ስለቴአትር ትንሳኤ

Wednesday, 19 April 2017 12:33


- “ጥሩ ቴአትር ከተሰራ፤ ጥሩ ተመልካች አለ”
                                                                         ተካልኝ ገ/ሚካኤል፤ በመቐሌ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር መምህር

“የአለም የቴአትር ቀን” በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ55ኛ ጊዜ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አማካኝነት ለሁለተኛ ጊዜ ባሳለፍነው ወር ተከብሯል። አዘጋጅ የነበረው የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ሲሆን፤ በርካታ ባለሙያዎች፣ ምሁራንና ተማሪዎችን ያሳተፈ ቴአትር ተኮር ፌስቲቫል እንደነበረም ተነግሯል። በአገራችን ለሁለተኛ ጊዜ በተከበረው በዚህ የቴአትር ቀን ላይ የተለያዩ ባለሙያዎች ለቴአትራችን ዕድገትና ከፍታ መንሰላል የሚሆኑ የጥናት ፅሁፎችን አቅርበዋል።


ለሶስት ቀናት በቆየውና በተለያዩ ዝግጅቶች በተከበረው የቴአትር ፌስቲቫል ላይ ተሳትፈው ከነበሩና የጥናት ፅሁፋቸውን ካቀረቡ ባለሙያዎች መካከል፤ በመቐሌ ዩኒቨርስቲ የቴአትር ጥበባት ትምህርት ክፍል መምህርና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የመልቲ ሚዲያ ቴአትር የማስተርስ ተማሪ የነው መምህር ተካልኝ ገ/ሚካኤል አንዱ ነው። መምህርና ተካልኝ “Theater Education in Ethiopia Higher Institutions” በሚል ርዕስ ፅሁፋቸውን ለታዳሚው አቅርቧል። በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የቴአትር ትምህርት አሰጣጥ ላይ ያሉ ክፍተቶችን በመፈተሽ መፍትሄዎችን የጠቆመ ጥናት እንዳቀረበ የሚናገረው መምህር ተካልኝ ገ/ሚካኤል፤ “እንደችግር ከጠቃቀስኳቸው መካከል የአቅርቦት ጉዳይ አንዱ ነው” ይላሉ። በወፍ በረርም ቢሆን በስምንቱ የአገራችን ዩኒቨርሲቲዎች (ማለትም በአዲስ አበባ፣ በጅማ፣ በመቐሌ፣ በወልቂጤ፣ በአክሱም፣ በጎንደር፣ በወሎ እና በአዲግራት ዩኒቨርሲቲዎች) የተደረገው ጥናት እንደሚያመለክተው አብዛኞቹ የአቅርቦት የችግሩ ተጋሪዎች መሆናቸውን ያሳያል።


በእነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በማስተማር ላይ ከሚገኙት መምህራትን መካከል 67 ነጥብ 3 የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ሲሆኑ፤ 56 የሚሆኑት ደግሞ ሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው ናቸው። ከእነዚህም ውስጥ 43 የሚሆኑት የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከቴአትር ትምህርት ውጪ ማግኘታቸውን ጥናቱ አመልክቷል። ይህ ቁጥር በትምህርት አሰጣጡ ጥራት ላይ የራሱ ተፅዕኖ እንደሚኖረውም መምህር ተካልኝ ይናገራል። ከዚህም ጋር በተያያዘ ለመማር ማስተማር የትምህርት ዘርፉ የሚፈልጋቸው ቁሳቁሶች በበቂ መጠን አለመቅረብ የራሱ ችግር እንደፈጠረም ያስረዳል። “ለቴአትር አቅርቦት የሚያስፈልግ መድረክ፤ የኦዶቪዥዋል ክፍሎች፤ የካሜራና የድምጽ እንዲሁም የአልባሳትና የሚካፕ አቅርቦትን ጨምሮ ብዙ ለማስተማሪያ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ቢኖሩም 100 በመቶ ተሟልቶ የቀረበባቸው ተቋማት ግን የሉም የሚያስብሉ ናቸው” ይላል። ምንም እንኳን በመሠረታዊ ደረጃ መሟላት የነበረባቸው አቅርቦቶች ባልተሟሉበት ሁኔታ የትምህርት ክፍሉ መከፈት ባይኖበትም አሁን ላይ ስምንት የሚደርሱ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን ተቀብለው እያስተማሩ እንደሚገኙም ተወስቷል።


