እውነተኛ የሰዶ ማሳደድ ታሪክ “ዘፍ ያለው”

Wednesday, 01 March 2017 12:06

 

የመጽሐፉ ርዕስ፡           “ዘፍ ያለው”

ደራሲ፡             ሌተና ኰ/ል ተፈራ ካሣ

የሕትመት ዘመን፡    2008 ዓ.ም

የገፅ ብዛት፡        340

ዋጋ፡              150 ብር

 

የአንድ ወቅት ክስተት የነበረን እውነተኛ የስለላና የአፈና ትንቅንቅን ታሪክ ይተርካል። ኢትዮጵያ ከውስጥ የኑሮ ውድነት፣ የስልጣን ሽኩቻና የኔ-በልጥ - እኔ በልጥ ጥላ አጥልቶባታል። ከውጭ ደግሞ የታጠቀና የሰለጠነ፣ ድጋፍ የበዛለት የሶማሊያ መንግስት በማን አለብኝነት ለጦርነት ተሰናድቷል። ይህን ውስብስብና መሳጭ ታሪክ በትረካ መልክ እንካችሁ ይለናል፣ የሌተና ኰ/ል ተፈራ ካሣ - “ዘፍ ያለው” መፅሐፍ።

 

አንድን መጽሐፍ በሽፋኑ ብቻ መፍረድ ብዙ ነገር ያሳጣል። ምናልባትም የሽፋን ምስሉ የሚስብ ባይመስልም፣ መፅሐፉ የያዛቸውን ቁም ነገሮችና ታሪክ ለማወቅ ገለጥ-ገለጥ ማድረግ ተገቢ ይሆናል። በዚህም መፅሐፍ ውስጥ የኢትዮጵያውያንን ፅናት፣ ቁጣ፣ የአፈና ትንቅንቅ፣ የአገር ደህንነትና ክብርን ለማስጠበቅ ስለተካሄደ እልህ አስጨራሽ ትግል ይተርክልናል።

 

ይህ የአገራችን ጀግንነት ደግሞ ለሌሎችም ምስክርነት የተሰጠበት ነው። በተለይ በድንበራችን ሲመጣብን እንዲህ ነን፣ “የአበሾችን መሬት ቆርሶ ለመውሰድ ሁለቱ ቅኝ ገዢዎች ሞክረው ያልቻሉትን፣ አሁን ‘እኛ ተዋግተን እናሸንፋለን!’ ማለቱ ለአበሾች በታሪክ ሲነገርላቸው የሰማነው በኰሪያና በኮንጐ ዘምተው የፈፀሙትን ገድል ሁሉ መዘንጋትና መናቅ አይሆንም?” (ገፅ፣ 26) ሲል ኰሎኔል ጋሌብ ይጠይቃል። ይህን የሚናገረው በእንግሊዞች ባህልና ትምህርት ተኮትኩቶ ያደገው ሶማሌያዊው የአየር ኃይል መኮንን ነው - ኰሎኔል ጋሌብ ሐጂ ዮኒስ ነው። ይህ ኰሎኔል ሀገሩን ጥሎና ኮብልሎ፣ የፖለቲካ ጥገኝነት ፍለጋ ወደ ኢትዮጵያ ስለመጣበት ምክንያት በዝርዝር ሲያስረዳ፣ የጐረቤት አገራትን አላስፈላጊ ጦርነት በመቃወም፣ የሶቬየት ኅብረትን በሶማሊያዊያን መንግስት ላይ ያላትን ጣልቃ ገብነት በመቃወምና በግልም አለቆቹ የማዕረግ ዕድገት እየነፈጉ የደረጃ በደል ከመፈፀማቸውም ባሻገር፣ በጐሳ ላይ ያተኮረ የስልጣን ድልድል መጀመሩ እንዳስቆጣው ይገልፃል። (ገፅ፣ 59)

 

