“ልምድ ካላቸው ባለሙያዎች ጋር በመሥራቴ እድለኛ ነኝ”

Wednesday, 12 April 2017 12:02

 

                          ድምፃዊት ሜሮን ኩርፋ (ሜሪ ውድድ)

በትምህርት ቤት ቆይታዋ የመረብ ኳስ አፍቃሪ ነበረች። ኳስ ሜዳ ተወልዳ ያደገችው የዛሬዋ የመዝናኛ እንግዳችን የአዲስ ከተማ ተማሪም ነበረች። የሙዚቃ ፍቅሯ በጥልቀት ዘፈኖችን በመስማት እንደጀመረች የምትናገረው ድምጻዊት ሜሮን ኩርፋ፤ በተማሪነት ዘመኗ “በሚኒ- ሚዲያዎች” አካባቢ ተሳትፎ እንደነበራትም ታስታውሳለች። በቅርቡ የመጀመሪያ አልበሟን “ሜሪ ውድድ” በሚል መጠሪያ ለአድማጭ አድርሳለች። ልምድባላቸው የሙዚቃ ባለሙያዎች ጋር በመቀናጀት የሰራችው አልበምና ስለቀጣይ ስለስራዎቿ አጠር ያለቆይታ አድርገናል መልካም ንባብ።

ሰንደቅ፡- እስቲ ለመጀመር ያህል ስለመጀመሪያው “አማተር” መድረክሽ እናውራ፤  በወቅቱ የማንን ዘፈን ነበር የተጫወትሽው?

ሜሮን፡- ተማሪ እያለሁ በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ ለመሳተፍ እሞክር ነበር። ነገር ግን ህዝብ በተሰበሰበበት መድረክ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የዘፈንኩት የብዙነሽ በቀለን “በነፍስ ስጋዬ” (አሁን ኩኩ ስብስቤ በድጋሚ ዘፍናዋለች) የሚለውን ስራ ነበር። በአጋጣሚ መድረኩን ያገኘሁት በደሳለኝ ሆቴል በተዘጋጀ የዘመድ ቅልቅል ፕሮግራም ላይ ነው። ሙዚቃውን አጥንቼው ሳይሆን ሳላስበው እስቲ ሞክሪ ተብዬ ተገፍቼ ነው ወደመድረክ የወጣሁት። ከዘፈንኩ በኋላ ግን የነበረው ምላሽ የሚያበረታታ ነበር። ያኔ ሜጋ ኪነ-ጥበባትም ሙዚቃን እማር ነበር።

ሰንደቅ፡- ከዚህ ዝግጅት በኋላ የምሽት ክለቦች ውስጥ የመስራት አጋጣሚውስ ነበረሽ?

ሜሮን፡- ክለብ ሰርቼ አላውቅም። ነገር ግን ስቱዲዮ የመስራት አጋጣሚውን አግኝቼ ብዙ ልምድ ካላቸው የሙዚቃ ባለሙያዎች ጋር አብሬ የመስራት ዕድሉን አግኝቻለሁ። በስራ አጋጣሚ ካወኳቸው ጓደኞቼ መካል ለመጥቀስ ያህል አቤል ሙሉጌታና ጌትሽ ማሞ ይገኙበታል። ከእነሱ ጋር “ጃም” በማድረግ ነው ድምጼን ይበልጥ የፈተሽኩት ማለት እችላለሁ።

ሰንደቅ፡- ወደአልበም ስራው እንዴት መጣሽ? ስራዎቹን የመምረጡ ሂደትስ ምን ይመስል ነበር?

ሜሮን፡- እውነቱን ለመነጋገር አልበም ለመስራት ሃሳቡ አልነበረኝም። ሜጋ እየተማርኩ ግን ዘላለም ካሳዬ የሚባል የሙዚቃ ባለሙያ ተዋወኩኝ። እሱ ነው እንደውም ፈትኖኝ ከሌሎቹም ጋር ያስተዋወቀኝ። እነሱም ድምፄን አይተው በሙሉ አልበም እንድወጣ መከሩኝ፤ ይህን ለማድረግ ቤተሰቤን ማሳመን ነበረብኝ። ከብዙ ሂደት በኋላ ነው እዚህ ያደረስኩት።

ሰንደቅ፡- አልበምሽን ከእነማን ጋር ሰራሽ?