በጥናቱ ካቀረበው የቁጥር መረጃዎች መመልከት እንደተቻለው በድፍረት ትምህርቱን በመስጠት ላይ ከሚገኙት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች መካከል የመድረክ አቅርቦት ያለው መቐሌ ብቻ ዩኒቨርሲቲ መሆኑ ተገልጿል። “ተገቢው የቴአትር አቅርቦ የሌላቸው መድረኮችን የያዙ አዳራሾች ለስብሰባ እንጂ ለቴአትር አይሆኑም” የሚለው ጥናት አቅራቢው ከአልባሳትና ሜካፕ ጋር በተያያዘም በርካታ ችግሮች መኖራቸውን እግረመንገድ ይጠቃቅሳል። የቴአትር ተማሪዎች ከመድረክ ስራዎች በተጨማሪ የሬዲዮ፣ የቲቪና የፊልም ፕሮዳክሽኖችን ለመማር የኦዲዮቪዠዋል አቅርቦት የሚያስፈልጋቸው ቢሆንም፤ አሁን ላይ የተሻለ አቅርቦት አላቸው የተባሉት ግን ወሎ እና ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ መሆናቸውን ጥናቱ ይናገራል።


“የቴአትር ትምህርት መጀመር ያለበት ከስር ነው” የሚል ሃሳብ በፅኑ የሚያነሳው መምህር ተካልኝ፤ በጥናቱ ውስጥም ቴአትርን ገና አንድ ብለው በዩኒቨርስቲ ደረጃ የሚተዋወቁ ተማሪዎች መበራከታቸው ራሱን የቻለ ፈተና ሆኗል ባይ ነው። የትምህርት አሰጣጣችን ቴአትርን በተመለከተ በዩኒቨርሲቲዎች ከዜሮ ጀምሮ መሰጠቱ የዳበሩ ባለሙያዎችን ለማውጣት እንደችግር መሆኑን ይጠቅሳሉ። በዚህም መፍትሄዎች እንደሙዚቃና ስዕል ሁሉ ቴአትርም ከመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤቶች አንስቶ ሊተዋወቅ ይገባል የሚል ሃሳብ በጥናቱ እንደመፍትሄ ተካቷል። “ይህን መሰል አካሄድ ብናዳብር ጥሩ የቴአትር ባለሙያ ባናፈራ እንኳን ጥሩ የቴትር ተመልካች ልናፈራ እንችላን” ሲልም መምህሩ ያስረዳል።


በሌላም በኩል ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ተመሳሳይነት ወይም ተቀራራቢነት ያላቸውን ትምህርቶች ወደአንድ የማምጣት የሥነ-ትምህርት ዘዴ (Mogularization System) ከቴአትር ትምህርት ባህሪይ አንፃር ሊሆን የማይችል መሆኑን ምሳሌ እየጠቀሱ ያስረዳሉ። አንድ ኮርስ በሁለት ሳምንት አስተምረህ እንድትጨርስ የሚጠበቅ ቢሆን፤ ቴአትር ግን ሰፋ ያለ ተግባራዊ የልምምድ ጊዜን ስለሚፈልግ ከተሰጠው ጊዜ ጋር አይሄድም። በዚህም ይህ የትምህርት አሰጣጥ ዘዴ ምቹ አይደለም ሲሉ ይተቻሉ። በሌላ በኩልም ተመሳሳይ ባህሪይ ያላቸው ትምህርቶች ወደአንድ “ሴሚስተር” እንዲመጡ ይፈልጋል። በዚህም ለምሳሌ አንድ የቴአትር ተማሪ በአንድ ሲሚስተር ውስጥ የተግባር ልምምድ የሚያስፈልጋቸውን (production course) ሙዚቃዊ ቴአትር፣ ትውፊታዊ ቴአትር፣ ቴአትር ለልማት፣ የህጻናት ቴአትርን የመሳሰሉት ሰፋ ያለ የልምምድ ጊዜ የሚፈልጉ ትምህርቶች በአንድ ጊዜ ለአንድ ተማሪ ብንሰጠው የቱን ይዞ የቱን ሊለቅ ይችላል? ሲልም አስቸጋሪነቱን ይጠይቃል።


አዲስ አበባ እና ጅማ ዩኒቨርስቲ የራሳቸውን የቴአትር ጥበብ ማስተማሪያ ዘዴ ሲተገብሩ፤ ወልቂጤ፣ መቐሌ፣ አዲግራት፣ ወሎ፣ አክሱምና ጎንደር በጋራ ተግባብተው አንድ የማስተማሪያ ዘዴን ለመከተል በዙር ውይይት አድርገው በ2008 ዓ.ም አዲግራት፣ ወሎ እና ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲዎች መጀመራቸውን ያስታወሰው ጥናት አቅራቢው መምህር፤ ቀሪዎቹ ግን ትምህርት ሚኒስቴር እስኪያፀድቀው ድረስ አንጀምረም በሚል ወደተግባር ሳይገቡ መቅረታቸውን ተናግረዋል።


