ከጎዳና መፅሐፍ አዟሪነት ወደ አሳታሚነት

Wednesday, 22 March 2017 12:16

 

ወደመካከለኛ ባለሃብትነት እየተጓዘ ያለ ወጣት ኢንተርፕረነር ነው። ስታዲየም አካባቢ ናሽናል ታወር ሕንጻ ሥር በሚገኘው የመጽሐፍት መደብሩ ጎራ ባልኩኝ ቁጥር መጽሐፍት ሲሸከም፣ ሲያወጣ ሲያወርድ አየዋለሁ። ይህ ወጣት መካከለኛ ባለሃብት ነውና ከፍሎ ለማሰራት አቅም አጥቶ አልነበረም። ከአቅም በላይ ካልሆነበት በስተቀር ይህን አማራጭ አይሞክረውም። ለድርጅቱ ዕድገት መሸከም ካለበት ይሸከማል። በቃ! ከሥጋና ከአጥንት ጋር የተሳሰረ የሥራ ፍቅር ይሉሃል ይሄ ነው።

የዛሬው የመዝናኛ ዓምድ እንግዳ አቶ ፋንታሁን አቤ ይባላል። ተወልዶ ያደገው ባህርዳር ዙሪያ በምትገኝ አዴት በምትባል ከተማ ነው። የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እዚያው አጠናቆ የከፍተኛ ትምህርቱን ለመከታተል ባህርዳር ዩኒቨርሰቲ ገባ። ሁለት ዓመት በዕጽዋት ሳይንስ ተማረ። ነገር ግን ትምህርቱን ወደፊት ለመግፋት የማያስችል የጤና እክል በድንገት ሲገጥመው ትምህርቱን ለማቋረጥ ተገደደ። ሳይደግስ አይጣላም ነውና ሕመሙ ወደአዲስአበባ እንዲመጣም ምክንያት ሆነው። አዲስአበባ እንደመጣ አጎቱ ጋር አረፍ ብሎ ሕክምናውን መከታተል ጀመረ። ጤናውም ተመለሰ። ወደባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ተመልሶ ትምህርቱን የመቀጠል ሃሳብ ነበረውና አመለከተ። ነገር ግን ዩኒቨርሲቲው ሊቀበለው አልቻለም። እናም ፊቱን ወደአዲስአበባ መልሶ ለእሱ የሚሆነውን ሥራ ማፈላለግ ያዘ። ፋንታሁን ከቅጥር ይልቅ እንዴት የራሱ ሥራ ባለቤት እንደሚሆን እያሰላሰለ፣ እያወጣ እያወረደ ባለበት ወቅት የመጽሐፍት ንግድ ላይ ዓይኑ አረፈ። ሥራውን ላይ ላዩን ተመለከተው፣ አጠናው። እንጀራው ሊሆን እንደሚችል ለመወሰን ጊዜ አልፈጀበትም። ግን ወደሥራው ዘው ብሎ ለመግባት የመነሻ ካፒታል ነገር የመጀመሪያው ማነቆ ነበር። አጎቱን ሲያማክር “በርታ” ከሚል ምርቃት ጋር 800 ብር አበደሩት። ገንዘብዋ ትንሽ ብትሆንም እሷኑ ይዞ ወደመጽሐፍ መቸርቸር ሥራ ለመግባት አላመነታም። ቄራ አካባቢ ጎዳና ላይ ሥራውን አሀዱ አለ። ፋንታሁን “የጎዳና ላይ የመጽሐፍ ንግድ እጅግ በበዛ ፈተና የተሞላ ነው” ይላል። አሁን ላይ ሆኖ ሲያስበውም ያንገሸግሸዋል። ጎዳና ላይ ሲነግድ እንደተለመደው ፖሊስ አባሮታል፣ የቀበሌ ደንቦች በሰዶ ማሳደድ ንብረቱን እስከመውረስ ቀጥተውታል፣ ድብደባም ገጥሞታል። ከሁሉም አስገራሚው የትራፊክ ፖሊስ ባልተለመደ ሁኔታ መንገድ በመዝጋት ካርኒ ቆርጦ ልክ እንደመኪና አሽከርካሪ መንገድ ትራንስፖርት ወስዶ ቀጥቶታል። ቅጣቱን ሊከፍል መንገድ ትራንስፖርት ሲሄድ የመኪና ታርጋ ተጠይቆ እግረኛ ተቀጪ መሆኑን ሲናገር ተገርመዋል። አንዳንዶቹም «እስቲ ደንብ አስከባሪ እያለ ትራፊክ ፖሊስ ምንአገባው፣ ቂም አላችሁ ወይ» እያሉ ገረሜታቸውን፣ አዘኔታቸውን አካፍለውታል።

