“በዓመት ሁለት ፊልሞችን የመሥራት ኀሳብ አለን”

Wednesday, 02 April 2014 12:18

አቶ ቶማስ ጌታቸው

የ“ፅኑ ቃል” ፊልም ደራሲና ፕሮዲዩሰር

 

“ቶም” ስሙ በብዙዎች ዘንድ በቪዲዮ ግራፊና በፊልም ፕሮዳክሽኖቹ የሚታወቅ ተቋም ነው። ከዚህ ተቋም ጀርባ ደግሞ ተደጋግሞ ስሙ የሚነሳ ባለሙያ አለ፤ የቶም ፊልምና ቪዲዮ ግራፊ ማሰልጠኛ ዋና ስራ አስኪያጅ እና ፕሮዲዩሰር ቶማስ ጌታቸው። የዛሬው የመዝናኛ አምድ እንግዳችን በፊልም ስራ ባለሙያ እና መምህር ከመሆኑ በተጨማሪ በተለየ መልኩ ፕሮዲዩስ ባደረጋቸው “ስርየት” እና “ፔንዱለም” ስራዎቹ በጉልህ ይጠራል። በቅርቡ ደግሞ ደረጃውን ከፍ በማድረግ አቅሙን ያሳየበትን “ፅኑ ቃል” የተሰኘ ፊልም ከፕሮዲዩሰርነቱ ባሻገር በደራሲነቱ ተከስቷል። ከቶማስ ጋር ይህ መሰል ቆይታ አድርገናል፤ መልካም ንባብ።

ሰንደቅ፡- ከፕሮዲዩሰርነትህ የሚቀድመው መምህርትህ ነውና እስቲ ስለመምህርነት ጊዜህ ትንሽ አጫውተኝ?

ቶማስ፡- ሁለት ሶስት ዓመት መምህር ሆኜ አገልግያለሁ። መጀመሪያ በማስተር ቪዲዮና ፎቶግራፍ ማሰልጠኛ ነበር ያስተማርኩት፤ ከዚያ በኋላ ነው ወደቶም የመጣሁት። ጥሩ ጥሩ ልጆችን ካወጣሁ በኋላ ነው ገንዘብ ጠርቀምቀም ሲልልኝ ወደፊልም ስራው የገባሁት።

ሰንደቅ፡- እስቲ ደግሞ ስለቶም ፊልምና ቪዲዮግራፊ ማሰልጠኛ አጀማመር ንገረኝ?

ቶማስ፡- በመጀመሪያ እኔ በሀገር ውስጥን በውጪ በተልዕኮም ጭምር በሚሰጡ ስልጠናዎች ስለፊልም ስራ ያካበትኩት ዕውቀት ነበረኝ። ከዚያ በኋላ በማስተር ት/ቤት ውስጥ ከረዳት መምህርነት ጀምሬ ነው ስራውን ስሰራ የቆየሁት። የሚገርምህ ነገር እያስተማርኩ በነበረበት ወቅት ራሱ ወደፊልም አለም ጠቅልዬ እገባለሁ የሚል ሃሳብ አልነበረኝም። ግን ደግሞ የማስተማሩን ስራ በጣም እወደው ስለነበር ሰዎች ፊልም እንዲሰሩ አበረታታለሁ። በተለይ ያስተማርኳቸው ተማሪዎች ፊልም ሰርተው ሳይ በጣም ነበር የምደሰተው። በነገራችን ላይ ለኔም የፊልም ስራ መነቃቂያዎቼ ተማሪዎቼ ናቸው ማለት እችላሁ። አይደለም ትልቅ ፕሮዳክሽን ሰርተው፤ የሁለትና የሶስት ደቂቃ ስራ ሰርተውም ቢሆን ሲያሳዩኝ ከእነርሱ በላይ እኔ ደስተኛ እሆናለሁ። ይህ ታዲያ እኔ ከማስተማር የዘለለ በፊልም ስራ ውስጥ ብሳተፍ የተሻለ ነገር ለመስራት አቅም እንዳለኝ ስላመንኩ ነው ቶም የፊልምና ቪዲዮ ግራፊ ማሰልጠኛን ያቋቋምኩት። እንደሚታወቀው የኛ ማሰልጠኛ አሁን በአገራችን መልካም ስም ያላቸውን ባለሙያዎቹን አፍርቷል።

ሰንደቅ፡- ስለመጀመሪያው ፊልምህ ምን የምታስታውሰው ነገር አለ?