በጥናቱ እንደችግር ከተገለፁት መካከል የዩኒቨርስቲዎቹ፣ የትምህርት ሚኒስቴርና የቴአትር ቤቶቹ መስተጋብር ልል መሆኑ አንዱ ሆኖ ተጠቅሷል። ያለመተዋወቅና ክትትል ያለመኖሩ ለዘርፉ እንቅፋት ፈጥሯል የሚለው መምህር፤ በቴአትር ፌስቲቫሉ ላይ የተገኙ የትምህርት ሚኒስቴር ተወካዮች የተጠቀሱ ችግሮች መኖራቸውን አምነው ለማስተካከል እንደተዘጋጁ መስማታቸውንም ጠቁመዋል። “በጋራ የመስራት ባህላችን ደካማ ነው” የሚለው ጥናት አቅራቢው እርስ በእርስ ለመገናኘት ከፌስቲቫልም ባሻገር መታሰብ አለበት ሲልም ምክረ - ሃሳብ አስቀምጧል።


በጥናቱ ከተዘረዘሩት ችግሮች ነፃ ለመውጣትና እንቅፋቱ የበዛውን ቴአትራችንን ደጋግፎ ትንሳኤውን ለማብሰር ከማን ምን ይጠበቃል? ተጠያቂውና ኃላፊነቱስ የማን ነው? የቴአትር ቤቶች በክልል ደረጃ መስፋፋትንስ? ስንል ላቀረብነው ጥያቄ መምህሩ መልስና መፍትሄ ያለውን ሃሳብ ይሰጣል። “ችግሮቹ ከአንድ አካል ብቻ እንዳልመጡ ሁሉ፤ መፍትሄውም ከአንድ አካል ብቻ አይመጣም” በማለት ይጀምራል። “ኢትዮጵያ ውስጥ ቴአትር አለ ለማለት አዲስ አበባ ውስጥ ቴአትር አለ ማለቱ ብቻ በቂ አይደለም” የሚለው መምህር ተካልኝ፤ በዘርፉ ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎችም የሚገጥማቸውን የቦታና የስራ እጥረት ለማካካስ ከተማሩት የትምህርት ዘርፍ በራቀ መልኩ ስራ ሲሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።


በሁሉም የክልል ከተሞችና ዩኒቨርሲቲዎች በተገነቡባቸው አካባቢዎች ቢያንስ አንድ ቴአትር ቤት ቢኖር የስራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ባህላችንና ማንነታችንን ለማስተዋወቅ፤ እንዲሁም የፈጠራ አቅማችንን ልንጠቀምበት እንችላለን የሚል ሃሳብ ቀርቧል። “ለዚህ እንደምሳሌ እኔ በቅርበት የማውቀውን መቐሌ መጥቀስ እችላለሁ። የአካባቢውን ህብረተሰብ ቴአትር ለማስለመድ ግፊት ተደርጎ በቅርቡ በስራ ላይ በሚውለው አዲሱ የመቐሌ ማስተር ፕላን ውስጥ የቴአትር ቤት እንዲኖር ተደርጓል” ሲል እንደለውጥ ማሳያ አድርጎ ይጠቅሰዋል። ይህን መሰል ለውጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ከማህበረሰቡ ድጋፍ ባለፈ የባለሙያው እና የመንግስት አካላት (በተለይም የባህልና ቱሪዝም) ድርሻ ቀላል የሚባል አለመሆኑንም መምህሩ አፅንኦት ይሰጥበታል።


ተመልካችን በተመለከተ ስጋት አለ ወይ? በሚል ላቀረብነው ጥያቄ መምህሩ ሲመልስ፣ “የተመልካች ችግር አለብዬ አላምንም” ሲል ይጀምራል። ነገር ግን ተመልካች ይኖር ዘንድ ጥሩ መስራት የሚችሉ ባለሙያዎችም መፈጠር አለባቸው ሲል ይሞግታል። ለዚህም በርካታ የመዝናኛ አማራጮች ቢኖሩም እንኳን “ጥሩ ቴአትር መስራት ከቻልን ጥሩ ተመልካቶችን ማግኘት እንችላለን” ይላሉ። ለዚህም የቴአትር ትርኢት “ህይወት” ያለው ከመሆኑ አንጻር እንደሌሎቹ መዝናኛዎች አርቲፊሻል (የተቀባባ) ነገር አይበዛውም የሚል ሃሳብን ይሰነዝራሉ።


