አንዳንድ ነገሮች ስለ “የኢትዮጵያ ታሪክ ከኢማም አሕመድ እስከ ዐጤ ቴዎድሮስ” መፅሀፍ

Wednesday, 26 March 2014 12:13

እርቅይሁን በላይነህ የሸዋን ታሪክ በኢትዮጵያዊያን ልማዳዊ ታሪክ ትረካና ትንታኔ ስልት፤ ነገር ግን ለዘመናዊው የአካዳሚክ የታሪክ ጥናት ስልት በቀረበ መልኩ በጥልቅ ትንታኔ አቅርቧል። . . .ይህ መፅሀፍ በታሪክ ተመራማሪዎች ብዙም ትኩረት ያልተሰጠው፤ ነገር ግን ምናልባትም ወሳኝ የሆነውን የኢትዮጵያ ታሪክ በአማርኛ ቋንቋ ስለሚዳስስ በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ አንባቢ ተመራጭ እዲሁም ወደፊት ለሚደረጉ ምርምሮች በመነሻነት የሚኖረው ድርሻ ከፍተኛ ነው። ይህን ያሉት በጥናትና ምርምር ተቋም የታሪክ ተመራማሪው ዶ/ር ተፈሪ መስፍን ናቸው። እኔንም መጽሐፉን እንዳነበው የገፋፉኝና በውስጡ ያለው የተለየ ታሪክ ደራሲው (አዘጋጁ) እንደሚለው ያልተነገሩ፤ ያልተሰሙ ያልተነበቡ ታሪኮች ዶ/ር ተፈሪ እንዳሉትም ትኩረት ያልተሰጠውና ወሳኝ የሆነው የኢትዮጵያ ታሪክ ምንድው የሚለውን ነገር እንድፈትሽን እንድመረምር ያደረገኝ ይኸው የዶ/ሩ የጀርባ ሸፋን ላይ የወጣው ጽሑፍ ነው።

“የኢትዮጵያ ታሪክ ከኢማም አህመድ እስከ አፄ ቴዎድሮስ” የተሰኘው ይህ መፅሐፍ በዋነኝነት ከቦታ አንፃር መሰረት ያደረገው በሸዋ በተለይም አሁን በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በሚባለው አካባቢ ይሁን እንጂ ሌሎችም የሀገራችን ወሳኝ ታሪኮች የተፈፀሙባቸው ቦታዎችም ተከልለውበታል። ከዘመን አንፃርም ቢሆን ታሪኩ ከተቀነባበረበት ከ1500-1851 ዓ.ም ካለው ጊዜ ወደኋላ ፈንጠር ብሎ የአክሱምን፣ የዛጉዌንና የሸዋ መንግሥት ወጣኒ የነበረውና የዐጤ ይኩኖአምላክን ዘመን ይዳስሳል። ወደፊትም ዘልቆ የአምስት ዓመቱን የፋሽስትን የወረራ ዘመን ከአርበኞቻችን ታሪክ ጋር አቀናጅቶ ያስነብበናል።

ለመፅሃፉ መነበብ በተለይ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ምክንያቶች፡-

1.በፎቶ የተደገፉ አዳዲስ መረጃዎች፡-

ዐጤ ምኒልክ ሙሴ ሞንዶን ቬዳሌ ከተባለው ፈረንሳዊ በተቀበሉት ምክር መሰረት በ1886 ዓ.ም የባህር ዛፍ ፍሬን ከአውስትራሊያ አስመጥተው ነበር። የባህር ዛፍ ፍሬ ተፈልቶ ለገበሬው ተከፋፍሎ በየአካባቢው እንዲተከል ተደርጓል። ከዚህ በፊት ግን አጤ ምኒልክ በአንኮበር መጀመሪያ የፈላውን ችግኝ ቆመው አስከትለዋል። ምኒልክ ያኔ ቆመው ካስተከሏቸው ባሕር ዛፎች መካከል አንደኛው በአንኮበር ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አቅራቢያ ዛሬም ድረስ አሉ። ይህ ከ119 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ዛፍ ከዚህ መፅሐፍ ውስጥ ከነታሪኩ በፎቶ ተደግፎ እናገኘዋለን። (ከገፅ194-197)።