ቶማስ፡- ያው አንተም እንደምታውቀው የመጀመሪያ ፊልማችን “ስርየት” ነበር። ከዚያም ከሁለትና ከሶስት ዓመት ቆይታ በኋላ ደግሞ “ፔንዱለም”ን ሰራን። ይህው አሁን ደግሞ ከሶስት ዓመት ቆይታ በኋላ “ፅኑ ቃል” ተሰራ። ከጀመርንበት ጊዜ አንፃር የሰራናቸው ፊልሞች ብዙ ባይሆኑም ፊልምን ጀምሮ መጨረሻ በራሱ ትልቅ አቅም የሚጠይቅ ከመሆኑ አንፃር መልካም ነው። እንደሚታወቀውም የሰራናቸው ስራዎች ሁሉ ጥሩ ስምን አትርፈውልናል ማለት ይቻላል።

“ስርየት” የመጀመሪያ ፊልሜ እንደመሆኑ ብዙ ትምህርት ያገኘሁበት ፊልም ነው። እውነቱን ለመናገር ፊልሙን ከመስራቴ በፊት ለምንድነው ፊልም የምሰራው ብዬ ራሴን ጠይቄ ነበር። በአንድ በኩል ንግድ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ፊልም በራሱ መናገር የምንፈልጋቸውን ነገሮች የምናስተላልፍበት ከመሆኑ አንፃር ነው የመረጥኩት። ባይገርምህ ከዚያ በፊት የወጡ ፊልሞች በሙሉ ለኔ ጥሩ ትምህርት የሰጡ ነበሩ። “ስርየት”ን ለመስራት ስነሳ ሁለት አቋም ነበረኝ። አንደኛው እንደማንኛውም ፕሮዲዩሰር ጥሩ ስራ ሰርቼ ገቢ ለማግኘት ሲሆን፤ ሁለተኛው እና ዋነኛው ሃሳቤ የነበረው ግን ማስተላለፍ የምፈልገውን ነገር በተሻለና ባልሰለቸ መንገድ በፊልም አማካኝነት ማሳየት እችላለሁ የሚለው ነበር፤ ስርየት እንደፊልም ሊታይም ሊነገርም የሚችል ታሪክ የነበረው ስራ በመሆኑ የተሳካልኝ ይመስለኛል።

ሰንደቅ፡- በስርየት ውስጥ የመረጥከውና ያስተላለፍከው መልዕክት ምን ነበር?

ቶማስ፡- ስክሪፕቱን እንዳየሁት እኔን የገዛኝ ሀሳብ ምን መሰለህ፤ በርግጥም በአንድ ወቅት፤ በታሪክ፣ በፖለቲካ አመለካከት፤ በባህል፣ ወዘተ በተለያየ ምክንያት ቁርሾ የነበረ ሰው ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዳይሻገር ምን መደረግ አለበት የሚልና የቂምን ድልድያ መስበር ለማሳየት ነበር። ይህንን አይነት ታሪክ ሊቀር እንደሚገባው መናገር የምንችለው በፊልማችን ነው። ይህ ነው እኔን የገዛኝ ሃሳብ።

ሰንደቅ፡- ተመልካቹ አንተን የገዛህ ሃሳብ ደርሶታል? ምን ምላሽ ነበረው?

ቶማስ፡- ሰው ፊልሙን ወደድኩት ሲል በብዙ መልኩ ይገልፃል። አንዳንዱ ሳውንዱን፣ አንዳንዱ ትወናውን፣ አንዳንዱ ዳይሬክቲንጉን ሊወደው ይችላል። ይህ ለተመልካች ነፃ ነው። ነገር ግን ተመልካች የወደደው ምንም ይሁን ምንም ታሪኩ ቀልቡን ካልገዛው ቁጭ ብሎ እነዚህን ሁሉ ነገሮች አይመለከትልህም። ከሁሉም በላይ ታሪኩ ሊገዛው ግድ ይል ነበር። ታሪኩ ፕሮፓጋንዳ በማይመስል መልክ ታይቶና ተወዶ የቆየ ፊልም ነበር ማለት እችላለሁ። በተለይ በሲኒማ ቤቶች ተገኝቼ የመጨረሻዎቹን ትዕይነት ከተመልካቹ ጋር ስመለከት ይሰማ የነበረው ነገር ታሪኩ ገብቶታል ማለት ነው እንድል የሚያስደፍር ነበር።

