በፍቅርና በነገር የተወጠረች “ገራገር”

Wednesday, 15 March 2017 12:14

 

የቴአትሩ ርዕስ    - “ገራገር”

ደራሲ          - ባሳዝን ገዙ

አዘጋጅ          - አብዱልከሪም ጀማል

አልባሳትና ቁሳቁስ  - የትምወርቅ በቃሉ

መብራት         - ወርቁ ታምራት

ድምፅ ባለሙያ    - ሬድዋን አወልና አምሳሉ ጌታቸው

ዝግጅት አስተባባሪ  - አብርሃም አይስሮ

ተዋንያን          - አበበ ተምትም፣ ሙሉነሽ ተሰማ፣ ፍቃዱ ከበደ፣ ሲሳይ አማረ፣ እታገኝ መልካ እና ራሄል አለሙ።

 

 

በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት መታየት ከጀመረ ሶስት ወራትን አስቆጥሯል። ስላቅ በተሞላበት የኑሮና የባህል፤ የቦታና የአስተሳሰብ፣ የፍቅርና የነገር ንፅፅሮሽን ገራገርነትና የተንኮለኝነት ሰዋዊ መነፅር በኩል ያሳየናል፤ “ገራገር” ቴአትር። . . . ኑሮዬን ባሸንፍ ብላ ከትውልድ ቀዬዋ የተሰደደችው አቻም (ራሄል አለሙ) በቴአትሩ ውስጥ የፍቅርም መቆስቆሻና መጠንሰሻ ገፀ -ባህሪይ ተደርጋ ተስላለች። ስለዚህች መሪ ገፀ ባህሪይ የቴአትሩ አዘጋጅ የሆነው ተዋናይ አብዱልከሪም ጀማል ሲናገር፤ “ከከተማ ወጣ ስንል እንደምናገኛቸው ብዙዎቹ ገራገር የባላገር ሴቶች ናት - አቻም። በተለምዶም ሆነ በተግባር የምናየው ነገር ገጠር አካባቢ ያሉ ሰዎች እጅግ ሲበዛ የዋህ ናቸው። ሞኞች ግን አይደሉም። ላመኑትና ለወደዱት ሟቾች ናቸው። በገራገር ቴአትር ውስጥ የተሳለችው ዋና ገፀ -ባህሪይም ይህንኑ የምናይባት ናት” ሲል ይገልጻታል።

ከተሜነትን በንቀት የምትታዘበው አቻም፤ ሲበዛ የዋህና ለእውነት ያደረች ሴት ናት። በቤት ሰራተኝነት በተቀጠረችበት ቤት ውስጥ ድንገት ዘመናዊና የተማረ ነው ከሚባለው አባወራው ጋር ፍቅር ብጤ የከጃጀላት አቻም፤ የፍቅራቸው ጥንስስ የጀመረበትን ቀንና ሁኔታ አስታውሳ “በጨለማ የፈፀምነውን ነገር ባህሉም ወጉም አይፈቅድም” ስትል ያደረጉትን ነገር እያስታወሰች ምክርና ተግሳጽ ታሰማለች። ይህም ብቻ አይደለም። የከተማው ወጣት ሁሉ በየመንገዱ ተቃቅፎና ተዛዝሎ ሲሄድ አስተውላ፣ “እናንተ የከተማ ሰዎች መላፋትና መላላስ ትወዳላችሁ” ስትል በትዝብት ጦሯ የሳቅ ርችትን ታፈነዳለች።

በቀድሞ ፍቅረኛው አላማ ቢስነት የተማረረው ደሳለኝ ( ሲሳይ አማረ) የአቻምን መምጣት ተከትሎ ነገሮች ሲለወጡበት እናያለን። ዳሩ ግን አንዳንድ ሰው፣ “የጣለውንም ቢሆን ሲያነሱበት አይወድምና” በቃኸኝ ብላው የሄደችው የቀድሞ ፍቅረኛው ስምረት (እታገኝ መልካ) በፍቅር ስም ለመመላለስ የነገርና የአሽሙር ስልቷን ስትሰነዝር በአቻም ባላገርነት ላይ ስትዘባበት እንመለከታታለን። በአቻም ላይ ለመሳለቅ ምክንያት የምትፈልገው ስምረት፣ “ደብሮኛል ልደበርባት ጥራት” እስከማለትም ትደርሳለች።

የአባቱን ገዳይ ለመበቀል ከተማ ላይ አደን የጀመረው የደሳለኝ የልብ ጓደኛ እንደልቡ (ፍቃዱ ከበደ) የጭቃ ውስጥ እሾህነት በሚታይበት ባህሪው አማካኝነት አንዴ ውሃ ሲለው ደግሞ እሳት እየሆነ የተንኮል እና የበቀል ድሩን ሲዘረጋ እንመለከታለን። በተለይም የእንደልቡ ገፀ-ባህሪይ “አዛኝ ቅቤ አንጓች” ዓይነት መሆኑ ተመልካች በንዴት መካከል እንዲስቅ ይገደዳል። እናም የአቻምን ገራገርነት ተጠቅሞ ደሳለኝንና ቤተሰቡን ለመበቀል የሄደበትን ርቀት ስንመለከት “ወቸው ጉድ!” ማለታችን አይቀርም።

