የ“መባ” እና “የነገን አልወልድም” ትንቅንቅ በጉማ

Wednesday, 03 May 2017 12:05

 

በአንቀልባ ያለውን የአገራችንን ፊልም ከመደገፍ አንፃር የራሱን አሻራ እያስቀመጠ ላለፉት አራት ዓመታት የተሰናዳው “ጉማ የፊልም ሽልማት”. . . ዘንድሮም ከደብዛዛ ድክመቶቹም ጋር ቢሆን የፊልሙን መንደር አባላት በሚያነቃቃ መንፈስ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ ባሳለፍነው ሰኞ (ሚያዝያ 23 ቀን 2009 ዓ.ም ) ተከናውኗል። በአገር ውስጥ ለዕይታ ከቀረቡ 120 ፊልሞች መካከል 71 ስራዎችን የመዘገበው “ጉማ” 18 ፊልሞችን በአስራ ስድስት ዘርፎች ያወዳደረ ሲሆን፤ የህዝብ ምርጫና የህይወት ዘመን አሸናፊዎችንም አካቶ ተካሂዷል።

በርካታ ታዳሚያን በተገኙበትና በኢ.ኤን.ኤን (ENN) ቴሌቪዥን ጣቢያ በኩል የቀጥታ ስርጭት ባገኘው በዚህ የሽልማት ምሽት ላይ በተለየ መልኩ ሁለት ፊልሞች ጎልተው ወጥተዋል ማለት ይቻላል። ካነሱት የታሪክ እና ካሳዩት ጥበብ በመነሳት ሁለቱን ፊልሞች በ2008 ዓ.ም በሀገራችን ከተሰሩ ፊልሞች በመጠኑም እንደሚለዩ ተመልካች አስቀድሞ ግምት ሰጥቷቸው ነበር ማለት ይቻላል። የዳይሬክተር አብርሃም ገዛኸኝ “የነገን አልወልድም” እና የዳይሬክተር ቅድስት ይልማ “መባ” የምሽቱ የጉማ ፊልም ሽልማት ትንቅንቅ ያሳዩ ነበር። በምሽቱ የሽልማት ፕሮግራም ላይም ይህ በግልፅ መታየቱን እማኝ ሆነን አረጋግጠናል።

የዘንድሮ የጉማ ፊልም ሽልማት የከባድ ሚዛን ተፋላሚዎች ሆነው የቀረቡት የአብርሃም ገዛኸኝ “የነገን አልወልድም” እና የቅድስት ይልማ “መባ” ፊልሞች ናቸው። በበካታ ዘርፎች በመታጨትም ቅድሚያውን ይዘዋል።

በጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ (ሊብሮ) መጽሀፍ ላይ ተመስርቶ የተሰራው “የነገን አልወለድም” ፊልም በዘንድሮ የጉማ ፊልም ሽልማት በአስራ አንድ ዘርፎች እጩ ሆኖ የቀረበ ሲሆን፤ በስድስት ዘርፎች አሸናፊ መሆን ችሏል። ይህም ሲባል ጋዜጠኛና ተዋናይ ብርሃኑ ድጋፌ ሁለት ጊዜ ወደመድረክ የመጣበትን የዓመቱ ምርጥ ተስፋ የተጣለበት ተዋናይን እና የዓመቱ ምርጥ መሪ ተዋናይን ዘርፍ አሸናፊ የሆነ ሲሆን፤ በምርጥ ረዳት ተዋናይ ዘርፍም ተስፋዬ ይማም አሸናፊ ሆኗል። በምርጥ ፊልም ስኮር ታደለ ፈለቀ አሸናፊ ሆኗል። በስተመጨረሻም ዳይሬክተሩ አብርሃም ግዛኸኝ ምርጥ ዳይሬክተር ሲባል፤ ፊልሙም የዓመቱ ምርጥ ፊልም ሆኖ ተሸልሟል።

