ከብዙ በጥቂቱ ስለኢትዮ- አየርላንዳዊቷ ተዋናይት ሩት ነጋ

Wednesday, 29 March 2017 11:47

 

ከሳምንታት በፊት በተካሄደው 2017 የኦስካር ሽልማት ስነ-ስርዓት ላይ በርካታ የዓለማችን የፊልም ባለሙያዎች በተለያዩ ዘርፎች እጬ ሆነው ቀርበዋል። ከአንጋፋ እስከወጣቶች፤ ከተለያየ ዓለማት የተውጣጡ የፊልም ባለሙያዎች በተለያዩ ዘርፎች ለዓመታዊውና አለማቀፋዊው የኦስካር ሽልማት በእጩነት ከመቅረብ አንስቶ ዕድሉ የቀናቸውም አሸናፊ ሆነዋል። ለ89ኛው ጊዜ በተከሔደው በዚህ የኦስካር የሽልማት ስነ-ስርዓት ላይ ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ሩት ነጋም በምርጥ ተዋናይት ዘርፍ ዕጩ ሆና መቅረቧ ይታወሳል። ምንም እንኳን የአሸናፊነት አክሊሉን ባትደፋም።

ዛሬ በዚህ በመዝናኛ አምዳችን ላይ ከብዙ በጥቂቱም ቢሆን ስለትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ተዋናይት ሩት ነጋ እንጨዋወታለን። እ.ኤ.አ. በ1982 በአዲስ አበባ ከተማ የተወለደችው ይህቺ ተዋናይት፤ በአባቷ ኢትዮጵያዊ በእናቷ ደግሞ የአየርላንድ ዘር አላት። እስከ አራተኛ ዓመቷ ድረስ እድገቷን በኢትዮጵያ ያደረገችው ሩት፤ ከዚያም ወደእንግሊዝ ማቅናቷንና የፊልም ትምህርትም በዚያው ቆይታ እንደተከታተለች ታሪኳ ይናገራል።

ከአባቷ ከዶ/ር ነጋ እና ነርስ ሆና ከአየርላንድ ወደኢትዮጵያ ከመጣችው እናቷ ኖራ የተወለደችው ተዋናይት ሩት ነጋ፤ ገና የሰባት ዓመት ህፃን እያለች አባቷን በመኪና አደጋ ያጣችና ለቤተሰቦቿ ብቸኛ ልጅ እንደሆነች ታሪኳ ይናገራል። ሆኖም ግን  በእናቷ በኩል ሰፊ የቤተሰብ ሀረግ ያላት በመሆኑ በፅኑ ቤተሰባዊ ፍቅር ውስጥ እንዳደገች ትናገራለች። የትምህርት ጊዜዋን በለንደን ያጠናከረችው ሩት፤ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ደብሊን ውስጥ በሚገኝ ትሪኒቲ የተሰኘ ኮሌጅ በትወና ዘርፍ አግኝታለች። አሁን ላይ ከታዋቂው የፊልም ባለሙያ ዶሚኒክ ኩፐር ጋር ከ2010 ጀምሮ በመሰረቱት ትዳር አብረው እየኖሩ እንደሆነ ቢታመንም አንዳንድ ወሬ አነፍናፊ ሚዲያዎች ግን ፍቅራቸው ነፋስ እንደገባው በተለያዩ ጊዜያት ሲናገሩ ተሰምቷል። ከዕድሜ እኩዮቿ ለየት ብሎ መታየቱ ሁሌም ቢሆን ግራ ያጋባት እንደነበር የምትናገረው ሩት፤ እያደኩ ስመጣ ግን ልዩ የሆንኩት ከሁለት ዘር በመገኘቴ ነው ትላለች።

ወደዓለም አቀፉ ሲኒማ የተቀላለችው “Capital Latters” (200 እ.ኤ.አ.) በተሰኘው ፊልም ነበር። በመቀጠልም “Isolation” (በ2005 እ.ኤ.አ.) የተሰኘ ፊልም ላይ ተሳትፋለች። በዚያው ዓመት “Breakfast on pluto” የተሰኘው ሳይንስ ፊክሽን ዘውግ ያለውን ፊልም ለተመልካች ይዛ ቀርባለች።

በ2016 (እ.ኤ.አ) “War craft” የተሰኘ ፊልም ይዛ ከመጣች በኋላም ከሲኒማ ቤት መልስ በቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማዎችም አቅሟን አሳይታለች። ከሰራቻቸው ተከታታይ ፊልሞች መካከልም “Doctors” እና “Criminal Justice” የተሰኙት ስራዎቿ በተመልካች ዘንድ እጅግ ተወዳጅ ከሆኑት መካከል ተጠቃሾች ናቸው።

ባሳለፍነው የፈረንጆች ዓመት መጨረሻ አካባቢ ለዕይታ የበቃው `Loving` የተሰኘ የፍቅር ድራማ ይዘት ያለውን ፊልም ተከትሎ በምርጥ ተዋናይት ዘርፍ በኦስካር መድረክ እጩ ሆና ቀርባለች። ምንም እንኳን ከአንጋፋዎቹ ሜሪል ስትሪፕ እና ናታሊ ፖርትማንን ከመሳሰሉ ተዋንያን ተርታ ተጠርታ ሽልማቱን ባታገኝም በእጩነት መቅረቧ በራሱ በመጪዎቹ ዓመታት የመድረኩ ንግስት እንደምትሆን ፍንጭ የሰጠ እንደሆነ ዓለምአቀፍ የፊልም ሃያሲያን ተናግረዋል። እዚህ ትደርሳለች ያልተባችው ይህቺ ተዋናይት አሁን የበርካታ አድናቂዎች አይን እና ጆሮ የሚከተላት አይነት ምስጉን ባለሙያ ሆናለች። “የዕውቅናዬ ምስጢር ስራዎቼን የምሰራው ለዕውቅና ብዬ አለመሆኑ ነው። ጥበብን እወዳለሁ። ስለምወደም ለእርካታዬ ነው የምሰራው” ስትል ትናገራለች። ስለትውልድ ሀገሯ ኢትዮጵያም በምታነባቸው የታሪክ መፅሐፍት ላይ ተመርኩዛ ብዙ እንደምታውቅ በተለያዩ አጋጣሚዎች ካደረገቻቸው ቃለ-ምልልሶች ስትናገር ትደመጣለች። 

