“ወጣቱ የሚዝናናበትን መንገድ መምረጥ አለበት”

Wednesday, 26 April 2017 12:09

 

ፀሐፊና የምክር አገልግሎት ባለሙያ አቶ ፈለቀ ብርሃኔ

 

በፍልስፍና፣ እና በአስተዳደር፣ ሥነ-መለኮትና በአመራር ዘርፎች ከዲፕሎማ እስከ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ስርተዋል። በወጣቶች ላይ ትኩረት ያደረገውን “ወጣቱና 21ኛው ክፍለ ዘመን” የተሰኘ መፅሐፍ አዘጋጅተው ለንባብ አብቅተዋል። ከዚህም ባለፈ ለአስራ አንድ ዓመታት በወጣቶች ዙሪያ በማማከር ስራ ላይ የቆዩ ባለሙያ ናቸው፤ የዛሬ የመዝናኛ አምድ እንግዳችን አቶ ፈለቀ ብርሃኔ። እኚህ ባለሙያ በቅርቡም “ከምባታነት እሴቶቹ፣ ትምህርት እና ልማት” የተሰኘ መፅሐፍ በጥናት አስደግፈው ለንባብ አብቅተዋል።

የዘመኑ ወጣቶች ያሉባቸውን ተግዳሮቶችና በእጃቸው ያለውን ዕድል በተመለከተ በስፋት የሚዘረዝሩት አቶ ፈለቀ፤ ተወልደው ያደጉት በቀድሞው የከምባታ አውራጃ (ዞን) ዋስራ በምትባል መንደር እንደነበር ይናገራሉ። ይህቺ መንደር ታሪካዊ ናት የሚሉ ሲሆን፤ ለታሪካዊነቷ ምስክርነቱንም ሲሰጡ በ1937 ዓ.ም በከምባታ የመጀመሪያው መደበኛ ትምህርት ቤት የተከፈተባት ቦታ ስለመሆኗ ያስታውሳሉ።

“ወጣቱና 21ኛው ክፍለዘመን” በተሰኘው ቀዳሚ መፅሐፋቸው ስላነሱት አንኳር ሀሳቡ ሲያስረዱ፤ “የዘመኑ ወጣት በርካታ ዕድሎችና ፈተናዎች በፊቱ የቀረቡለት ነው። እኔ በመፅሐፌ በተለይም ከቴክኖሎጂ እና ከትዳር ጋር ተያይዞ ያሉ ጉዳዮችን በስፋት አይቻለሁ” ይላሉ። በወጣቱ ዘንድ ትዳር የመበርከቱን ያህል ፍቺውም የዛኑ ያህል ነው የሚሉት ባለሙያው፣ “በአዲስ አበባ ከተማ ስር ብቻ 65 በመቶ ወደ ፍርድ ቤት የሚሄደው የቤተሰብ ጉዳይ በፍቺ የሚጠናቀቅ ሆኗል” ያሉ ሲሆን፤ ይህ ለምን ሆነ ብለው የሚጠይቁት አቶ ፈለቀ፤ ቴክኖሎጂ ይዞት የመጣው በረከትና መርገም እንዳለ ሆኖ፤ ማህበራዊ እሴቶቻችን እየተሸረሸሩ መምጣታቸው ነው ሲሉ በጥናታቸው መፈተሻቸውን ይናገራሉ። ከዚህም ባለፈ የወላጆች የልጅ አስተዳደግና የሥነ-ምግባር ግንባታ ላይ ያተኮረ ሀተታ በመፅሐፋቸው አስፍረዋል።

“እኔ ገና በወጣትነቴ በሳል ነበርኩ፤ ለዚህም ያሳደገኝ ማህበረሰብ የነበረው አስተዋፅኦ ቀላል አይደለም” የሚሉት አቶ ፈለቀ፤ ድሮ ልጅን የሚያሳድገው ማህበረሰባችን ነው። ዛሬ ላይ ግን የአንድ ልጅ ጉዳይ የቤተሰቡ ብቻ እንጂ በተቀረው ህብረተሰብ ዘንድ እንደፍጥርጥሩ ተብሎ ቀርቷል ይላሉ። ለዚህ እንደስህተት ያቀረቡት ደግሞ በዴሞክራሲ ስም የተሳሳተ ግንዛቤ መፈጠሩን ነው። “ዛሬ ላይ አለመማርን እንደመብት የሚቆጥር ወጣት እየመጣ ነው። ይህም በሥነ-ምግባርና ሥነ-ዜጋ ትምህርት በኩል ያገኘውን ዕውቀት ተንተርሶ “መብቴ ነው” በሚል ብቻ መብትና ግዴታውን በተሳሳተ መንገድ ከመተርጎም የመነጨ ይመስለኛል” ይላሉ።