ሰንደቅ፡- ወደሁለተኛው ፕሮዳክሽን ስንመጣስ “ፔንዱለም” እንደጠበከው ነበር? “ስርየት” ልብ አንጠልጣይ የፍቅር ፊልም ሲሆን፤ “ፔንዱለም” ደግሞ የፍቅር ኮሜዲ ዘውግን የያዘ ነው።

ቶማስ፡- አንድ ነገር የተረዳሁት በየትኛውም ዘውግ ቢሆን ጥሩ ፊልም ከሰራህ ተመልካች አለ። በሌላ በኩል መልዕክቶችን ለማስተላለፍ የግድ አንድ አይነት ዘውግን ብቻ መከተል የለብህም። ትላልቅ የሆኑ ቁም ነገሮችን በድራማ ዘውግ ውስጥ ማስተላለፍ እንደምትችል ሁሉ በኮሜዲ ዘውግም ውስጥ በትክክል ከሰራህው ይተላለፋል። በፔንዱለም ፊልም በኩል ላስተላልፈው የፈለኩት ነገር ከዕለት ተዕለት ኑሯችን መካከል የአንድን ሰው ውስጣዊ የሥነ-ልቦና ችግር ማሳየት ነበር። ከዚያ ሌላ የሰው ልጅ ክብርና ዋጋ ሊሰጠው የሚገባው ከውጫዊው ውበት ይልቅ የውስጣዊ ስብዕናው መሆን አለበት የሚል ሲሆን ይህም በግልጽ በፊልሙ በኩል ታይቷል። እንዳየኸው ሁለቱ “ሳሮን” የተሰኘ ተመሳሳይ ስም ያላቸው ገፀ-ባህሪይ ቆንጆዎች ናቸው። በዚህ ላይ በተመሳሳይ አፓርትመንት ውስጥ ነው የሚኖሩ ሴቶች ናቸው፤ ነገር ግን በፀባይ ፈፅሞ ይለያያሉ። በዚህ ፊልም ውስጥ ተመልካች ሁለቱን ገፀ-ባህሪያት ሲያወዳድር የሚለየው በመልክ ወይም በስም ሳይሆን መልካሙዋ እና ክፉዋ በሚል ይሆናል ማለት ነው። “ፔንዱለም” በራሱ ከነጥቃቅን ስህተቱ አሪፍ ነበር፤ ተመልካች ወዶት ያየው ነው።

ሰንደቅ፡- በሁለቱም ቀደምት ስራዎችህ አዳዲስ ተዋንያን በጥሩ ሁኔታ አስተዋውቀሃል፤ ስለምርጫህ አሁን ስታስበው ምን ይሰማሃል?

ቶማስ፡- በጣም አሪፍ ነበሩ። በሁለቱም ፊልሞች ላይ የዳይሬክተሮቹ እጅ ነበረበት። በቀረፃ ወቅትም በጣም ደስ የሚል ነበር ብዬ አስባለሁ። በነፃነት የሰሩት ስራ በመሆኑ ተዋንያኖቹም ተዋጥቶላቸዋል። ሰለሞን ታሼ (ጋጋ) በ “ስርየት” ፊልም ላይ ሲወጣ፤ አማኑኤል ይልማ ደግሞ በ“ፔንዱለም” ፊልም ላይ ተሳክቶላቸዋል። ለባለሙያዎቹ የመስራት ነፃነታቸውን በሰጠኋቸው ቁጥር ጥሩ ስራ ይሰሩልሃል፤ በውጤቱም አንተ ተጠቃሚ ትሆናለህ የሚለውን ነገር በነዚህ ስራዎች አረጋግጫለሁ።

ሰንደቅ፡- ከፊልም በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት የቲቪ ተከታታይ ድራማዎች ተመልካችን እየሳቡ ነውና ስለቲቪ ድራማ ምን ታስባላችሁ?

ቶማስ፡- በጣም ሰፊ እቅድ አለን። ስንሰራም ለቀደሙት ስራዎች ክብር አለን። ምክንያቱም ከዚህ በኋላ ወደቲቪ ድራማ ለምንመጣ ሰዎች መንገድ ማሳየት የቻሉ ናቸውና። እርግጠኛ ነኝ በቅርቡ ጥሩ የሚባል የቲቪ ድራማ ይዘን መምጣታችን አይቀርም። የራሳችንን ጥናት አድርገናል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተገናኝነተን በመነጋገር የምንሰራ ይሆናል። ነገር ግን ከዚህ በኋላ በቋሚነት በዓመት ቢያንስ ሁለት ፊልሞችን የመስራት ሃሳብ አለን።

ሰንደቅ፡- በፊልም ስራ ምርታማ ከመሆን በተጨማሪ የምታስበው ነገር አለ?