የዐጤ ምኒልክ አባት ንጉሥ ኃይለመለኮት አባታቸው ጀምረውት ሳይጨርሱት የሞቱትን የአንኮበር መድኃኒዐለም ቤተክርስቲያን በትከሻቸው ድንጋይ እየተሸከሙ ከአሸከሮቻቸው ጋር በመሆን ሰርተው ጨርሰዋል። ይህን ዳፋ ቀናቸውን የተመለከተ ወርቄ የተባለ ግንበኛ የቤተ ክርስቲያኑ መሰረት በሆኑት ድንጋዮች ላይ መታሰቢያ የሚሆናቸውን ቅርፅ ቀርፆላቸዋል። እነዚህ ቅርፆችና የግንበኛው ወርቄ መቃብር መሆኑን የሚያመላክተው ቦታ ላይ ያለውን ጉቶ በፎቶ ከትቦ ያሳየናል፤ (ከገጽ 299-302)። ከእነዚህም በተጨማሪ ንጉሥ ሳህለሥላሴ ክርስትና የተነሱበት ቁሮ ገደል ስላሴ፤ ሙቅ ምድር የተባለችው እንዲሁም ሌሎችን ሰንዶች ይዟል።

2.የተዘነጉ ታሪኮችና ባለታሪኮች፡-

እንደሚታወቀው በ1500 ከምስራቁ የሀገራችን ክፍል በተነሳው አህመድ ኢብን አብራሂም አል ቃዚ የኢትዮጵያ መንበረ መንግስት ተነቃንቋል። ከሸዋ ለቅቆም ከብዙ መዋዠቅ በኋላ በጎንደር ረግቷል። አብዛኞች የታሪክ መፅሐፍትም በኢትዮጵያ መንበር መንግስት ላይ የተቀመጡትን ነጋሲዎች መሰረት በማድረግ የሀገራችንን ታሪክ ያስነብቡናል። “የኢትዮጵያ ታሪክ ከኢማም አህመድ እስከ ዐጤ ቴዎድሮስ” ግን ከዚህ በተቃራኒው በተለይም ዐጤ ልብነ ድንግል ሸዋን ለቀው ከመውጣታቸው በፊት መንዝ ውስጥ አቤቶ ያእቆብ የተሰኘ ልጃቸውን ልብሰ መንግሥት አልብሰው ትተውት ሄደው ስለነበር የሱን የዘር ሐረግ መሰረት አድርጎ የሀገራችንን ታሪክ ያስነብበናል። በያዕቆብ የተመሰረተው የሸዋ መሳፍንት ታሪክ በአግባቡ በጽሁፍ ባለመሰነዱና ባለመታወቁ የሸዋ ታላቅነት የሚጀምረው ከአቤቱ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘመን ጀምሮ ነው የሚል ታሪክ ሲነገር ይስተዋላል። ነገር ግን ለዐጤ ምኒልክና ለተከታዮቻቸው መሰረት የሚሆነው ትውልድ መሰረቱ ዐቤቶ ያዕቆብና ልጆቹ ናቸው። መጽሐፉ ከዚሁ ከዐቤቶ ያዕቆብ ጀምሮ ያሉትን ስለሞናዊ የሸዋ መሳፍንት እስከ መርዕድ አዝማች ኃይሌ ድረስ ሙሉ ታሪካቸውን በአንድ አሰባስቦ ያስነብበናል።

የሸዋ መሳፍንት ከዐጤ ቴዎድሮ መነሳትና ከንጉሠ ኃይለ መለኮት መሞት ጋር ተያይዞ አብቅቷል ለሚለውም ታሪክ የለም መርዕድ አዝማች ኃይሌ ላይ ነው ያበቃው የሚለውን የታሪክ ሙግት ከነምክንያቱና አለኝ ብሎ ከሚጠቅሰው ነማስረጃ ጭምር ያቀርባል። (ከገጽ 327)