በእርሳቸው የወጣትነት ዘመን ወጣቱ መዝናናትን የሚያገኘው መፅሐፍትን ከማንበብና ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በመሳተፍ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ፈለቀ፤ “የኔ ለንባብ መጋለጥ ከአባቴ መምህርነት ጋር የተያያዘ ነው። አባቴ ብዙ መፅሐፍ ያመጡ ስለነበር የማንበቡን ዝንባሌ ያዳበርኩት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው” ይላሉ። አሁን ላይ ብዙ ወጣቶች በቴክኖሎጂ ሱስ (በተለይ በፌስ ቡክ) የታሰሩ ናቸው የሚሉ ሲሆን፤ በአግባቡና በጥንቃቄ መጠቀም ካልቻልን አደጋ እንዳለው ሊታወቅ ይገባል ሲሉ ወጣቱን ይመክራሉ።

በቅርቡ የወጣውን “ከምባታነት፣ እሴቶቹ፣ ትምህርት እና ልማት” የተሰኘ መፅሐፍ ለመፃፍ ስላነሳሳቸው ምክንያት ሲናገሩ፤ “በከምባታ አካባቢ ከፍተኛ የስደት መንፈስ እየታየ ነው። ቀደም ብሎ ከምባታ በትምህርት የሚያምን ህዝብ ነበር። ከመሬት ጥበቱና ከህዝብ ብዛቱ አንጻር ትምህርት ዋንኛ ኑሮን ማሸነፊያ መሳሪያው ነበር” የሚሉት አቶ ፈለቀ፤ አሁን ላይ ወጣቱ ልቡ ወደ ደቡብ አፍሪካና ወደተለያዩ አገራት ተሰዷል። ብዙ ወጣቶች በህገወጥና አደገኛ የስደት መንገድ ላይ መታየታቸው ችግሩን ከስር በመመርመር መፍትሄ የሚጠቁም መፅሐፍ ለማዘጋጀት ስለመነሳታቸው አቶ ፈለቀ ያስረዳሉ።

ለተከታታይ ሶስት ዓመታት በተደረገ ጥናት ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀው “ከምባታነት፣ እሴቶቹ፣ ትምህርት እና ልማት” መፅሐፍ፣ የከምባታ ማህበረሰብን ችግር ለመፍታት ብሎም የመፍትሄ ሃሳብ ለመጠቆም የተሰናዳ እንደሆነ ተነግሯል። አሁን ላይ የሚታየው ከከምባታ ህዝብ ብዛት አካሄድን ተንተርሰው አቶ ፈለቀ ባጠኑት ጥናት በ2058 ዓ.ም አንድ ገበሬ ሊኖረው የሚችለው የመሬት ስፋት 100 ካሬ ሜትር ብቻ እንደሚሆን ይጠቁማሉ። ለዚህ ማህበረሰብ ከችግር መውጫው ብቸኛውና ብቸኛው ነገር ተደርጎ በጥናቱ የተቀመጠው ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት እንደሆነ መፅሐፉ አፅንኦት ይሰጥበታል።

“በሀገር አቀፍ ደረጃ የትምህርት ጥራት ጥያቄ ውስጥ መግባቱ የምናየው ነገር ነው” የሚሉት አቶ ፈለቀ፤ በከምባታ አምስት ወረዳዎች ውስጥ ባደረጉት ጥናት ኩረጃ እንደባህል እየተወሰደ መሆኑን ስለመታዘባቸው ይናገራ። ለዚህም እንደአብይ ምክንያት የጠቀሱት ከዓለምአቀፍ ለጋሾች አንደኛ ለወጣ ትምህርት ቤት የሚሰጥ የገንዘብ ድጋፍ መኖሩን ተከትሎ የትምህርት አመራሮቹም ተማሪውን በጥብቅ ከመከታተል ይልቅ በቁጥር የሚታይ ውጤት እንዲመጣ ሲሉ ለኩረጃ በር ከፍተዋል በማለት በአፅንኦት ይሞግታሉ።