እዚህ’ጋ በስድስት ዘርፎች አሸናፊ ሆኖ ሽልማቱን ያገኘው “የነገን አልወልድም” ይገባዋል የሚያስብል ቢሆንም፤ በአንዳንድ ተመልካቾች ዘንድ ለታዳጊ ወጣቶች መስጠት በነበረበት “ተስፋ የተጣለበት ተዋናይ” ዘርፍ ብርሃኑ ድጋፌ አሸናፊ መሆኑ ያልተዋጣላቸው እንደነበር አስተውለናል። ባለሙያዎቹ ግን ጀማሪ እንደመሆኑ መጠን ተስፋ የተጣለበት የሚለው ዘርፍ ስር መካተቱ ተገቢ ነው ብለው ሲሞግቱ አምሽተዋል።

በተረፈ ግን መፅሐፍትን ወደፊልም በመመለስ ከዚህ ቀደም “ሎሚ ሽታ” በተሰኘውና በአዳም ረታ መፅሐፍ ላይ ተመስርቶ በተሰራው ፊልሙ ሽልማትና አድናቆትን ያተረፈው ወጣቱ ዳይሬክተር አብርሃም ገዛኸኝ ምሽቱን ከስራ ባልደረቦቹ ምስጋናን ብቻ ሳይሆን የዳይሬክተርነት ፈጣሪነቱንም በይፋ ሲያስመሰክር ሰምተናል። ለዚህም ይመስላል ጋዜጠኛ ብርሃኑ ድጋፌም ሆነ ረዳት ተዋናይ ተስፋዬ ይማም “ዳይሬክተር ተዋናይን እንደሚሰራ አሳይቶናል” እስከማለት የደረሱት።

በምሽቱ ከ“የነገን አልወልድም” ባልተናነሰ መልኩ የሽልማት መድረኩን ደጋግሞ የተሳለመው “መባ” የተሰኘው የቅድስት ይልማ ፊልም ነው። በአእምሮ ህሙማን ታሪክ ላይ ተመስርቶ የተሰራውና በበርካቶች ዘንድ የተወደደው “መባ” ፊልም በአስራ አራት ዘርፎች እጩ ሆኖ መቅረብ ችሏል። ይህም በዕጩነት ከፍተኛው ደረጃ ላይ የደረሰ አሰኝቶታል። ነገር ግን “መባ” በምርጥ ገፅ ቅብ ዘርፍ ደረጄ ፍቅሬን ተሸላሚ ሲያደርግ፤ በምርጥ ሲኒማቶግራፊ ዘርፍ ብስራት ጌታቸውን አሸልሟል። በማስከተልም በምርጥ ተስፋ የተጣለበት ተዋናይት ዘርፍ ዓለም ካሳሁንን ሲያሸልም፤ በምርጥ ተዋናይት ዘርፍም እንዲሁ እድለወርቅ ጣሰውን ተሸላሚ አድርጎ አስፈንጥዟል።

የ“መባ” ፊልም ደራሲና ዳይሬክተር ቅድስት ይልማ ከዚህ ቀደም በሰራችው “ረቡኒ” ፊልሟ የበርካቶች ልብ የገዛች እንደነበረች ይታወሳል። በምሽቱም በስራ ባልደረቦቿ ዘንድ ከመድረክ ተደጋግሞ ስሟ በአድናቆትና በምስጋና ሲነሳ ሰምተናል።

የአራተኛው ዓመት የጉማ ፊልም ሽልማት ዘርፎች ውስጥ በምርጥ ፊልም ስር በእጩነት የቀረቡት “የነገን አልወልድም”፣ “መባ”፣ “አትውደድ አትውለድ”፣ “ስስት (ቁጥር 2)” እና “ዮቶጵያ” ሲሆን አሸናፊው “የነገን አልወልድም” ሆኗል። እዚህ’ጋ በንፅፅር መነሳት ያለበት በአብዛኛው የሽልማቱ ተቀራማች ሆነው የቀረቡት “መባ” እና “የነገን አልወልድም” ያልተካተቱበት ዘርፍ መኖሩ ነው። ይህም የበደሌ ስፔሻል የተመልካቾች ምርጫ ይሰኛል። በዚህ ዘርፍ ውስጥ እጩ ሆነው የቀረቡት ፊልሞች “እውነት ሀሰት”፣ “ይመችሽ፣ ያራዳ ልጅ”፣ “ወፌ ቆመች”፣ “ስስት (2)” እና “ሀ እና ለ” የተሰኙ ፊልሞች ናቸው። አሸናፊው “ወፌ ቆመች” ሆኗል። ይህ ክስተት የተመልካቹና የባለሙያው ዕይታና ምርጫ ምን ያህል የተራራቀ እንደሆነ የሚያመላክት ነበር ማለት ይቻላል።

