“ጥምረታችን ምክንያታዊ ነው”

Wednesday, 08 March 2017 11:44

 

 

ሮቤል ሙላቱ

የኮንሶ የባህል ቡድን መስራች

 

በቁጥር ከሃምሳ በላይ የሚሆኑና ትልቅ ህልም ያላቸውን ወጣቶች የመሰረቱት የባህል ቡድን ነው-ኮንሶ የባህል ቡድን። የዛሬ አስር ዓመት እንደቀላል ሲመሰረትም ህልሙ የባህል ማዕከል የሚሆን “ካምፕ” እስከማቋቋም ድረስ የተለጠጠ ነበር። አሁን ላይ በባህላዊና ዘመናዊ ውዝዋዜ፣ በሙዚቃ መሣሪያ አጨዋወት፣ በሰርከስ ትርዒትና በድምፃዊያን ስሙን እየተከለ የሚገኘው ይህ የባህል ቡድን የተመሰረተው በአንድ ሰው ቆስቋሽነት ነበር።… ይህ ወጣት ከጓደኞቹ ጋር ፒያሳ አካባቢ ሆኖ የባህል ቡድን ስለመመስረትና የባህል ማዕከል ስለማቋቋም የሚያትት ሀሳብ ይዞ መሠረቱን ጣለ። መስራቹና የቡድኑ አባል ወጣት ሮቤል ሙላቱ ይባላል።\

 

ኮንሶ የባህል ቡድን የተመሰረተበትን አስረኛ ዓመት ለማክበር በሚሰናዳበት በዚህ ወቅት የቡድኑ አባላት ወደሚለማመዱበት ግቢ ጐራ ብለን ነበር። ቁጥራቸው በርከት ያሉ ወጣት ሴቶችና ወንዶች የውዝዋዜ ስራቸውን ቄራ በሚገኘው የወረዳ 04 አዳራሽ ውስጥ እያቀለጣጠፉ ነበር። ኮንሶ የባህል ቡድን ሲመሰረት አላማው የነበረው ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ የባህል ቡድኖች ጋር አብሮ በማደግ የራሱን የተለየ አሻራ ለማኖር አስቦ እንደነበር መስራቹና የቡድኑ አባል ወጣት ሮቤል ሙላቱ ይናገራል። “የቡድኑ መመስረት ባህልን ከማስተዋወቅ ባለፈ ሀገር አቀፍ ፋይዳ ያለው “ካምፕ” ለመመስረትም ምክንያት እንዲሆን ያለመ ነው” ሲል መነሻ ምክንያቱን ያስረዳል።

ገና ሲጀመር በአስራ አምስት ዓመታት ውስጥ ግቡን ሰፋ አድርጐ የተነሳው ይህ የባህል ቡድን በሂደቱ አባላቱን በአካልና በመንፈስም የማበልፀግ ስራን እየሰራ እንደቆየ ወጣት ሮቤል ይናገራል። ይህንን የሮቤልን ሀሳብ የቡድኑ አባላትም የሚስማሙበት ነው።

 

የወጣትነት ዕድሜውን በአስገዳጅ ፈተናዎች ውስጥ የማሳለፍ ዕጣ-ፈንታ ገጥሞት እንደነበር የሚናገረው ሮቤል፤ የዛሬ አስር ዓመት ይህንን የባህል ቡድን ለመመስረትም ፈተናዎችን ተጋፍጦ ከዳር ለመድረስ ተስፋው የፀና እንደነበር ያስታውሳል። ከባህል ቡድኑ በፊት በዘመናዊ ዳንስ ስር ራሱን ያሰባሰበው ኮንሶ የባህል ቡድን በቀላሉ መራመድ ችሏል። ይህንንም ምርጫ እንዲወስዱ ስላስገደዳቸው ሁኔታ ሮቤል ሲናገር፣ ገና ከመነሻው “የባህል ቡድን ብለን ብንጀምር የብሔር ብሔረሰቦችን ባህል ለማሳየት የውዝዋዜዎቹን አይነት ማጥናትና የባህል አልባሳቱንም ማግኘት ግድ ይሆንብን ነበር። ይህን ፈተና ለማለፍ እና አቅማችንን ለመገንባት ስንል መጀመሪያ ላይ ዘመናዊ የዳንስ ቡድን ሆነን ነው የጀመርነው” ይላል።