ሜሮን፡- ዕድለኛ ነኝ፤ በመጀመሪያ አልበሜ ላይ ልምድና ስም ያላቸው ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል። ከኔም በላይ የእነሱ ድጋፍ ወሳኝ ማለት እችላለሁ። እዮቤል ብርሃኑ፣ ተዘራ ተችሎ፣ ጌትሽ ማሞ፣ አቤል ሙሉጌታና አበበ ብርሃኔ ግጥምና ዜማዎቹን ሰጥተውኛል። በነገራችን ላይ እነዚህን አስራ ሶስት ስራዎች ለመምረጥ በራሱ ከአንድ ዓመት በላይ ጊዜን ወስዶብናል። ቅንብሩን ደግሞ ወንድሜነህ አሰፋ፣ ሚካኤል ሃይሉና ካሙዙ ካሳ ሲሰሩልኝ፤ ማስተሪንጉን አበጋዝ ክብረወርቅ ሺዎታ ነው የሰራልኝ። ለዚህም ነው በመጀመሪያ ስራዬ ከእነዚህ ባለሙያዎች ጋር በመስራቴ እድለኛ ነኝ የምለው። በዚህ አጋጣሚ በዚህ አልበም ላይ የተሳተሰፉትንና በስራዬ የደገፉኝን በሙሉ ላመሰግናቸው እፈልጋለሁ።

ሰንደቅ፡- እንደመጀመሪያ አልበም ያስቸገረሽ ነገር ምንድነው?

ሜሮን፡- ለኔ እንደፈተና የምጠቅሰው የሰጡኝን ዜማና ግጥም እነሱ በፈለጉት ደረጃ ማምጣቱ ነበር። እውነቱን ለመናገር ባሰቡት ደረጃ ለመሆን በጣም ለፍቻለሁ። በተለይ ወንድሜነህ አሰፋ ብዙ ረድቶኛል። አንዳንዴ ሳስበው ግጥምና ዜማን ከዘፋኝ ስትቀበልና ከሌላ ሰው ስትቀበል ክብደቱ የሚለያይ ይመስለኛል። የሚሰጥህ ሰው ዘፋኝ ከሆነ በሱ ደረጃ ለመስራት የድምፅ አወጣጥህ ፈተና ላይ ይወድቃል። ከሌላ ሰው ከሆነ ግን የራስህን አቅም በመጠቀም አዲስ “ከለር” መፍጠር ትችላለህ ብዬ አስባለሁ።

ሰንደቅ፡- “ሜሪ ውድድ” የተሰኘው አልበምሽ ለአድማጭ ከደረሰ በኋላ ምን አይነት ምላሽ አገኘሽ?

ሜሮን፡- ከኔ በላይ አብረውኝ የሰሩት ልምድ ያላቸው ባለሙያዎችም ጥሩ ስራ እንደሰራሁ ይናገራሉ። አልበሙን የሰሙት ሰዎች ጥሩ እንደሆነ ነግረውኛል። በተለይም ደግሞ የሙዚቃ ባለሙያዎች የሆኑት የሚሰጡኝ አስተያየት ለቀጣይ ስራዬ ጭምር ብርታት ሆኖኛል።

ሰንደቅ፡- ለምንድነው የአልበምሽን መጠሪያ “ሜሪ ውድድ” ያልሽው?

ሜሮን፡- ለአልበሙ መጠሪያ የሚሆን ብዙ ርዕስ ወጥቶ ነበር። ስራዎቼን ሁሉንም እወዳቸዋለሁ። አንዱን ለይቼ ይሄ ይሁን ማለት ስላልቻልኩና ሁሉንም ስለወደድኳቸው ነው “ሜሪ ውድድ” እንዲባል የወሰነው። (ሳቅ)        

ሰንደቅ፡- በቀጣይስ ምን ለመስራት እያሰብሽ ነው?

ሜሮን፡- እንግዲህ ይህ አልበም ከወጣ ቅርብ ጊዜ ነው። እንደውም በሚቀጥለው ሐሙስ (ሚያዚያ 12 ቀን 2009 ዓ.ም) በክለብ H2O በደማቅ ሥነሥርዓት ለማስመረቅ እየተዘጋጀን ነው። ዝግጅቱን ለየት ለማድረግም አስተባባሪዎቹ “አፍሮ አድቨርታይዚንግ” በኢንተርኔት የቀጥታ ስርጭት ያስተላልፉታል። ከዚህም በተጨማሪ አንድ አዲስ የሙዚቃ ቪዲዮ (ክሊፕ) በዕለቱ ይለቀቃል ማለት ነው።

ሰንደቅ፡- አንዳንድ ስራዎችሽን ያደመጡ ሰዎች ድም ከሄለን በርሄ ድምፅ ጋር ይመሳሰላል ይላሉ። አንቺ ምን ትያለሽ?