በዘመነ መሳፍንቱ ጊዜውንም ሆነ ከዚያ በፊት ባለው የዐጤዎች የግዛት ዘመን ሰሎሞናዊ የዘር ሐረግ ባለው መስፍን ስትመራና በጠንካራ አስተዳደር ላይ ሆና የቆየችው ግዛት ሸዋ ብቻ መሆኗን ያሳየናል።

ሸዋ በተፈጥሮ ምሽግ መሆን የቻለችና በጦርነት ጊዜ ምቹ መሆኗን በማስቃኘት በሞከረበት በሁለተኛው ምዕራፍ (ከገፅ57-59) ድረስ ባሉት ገፆች ውስጥ ስለዝረት ዋሸና በውስጡ ስለተፈፀሙት የአርበኝነት ገድል በውስጡም ስላሉት ቅሪቶች ያስቃኘናል። ይህ ዋሻና በውስጡ ያለውም ታሪክ በምርምር በቅርቡ የተገኘ በመሆኑ ከዚህ መፅሀፍ በፊት በታተመ መፅሀፍ ላይ ተከትቶ አላየሁም፤ አላነበብኩም።

በአምስት ዓመቱ የፋሽስት የወረራ ዘመን ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ሀገር ጥለው ሎንደን በገቡ ጊዜ እነራስ አበበ አረጋይና ሌሎች የሸዋ አርበኞች ንጉሥ አንግሰው እንደነበር እና ሂደቱን በዝርዝር ከመተረኩም ባሻገር፤ ይህ መጽሐፍ እንግዳሸት ስለተሰኘው የዛን ዘመን ልዑል (ከገጽ 67-68) አሳፍሮ ያስነብበናል።  

3.አህመድ ኢብን አብራሂም አል ቃዝ ወራሪ ወይስ ገዥ?

የቅፅል ስሙ ግራን አህመድ በመባል የሚታወቀው ጦረኛ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሳ ወራሪ ተደርጎ ከብዙ የታሪክ መፅሀፍት ላይ ተጽፎ ሲነበብ ይስተዋላል። በአፍም ሲነገር ይሰማል። ይህ መፅሀፍ ግን የጦረኛውን ታሪክ ባተተበት ሶስተኛ ምዕራፍ ከወረራ ያለፈ የገዢነት ሚና እንደነበረው ከገፅ 98 ጀምሮ ያስነብበናል። “ኢማም አህመድ የበላይነቱን ይዞ አልገዛም የሚል ሀሳብ ከተነሳ ዐጤ ልብነድንግል ገዝተዋል ወይ? የሚል ጥያቄ ሊነሳ እንደሚችል አስባለሁ”። /ገፅ 99/ ይለናል።

4.የጠራ ታሪክ

     የኢትዮጵያ ታሪክ ከኢማም አህመድ እስከ ዐጤ ቴዎድሮ የሚለው ይህ መፅሀፍ ብዥታ ያለባቸውን የሀገራችንን ታሪክና ባለታሪክ በተለይም ትኩረት ባደረገበት ዘመንና ቦታ ላይ ባሉት መሳፍንቶች ዙሪያ እርስ በእርሳቸው የሚጣረሱ መረጃዎችንና ታሪኮችን አጥርቶ ሲስቀምጥ ይታያል። በታሪክ ቅደም ተከተል ሔዶ ተዓማኒ የሆነውን እውነተኛ ታሪክ ሲያስነብብ ይታያል። ምርምሩ የጽሁፍ ድርሳናትንና የቃል ትርክትን /አፈታሪክን/ እንዲሁም ቦታው ድረስ በመሄድ በቅኝት /observation/ የተደገፈ በመሆኑ እርግጠኛነቱ ይስባል። አፈታሪክን ከፀሀፍ ድርሳናት ጋር ያመሳክራል፣ እንደገናም በኦብዘርቬሽን ካገኘው እውነት ጋር ያገናዝባል። ይህ ዓይነቱ ጥልቅ ምርምር ደግሞ በዘመናዊው የአካዳሚ የታሪክ ጥናት ቅርብ ነው።

ይምረጡ
(54 ሰዎች መርጠዋል)
13926 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us