የአባይ ዳር ጨዋታ

Wednesday, 05 April 2017 12:19

በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ስለነገ ተስፋ ከሚያደርጉበት ነገር መካከል አንዱና ዋነኛው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ስለመሆኑ ማሳያዎቹ ብዙ ናቸው። በርካቶች ወደው የቦንድ ግዢ ያደርጋሉ፤ ጥቂቶችም በውዴታ ግዴታ ውስጥ ሆነው የቻሉትን ያዋጣሉ። ቀሪዎቹ ደግሞ “ተገደን ነው” በሚል መንፈስም ውስጥ ሆነው ቢሆን ለግድቡ ጠጠር መወርወራቸው አልቀረም። ይህም ከምንም በላይ በማጣት፣ በማጉደልና በተስፋም ቢሆን ኢትዮጵያውያንን ያስተሳሰረ ታላቅ ግድብ ለመሆኑ ምስክር ይመስላል።

ዘንድሮ የታላቁ የህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበትን 6ኛ ዓመት በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች መከበሩ ይታወቃል። ከዚህም መካከል ባሳለፍነው እሁድ (መጋቢት 24 ቀን 2009 ዓ.ም) በጋምቤላ ክልል ጎባ ወረዳ በሚገኘውና የአባይ ግድብ መሰረቱን ጥሎ ከሚሳለጥበት ስፍራ የነበረው ዝግጅት አንዱ ነበር። በርካታ ባለስልጣናት፤ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ ባለሙያዎችና፣ የኪነ-ጥበብ ሰዎችም ተገኝተዋል። ወደስፍራው ለማቅናት ካደርንበት የጋምቤላ ክልል ዋና ከተማ አሶሳ የተነሳነው በሌሊት ነበር። የፀሐዩዋ ግለት ከንዳድነት አልፎ የሚፈጥረው ወበቃማ አየር ለበርካቶች ፈተና ነበር። ዳሩ ግን ይህን የአየር ሁኔታ ተቋቁመውም ቢሆን ላለፉት ስድስት አመታት በዚያው ስራ ላይ የቆዩ ባለሙያዎችን ባሰብን ቁጥር መደነቃችን አልቀረም።

በጉዟችን መካከል ካገኘናቸው አንጋፋ አርቲስቶች መካከል አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬ እና አርቲስት ሽመላሽ ለጋስ ይገኙበታል። . . . በመንገዳችን ላይ “የህዝቡን ስሜት የሚያንፀባርቁ ጥቅስ አከል መፈክሮችና ግጥሞች እንዲህ ይላሉ፡- “አባይ ድሮ ይጠጣ ነበር፣ አሁን ግን ሊበላ ነው። አባይ ከነአፈሩ ወደሀገሩ!” ሌላኛውም ይቀጥላል፣

“አባይ ተገድቦ ልማቱን አይቼ፣

እኔ ነገ ልሙት ልጆቼን ተክቼ”

ይህንን የህዝብ ስሜት በአርቲስቶቻችን አስተያየት ውስጥ እናገኘዋለን። በበርካታ የሬዲዮና የቲቪ ድራማዎቹና ማስታወቂያዎቹ የምናውቀው አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬ፤ እነሆ እንደዘመኑ በርካታ ፊልሞችን ከመስራት አልፎ ሉሲ ኤፍ ኤም 107.8 ከአጋሮቹ ጋር ይዞልን ሊመጣ ወራት ቀርተውኛል ይላል። ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ጉብኝት መልስ አሶሳ ላይ ስንገናኝ፣ “አባይን ከመሰረቱ ጀምሮ እናውቀዋለንና እንደልጃችን ነው የምናየው” ሲል ይጀምራል ስለታላቁ የህዳሴ ግድብ ሲናገር። ገና ከመነሻው (ከመሰረት ድንጋይ መጣሉ) ጀምሮ አብሮ እንደነበር የሚናገረው አርቲስት ሰራዊት፣ “እዚህ ድረስ መጥህ ስታየው፤ ሚዲያዎቻችን ከግድቡ ግዝፈትና ውስብስብነት አንጻር በደንብ እንዳልገለፁት ትረዳለህ” ይላል። መደነቁን በሚያሳብቅበት መንፈስ ሆኖ ይናገራል።

ገና የመሰረት ድንጋይ ሲጣል ጀምሮ ትልቅ ደስታ ተሰምቶት እንደነበር የሚናገረው ደግሞ አርቲስት ሺመላሽ ለጋስ ነው። ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የግድቡን ግንባታ በቦታው ተገኝቶ ጎብኝቷል። “ሁላችንም አባይን በቁጭት ነበር የምንዘፍንለት። አሁን እንዲህ በአካል ሳየው በእጅጉ ተነቃቅቻለሁ። እስካሁንም ቦንድ ገዝቻለሁ። ስለአባይ ማስታወቂያው በነፃ ሰርቻለሁ። ወደፊትም ግድቡ እስኪያልቅ የአቅሜን አደርጋለሁ” የሚለው አርቲስት ሺመላሽ ተጠናቆ በጀልባ መንሸራሸርና አሳ በልቶ መመለስንም ይመኛል።