ሁለተኛውን መፅሐፋቸውን ለማዘጋጀት ወደደቡብ አፍሪካ በሄዱበት ወቅት ስላጋጠማቸው ነገር ሲናገሩ፤ “የእኔ መዳረሻዎች ኬፕታዎን እና ጆሃንስበርግ ነበሩ። በርካታ የከምባታ ወጣቶች እዛ ይገኛሉ። ሀገር ቤት ደርሰው የሚያሳዩት ነገር ሌሎችን ወጣቶች ይስባል። ነገር ግን በየሳምነቱ ወደሀገር ቤት “ሬሳ” መምጣቱን ለመስማት የሚፈልግ ጆሮ የለም። ለዚህም በከምባታ ማህበረሰብ ዘንድ የደቡብ አፍሪካ ጉዞ ዋነኛው ህይወትን መለወጫ ተደርጎ በወጣቱ ዘንድ ተወስዷል” ሲሉ ይናገራሉ። ከዚህ ሁሉ በላይ ግን አንድ ነገር ላረጋግጥልህ ይላሉ፤ “ደቡብ አፍሪካ ውስጥ አንድም ሰው በስደት ህይወቱ ተረገግቶ የሚኖር የለም” ሲሉ የሰቆቃ ጥልቀት ይገልጹታል።፡

“ከምባታነት፣ እሴቶቹ፣ ትምህርት እና ልማት” በተሰኘው መፅሐፋቸው “መቅድም” ላይ እንዲህ ይላሉ። “ከምባታና ትምህርት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ናቸው። ሁለቱም የማይነጣጠሉና የተሳሰሩ ናቸው ቢባልም ተጋነነ ሊያስብል አይችልም” ሲሉ የማህበረሰቡንና የትምህርትን ቁርኝት በተመለከተ ይጠቁማሉ። እናም አሁን ላይ ከባህል ከእሴትና ከልማት አንፃር እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች የሚፈቱት በጠንካራ ትምህርት መሆኑን አጥኚው በአፅንኦት ያስረዳሉ።

የዘመናችንን ወጣት በረከትና መርገምት በዘረዘሩበት መፅሐፋቸው በርካታ ጉዳዮችን ስለመዳሰሳቸው ይናገራሉ። በ2006 ዓ.ም ለንባብ የበቃው ይህ ቀዳሚ ስራቸው “ወጣቱ እና 21ኛው ክፍለ ዘመን” የሚሰኝ ሲሆን፤ ቀደም ተብሎ ለመጥቀስ እንደተሞከረው የወጣቱን ህይወት ከቴክኖሎጂና ትዳር አንፃር እንዲሁም የወላጆችን የአስተዳደግ ስርዓት የሚፈትሽ መፅሐፍ እንደሆነም ይናገራሉ።

ወጣቱ በቴክኖሎጂ ሙሉ በሙሉ ከመዋጥ ስለራሱ ባህልና ማንነት ቢያውቅ ቴክኖሎጂውን እንደማስተዋወቂያና መማማሪያ መድረክ ሊጠቀምበት ይችላል የሚሉት አቶ ፈለቀ፤ የቴክኖሎጂው አጠቃቀማችን ሊፈተሸ ይገባል ሲሉም ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ። በሌላም በኩል ወጣቱ ከሚመሰርተው ትዳር በላይ ፍቺው አሳሳቢ ሆኗል የሚሉት አቶ ፈለቀ፤ ወጣቱ ከትዳር በፊትና በኋላ ምን አይነት የአኗኗር ዘዴን መከተል እንዳለበት ሳይንሳዊ ምክር ስለማስቀመጣቸው ተናግረው በዚህም መፅሐፍ ከበርካታ ወጣቶች ጥሩ ምላሽ ስለማግኘታቸው ይናገራሉ።