አንድ ጊዜ ደግሞ የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ መጣና መጽሐፍት አዟሪዎች ንብረታቸው ታሰረ። ከእነዚህ መካከል ፋንታሁን አንዱ ነበር። አንድ ወር ገደማ ንብረቱ ባለመመለሱ የዕለት ዳቦ ለመብላት እንኳን የሰው እጅ ለማየት ተገደደ። ቤት ኪራይ መክፈል ባለመቻሉ ቤቱን ለቅቆ በአንድ ጓደኛው በጎ ፈቃድ እቤቱ ተዳበለ። የተያዘባቸውን መጽሐፍት ከአንድ ወር በኃላ ሲለቀቅ በቅጣት መልክ ገንዘብ ክፈሉ ተባለ። ፋንታሁን ሌላ ፈተና ከፊቱ ተደቀነ። የሚከፍለው ገንዘብ አልነበረውም። በኋላም በዚሁ ዘርፍ ውስጥ የሚገኘው ጃፋር ገንዘብ ሰጥቶት የተያዘበትን መጽሐፍት ማስለቀቅ ቻለ። እንደገና ለንግድ ወደጎዳና ቢመለስም ነገሮች አልጋ በአልጋ ሊሆኑለት አልቻሉም። እናም ሌሎች አማራጮችን ማየት ነበረበት። ለገሀር አካባቢ በተለምዶ አርከበ ሱቅ ተብለው ከሚታወቁት አንዱን ከግለሰቦች በኪራይ መልክ ለማግኘት ቻለ። እነዚህን ሱቆች ደግሞ ለሌላ ሶስተኛ ወገን ማከራየት ሕገወጥ ስለነበር ትንሽ እንደሰራበት ሌላ ችግር ገጠመው። ከሱቁ ተባረረ። ፋንታሁን በእንደዚህ ዓይነት ችግሮች ውስጥ አልፎ የራሱን አነስተኛ ኪዮስክ እስኪከፍት ድረስ በኑሮ ውጣውረድ ተፈትኗል። ባለታሪኩ ጋር ያደረግነው ቆይታ ይቀጥላል።….

      ሰንደቅ፡- ከጎዳና መጽሐፍ መቸርቸር እንዴት ልትወጣ ቻከልክ?

አቶ ፋንታሁን፡- ለእኔ ዕድገት መሰረት የሆኑኝ ኤሚ እንግዳ እና ጥበቡ በለጠ የሚባሉ ሰዎች ናቸው። ትልቅ ውለታ ውለውልኛል። መንገድ ላይ እያለሁኝ ነው «ያ- ትውልድ» የተሰኘ የክፍሉ ታደሰን መፅሐፍ እንዳከፋፍል ሰጡኝ። ኤሚ ሸጠህ ትከፍለናለህ ብላ ሥራውን ከጠችኝ በሃላ በዚያው መንገድ ተጉዤ መጽሐፍ ወደማከፋፈልና በኋላም ወደማሳተም ተሸጋግሬአለሁ።

      ሰንደቅ፡- በአሁኑ ሰዓት ስላለህበት ደረጃ ብትነግረኝ?