የጉማ ዓመታዊ የፊልም ሽልማት እንደተጠበቀው አልሆነም የሚሉ ተመልካቾች ያልታጡ ሲሆን፤ ምሽቱ በተባለው ሰዓት ባለመጀመሩና የተቀላጠፈ መግባባት (coordination) ችግር መታየቱ ለመቀዛቀዙ እንደዓብይ ምክንያት ተነስቷል። የፕሮግራሙ መስራችና ስራ አስኪያጅ ዳይሬክተር ዮናስ ብርሃነ መዋም ስለመዘግየቱ በፕሮግራሙ አሸናፊ ኢትዮ- ፊልም ፕሮዳክሽን ስም በይፋ ይቅርታ ጠይቋል።

በአንጻሩ ደግሞ መድረክ መሪው ሽመልስ በቀለ የፕሮግራሙ አስተባባሪዎች አስቀድመው ለሸላሚዎቹ ማሳወቅና ማስጠንቀቅ የሚገባቸውን ባለማድረጋቸው የተፈጠረውን ስህተት ተንተርሶ በሸላሚዎች ላይ ለመሳለቅ መሞከሩ ለትችት ዳርጎታል። ይህም ተግባር ወደፊት እንደማይቀጥል ተስፋ አለን። አዘጋጆቹ እርስ -በእርስ ሆነ በእንግድነት ተጋብዘው ከሚሸልሙት ግለሰቦች ጋር በቅድሚያ መነጋገርና መግባባት ይጠበቅባቸዋል እንጂ፤ እንደድንገት ፈጠራ ግራ አጋቢ ክስቶችን መደጋገም ከፕሮግራሙ ከፍታ አንጻር አይጠበቅም።

የምሽቱን የጉማ ፊልም ተሸላሚዎች በወፍ በረር ለማስታወስ ያክል፤ የህይወት ዘመን ተሸላሚ የሆኑት በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ታሪክ የምስል ቀረፃ ሂደት የካሜራ አባት የተሰኙት የዕድሜ ባለፀጋው አቶ ካሳ ምህረቴ ናቸው። በዚህ አጋጣሚ የመጀመሪያ ተሸላሚ ሆነው ወደመድረክ ከመቅረባቸው ጋር ተያይዞ ስለታሪካቸው በጥቂቱ የሚያሳይ የአጭር ደቂቃ ዘጋቢ ፊልም ቢኖር መልካም ነበር። ይህም ባይሆን ስለታሪካቸው በመድረክ አጋፋሪው በኩል ቢነበብ ጥሩ ነበር ያሉ ተመልካቾች ብዙ ነበሩ።

በመቀጠል የዓመቱ ምርጥ አጭር ፊልም ዘርፍ “ፈዲስቱ”፣ “ሳይቃል በቅጠል”፣ “ዘመን”፣ “ያልተሳለ ግርፊያ” እና “1>2” ፊልሞች በዕጩነት የቀረቡ ሲሆን፤ አሸናፊ የሆነው የሚካኤል ሽመልስ ፊልም የሆነው “ፈዲስቱ” ነው።

በምርጥ ድምፅ ዘርፍ ረድኤት ከበደ “ከደመና በላይ”፤ አናኒያ ሃይሉ “በመባ”፤ ጥቅሌ ደበበና ብሩክ አየለ “የነገን አልወልድም” እንዲሁም ብሩክ አየለ “አትወደድ አትውለድ” ዕጩዎች ሲሆኑ ብሩክ አየለ “በአትወደድ አትወለድ” ፊልም ምርጥ ድምፅ ተብሎ ተሸላሚ ሆኗል።