 

በኮንሶ የባህል ቡድን ውስጥ ረጅም ዓመታትን አብረው ከተጓዙት ወጣት ተወዛዋዦች መካከል ሳንታ ወዳጁ እና እመቤት አዱኛ ይጠቀሳሉ። በዕለቱ በውዝዋዜ ልምምድ ላይ ሆነው አግኝተናቸው ነበር። “ከተማሪነት ጋር ተግዳሮት የሚሆኑ ብዙ ነገሮች ቢኖሩም፤ ከዚህ ቡድን ጋር በመሆን ህልሜን እያሳካሁ ነው” የምትለው ሳንታ፤ የምታልመውን ሁሉ ከቡድኑ ጋር ለማሳካት እየሰራች እንደምትገኝ ትናገራለች። በፊት ላይ የቤተሰብና የአካባቢው ሰው ካለመረዳት የተነሳ ጫናው ቀላል እንዳልነበር የምታስታውሰው ሳንታ፤ አሁን ብዙ ነገሮች ተሻሽለዋል ባይ ነች። ይህንን የሳንታን ሀሳብ የምትጋራው እመቤትም፣ “ገና በልጅነቴ ክረምት ላይ በተቀላቀልኩት የባህል ቡድን ነው። ወደፊት ቤተሰቤን የማስተዳድርበት አቅም የሚሆነኝ ሙያ ላይ እንደተሰማራሁ ይመስለኛል” ስትል በቡድኑ ላይ ስላላት ተስፋ ትናገራለች።

 

ለኮንሶ የባህል ቡድን የመጀመሪያው የመድረክ ትርዒት የነበረው በ1999 ዓ.ም በኤግዚቢሽን ማዕከል ባዛር ላይ መታየት እንደነበር አባላቱ ያስታውሳሉ። ዳሩ ግን ትርዒቱ ፈተና የሞላበት ሆነ። “የመጀመሪያ መድረካችን ከመሆኑ የተነሳ የተጠኑ ውዝዋዜዎችን የመርሳትና የመደናገጥ አደጋ አጋጥሞን ነበር” ሲል ሮቤል አይረሴውን ዕለት ያስታውሰዋል። ያም ሆኖ በቁጭትና በእንችላለን መንፈስ ተጨማሪ ዕድል እንዲሰጣቸው የጠየቁት የኮንሶ ባህል ቡድን አባላት ማንነታቸውንና አቅማቸውን ለማሳየት ከአንድ ቀን በላይ እንዳልፈጀባቸው ያስታውሳሉ።

 

“ምክንያታዊ ጥምረት ነው ያሰባሰበን” የሚሉት የኮንሶ የባህል ቡድን አባላት፤ በፍላጐትና በውዴታ የተሰባሰቡ እንደሆኑ መስራቹ ሮቤል ይናገራል። አብዛኞቹ የቡድኑ አባላት ከዓመታት በፊት ሲሰባሰቡ ጥልቅ የሆነ ፍላጐታቸውንና ለመማርና ለመለወጥ ዝግጁ መሆናቸውን ብቻ ይዘው የመጡ እንደሆኑ ያስታውሳል። አሁን ላይ በተለያዩ መድረኮች በመስራትና በተለያዩ ድምፃዊያን ክሊፖች ውስጥ በመታየት እየታወቁም ይገኛሉ። በቅርቡም “አብሽር በለው” የተሰኘ የባህል ቪሲዲ ከድምፃዊ ሰማኸኝ በለው፣ ከተስፋይ ግደይ፣ ከነስሩ ሙክታር፣ ከፍቃዱ ብርሌ፣ ከታደሰ ዳቢ፣ ከያለው አንለይ፣ ከዳኛቸው መላኩና ከጠና ዘመላክ ጋር ሰርተው ለተመልካች አድርሰዋል። በዚህም ቪሲዲ ውስጥ የተለያዩ ባህላዊ ውዝዋዜዎችን በብቃት በመቀመር አድናቆትን እንዳገኙ ይናገራሉ።