የሶማሊያን ወረራ አላስፈላጊነት በማጤን ወደጐረቤት አገር ኢትዮጵያ የኮበለለው ይህ ኰሎኔል፣ አገሩ ለጦርነት እየተዘጋጀች ከመሆኗም ባሻገር በምን ያህል ደረጃ ላይ እንዳለች ለኢትዮጵያ የደህንነት ሰዎችና ከፍተኛ ባለስልጣናት በሰጠው ቃል ያስረዳል። ይህን ምስጢር ለኢትዮጵያ መንግስት አሳልፎ ሰጥቷል የተባለው ኰሎኔል ጋሌብ በሶማሊያ መንግስት በኩል ከሃዲ ከመባሉም ባሻገር በህይወት የሚፈለግ ወንጀለኛ ተደርጐ ተቆጥሯል። ይህንን ኰሎኔል ከኢትዮጵያ የደህንነት ሰዎች መንጋጋ ፈልቅቆ ለማውጣት፣ በቁጥጥር ስር ለማዋል፣ የሶማሌያ መንግስት ባለስልጣናትና የሶቪየት ኅብረት የስለላ ቢሮ ኬጂቢ የመጨረሻ ውሳኔ፣ “የወጣው ገንዘብ ይውጣ፣ የሚከፈል የህይወት መስዋዕትነትም ይከፈል ብቻ ኰሎኔል ጋሌብ በቀጥታ ኢትዮጵያዊያን ዓይኖቻቸው እየተቁለጨለጩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሞቃዲሾ እንደሚመጣ የከበደ የስለላና የአፈና መረብ መጣሉንና ተግባራዊም ሆኖ ውጤታማነቱም ጊዜ እንደማይወስድ አረጋግጠው በአስተርጓሚያቸው በሻለቃ ሱለይማን ዑመር አማካይነት በስብሰባው ተገለፀ።” (ገፅ፣90) ሲል የስለላና የአፈና እንቅስቃሴውን ጥንስስ ይተርክልናል።

 

በኢትዮጵያዊያን የፀጥታ ሰራተኞች ቁጥጥር ስር ሆኖ እንክብካቤ የሚደረግለት ሶማሌያዊው የአየር ኃይል አዛዥ፣ በኬጂቢ፣ በሶማሊያ ኤምባሲና በሰሜን አፍሪካ ዓረብ አገራት ትብብር ይፈለጋል። ኰሎኔሉን መጠበቅና የሀገር ክብርን አለማስደፈር በአንድ በኩል፣ በሌላ ደግሞ የውስጥ ሽኩቻው ማየሉንም መፅሐፉ ይተርክልናል። በ1953 ዓ.ም የተሞከረውን የመንግስት ግልበጣ ሙከራ ተከትሎ ስልጣናቸውንና ዘመዶቻቸውን ያጡ ሚኒስትሮች፣ የጦር ጄኔራሎችና መኮንኖች ሁሉ ቂም ይዘው እንደነበርና ይህም አካሄድ ለአገሪቱ የደህንነት ጥበቃ የራሱን ጋሬጣ እንደጣለ በመፅሐፉ (በገፅ፣ 74) ተተርኳል።

 

ለመሆኑ የሶማሌያ መንግስት በጐረቤት አገር (ኢትዮጵያ) ላይ ጦርነት ለማስነሳት እንደዋነኛ ምክንያት የሆነው ምንድነው? ይህን ጉዳይ በተመለከተ ደራሲው “ስንቅ የሌለው ዘመቻ” በሚለው ንዑስ አርዕስት ስር ይተርካል። በዚህ ክፍል ጃንሆይ የሶማሊያን ለወረራ (ለጦርነት) መሰናዳት በተመለከተ ረዘም ያለ ትካዜ የተሞላበት የሀሳብ ውጣ ውረድ ውስጥ ቆይተዋል። ሶማሌያዊያን “ከአዋሽ ወንዝ በመለስ ይገባናል!” ስለማለታቸው በሚተርከው (ገፅ፣117) ላይ እንዲህ የሚል ጽሁፍ ሰፍሯል፣ “በኢጣሊያ ሶማሊያ ቅኝ ግዛት የነበረው የደቡብ ሶማሊያ ወሰኖችን ግን፣ ጣሊያኖች ለሙን የኦጋዴን መሬታችንን በኃይል ለመያዝ ዘምተው በጀግኖች አባቶቻችን አልበገርም ባይነት ወሰኑ በደማቸው ቀይ መስመር ሲሰመርበት፣ አጥንታቸው ደግሞ የወሰን መልክት ሆኖ ተከልሏል” ይለናል።