የተንሸዋረሩ ጥናቶችን በመጥቀስም አሁን ላይ ተመልካችን መምራት የሚገባው ባለሙያ በተመልካች እየተመራ እንደሚገኝ በቁጭት የሚናገረው መምህር ተካልኝ፤ በቅርቡ አየሁት ያለው አንድ ጥናት መሠረት አድርጎ ሲናገር፤ “አሁን ላይ ተመልካቹ የሚወደው ኮሜዲ ስራ ነው” በሚል በርካታ ባለሙያዎች በኮሜዲ ስራ ተጠምደዋል ይላል። ኮሜዲ መሠራቱ ችግር የለውም የሚለው መምህሩ ነገር ግን “ተመልካቹ ይወዳል” ስለተባለ ብቻ ባለሙያው ሊመራ አይገባውም ባለሙያው በጥበቡ ላይ የመሪነት ሚናው መጎልበት አለበት ሲል ይሞግታል።


በጣት በሚቆጠሩ ቴአትር ቤቶቻችንም ቢሆን፤ ቀደም ብለው የተሰሩና ከመድረክ የወረዱ ቴአትሮች ተመልሰው ለተመልካች መቅረባቸው የፈጠራ ንጥፈትን እና የአዳዲስ ባለሙያዎች እጥረትን አያሳይም ወይ? በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄ መምህር ተካልኝ የግል ምልከታውን ተንተርሶ የሚከተለውን ይናገራል። “የድሮ ቴአትሮች መደጋገማቸው ችግር የለውም። ከአመታት በፊት የታየ ቴአትር አሁን ቢመጣልኝ ያኔ ያጣሁትን አጋጣሚ አግኝቼ አያለሁ። ይህ መልካም ነገር ነው። ነገር ግን ለምንድ ነው ቴአትሮቹ ደግመው ለመድረክ የበቁት? የሚለው አጥጋቢ ምላሽ ማግኘት አለበት” ሲሉ ይሞግታሉ። እውነት አዲስ ቴአትር ጠፍቶ ነው? ተመልካች እንዲደገም ጠይቆ ነው? ቴአትር ቤቱ ስለፈለገ ነው? የሚለው ከተመለሰልን በኋላ ነው በጥልቀት መነጋገር የምንችለው ሲልም ጉዳዩ የበለጠ ጥናት እንደሚያስፈልገው ይናራል።


ከዓመታት በፊት በርክተው ይታዩ የነበሩ የቴአትር ክበባት አሁን ላይ ተዳክመዋል። ከስምንት ዩኒቨርሲቲዎች ተመርቀው የሚወጡ ባለሙያዎች ግን በዛው ልክ ጨምረዋል። የቴአትርና የቴአትረኛው ትንሳኤ ይመጣ ዘንድ ምን መደረግ አለበት? በሚል ላነሳነው ጥያቄ የሚከተለውን ይመልሳል፣ “ቴአትር ማህበረሰብን መቀየር የሚችል ጥበብ ነው። አስተሳሰብን ይቀይራል። ይህ የሚሆነው ግን ጥበቡንበሚገባ ስንጠቀምበት ነው። ስለቴአትር ትንሳኤ ስናወራ ቴአትር ሞቷል ማለታችን እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል።” የሚለው መምህር ተካልኝ፤ ቴአትር አሁን ካለበት የተሻለ ደረጃ ይደርስ ዘንድ ተመርቀው የወጡ ተማሪዎች ቴአትር ቤት ካልተቀጠሩ፤ ወይም በተጓዳኝ የሚሰሯቸውን ስራዎች ካላገኙ ልክ እንደሌላው መሰል ማህበር እንዲያቋቁሙ ተደርጎ በተለያዩ ከተሞች ውስጥ “የቴአትር ቡድን” ሊኖር ይገባል። ይህን የሚደግፍ መሠረት ግን የለም የሚለው መምህሩ፤ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራበት የሚገባ እንደሆነ በአፅንኦት ያስገነዝባል። ዩኒቨርሲቲዎችን የቴአትር ተማሪዎችን ከማስመረቅ ባለፈ ለቴአትር ኢንዱስትሪው የሚያበረክቱት ነገር ሊኖር ይገባል ብዙ ስራ ይጠበቅባቸዋል የሚለው ወጣቱ መምህርና የጥናት ፅሁፍ አቅራቢ “ለውጡን ከባለሙያውና ከባለድርሻ አካላቱ እንጠብቃለን” ይላል።

Last modified on Wednesday, 19 April 2017 12:38
ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
15938 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 895 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us