስ አይቻልም። አንድ አይነት መግባባት ላይ መድረስ ግን ይቻላል” አያይዘውም፤ ይህም ስርዓት አልባ አስተሳሰቦች በሰዎች መካከል እንዳይፈጠር ያደርጋል ብለዋል።

የሂስ መንገድ ደግሞ ኪነ-ጥበብ ለኪነጥበብ የሚል መሆኑም ተወስቷል። ይህ የሂስ መንገድ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ ብቅ ያለ የቅርፃዊያን ሃሳብ እንደሆነ ሃሳብ አቅራቢው ያስረዳሉ። ቅርፃዊያን፣ አንድ የኪነ-ጥበብ ስራ ለውስጠ ባህሪው ብቻ እንጂ ከዚያ ውጭ በሆነ መለኪያ መገምገም የለበትም ብለው የሚያምኑ ቡድኖች ናቸው።

በመድረኩ ከተነሳው ሃሳብ መካከል የሂስና የሳንሱር (ቅድመ ምርመራ) ጉዳይ ይጠቀሳል። በመሰረቱ ሁለቱንም ነጥቦች በጋራ የሚያስተሳስር ዓላማ እንዳለ ሃሳብ አቅራቢው ያስረዳሉ። ይህውም የአንድን ህብረተሰብ ባህልና ማንነት የመጠበቅ ዓላማ አላቸው። ነገር ግን ሁለቱም የማይገፉበት መንገድ እንደሆነም ተወስቷል። ሳንሱር (ቅድመ ምርመራ) የመንግስት አባል ሆኖ ደራሲያንን መጨቆኛ ሆኖ ሲያገለግል፤ በአንፃሩ ሂስ ግን ቢኮረኩምም የተሻለ የፈጠራ ስራ እንዲመጣ ለማስቻል የሚተጋ እንደሆነም ተነግሯል።

ከመድረኩ ሲነገር እንደተሰማው እኛ ኢትዮጵያውያን በአንድ ድምፅ የምንጠራው “ሃያሲ” እንዳይኖረን ያደረገን እርስ በእርስ ያለመከባበራችንና በጋራ የኛ የምንለውን ታላቅ ባለሙያ ማየት አለመቻላችን አንዱ ነው ተብሏል። በሌላ በኩል በቂ የስነ-ፅሁፍ ስራዎች ለአንባቢ አለመቅረባቸው (ምንም እንኳን አሁን-አሁን መሻሻልን እያሳየ ቢሆንም) ለዚህም በርካታ ምክንያቶች ተጠቅሰዋል። ከዚህም ጋር በተያያዘ የሂስ ጥበብን ለማሰልጠን (ለማስተማር) በቂ አቅም አለመረኖሩ ተጠቅሷል። ሌላው የሃያሲያን ችሎታ ዝቅተኝነት ነው። ሃያሲያን ጥልቅ አስተሳሰብና ቆራጥነት ያስፈልጋቸዋል። ለዚህም ሃያሲያንን ለማሰልጠን ብዙ ጊዜ መፈለጉና በሙያው የሰለጠነውም ቢሆን ብቁ ይሆናል ብሎ መወሰዱ ስለማይቻል ሃያሲያን ይወለዳሉ እንጂ ተጠፍጥፈው አይሰሩም ማለት ይቻላል ብለዋል። በአንፃሩ ደግሞ የኪነ-ጥበብ ሰዎች ቆዳቸው ስስ መሆኑ ለሂስ ጥበብ በሀገራችን አለመዳበር አስተዋፅኦ አድርጓል የሚል ሃሳብም ወደ መድረኩ ተሰንዝሯል።

“የሂስ ጥበብ ሂደት በኢትዮጵያ” በሚለው መድረክ ላይ ስለሃያሲ ማንነት፣ ስለሂስ ምንነት፣ ስለሂስ አይነትና ተግባራት የተወሱትን ያህል፤ ሂስ በኢትዮጵያ ያለበት ደረጃ አልተብራራም። ነገር ግን በውይይቱ ሂደት በርካቶች እንደተናገሩት “አገራችን ኢትዮጵያ የዘመናት የሊቃውንትና የሃያሲያን የነበሩባት እንደሆነች፤ በተለይም የአብነት ትምህርት ቤቶችና ገዳማትና አብያተ ክርስትያናቱ ለሃያሲያን መኖር ትላልቅ ስፍራዎች እንደነበሩ ከተወያዮቹ ሲነሳ ተሰምቷል።

ሃያሲያንን የማፍራት ጉዳይ እንደማንኛውም የአገር አበይት ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶትና ፕሮግራም ተይዞለት ወደተግባር መተርጎም አለበት የሚል የመደምደሚያ ሃሳብም በጥናት አቅራቢው ተሰንዝሯል። ለዚህም መወሰድ ከሚገባቸው ተግባራት መካከልም የዳሰሳ ጥናት አቅራቢው የሚከተሉትን ምክረ-ሃሳቦች እንካችሁ ብለዋል። አንደኛ፣ መንግስትና ህብረተሰብ በአጠቃላይ በሃያሲያን አስፈላጊነት ላይ ማመን አለባቸው። ሁለተኛ፣ በተለይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና በቋንቋ ኮሌጆች ውስጥ ከነበሩ የሂስ ጥበብ ጋር የሚተዋወቁ ወጣቶች እንዲኖሩ ያልተቆጠበ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። ከዚህም ባሻገር በሀገር ውስጥ ያሉ አማተር ሃያሲያን ከውጪ ከሚጋበዙ ባለሙያዎች ጋር እንዲተዋወቁና ልምድ እንዲለዋወጡ ቢደረግ መልካም ይሆናል ሲሉ የዳሰሳ ጥናታቸውን ደምድመዋል። 

ይምረጡ
(4 ሰዎች መርጠዋል)
16056 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 890 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us