ሜሮን፡- አዎ ይመሳሰላል የሚሉ ሰዎች አጋጥመውኛል። በርግጥ ሄለንን አደንቃታለሁ፤ ነገር ግን እኔ የራሴን ስልት ተከትዬ ነው የሰራሁት ብዬ አምናለሁ። ለአድማጩ ሊመስለው ይችላል። ባይገርምህ የሄለንን ስራዎች አንድም ቀን መድረክ ላይ እንኳን ተጫውቼ አላውቅም። ያው እንግዲህ በአጋጣሚ ተመሳስሎባቸው ሊሆን ይችላል።

ሰንደቅ፡- ወደአልበም ስራ ከመምጣትሽ በፊት የአንጋፋዎቹን ድምጻዊያን ስራዎች ታደምጪም፣ ትጫወቺም እንደነበር ነግረሽኛል። እንደው ግን እድሉ ቢሰጥሽ የማንን ስራ እኔ ብጫወተው ብለሽ ትመኛለሽ?

ሜሮን፡- (ሳቅ) እኔ ጀማሪ ድምፃዊ ነኝ። ድፍረት አይሁንብኝና የጂጂን ስራዎች በሙሉ አደንቅላታሁ፤ እወድላታለሁ። እኔ የመዝፈን እድሉን ባገኝ የምመኘው “አባይ” የሚለው ስራዋን ነው። ይህን ስራ ስሰማው “ነርቨስ” ያደርገኛል። በጣም ነው የምወደው። ጂጂም በጣም አሪፍ አድርጋ ተጫውታዋለች። ምናልባትም በህይወቴ ብዙ ጊዜ ደጋግሜ የሰማሁት ይህንን ስራ ሳይሆን የሚቀር አይመስለኝም።

ሰንደቅ፡- ከህይወትሽ ጋር የተያያዘ ስራ በዚህ አልበም ውስጥ አለ?

ሜሮን፡- ስለእናቴ የዘፈንኩት አለ። ለኔ ልዩ ትርጉም ያለው ስራ ነው። “አይበቃሽም” የሚለው ስራዬን ለእናቴ ስል ዜማና ግጥም ስሩልኝ ብዬ የዘፈንኩት ነው። እናቴን አስራተገነት ከበደንና መላው ቤተሰቦቼ ስለሚደግፉኝ በጣም አመሰግናቸዋለሁ።

ሰንደቅ፡- ከአልበምሽ የሙዚቃ ቪዲዮ (ክሊፕ) የሰራሽላቸው ዘፈኖች አሉ?

ሜሮን፡- አዎ የመጀመሪያው በጉራጌኛ ስልት የተሰራው “ቼቼ” የሚለው ስራዬ ነው። በህዝብ ዘንድ በጣም ተወዷል። በቀጣይም በአልበሜ የምርቃት ቀን “ዱማ” የሚለው ዘፈን ክሊፕ ይለቀቃል። ከዚያ በኋላም ሶስተኛውን ክሊፕ ሰርቼ ለተመልካች አቀርባለሁ።

ሰንደቅ፡- ከአንድ አንጋፋ ድምጻዊ ጋር የሙዚቃ ድግስ ይኑርሽ ብትባይ ከማን ጋር መስራትን ትመርጫለሽ?

ሜሮን፡- አንዱን መምረጥ ከባድ ነው። ነገር ግን ምረጪ ካልከኝ ከቴዎድሮስ ታደሰ ጋር ብሰራ በጣም ደስ ይለኛል። የቴዲን ስራዎች ስሰማ በጣም ነው የምደነቀው። አብሬው ብሰራ ደግሞ በጣም ነው ደስ የሚለኝ።

ሰንደቅ፡- እንግዲህ ይህ ሳምንት የበዓል ሳምንት ነው። ዓመት በዓል ሲመጣ ምን ስሜት ይሰማሻል?

ሜሮን፡- ዓመት በዓል በጣም ደስ የሚል ስሜት በሁሉም ሰው ዘንድ መፍጠሩ አይቀርም። ለኔ ደግሞ ይሄ በዓል በብዙ መልኩ ይለያል። በተለይም የመጀመሪያ የሚባለውን አልበሜን በጨረስኩበት ወቅት የማከብረው የመጀመሪያ በዓል በመሆኑ በጣም ደስ ብሎኝ የማሳልፍበት በዓል ይሆናል ብዬ እጠብቃለሁ።

ሰንደቅ፡- ሙዚቃን ከመስማትና ሙዚቃን ከመስራት ባለፈ ምን ያዝናናሻል?

ሜሮን፡- ዋና በጣም እወዳለሁ፤ ዋና ያዝናናኛል። (ሳቅ) ምናልባት ከመረብ ኳስ ስፖርት ውጪ ብሆን ዋናተኛ የምሆን ይመስለኛል። በተጨማሪ ግን አዳዲስ ነገሮችን ማየትና መልመድ ደስ ይለኛል።

        

       

       

        

         

        

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
15961 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 965 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us