አባይ ከስነ ቃል ማጣፈጫነቱና ከዘፈን ማድመቂያነቱ በዘለለ ለሀገራችን ኪነ-ጥበብ እንደግብአትና የመነሻ ሀሳብነት መነገር አለበት የሚለው አርቲስተ ሰራዊት፣ “ይህ ግድብ በስኬት ሲጠናቀቅ የድሮ ቅኝታችን ሙሉ በሙሉ ይቀይረዋል። የአባይን ልጅ ውሃ ጠማው” “አባይ ማደሪያ ያለው ግንድ ይዞ ይዞራል” ይሉት ተረት ሁሉ ይቀየራል። ከዚያ ውጪ ደግሞ ኪነ-ጥበብ የበርካታ ነገሮች ውጤት እንደመሆኑ መጠን፤ አንድ ጥሩ ሙዚቃ ካለ ጥሩ ፊልም ሊወጣው ይችላል። ጥሩ ፊልም ጥሩ መፅሐፍ ሊወጣው ይቻላል። ጥሩ መፅሐፍ ደግሞ መልሶ ጥሩ ዘፈን ሊወጣው ይችላል። በተመሳሳይ ይሄ ግድብ ጥሩ ሆኖ ሲጠናቀቅ ብዙ ጥሩ ጥሩ ሃሳቦችን የምናነሳበት ይሆናል ብዬ አስባለሁ። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ታላቅነት፣ አሁን እያደረግን ያለነውን ጉዞ፣ የጀመርነውን ነገር መጨረስ እንደምንችል ሁሉ ማሳየት የምንችልበት ነው” ይለናል። ይህንንም ተንተርሶ “ድር ቢያብር አንበሳን ድብን  አድርጎ እንደሚያስር የሚያሳየን ግድብ ይሆናል” ሲል በግድቡ ላይ ያለንን የመተባበር ጥንካሬ ይገልጸዋል።

“የኪነ-ጥበብ ባለሙያው አሁን እየሰራ ካለውም በላይ በአባይ ዙሪያ መስራት አለበት” የሚለው አርቲስት ሺመላሽ፤ “ኪነ-ጥበብ ያላትን ሃይል ተጠቅመን ህዝቡን ለማንቃት የሚመለከታቸው አካላትም በትብብር ሊያሰሩን ይገባል” ሲል አስተያየቱን ይሰጣል። አክሎም ህዝባችን እስካሁን ድጋፉን እንደቀጠለ ሁሉ “ጋን በጠጠር ይደገፋልና” ያለውን ይወርውር ሲል ይመክራል። አሁን ላይ በመጠኑም ቢሆን ከህዝቡ አካባቢ መቀዛቀዝ እየታየ መሆኑን አስተውያለሁ የሚለው አርቲስቱ፤ “ሁላችንም አባይ የወዴት ግዴታችን እንደሆነ መርሳት የለብንም” ባይ ነው።

ከዘመናት በፊት ስለአባይ ወንዝ ሲያስብ በጣም ረጅሙ ወንዛችን እንደሆነና ለአፍሪካውያን ወንድሞቻችንም የመጠቀሚያቸው ምንጭ እንደሆነ በቁጭት አስበው ነበር የሚለው አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬ፤ “አሁን ላይ ግን ለውጥ የመጣ ይመስላል። እንደምታውቀው እኔ ከዚህ ቀደም “ሰማያዊ ፈረስ” የተሰኘ ፊልም ሰርቼ ነበር። በፊልሙ ውስጥ የአባይ ውሃ አትንኖ ማዝነብ እንደሚቻል አሳይቼ ነበር፤ በፊልም ጥበብ አማካኝነት ማለቴ ነው። እውነቱን ለመነጋር በኔ ዘመን አባይ ተገድቦ አያለው ብዬ አስቤ አላውቅም። ፊልሙንም የሰራሁት ወደፊት አንድ ቅዠታም ሰራዊት የሚባል ሰውዬ እንዲህም አለ ብሎ ሰርቷል እንዲባል ነበር። የሚገርመው ግን ፊልሙ በተሰራ በአራትና አምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ነው የአባይ ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተጣለው፤ ይሄ ለኔ ትልቅ ትርጉም ያለው ነገር ነው” ይላል። አሁን ላይም አባይን ተንተርሶ ሀሳብ ወለድ ዘመን ተሻጋሪ ፊልም የመስራት ዕቅድ እንዳለው በዚሁ አጋጣሚ ጥቆማውን ሰጥቷል።

