“ውህደት” የሥዕል አውደ-ርዕይ በየአብዘር አርት ጋላሪ

Wednesday, 22 February 2017 11:27

የካቲት 4 ቀን 2009 ዓ.ም አምስት የአንድ ዘመን ሰዓሊያንን ያጣመረው “ውህደት” (Harmony) የሥዕል አውደ-ርዕይ በየአብዘር አርት ጋላሪ በይፋ ተከፍቷል። ይህ አውደ-ርዕይ እስከ መጋቢት 6 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ ለተመልካች ክፍት እንደሚሆንም አዘጋጆቹ ተናግረዋል። በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ ወቅት ያገኘናቸው የኢትዮጵያ ሰዓሊያን ማህበር ፕሬዝዳንት ሰዓሊ ስዩም አያሌው እና የማህበሩ ዋና ፀሐፊ ሰዓሊ ሰይፉ አበበ ስለቀረቡት የስዕል ስራዎችና ሰዓሊያኑ በጥቂቱ አጫውተውናል።  Harmony (ውህደት) በተሰኘው በዚህ የስዕል አውደ-ርዕይ ላይ የተሳተፉት ሰዓሊያን ዮሴፍ አባተ፣ ቴዎድሮስ ግርማ፣ ዮናስ ደገፋ፣ አብይ እሸቴ እና መሀሪ ተሾመ ናቸው። በአጠቃላይም ሁሉም ወጣት ሰዓሊያን አሻራዎቻቸውን ያሳረፉባቸው 44 ስራዎች ለዕይታ ቀርበዋል።

በየአብዘር አርት ጋላሪ ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረቡት እነዚህ የሥዕል ስራዎች ጋላሪውን ከማስተዋወቅ ባለፈ፤ “ስፍራው ለስዕል ወዳጆች አማራጭ ሆኖ ቀርቧል” ሲል የኢትዮጵያ ሰዓሊያን ማህበር ዋና ፀሐፊና ሰዓሊ ሰይፉ አበበ ገልጿለወ። አያይዞም ይህ ውህደት “ሀርመኒ” የተሰኘው ስብስብ በጋላሪው በቡድን የቀረበ የመጀመሪያ አውደ-ርዕይ  ነው” መሆኑን አክሏል። ስራዎቻቸውን ያቀረቡት አምስቱ ወጣት ሰዓሊያን በከተማችን ጥሩ ተመልካች ያላቸው ባለሙያዎች ስለመሆናቸው የሚናገረው ሰዓሊ ሰይፉ፤ “ስራዎቻቸው በአብዛኛው በእውነታዊ (Realistic) ዘይቤ የተሳሉ ናቸው” ሲል ይገልፃቸዋል። የአውደ-ርዕይው በማስተባበርና አብይ -ርዕሱን በማውጣት ጭምር ተሳትፎ የነበረው ሰዓሊ ሰይፉ፤ የቀረቡትን ስራዎች ከሰዓሊያኑ የአሳሳል ዘይቤ በመነሳት እንደሚከተለው ይዘረዝራል።

ብዙ ጊዜ በመልከዓ ምድር- አቀማመጥ ዙሪያ ይሰራል የተባለው ሰዓሊ አብይ እሸቴ፤ ፎቶችንና ቀለም ቅብን በማዋሃድ የሚሰራቸው ስዕሎች በበርካቶች ዘንድ እንደሚወደዱለት ተናግሯል። በዚህ አውደ-ርዕይ ላይ ግን በብዛት ያቀረበው ትኩረት ያደረገበት “ታቦትን” ነው። ይህም ስራ በዕለቱ የነበሩ ተመልካቾችን ቀልብ ስቦ ነበር።