 

መፅሐፉ በአፄ ኃ/ስላሴ መንግስት ውስጥ የነበረውን ሰንኮፍ ሲተርክም፣ “ዘመኑ ሚዛን የጐደላቸው አፈፃፀሞች እየታዩ፣ ፍትህና ርትዕ በተፃፈው ሕግ ተስተካክሎ እንዳይሰራባቸው በመደረጉ፣ አልጠግብ ባይነት ሩጫ በባለስልጣኖች፣ በጦር አለቆች፣ በቢሮክራቶች፣ በመሬት ከበሬቴዎችና በከተማ ነጋዴዎች መካከል በውድድር መልክ ስግብግብነት ነግሶ እብሪት፣ ጥጋብና ሽኩቻ የተጧጧፈ የሆነበት ነበር።” (ገፅ፣ 127) ሲል ይተርካል።

 

በዚህ ሁሉ ውስጣዊና ውጫዊ ግብ-ግብ መካከል የተወጠረው የኢትዮጵያ መንግስት እጅ የገባውን የሶማሊያ አየር ኃይል አዛዥ፣ “ከአንበሳ መንጋጋ ስጋ የመውሰድ ያህል” ድንገት ያልታሰበ ነገር ይከሰታል። ኰሎኔል ጋሌብ ካረፈበት ሆቴል ድረስ በውድቅት ሌሊት የመጡት የኬጂቢና የሶማሊያ መንግስት ሰዎች፤ የቀድሞ እጮኛውን ተገን አድርገው፤ የእፉዬ ገላን ያህል በቀለለ ዘዴ አፍነው ወደኤምባሲያቸው ይወስዱታል። አንድ አንባቢ ከባድ የአገር ምስጢር እንደያዘ የሚታወቅና ጥብቅ ጥበቃ የሚያስፈልገው ሰው ሆኖ ሳለ፤ እንዴት እንዲህ በቀላሉ ታፍኖ ይወሰዳል? ብሎ ሊጠይቅ ይችላል። መልሷን የሚሰጡን የህዝብ ፀጥታ ጥበቃ ኃላፊው ኰሎኔል ማህተመ ናቸው፣ “ይህ የሆነው በአንተ ጥያቄ መሰረት ‘ብዙም ቀርባችሁና ተጠግታችሁ እንደ እስረኛ አትንከባከቡኝ’ ስላልከን ጥያቅህንና መብትህን ላለመጋፋት ነበር እንጂ ‘ጥብቅ ጥበቃ ይደረግልኝ’ ብትለን ኖሮ ይህ ባላጋጠመ ነበር” (ገፅ፣ 301) በእውነቱ ይህ የህዝብ ፀጥታ ጥበቃ ቢሮውን የሚያስወቅስ ተግባር ነው። መደረግ የሚገባውን ማድረግ እንጂ፣ በእነርሱ ቁጥጥር ስር ያለ ሰው እንዲህ አድርጉልኝ ብሎ እስኪፈቅድ መጠበቅ አልነበረበትም። ምክንያቱም ጉዳዩ የአገር ክብርንም ከመጠበቅ አንፃር የሚታይ መሆኑ ስለሚታወቅ ነው።

 

በዚህ መፅሐፍ ውስጥ ተደጋግሞ መነሳት የሚችለው “የሰዶ ማሳደድ” ታሪክ ነው። ይህ ሀሳብ በንዑስ ርዕስነት የቀረበ ቢሆንም፣ በሙሉ በመፅሐፉ የታሪክ ሂደት ውስጥ በጉልህ መንፀባረቅ የቻለ ነው ለማለት ያስደፍራል።