“አባይ ቁጭታችን ነበር” የሚለው አርቲስት ሺመላሽ ለጋስ በበኩሉ፤ “በተያዘለት ጊዜ ውስጥ የአባይ ግድብ ካለቀ ጮማ እንቆርጣበታለን” ባይ ነው። ልክ እንደሰራዊት ሁሉ የአባይ ግድብ ከተጠናቀቀ ከኃይል ምንጭነቱ ባለፈ የዓሳ ሀብትና የቱሪዝም መስህባችንም እንደሚሆን አምናለሁ የሚለው ሺመላሽ፤ “የድህነታችንን ቆሻሻ የምንታጠብበትና የምናፀዳበት እንደሚሆን ተስፋ አለኝ” ይላል።

በመገንባት ላይ ያለውን ታላቁ የህዳሴ ግድብ በደንብ ልናውቀው ይገባል የሚል ሃሳብ የሚሰጠው ሰራዊት፣ “ስለግድቡ በደንብ አውቀን በደንብ መግለፅ መቻል አለብን” ሲል በተለይም ይህን ተግባር በትኩረት መስራት ያለባቸው መገናኛ ብዙሃንና የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች መሆናቸውን አፅንኦት ይሰጥበታል። በተለይ ስለግድቡ ሂደትና ቀጥሎ ስለሚመጣው ሃይቅ ስታስብ “ዓሳ ወዳጆች ሆነን አመጋገባችን ሁሉ እንደሚለወጥ አትጠራጠር” ይላል። አክሎም ምናልባት ይህ ትውልድ ከአባይ ዝቅ የማይጨርሰው የአሳ ሀብት ባለቤት ይሆናል ባይምነው። ከዚህም ባለፈ የቱሪስት መስህብ ሆኖ ከፍተኛ የገቢ ምንጫችንም ይሆናል የሚል ተስፋ አለኝ ይላል።

“ስለአባይ ግድብ ሁላችንም አንድ ልብ ሆነን እስካልቆምን ድረስ ቀጣዩን ሳስበው ያሰጋኛል” የሚለው ሰራዊት፤ ከዚያ ወጪ ግን ግድቡን በድል ከተወጣነው አባይ ማለት እንደአንበሳ የምንፈራቸውን የርሃብ፣ የችግርና የችጋር ዘመናቶቻችንን አንድ ሆነን እንደድር የምናስርበትና የምንመክትበት ጋሻችን ነው” ሲል ይገልፀዋል።

አሁን ላይ ከማስታወቂያ በቀር በተቀሩት ስራዎቹ ከተመልካች አይን የራቀው አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬ በቅርብ “ዶግአመድ” የተሰኘ ፊልሙን ይዞ እንደሚመጣም ተናግሯል። ከዚህም ባሻገር ከህዝብ ጋር አስተዋውቆኛል በሚለው የሬዲዮ ሞገድ ከአጋሮቹ በቅርቡ ሉሲ ኤፍ ኤም 107.8ን በመክፈት ጣቢያው የራሱን ቀለምና ይዘት ያለው ፕሮግራሞችን ለመጀመር በመሰናዳት ላይ መሆኑን ጠቁሟል።

አርቲስት ሽመላሽ ለጋስ በበኩሉ ቀድሞ ከሚሰራባቸው ቴአትር ቤቶች በጡረታ ከተሰናበተ ስድስት ዓመታት ያለፈው ቢሆንም አሁን ላይ ማስታወቂያዎችን፣ ቴአትሮችን፣ ፊልሞችንና የሬዲዮ ድራማዎችን እየሰራ መሆኑ ይታወቃል። በአሁኑ ወቅት በአቢሲኒያ የስነጥበብ ትምህርት ቤት እና በህፃናትና ወጣቶች ቴአትር ቤት ባህላዊ ውዝዋዜ በማሰልጠን ላይ ይገኛል። በቅርቡ የሰራውን ባህላዊ ክሊፕ የሚለቅ መሆኑን ያስታወቀው አርቲስት ሺመላሽ፤ መሰነባበቻችን ያደረገው አርቲስቶቹ በጋራ በህዳሴው ግድብ ጉብኝታቸው ወቅት ያቀነቀኗትን ህብረ ዝማሬ በማስታወስ ነበር።       

አልሰማም ወይ አዋሽ አልሰማም ወይ

አልሰማም ወይ ቦርከና አልሰማም ወይ

ወንድማቸው አባይ የሰራውን

ግንዱን ይዞት ሄደ አብሮት ያደገውን።     

በስተመጨረሻም የዘንድሮውን መሪ ቃል እናስታውሳችሁ፤ “ታላቁ የህዳሴ ግድባችን የሀገራችን ህብረ -ዜማ፣ የህዳሴያችን ማማ!”

ይምረጡ
(6 ሰዎች መርጠዋል)
15758 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 927 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us