በፈረንጆቹ አቆጣጠር የካቲት 26 ቀን 2017 የኦስካር ምሽት ላይ የኛዋ ሩት ነጋ በ“Loving” ፊልም በምርጥ ተዋናይት ዘርፍ እጩ ሆና ስትቀርብ አብረዋት የቀረቡት ደግሞ፤ ናታሊ ፖርትማን በ“Jackie”፣ ለ20ኛ ጊዜ ዕጩ ሆና የቀረበችው ሜሪል ስትሪፕ በ“Flarance Foster Jenkins”፣ ኢማ ስቶን በ“La La Land” እንዲሁም ኢሳቤል ሃፐርት በ“Elle” የመጨረሻ አምስት ዕጩዎች ሆነው ቀርበዋል። በምሽቱ የ89ኛ ኦስካር አሸናፊ ሆና ለሽልማት የበቃችው ኤማ ስቶን በ “La La Land” ፊልሟ ሆናለች።

የኛዋ ሩት ነጋ የተሰጧትን ገፀ-ባህሪያት በብቃት በመተወን በመድረክም ሆነ በፊልም ስራዎቿ ከፍታዋን ስታሳይ፤ በበርካታ የፊልም ዳይሬክተሮች አይንም ለመታየትና ለመፈለግ በቅታለች። እናም በርካታ ፊልሞችንና ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች ላይ መተወኗን ቀጠለች። ኢትዮ - አየርላንዳዊቷ የ35 ዓመት ተዋናይት ሩት ነጋ፤ ወደትውናው ዓለም ከተቀላቀለችበት ጊዜ ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ ሰባት አጫጭር ፊልሞችን፤ አስራ ሦስት ረጃጅም ፊልሞችን፣ አስራ ሁለት ተከታታይ የቴሌቭዥን ድራማዎች እና በርከት ያሉ ቴአትሮች ላይ ተሳትፋለች።

ከፊልምና ከተከታታይ የቴሌቭዥን ስራዎቿ በተጨማሪም በመድረክ የሰራቻቸውም ቴአትሮች በርካታ ናቸው። ከእነዚህም ውስጥ በ2010 (እ.ኤ.አ.) ፓን-ፓን ከተሰኘው የአይሪሽ ቴአትር ቡድን ጋር በመሆን “ሀምሌት” ተሰኘውን የዊሊያም ሼክሰፒር ስራ ውስጥ የኦፌላን ገፀ-ባህሪይ ድንቅ አድርጋ ተውናበታለች። በካርቱን ፊልሞችም ቢሆን ሩት ነጋ “Dark Souls II” የተሰኘ ፊልም ውስጥ በድምፅ ተሳትፋለች።

በእውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ የተሰራውና ዘንድሮ ለኦስካር እጩ የሆነችበት “ላቪንግ” ፊልም በካን ፊልም ፌስቲቫልም ዕጩ ሆኖ መቅረብ የቻለ ተወዳጅ ስራ እንደሆነ የፊልም ባለሙያዎች ይናገራሉ። የፊልሙ ታሪክ የሚያተኩረው በቀለም የሚለያዩ ነገር ግን በእጅጉ ስለሚዋደዱ የ1950ዎቹና 60ዎቹ የቨርጂኒያ ነዋሪዎች ታሪክ ነው። ሩት ነጋ በዚህ ፊልም ኦስካርን ጨምሮ በአፍሪካ ፊልም ከሪቲክስ አዋርድና በሌሎችም በርካታ መድረኮች ዕጩ ሆና ከመቅረብ ባለፈ ስድስት ያህል ሽልማቶችንም አግኝታበታለች።

ከዚህ “Loving” ከተሰኘው ፊልም ውጪም ቢሆን ሩት ነጋ ለበርካታ ጊዜያት በተለያዩ የሽልማት መድረኮች ላይ ስሟ ተነስቷል። ለመጠቃቀስ ያህልም በ2003 በሰራችው “ደክ” በተሰኘ የመድረክ ቴአትር በምርጥ አዲስ ተስፋ የተጣለባት ተዋናይት ዘርፍ በሀገረ-እንግሊዝ በሚካሄደው ኦሊቨር አዋርድ መድረክ ዕጩ ሆና ቀርባለች። በመቀጠልም በ2006 በብርሊን ፊልም ፌስቲቫል በአየርላንድ እያንፀባረቀች የመጣች ኮከብ በሚል ተሸላሚ ሆናለች።

በቲቪ ድራማ ዘርፍ “Doctors” የመጀመሪያ ተከታታይ ድራማ ስራ ሲሆን፤ በመቀጠልም “Criminal Justice” እንዲሁም የታዋቂዋን ድምፃዊ ሺርሊ ቤዝን ገፀ-ባህሪይ ተላብሳ የተወነችበት “Shirley” (2011) የተሰኘው ተከታታይ ድራማ በኦይሪሽ ፊልምና ቴሌቪዥን የሽልማት መድረክ (IFTA) ላይ በምርጥ መሪ ተዋናይት ዘርፍ ተሸላሚ እንድትሆን አድርጓታል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
16000 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 936 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us