አቶ ፋንታሁን፡- ቢቀረኝም ካሰብኩት ደረጃ ላይ ደርሼያለሁ ብዬ ነው የማስበው። ብዙ ነገሮች መሥራት እፈልጋለሁ። አሁን ከደራሲዎች መፅሐፍ ተረክበን የምናከፋፍለው ከደራሲዎች ሸጠን መጨረሻ ላይ ልንከፍላቸው ተስማምተን (በኮንሳይመንት)  ነው። ደራሲዎች የላባቸውን ፍሬ እንዲያገኙ መጽሐፍ ስንረከብ በእጅ በእጅ ሽያጭ ለመቀበል አቅደን መተግበርም ጀምረናል። ለምሳሌ በቅርብ የታተመው «በፍቅር ሥም» የሚለውን የአለማየሁ ገላጋይ መጽሐፍ በካሽ ገዝተን እያከፋፈልን ነው። ሌሎችም በርካታ መጽሐፍት በተመሳሳይ መንገድ የተረከብናቸው አሉ። በተጨማሪም የኤፍሬም ሥዩም “ተዋናይ” የሚል፣ «እመጓ»፣ «ዝጓራ»፣ የክፍሉ ታደሰ “ያ-ትውልድ” ከአንድ እስከ ሶስት፣ እና ሌሎች በርካታ መፅሐፍት አከፋፍለናል፣ በማከፋፈል ላይም እንገኛለን። የ“ሳጥናኤል ጎል”፣ «ማንተቄል»፣ «ወደጥቁር ገዳም» ጨምሮ በአጠቃላይ ወደሰባት የሚሆኑ መጽሐፍትን አሳትመን አከፋፍለናል።

      ሰንደቅ፡- ስለዘርፉ ምን ትላለህ?

አቶ ፋንታሁን፡- ይህ ዘርፍ ትልቅ ግን በአሳዛኝ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው። ሌሎች ዘርፎች ማህበር ሲኖራቸው ይህ ዘርፍ የራሱ ማህበር እንኳን የሌለው ነው። የመጽሐፍ ሻጭ/አከፋፋዮች ማህበር የሚባል የለውም። ዘርፉ እያደገ ያለ ነው። ይበልጥ ለማደግም ተስፋ ያለው ነው። ዘርፉ የበለጠ እንዲያድግ የንባብ ባህል ማደግ አለበት። በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ውስጥ 100 ሚሊዮን ሕዝብ አለ ነው የሚባለው። ከዚህ ሕዝብ ውስጥ ግማሽ ያህሉ በዕድሜው ወጣት ነው። በአንጻሩ ግን ይህን ያህል ሕዝብ እያለ 3ሺ መጽሐፍ ተሸጦ የማያልቅበት አጋጣሚ አለ። ይሄ ምን ያህል አንባቢ እንደሌለ የሚያሳይ ነው። ምን ያህል የማንበብ ባህላችን ደካማ መሆኑን ያሳያል። 3ሺ መጽሐፍ ለአንድ ሕንጻ ነዋሪ የማይበቃ ነው። ይሄ ዘርፍ በዚህ ረገድ ወደኋላ ቀርቷል። ሀገር የሚያድገው አንባቢ ትውልድ መፍጠር ሲቻል ነው። ይህ ዘርፍ የራሱ ማህበር ኖሮት ወደፊት ደራሲውም፣ አከፋፋዩም የሚጠቀምበት ዘርፍ እንዲሆን ሁላችንም መጣር አለብን።

      ሰንደቅ፡- አንባቢ ቀንሷል፣ አልቀነሰም የሚሉ ክርክሮች አሉ። አንተ በዘርፉ ውስጥ እንደመኖርህ ይህን ጉዳይ እንዴት ነው የምታየው?