በምርጥ የፊልም ማጀቢያ ሙዚቃ ዘርፍ፤ ብሩክ አሰፋ - ከ“መባ”፣ አብነት አጎናፍር ከ“ስስት -2”፣ ሰምአገኘሁ ሳሙኤል፣ ሙሉጌታ ሱጋሞና ዳንኤል ጌታቸው ከ “ሔሮል”፣ ብሩክ አሰፋ ከ“መባ” ፣ አዳነች ወ/ገብርኤልና ተገኝ ብሩ ከ“ሔዋን ስታፈቅር” እንዲሁም ማክዳ አፈወርቅና ኤልሳቤጥ መንግስቱ ከ“ዮቶጵያ” ፊልሞች ዕጩ ሆነው የቀረቡ ሲሆን፤ አሸናፊው ድምፃዊ አብነት አጎናፍር ሆኗል።

በምርጥ የፊልም ስኮር ዘርፍ ዕጩ ሆነው የቀረቡት ቴዎድሮስ ሞገስ (ከደመና በላይ)፣ ታደለ ፈለቀ (የነገን አልወልድም) ስምአገኘሁ ሳሙኤል (ሔኖክ) እና ብሩክ አየለ (አትወደድ አትወለድ) ናቸው። አሸናፊው ደግሞ ታደለ ፈለቀ ከ“የነገን አልወልድም” ፊልም ሆኗል።

በምርጥ ፊልም ጽሑፍ ዘርፍ ፍፁም ካሳሁን (ስስት - 2)፣ ጌታቸው ታደለ (ባማካሽ)፣ በሃይሉ ዋሴ (ዮቶጵያ)፣ ቅድስት ይልማ (መባ) እና ናኦድ ጋሻው (አትወልድ አትወለድ) ዕጩ ሆነው ቀርበዋል። አሸናፊው ደግሞ ናኦድ ጋሻው ሆኗል።

የዓመቱ ምርጥ ቅንብር (ኤዲተር) ዘርፍ ዕጩ ሆነው የቀረቡት ብስራት ጌታቸው (መባ)፣ ዳንኤል አንማው (ሔሮል)፣ ዘርዓይ ያቆብ (ስስት - 2) ፣ ናኦድ ጋሻው (አትወደድ አትወለድ) እና ናሆም ግርማ (የነገን አልወልድም) ናቸው። አሸናፊ ሆኖ የተሸለመው ዳንኤል አንማው ከ“ሔሮል” ፊልም ነው።

በምርጥ ረዳት ተዋናይት ዘርፍ ማርታ ጎይቶም ከ“ስስት - 2” አሸናፊ ስትሆን፤ አብረዋት በዕጩነት የቀረቡት ደግሞ ዘሪቱ ከበደ (መባ)፣ ህይወት ግርማ (የነገን አልወልድም)፣ ድርበወርቅ አሰፋ (ወፌ ቆመች) እና ማህሌት ፍቃዱ (በቁም ካፈቀርሽኝ) ነበሩ። በምርጥ ረዳት ወንድ ተዋናይ ዘርፍ ደግሞ ተስፋዬ ይማም ከ“የነገን አልወልድም” ተሸላሚ ሆኗል። በዚህ ዘርፍ ዕጩ ሆነው የቀረቡት ደግሞ ጆሲና ዳንኤል (መባ)፣ ፍቃዱ ከበደ (ሀ እና ለ)፣ እዮብ ዳዊት (ይመችሽ) እና ሽመልስ በቀለ (አትውደድ አትውለድ) ናቸው።

በ3ኛው የጉማ ፊልም ሽልማት ላይ የዓመቱ ምርጥ ፊልም ሆኖ የተሸለመው የአንተነህ ሃይሌ “ላምባ” ፊልም እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፤ በዘንድሮው ደግሞ ምርጥ ፊልም ሆኖ በተመልካችም ሆነ በባለሙያ ድምፅ የተመረጠው “የነገን አልወልድም” የተሰኘው የአብርሃም ገዛኸኝ ፊልም ነው።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
15991 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 977 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us