ቶማስ፡- አሁን አንድ ፊልም ሰርተህ ትርፋማ የመሆን ያለመሆን ጉዳይ ብቻ አይደለም የሚያሳስበኝ። ፊልሞቻችን በአለም አቀፍ ደረጃ መታየት የሚችሉበትን ሁኔታ እንዴት መፍጠር እንችላለን በሚለው ነገር ላይ መስራት አለብን። ይሄ በኔ ብቻ ሳይሆን የጠቅላላ ባለሙያው የትብብር ስራ ቢሆን እናሳካዋለን የሚል ተስፋ አለኝ።

ሰንደቅ፡- በስርየትና በፔንዱለም ፊልሞችህ ሁለት ምርጥ የትወና ብቃት ያሳዩ አዳዲስ ባለሙያዎችን አሳይተኸናል። አሁን ደግሞ በ“ፅኑ ቃል” ፊልምህ አንተ ራስህ የፊልም ድርሰት መፃፍ እንደምትችል አሳይተኸናል። ሌላስ ምን አዲስ ነገር አለ?

ቶማስ፡- አዎ! በ “ፅኑ ቃል” ፊልም ራሴን በድርሰት አምጥቻለሁ። አሁንም ግን ራሴን ደራሲ ነኝ ብዬ ማስቀመጥ አልፈልግም። እውነቱን ለመናገር ታሪክ ቢቸግረኝ ብዬ ነው የገባሁበት። ብዙ የፊልም ፅሁፎች ይመጣሉ ግን እኔ ልሰራው እንደምፈልገው አይነት አልሆኑልኝም። በመሆኑም ቁጭ ብዬ እስቲ የአቅሜን ልምከር ከኔ የተሻለ ስራ ከመጣ ደግሞ ቅድሚያ ይሰጠዋል በሚል መንፈስ የሰራሁት ፊልም ነው። በነገራችን ላይ ጥሩ የፊልም ፅሁፍ ሙሉ በሙሉ የለም ለማለት ሳይሆን ላስተላልፈው የምፈልገውን ማህበራዊ ፋይዳ ያለው ስራ ማግኘት ባመቻሌ የራሴን አማራጭ መውሰዴን ልብ እንድትልልኝ ፈልጌ ነው። እንጂ እኛ ጋር በቁጥር መግለፅ በሚያዳግት ደረጃ የፊልም ፅሁፎች ይመጣሉ። አንዳዴ በሳምንት 15 እና 20 ስራዎች ሊመጡ ይችላሉ። በዓመት ውስጥ ከ50 ያላነሱ የፊልም ፅሁፎችን አይቻሁ። ግን መናገር የምፈልገውን ታሪክ አላገኘሁም ለዛ ነው የራሱን ፅሁፍ የሰራሁት። “ፅኑ ቃል” አንዳች መልዕክት ለመናገር በደንብ ታስቦበት የተሰራ ስራ ነው እስከሁን እደምሰማውም ተመልካች የወደደው መስለኛል።

ሰንደቅ፡- በተለየ ብሰራው ብለህ የምታስበው አይነት ታሪክ ይኖራል ከባለሙያዎችን ከመናም ጋር መስራት ትመርጣለህ?

ቶማስ፡- ባይገርምህ ከማንኛውም ባለሙያ ጋር ለመስራት ዝግጁ ነኝ። ተዋናይ “እከሌ” ፤ ዳይሬክተር “እከሌ” የሚል ምርጫ የለኝም። ለሚመጣው የፊልም ታሪክ የሚመጥን አቅም ያለው ሰው ሁሉ (አማተርም ቢሆን) አብሮኝ ሊሰራ ይችላል። ከችሎታው በተጨማሪ ደግሞ በዲስፒሊን ጉዳይ ላይ አልደራደርም። የፈለገውን ያህል ታዋቂና ጎበዝ ባለሙያ ቢሆን እንኳን ዲስፕሊን ከሌለው ዋጋ እከፍላለሁ እንጂ በጭራሽ አብሬ መስራትን አልፈልግም።

ሰንደቅ፡- ቶም ፊልም ፕሮዳክሽን ለፊልም ባለሙያዎች አሪፍ ከፋይ ነው ማለት ይቻላል?