የሶማሊያ መንግስት የሰለጠነና ብዙ ዕውቀት ያለውን የአየር ኃይል አዛዥ፣ ኰሎኔል ጋሌብን ለሀገር አንድነት በሚበጅ መልኩ ሀሳቡን ተቀብሎ የሚታረመውን አርሞ አብሮ እንዲቀጥል ማስቻል ሲገባው ድንገት አምልጦት የሰዶ ማሳደድ ትንቅንቅ ውስጥ ሲገባ እንመለከታለን። በሌላም በኩል የኢትዮጵያ መንግስት በርካታ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቹን በወቅቱ መፍታት እየቻለ ድንገት ቀውሱ ተባብሶ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ድረስ የሚመጣ ፖለቲካዊ ቀውስ ፈጥሯል። ይህም የሰዶ ማሳደዱ ማሳያ ሊሆን ይችላል።

 

በአንፃሩ ደግሞ በኤምፔሪያሊስት ጥላ ርዕዮተ-ዓለም ስር የምትተዳደርና ዘውዳዊ አገዛዝ ያላት ሀገር ወጣቶቿ በማርክሲዝም ሌኒንዝም ዕውቀት ራሳቸውን ሲያንፁ ዝም ማለቷ - ሌላኛው የሰዶ ማሳደድ ማሳያ ሳይሆን አይቀርም። የወቅቱን የተማሪዎች እንቅስቃሴ በተመለከተ መፅሐፉ ሲተርክ፣ “ማርክሲዝም ሌኒኒዝም በርግጥ በተማሪዎች መካከል ይነበባል። ይህም በትምህርት ያገኙት እንጂ፣ የሶሻሊስት አገር ኤምባሲዎች በጣም ጥቂት ስለነበሩ፣ ካሉትም ጋር ቢሆን ለንቅናቄያቸው ግንኙነት ፈጥረው መታገዛቸውን ያረጋገጥንበት ማስረጃ ስለሌለ፣ ‘የተማሪዎች ንቅናቄ የውጭ እጅ አለበት’ የተባለውን አጣርተን ምንም የተጨበጠ ማረጋገጫ አለመገኘቱን በማብራሪያ ሪፖርት ለጃንሆይ ቀረበ።” (ገፅ፣ 175) ይላል።

በስተመጨረሻ ሊጠቀስ የሚገባው የሰዶ ማሳደድ ታሪክ ማሳያው የሚሆነው ኰሎኔል ጋሌብ የሚገባውን ጥበቃ ባለማግኘቱ ድንገት ታፍኖ መወሰዱ የደህንነት ቢሮው ሰዶ ማሳደድ ውስጥ መግባቱን ያየንበት ክስተት ይሆናል።

 

“ዘፍ ያለው” የተሰኘው በሌተና ኰ/ል ተፈራ ካሣ የተፃፈው የስለላና የአፈና ትንቅንቅን የሚያሳየው ታሪክ በርካታ አገራዊ ጉዳዮችን ማሳየት የቻለ ነው። ከቋንቋ አንፃር በመፅሐፉ ውስጥ የተጠቀሱ ብዙ ዓይነት ማራኪ አገላለጾች መኖራቸው እንደተጠበቀ ነው። ነገር ግን ከሁሉም የስልጣንና የኃላፊነት ክብደት በተመለከተ አፄ ኃ/ስላሴ ብሩህ ልቦናና የሀገር ፍቅር ላላቸው ኰሎኔል ነቅዓጥበብ፣ የፊታቸውን ፈገግታ ተመልክተው እንዲህ ይላሉ፣ “መከፋት የጀመርከው ሹመት ከሰጠንህ ጊዜ ጀምሮ መሆኑን አታውቅምና ነው? ታላቅ ሹመት ከደስታ ያርቃል። (መስመር የኔ) ደስታ ያን ዕለት ከአንተ ሸሽታ ወደ አላሰብናቸውና ወደ አልሾምናቸው ሰዎች ቤት ሄዳለች።” (ገፅ 289) ይላል።

 