ተፈጥሯዊ ገፅታ ያላቸውን አበባዎች ያቀረበው ሰዓሊ መሐሪን በሚመለከት ሰዓሊ ሰይፉ ሲገልጽ፣ የቀለምና የብርሃን አጠቃቀሙ በተለይ ለሥዕሉ ጉልበት እንደሆነለት ይመሰክራል። “ሰዓሊያን የሚጠቀሙበትን ቢላዋ በመጠቀም የሰራቸው ስራዎች የብዙዎችን ቀልብ መሳብ የሚችል ነው” ይላል። ይህ አይነቱ አሳሳል ችሎታና ዕውቀትን የሚጠይቅ እንደሆነም ይናገራል። መሐሪ በስራዎቹ ያደመቃቸው በቅርብ የምናውቃቸውን አበባዎች መሆኑን የሚናገረው ሰይፉ፤ ስራዎቹን በቤታችን ውስጥ ብንስቅላቸው የምር መንፈስን የማደስ ሃይል አላቸው ባይ ነው።

ሰዓሊ ቴዎድሮስ ግርማ ያቀረባቸውን የስዕል ስራዎች በተመለከተ ሰይፉ ሲናገር ትንሽ ለየት ያለ እንደሆነ  ይናገራል። “የቴዲ የአሳሳል ዘይቤ የአብስታራክትና የእውነታዊነት ድብልቅ ነው”። በተለይም ወደእነውታዊነት የቀረቡት ስራዎቹ የተመልካችን ዓይን መማረክ እንደሚችሉ ያለውን እምነት ይገልፃል። በእውነታዊ አሳሳል ዘይቤው እንዲቀጥልም እመክረዋለሁ ሲል በስራዎቹ ላይ የተሰማውን ይናገራል።

የኢትዮጵያን ቁጥሮች፣ ፊደላትና ጥለቶችን በመጠቀም በሚያቀርባቸው ስዕሎቹ ይለያል - ሰዓሊ ዮናስ ደገፋ (ኪንግ)፤ ስለዮናስ ስራዎች ምስክርነቱን የሰጠው ሰዓሊ ሰይፉ እንዲህ ይላል፣ “ዲዛይን የበዛባቸውና ኢትዮጵያዊነትን የሚያሳዩ ስራዎችን ሰርቶ አቅርቧል፤ ይህ የሰዓሊው መለያ ነው። ተመልካቹም እንደሚወደው ተስፋ አለኝ” ሲል በአውደ-ርዕይው ከቀረቡ ስራዎች መካከል ትኩረትን ሊያገኝ እንደሚችል ይገልፃል።

ሌላኛው በአውደ-ርዕይው ስራዎቹን ያቀረበው ሰዓሊ ዮሴፍ ነው። ጎጃም ተወልዶ ያደገው ሰዓሊ ዮሴፍ አባተ ስራዎቹም ላይ የትውልድ አካባቢው ይንፀባረቅበታል ይላል። በስራዎቹ ላይ ምስክርነቱን የሚሰጠው ሰዓሊ ሰይፉ፤ ይህ ሰዓሊ ተፈጥሮአዊ አካባቢዎችን በስዕል ሲያሳየን ወደእውነታዊነት በጣም ከመቅረቡ የተነሳ ስዕል ነው ወይስ ፎቶ ነው? የሚያሰኝ መደነቅን ይፈጥራል” ሲል አግራሞቱን ገልጿል።

ሰዓሊ ዮናስ ደገፋ

በአወደ-ርዕይው ስምንት የሚደርሱ ስራዎቹን ያቀረበው ሰዓሊ ዮናስ ስለስራዎቹ ሲናገር፣ “ስዕሎቹ የሚያሳዩት የኢትዮጵያን የባህልና ቅርስ መስህቦችን ጨምሮ በማህበረሰባችን ውስጥ ያለውን ዕለታዊ እንቅስቃሴዎቻችንን ነው” ይላል። ኢትዮጵያዊነቴን ስለምወደው ኢትዮጵያዊ በሆኑ ነገሮች ላይ አተኩራለሁ የሚለው ዮናስ፤ “ስራዎቼ የነበረንን ነገር ዶክመንት በማድረግ ያለፈውንና የአሁኑን ዘመን ማንነታችንን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ በሚል መንፈስ የሰራዋቸው ናቸው” ሲል ያስረዳል። ስለስዕል ሲገልጽም “የሰወ ልጅ ቀደምት ስልጣኔ የሚጀምረው ከዚህ ጥበብ ነው” ሲል የስዕል ዋጋ የቱን ያህል ከፍ ያለ እንደሆነ ያስረዳል።