“የቴክኖሎጂ መስፋፋት ወጣቱን ከማህበራዊነት ነጥሎ ወደግለኝነት እያመጣው ነው” የሚሉት አቶ ፈለቀ፤ ይህም አጠቃላይ ውጤቱ መጥፎ እንደሚሆን ይናገራሉ። “መዝናናት ማለት ዛሬ ላይ ያለህበትን የድብርት መንፈስ አላቀህ ለቀጣይ ስራ ኃይል የምታጠራቅምበት ነው” የሚሉት ባለሙያው መዝናናታችን ነገን የሚያሳጣን አይነት መሆን የለበትም ሲሉ ይመክራሉ። ስለወጣቱ ዘመን ቅብብሎሽ ሲያትቱም ዘመናዊ ናቸው ብለን የምንቀበላቸው ነገሮች በጥልቀት ተመርምረው ክፉና ደጉ በግልጽ መቀመጥ አለበት ባይ ናቸው። ይህንንም በቀዳሚ መፅሐፋቸው “ወጣቱ እና 21ኛው ክፍለ ዘመን” መግቢያ ላይ እንደሚከተለው አስፍረውት እናገኛለን።

“ትውልድ ከትውልድ ሲሸጋገር የሚመጣው ማንኛውም ጥበብ ማንነትን ሰርቆ ሌላ ክፍተት መፍጠር የለበትም። የሚፈጥር ከሆነ ግን ከዘመናዊነት ጋር የተቸረልን ነገር ሁሉ ከጥያቄ ገብቶ መልስ ሊሰጥበትና ሊሰላሰል ይገባል። በሰው ልጆች ህይወት ጉዞ ከዕድገት ጋር ተያይዘው የሚንጸባረቁ ማናቸውም ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ግላዊ አስተሳሰቦች ከተጨባጭ ሁኔታ ጋር ተዛምደው ምን እየፈየዱ ነው ብሎ መጠየቅ ከአንድ ትውልድ የሚጠበቅ ማህበራ ግዴታ ነው። አስተሳሰቦች ተፈትገውና ተብላልተው የሚያመጡት ገፀ-በረከት አሊያም ቸል ተብለው የሚያመጡት ቀውስ አንድን ህብረተሰብ አደጋ ላይ የሚጥሉ ወይም ትክክለኛ አቅጣጫ እንዳይዝ እንደምክንያት ሊቀመጡ የሚችሉ ነገሮች ናቸው” ሲሉ ይንደረደራሉ።

 “ወጣቱ ሊዝናና ይገባል፣ ነገር ግን የሚዝናናበትን መንገድ መምረጥ ደግሞ ግዴታው ነው” የሚሉት አቶ ፈለቀ፤ አለማችን በርካታ የመዝናኛ አማራጮችን እያቀረበች መሆኑን ታሳቢ በማድረግ መዝናናት በምርጫችን የተወሰነ ነው ይላሉ። አሁን አሁን ወጣቱ በፌስቡክ የሚቀርብለትን ፅሁፍና መረጃ ሳይመረምር እንደወረደ መቀበሉ ስህተት ነው የሚሉት አጥኚው፤ ያነበብነውን ነገር መመርመር ይገባናል ሲሉ ይመክራሉ።       

መጽሀፎቹን ከማሰናዳት አንጻር በተለይም ሁለተኛውን መፅሐፍ ለማዘጋጀት በርካታ ተግዳሮቶች አጋጥመዋቸው እንደነበር ይጠቅሳሉ። በቂ መረጃ ያለመኖር፤ መረጃውን የያዘው አካል ለመስጠት ብሮክራሲ ማብዛት፤ የመረጃ አያያዞችን ደካማ መሆንና የአቅም ውስንነት ከሚጠቀሱት ፈተናዎች መካከል ጥቂቶቹ እንደሆኑ አጥኚው አቶ ፈለቀ ያስረዳሉ። በዚህ አጋጣሚ ጥናቱን በሚያካሄዱበት ወቅት የረዷቸውን በአዲስ አበባ ያሉ የከምባታ ምሁራንን በጠቅላላ አመስግነዋል።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
15930 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1073 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us