በስድስት ትዕይንቶችና በስድስት ገፀ-ባህሪያት ተሰርቶ ለሁለት ሰዓታት በመድረክ ላይ የሚቆየው “ገራገር” ቴአትር፤ በፍቅር፣ በተስፋ፣ በሀዘንና በበቀል ሰንሰለት ተተብትቦ ገፀ-ባህሪያቱን እየጋለበ በተመልካች ፊት ራሱን ለፍርድ ያስቀምጣል። ከቴአትር ሁሉ ድራማ ለሆነ ዘውግ ልቤ ይሸፍታል የሚለው አዘጋጁ፤ ይህን ቴአትር እንዴት  እንደመረጠውና እንዳዘጋጀው ሲናገርም “የታሪክ ፍሰቱን የካራክተር (ገፀ - ባህሪይ)  ምጣኔው ገና ከመነሻው በፅሁፍ ደረጃ እንድወደው አድርጎኛል” ይላል። አክሎም የቴአትሩ አዘጋጅ አብዱልከሪም፤ “ገራገር” ማዘጋጀት ከምፈልገው ስሜት ጋር የሚሄድ በመሆኑ ደስ ብሎኝ የሰራሁት ቴአትር ነው ይላል።

ከገጠር እስከከተማ የተዘረጋውን የበቀል ወጥመድ በተመለከተም አዘጋጁ ሲያስረዳ፣ “ይህ በእውነታው አለምም ቢሆን ያለ ነገር ነው። እንደውም ታሪኩን ገና በፅሁፍ ደረጃ ሳነበው ከዚህም በላይ ነበረ። በቴአትር ጥበብ ሞርደን አስተካከልነው እንጂ የበቀል ጥማቱ እጅግ የበዛ ነበር ማለት እችላለሁ” ሲል ይገልፀዋል።

“ገራገር” ቴአትር በዝግጅት ሂደቱ ፈተና የገጠመው እንደነበር አዘጋጁ ያስታውሳል። ተዋንያኑ በተለያዩ ስራዎች ተወጥረው እንደነበር ያስታወሰው አብዱልከሪም፤ “ተዋንያኑ የሬዲዮና የቲቪ ድራማዎች ላይ እንዲሁም በፊልም ስራዎች ውስጥ ስለነበሩ ተሰባስበን ወደስራ ለመግባት ትንሽ ፈተና ሆኖብን ነበር” ይላል። ጊዜን አመቻምቶ ከመስራት ውጪ የልምምድ መድረኮችን ለማግኘትና ቴክኒካል ድጋፍ ለማግኘት የነበረው ቢሮክራሲ ራሱን የቻለ ፈተና ነበር የሚለው አዘጋጁ፣ ነገር ግን ሁላችንም በመግባባትና በመተባበር ስለስራን ለመድረክ ልናበቃው ችለናል ሲል ያስረዳል።

ገፀ-ባህሪያቱ እነርሱን የሚመጥን የቋንቋ እና የንግግር ዘዬ በትክክል ተወጥተውታል። ከሁሉም ውበትን እንድናይበት እንደልቡ (ፍቃዱ ከበደ) የተጠቀማት አገላለጽ ትማርካለች። ይህ ገፀ- ባህሪይ ስለ አቻም ውበት ሲናገር፣ “የውበት መዝገብ ናት” ይላታል። በፍቅሯ እፍ ክንፍ ያለው ደሳለኝ፤ አቻምን ለማግባት ሲወስን፣ “እወድሻለሁ፣ አገባሻለሁ፤ ከእንግዲህ ሰራተኛዬ ሳትሆኚ ሚስቴ ነሽ” ይላታል። አቻም በበኩሏ የአነጋገር ዘዬዋ እንዳለ ሆኖ በሆነ ባልሆነው “ከኔ ሌላ ማን አላቸው ብዬ” እያለች የፈጸመችውን ገድል ስትተርክ ተመልካችን በሳቅ ባህር ላይ ታንሳፍፋለች። የመጀመሪያዋን ምሽት ግንኙነት ስትተርክም፣ “ግልገል ሱሪ ገዝተው ለኪው አሉኝ። . . . እኔም ከኔ ሌላ ማን አላቸው ብዬ ግልገል ሱሪዋን አጠለኩ። መልሰው ብርድ -ብርድ ብሎኛልና ከጎኔ አረፍ ብለሽ አሙቂኝ አሉኝ። . . . እኔ ደግሞ ከኔ ሌላ ማን ሊመጣላቸው ብዬ ልብሴን አውልቄ ከጎናቸው ሻጥ አልኩ” ትላለች።

ዘወትር ረቡዕ በ11፡30 ሰዓት በሀገር ፍቅር ቴአትር በመታየት ላይ የሚገኘው “ገራገር” ለመድረክ ከበቃበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ተመልካች እንደወደደው የሚናገረው አዘጋጁ፤ አሁንም ሌሎች ተመልካቾች መጥተው በማየት የሚሰማቸውን ነገር ቢገልጹላቸው ከደስታ ጋር እንቀበላቸዋለን ይላል። በአንጋፋና ወጣት ተዋንያን የተቀመረው “ገራገር” ቴአትር፤ በገራገር ልብ ውስጥ የተቀበረን ርህራሄ፣ ፍቅርና ተስፋ በአንድ በኩል በሌላ ፅንፍ ደግሞ በቀል፣ ተንኮልና ቅናት እዚህና እዚያ ይጓተታሉ። ማን ያሸንፍ ይሆን? መልሱን ከቴአትሩ ተመልከቱ!

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
16356 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1081 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us