ሰዓሊ መሐሪ ተሾመ

በየአብዘር አርት ጋላሪ አስር የሥዕል ስራዎችን ያቀረበ ወጣት ሰዓሊ ነው። ከዚህ ቀደም በማህበራዊ ድረ-ገፆች ዙሪያ ብዙ ስራዎችን እንደሰራ የሚናገረው ሰዓሊ መሐሪ፤ “በዚህ አውደ-ርዕይ ያቀረብኳቸው ስዕሎች ግን የተፈጥሮ ውበት ላይ ያተኮሩ ናቸው”። ለዚህም እንደምክንያት የሚጠቀሰው ለውጥ በመፈለግ ስሜት መስራቱን እንደሆነ ያስረዳል። “ውበት ላይ ያተኮረ ስዕል ስሰራ መልካሙን የቀን ውሎ እንደማጉላት ሆኖ ይሰማኛል። ይህም በመሆኑ ልክ እንደ ዲያሪ በየዕለቱ የውስጥ ስሜትህን የምትገልፅበት ይሆናል” ሲል ያስረዳል። ስዕልን በቀላሉ መግለፅ ይከብዳል የሚለው ይህ ሰዓሊ፣ “ስዕል ለኔ ተፈጥሮን የምተረጉምበት ዓይን ነው” ሲል ይናገራል።

የኢትዮጵያ ሰዓሊያን ማህበር ፕሬዝዳንት የሆነው ሰዓሊ ስዩም አያሌው ስለቀረቡት ስራዎች ማዕከላዊ ጭብጥ ሲናገር፣ “ወጣቶቹ ሰዓሊያን የሚሰማቸውን በስዕል ቋንቋ ለታዳሚው አቅርበዋል” ብሏል። እግረ-መንገድ ስለራሱ ስራዎች ሲጠየቅም “በግሌ የኔ ስራዎች የኖርኩበትንና ያደኩበትን ማህበረሰብ የሚያሳዩ ናቸው። አንድ ሰዓሊም ማድረግ የሚችለው፤ ማሳየትም ያለበት የሚያውቀውን ነገር መሆን አለበት የሚል እምነት” እንዳለው ገልጿል። በስዕል ስራዎቹ ውስጥ በጉልህ ስለሚያንፀባርቃቸው ጉዳዮች የሚያትተው ሰዓሊ ስዩም፤ ጠጅ ቤቶች የማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ነፃነታችንን የቀረፅንባቸው ቦታዎች ናቸው” ሲል ያስታውሳቸዋል። አሁን ላይ ዘመናዊነት በርካታ ጠጅ ቤቶችን እንዳጠፋቸው በቁጭት የሚገልፀው ስዬም፣ በሰፈሬ ከነበሩት አስር ጠጅ ቤቶች አሁን ላይ የቀረው አንድ ብቻ ሲሆን ቀሪዎቹ ዘጠኝ ጠጅ ቤቶች ግን በኔ የስዕል ስራ ላይ ቀርተዋል ሲል ፈገግ አሰኝቶናል።

በተለያዩ የአሳሳል ስልት፤ ነገር ግን ውህደት በሚታይበት መልኩ አይነ-ግቡ የሆኑ ስራዎችን፤ ወጣቶቹ የአንድ ዘመን ሰዓሊያን የሚሰማቸውንና የምናባቸው አቅም የፈቀደላቸውን የስዕል ስራ በየአብዘር አርት ጋላሪ እንድትመለከቱ እነሆ ይላሉ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
16016 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 959 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us