 

“ ‘ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ፤ ለሃምሳ ሰው ጌጡ’ እንደሆነ ስለምናምን አሁን ላይ በጋራ የተሻለ ስራን እየሰራን ነው” የሚለው ሮቤል፤ ከትንሽ እስከትልቅ መድረክን በመስራት ዕውቅናቸውንና ልምዳቸውን እያዳበሩ እንደሚገኙ ይገልፃል። በሚሊኒየም አዳራሽ፣ በስብሰባ ማዕከል አዳራሽ፣ ኮከብ አዳራሽ፣ በጊዮን፣ በኤግዚቪሽን ማዕከል እና በቤተመንግስትም በተለያዩ ጊዜያት ባህላዊ ትርዒቶቻቸውን ማቅረብ መቻላቸውን ይናገራሉ። በአጠቃላይም ባለፉት አስር ዓመታት ውስጥ በአገር አቀፍ ደረጃ ተዘዋውረው ከሰባት ሺህ ያላነሱ መድረኮችን እንደተጫወቱ ያስታውሳሉ።

 

ከወራት በኋላ “አስር የሙዚቃ ኮንሰርት” የተሰኘ ዝግጅት ማሰናዳታቸውን አባላቱ ይናገራሉ። ይህም ዋና አላማው ኮንሶ የባህል ቡድንን በገንዘብ አቅም ለመደገፍ፤ ቀጥሎ ለመስራት ስለታቀደው የባህል ካምፕ ስራ ይውላል ተብሏል። በዚህ ካምፕ ላይም የኢትዮጵያውያን ባህል የሚያስተዋውቁ ስራዎች ይሰሩበታል፣ ፍላጐት ያላቸው ወጣቶች በነፃ ስልጠና ያገኙበታል ተብሎ ታቅዷል። በሙዚቃ ድግሱ ላይ አርቲስት ኩኩ ሰብስቤ፣ አቤል ሙሉጌታ፣ ሄለን በርሄና ሚኪያስ ቸርነት ተገኝተው ስራዎቻቸውን እንዲያቀርቡ በማግባባትና በመነጋገር ላይ እንደሚገኙም ታውቋል። የሙዚቃ ድግሱም ለተከታታይ አምስት ዓመታት ዓመታዊ ድግስ ሆኖ እንዲቀጥልም እንደሚፈልጉ የቡድኑ መስራችና አባላቱ ይናገራሉ። ስለሚገነባው የባህል ካምፕም ሲናገር፤ “በእኛ ጥረት ተሳክቶ የምንገነባው ከሆነ በስተመጨረሻ ሐብትነቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው” ሲል የቡድኑ መስራች ያስረዳል። ለመሆኑ ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ የሚለፋው ኮንሶ የባህል ቡድን ስያሜውን እንዴት መረጠው? ለዚህ ጥያቄ የቡድኑ መስራች ወጣት ሮቤል መልስ አለው። “በወቅቱ የኮንሶዎች ባህልና አጨፋፈር እጅግ የሚማርክ ነበር። ኢትዮጵያን በቱሪዝም ማስተዋወቅ የሚያስችል ሀብት ያለው ህዝብ በመሆኑ ጭምር ተነሳስተን ነው ስያሜያችንን ያወጣነው። በነገራችን ላይ በውስጣችን እንደማንኩሳና እንደነጉማ የመሳሰሉ አነስተኛ ቡድኖችን አቋቁመናል” ሲል ይዘረዝራል። ይህም በተለያዩ ክልሎች ያሉ ባህላዊ ጭፈራዎችን በተሰባጠረ መልኩ ለማወቅ እንደሚረዳቸው ሮቤል ይናገራል።  