ቶማስ፡- (ሳቅ) በጭራሽ! እንደዚያ ብለን አናስብም። በነገራችን ላይ ጥሩ መክፈል አንጻራዊ ነው። ምናልባት ሀገር ውስጥ ካሉ ከፋዮች በአንድ ብርና በአንድ ብር ከሃምሳ እንበልጥ ይሆናል። ነገር ግን ክፍያው በቂ እንዳልሆነ በግሌ አምናለሁ። ኢንዱስትሪው ከዚህ በበለጠ ተሻሽሎና አድጎ ፕሮዲዩሰሩም አትርፎ ባለሙያዎቹም የሚገባቸውን ቢያገኙ መልካም ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ግን ባለሙያዎቹም ፕሮዲዩሰሮቹም የሚገባቸውን እያገኙ እንዳልሆነ አምናለሁ። በአደጉ ሀገራት እንደምናየው ቢሆን እኮ አንድ ተዋናይ ጥሩ ፊልም ከሰራ ወዲያው ነው አሉ ከሚባሉ ሀብታሞች አንዱ የሚሆነው። እኛ’ጋ ግን ይሄ የማይታሰብ ነው። ነገር ግን አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ከአገሪቱ የፊልም ኢንዱስትሪ አቅም አንፀር በጣም የወረደ ነው የምንከፍላቸው ለማለት አይደለም። በተቻለን ሁሉ ለባለሙያዎቹ የሚመች ክፍያ እንከፍላለን።

ሰንደቅ፡- እንደፕሮዲዩሰር የፊልም ስራ አዋጭ ነው?

ቶማስ፡- ለዚህ ጥያቄ መልሴ በተቃርኖ የተሞላ ነው። ይሄ በጥንቃቄ መመለስ ያለበት ጥያቄ ነው። እውነቱን ለመናገር ፊልም በኢትዮጵያ ውስጥ በጣም አዋጭ ስራ ነው። የራሱ ባህልና ቋንቋ ያለው 80 ሚሊዮን ህዝብ አለ። ከዚያ ውስጥ ከግማሽ በላይ ወጣት የሆነ ነው። ስለዚህ ተመልካች አለ ማለት ነው። በከተማችን ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ሲኒማ ቤቶችን ብትመለከት ጥቂቶች ናቸው የውጪ ፊልሞችን የሚያሳዩት። አብዛኛው ተመልካች ሰልፍ ይዞ የሀገር ውስጥ ስራዎችን የሚመለከት ነው፤ ይሄ ትልቅ ነገር ነው። በሌላ በኩል ግን እየወጡ ካሉት ፊልሞች ውስጥ 80 እና 90 በመቶዎቹ ከስረው ይቀራሉ። ይሄ ለምን ሆነ? የሚለው ነገር የፊልሞቻችን ጥራትና ታሪኮች በተመለከተ ሰፋ ያለ ጥናት የሚጠይቅ ይመስለኛል። ነገር ግን ፊልም በኢትዮጵያ ውስጥ ገና ያልተነካ ገበያ አለው ማለት ይቻላል።

ሰንደቅ፡- በፊልም ስራ ውስጥ በተለየ ሊታስብበት ይገባል የምትለው ነገር?

ቶማስ፡- ሶስቱንም ፊልሞች ስንሰራ ባለሙያዎቻችን ለአደጋ የተጋለጡ እንደነበሩ አስታውሳለሁ። አሁን አንድ ነገር በጣም ያሳስበናል። ይህውም ምንድነው ለፊልም ባለሙያዎች የመድህን ዋስትና ያስፈልጋቸዋል የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሻለሁ። ይህ ነገር በኔ ካምፓኒ ብቻ ሳይሆን ሌሎም ሊያስቡበት የሚገባ ይመስለኛል።

ሰንደቅ፡- ቶም በምን ትዝናናለህ?

ቶማስ፡- ሁለት ነገር ያዝናናኛል። ከቤተሰቤ ጋር ነፃ ጊዜን ማሳለፍ እና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረግ ያስደስተኛል።

ሰንደቅ፡- ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ?

   ቶማስ፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ። በዚሁ አጋጣሚ ግን በሰራናቸው ፊልሞች ሁሉ ከፊትም ከኋላም ሆነው አብረውን ሊሰሩ ባለሙያዎች ያለኝን ምስጋናና ክብር ንገርልኝ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
9352 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us