መፅሐፉ እንደክፍተት የሚነሳበት ነጥብ ቢኖር ረጃጅም ዓረፍተ ነገሮችን አብዝቶ መጠቀሙ ነው። ከረጃጅም ዓረፍተ ነገሮች ጋር ረጃጅም ሀሳቦችም ሰፍረው እናገኝበታለን። ለምሳሌ “የሙያ አሻራ” በተሰኘው ንዑስ ርዕስ ስር ታፍኖ ስለተወሰደው ኰሎኔል ጋሌብ ለመነጋገር የተቀመጠበት አባላት ከዋናው የስብሰባ ጉዳይ ርቀው የሀገሪቱን የደህንነትና ፀጥታ መ/ቤት በተመለከተ ከገፅ 167 እስከ 177 በብርጋዴየር ጄኔራል አርቅነህ ይተረክልናል። ይህ ምናልባት አንባቢን ያሰለች ይሆናል። ከዚህ ውጪ ግን በርካታ ጠንካራ ሀሳቦች ያነሳ መፅሐፍ በመሆኑ ሊነብ፣ ከስለላና ከአፈናው ትንቅንቅ በስተጀርባ የወቅቱን የማኅበረሰባችንን ሁኔታ ለማየት እንደታሪክ ግብዓት መሆን ይችላል።

 

“ዘፍ ያለው” መፅሐፍ በተለያዩ ንዑስ ርዕሶች በተጨማሪ በክፍል ሁለት “ጉም የሸፈነው ቀዩ ገደል” በሚል ርዕስ የቀረበው ሐተታ የፀሐፊውን ማንነትና ሀሳብ የምናገኝበት ሆኖ ቀርቧል። እዚህ’ጋ ለማስታወስ ያህል “የአሳታሚው ማስታወሻ” በተሰኘው ቀዳሚ ገፅ ላይ ስለደራሲው ማንነት፣ “የመፅሐፉ ደራሲ ሌተና ኰሎኔል ተፈራ ካሣ በፖሊስ መኮንንነት እና በመረጀ ባለሙያነት ሀገራቸውን በታኝነት፣ በቅንነትና ሕግን አክብሮ በማስከበር የሚያገለግሉ ባለሙያ ነበሩ።” ሲል ልጃቸው ቴዎድሮስ ተፈራ አስፍሮት እናነባለን። ይህም ደራሲው በስማ በለው የፃፉት ሳይሆን፤ ለታሪኩ ቅርበት ያላቸው ሰው እንደነበሩ እንረዳለን። በዚያው ቀጥለን እንደማስረጃ መጥቀስ ከለብን ደራሲው ራሳቸው መፅሐፉ የተዘጋጀበትን ምክንያት ሲያስረዱ፣ “በትረካ መልክ የቀረበው ይህ ታሪካዊ ማስታወሻ ‘የስለላና የአፈና ትንቅንቅ’ በኢትዮጵያ በአንድ ወቅት ተከስቶ የነበረውን ያህል ወደፊትም አይቀጥልም ብሎ ማመን ስለሚያስቸግር፣ ተተኪዎች እንዳይዘናጉ ይረዳል በሚል ግምት ቀርቧል።” (ገፅ 315)

 

ከዚህም በተጨማሪ በአገራት መካከል ቂምን ላለመተው ፀሐፊው ከሶሊያ ጋር አብራ ስለታገለችን አንዲት ሀገር “አፈሪካዊት ዓረብ አገር” በሚል ብቻ ያለፉበትን ምክንያትና በመፅሐፉ ውስጥ የተሳሉት ገፀ-ባህሪያት በህይወት የነበሩ ቢሆኑም እውነተኛ ስማቸውን ይፋ ያላደረጉበትን ሰበብ ዘርዝረው ለማሳመን ሞክረዋል። በተረፈ ግን “ዘፍ ያለው” የተሰኘ ታሪክ ቀመስ የስለላና የአፈና ትረካ ለትውልድ የቀድሞውን ታሪክ ከመተረክም ባለፈ ለታሪክ ባለሙያዎችም ግብዓት የሚሆኑ ሀሳቦችን አንፀባርቋልና ቢነበብ የመረጃን ጉልበት ያሳየናል ማለት ይቻላል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
16107 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1060 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us