 

“መልፋት የምንፈልገው የማይጠፋ ስም ለመትከል ነው” የሚለው ወጣቱ የኮንሶ ባህል ቡድን መስራች፤ በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ ለማለፍ ያስቻላቸው እርስ-በእርስ ያላቸው መማማርና መደጋገፍ እንደሆነም ይናገራል። ወደፊት ከተለያዩ አርቲስቶች ጋር በመስራትና ዓለምን በመዞር የአገራችንን ባህላዊ ውዝዋዜዎች የማስተዋወቅ ፅኑ ፍላጐት እንዳላቸውም የቡድኑ አባላት ከሚናገሩት በላይ በፊት ገፃቸው ይነበባል። “ከድሮም ጀምሮ ከይሁኔ በላይ ጋር ስራ የመስራት ፍላጐቱ አለኝ” የምትለው የኮንሶ ቡድን ተወዛዋዧ እመቤት፤ “ይህም አንድ ቀን እውን እንደሚሆን ተስፋ አለኝ” ባይ ናት።

 

ኮንሶ የባህል ቡድን በሚሰራቸው ስራዎች ባህላዊ ውዝዋዜዎችን በትክክለኛ ይዞታቸው ከመስራት በተጨማሪ አልባሳቱንም በቀጥታ ከቦታው በማስመጣት እንደሚሰራ፤ ለዚህም የሚከፈለው ዋጋ ሁሉ ውጤቱን እንደሚያሳምረው የቡድኑ አባላት ይናገራሉ። እናም ለትርኢታቸው ሲቀርቡ በእውነተኛ አልባሳትና ቦታው ድረስ በመሄድ የተጠና ውዝዋዜን ይዘው እንደሚቀርቡ በሙሉ ልብ ይናገራሉ።

አካላዊና ሥነ-አዕምሯዊ ዝግጁነትን በሚፈለገው የሙዚቃና የውዝዋዜ ስራ ውስጥ ያሉት እነዚህ ወጣቶች የላብ መተኪያቸው እነሱ “ኢትዮጵያዊት” የሚሏት “በሶ” እና “ድንች በዳቦ” እንደሆኑ ሲናገሩ ሰምተናል። ኮንሶ የባህል ቡድን የተመሰረተበትን አስረኛ ዓመት ሲያከብር በቀጣይ ያሰባቸው ነገሮች ይሳኩለት ዘንድ መንግስታዊም ሆኑ መንግስታዊ ካልሆኑ አካላት የሚጠበቀውን ድጋፍ እንደማያጡ ተስፋቸው ተስፋችን ነው።

 

በቡድናቸው የአንድነት፣ የተስፋና የእንችላለን መንፈስ ውስጥ ሆነው በመደጋገፍ ትልቅ ቦታ የመድረስ ዓላማን ያነገቡት እነዚህ ወጣቶች፤ በትግላቸው መካከል ያገዟቸውንና አሁንም ድረስ የሚደግፏቸውን አካላት ያስታውሳሉ። በተለይም በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የወረዳ 4 አስተዳደር የመለማመጃ አዳራሹን በማመቻቸት ለዓመታት ፍቃደኝነቱን በማሳየቱ ወጣቶቹ ከልባቸው ያመሰግኑታል። ከዚህም ባሻገር አሁን ላይ ተስፋ እየጣለባቸውና በስራቸው እየመዘናቸው የሚገኘውን የአካባቢውን ሰውና ቤተሰቦቻቸውንም እምነት ስለጣሉባቸው ምስጋና ይገባቸዋል ይላሉ። የባህል ቡድኑን ከማገዝ አንፃር የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮን፣ የአዲስ አበባ ወጣቶች ፌዴሬሽን፣ የአዲስ አበባ ሴቶችና ህፃናት ቢሮን፣ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በእጅጉ ተመስግነዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
16002 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1009 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us