አቶ ፋንታሁን፡- እንደምንሰማው ከዛሬ ሃያ እና ሰላሳ ዓመታት በፊት በኢትዮጽያ አንድ መጽሐፍ እስከ 60ሺ ኮፒ የሚታተምበት ሁኔታ ነበር። በጣም አንባቢ እንዳለ ያሳያል። አሁን በአብዛኛው እንደዚህ አይደለም። በመካከል የሆነ ክፍተት አለ። የአሁኑ ትውልድ አንባቢ ነው ማለት ይከብደኛል። ከማየው፣ ከሥራዬ አኳያ ስገመግመው ማለቴ ነው። ለዚህ ብዙ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። አንደኛ ግልብ ትውልድ ነው ይባላል። ላይ ላዩን የሚሄድ ነው ብለው የሚወቅሱት አሉ። ዘመኑ በፈጠረው የኢንተርኔት ወሬ ብቻ የተወሰነ ነው። ጠለቅ ብሎ የመመርመር፣ ታሪክን የመፈተሽ ነገር ይጎድለዋል። አንዳንዶች ደግሞ አንባቢው ቀድሞ ሄዶ ጸሐፊዎች (ደራሲዎች) ወደኋላ ቀርተዋል ብለው የሚሉ ወገኖች አሉ። ትውልዱን የሚመጥኑ ሥራዎች እየቀረቡ ባለመሆናቸው ነው አንባቢ የሸሸው የሚሉ አሉ። እርግጥ ነው እኛም በሥራችን ስናይ ጥሩ ዋጋ የሚያወጡት፣ የሚፈለጉት የድሮ መፅሐፍት ናቸው። ለምን ሲባል የዚያኔ ፀሐፊዎች ቀጣዩን ትውልድ ጭምር አይተው ስለሰሩ ይመስለኛል። ሥራቸው ዘመን ተሻጋሪ ነው። በአሁኑ ጊዜ ያሉ ፀሐፊዎች ትንሽ ወደኋላ የመቅረት አዝማሚያ ያላቸው መሆኑ እውነት አለው። በአሁኑ ጊዜ ያልበሰሉ ሥራዎች ታትመው ይወጣሉ። ተጨባጭነት የሌላቸው፣ ድግግሞሽ የሚታይባቸው ሥራዎች ይመጣሉ። ዝም ብሎ በስሜት የሚፃፉ መጽሐፍት በብዛት አሉ።

 በአጠቃላይ ዘርፉን በተመለከተ መደገፍ፣ መበረታታት ያለበት ነው። ትውልድ የሚቀርጽ፣ የሚያነቃ ዘርፍ ነው። ይሄ ትኩረት ተሰጥቶበት ቢሰራበት በአሁኑ ጊዜ ብቻውን በራሱ ጥረት ብቻ እየተውተረተረ ያለበት ሁኔታ ነው። “ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል” የሚለው በተግባር መተርጎም መቻል አለበት። በየቦታው የሕዝብ ቤተመፃህፍት መስፋፋት አለባቸው። ተንቀሳቃሽ የመፅሐፍት ላይብረሪዎች፣ በየአውቶቡስ ፌርማታው ሁሉ ቢኖሩ የበለጠ ትውልዱን ለንባብ ለማነቃቃት ይረዳል ብዬ አስባለሁ።

      ሰንደቅ፡- የመጽሐፍት ዋጋ መብዛት ተነባቢነትን ቀንሷል የሚሉም ወገኖች አሉ?

አቶ ፋንታሁን፡- እንደምታየው የሸቀጦች ዋጋ በየጊዜው እየጨመረ ነው። ለመጽሀፍት ህትመትም የሚወጣው ወጪ እንዲሁ እየጨመረ መጥቷል። ከምንም በላይ መፅሐፍት የዕውቀት ምንጮች ናቸው። ዕውቀትን ደግሞ በገንዘብ አትለካውም። ዕውቀት መጋቢዎች ናቸው። አንድ ኪሎ ሥጋ 300 ብር ገዝተን እየበላን እኮ ነው። ለሆዳችን ይህን ያህል ካወጣን ለአእምሮ ምግብ ከዚህም በላይ ብናወጣ እንኳን ተገቢ ነው። ሆዳችን ምግብ እንደሚያስፈልገው ሁሉ፣ ለአእምሮአችንም ምግብ ያስፈልገዋል። የአእምሮ ምግብ መፅሐፍት ናቸው። የአእምሮ ምግብ የማይጠፋ ቋሚ ሐብት ነው። እነዚህ በዋጋ የምንለካቸውም አይደሉም። ስለዚህ በግሌ ተወዷል ለማለት አልችልም።    

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
16180 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1159 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us