ድብቁን ማንነት ፍለጋ

Wednesday, 10 May 2017 12:03

 

በአሸናፊ ደምሴ

የፊልሙ ርዕስ             “ፈልጌ አስፈልጌ”

ዳይሬክተር          አቦወርቅ ሐብቴ

ደራሲ              መላኩ ደምለው

ፊልም ጽሁፍ        ለገሰ ታደሰ

ፕሮዲዩሰር          አሰፋ ገረመው

ሜካፕ             አዜብ ወንደሰን

ተዋንያን           ያየህይራድ ማሞ፣ ፍፁም ፀጋዬ፣ ተዘራ ለማ፣ ዝናህብዙ ፀጋዬ፣ እየሩሳሌም ደረጀ፣ ዳንኤል አበበና ሌሎችም።

ያፈጠጠ እውነት፣ የተደበቀ ማንነትና በፍቅር የፀና ቤተሰብ የገባበትን ማጥ የሚተርክ ልብ አንጠልጣይ የቤተሰብ ድራማ ዘውግ ያለው አዲስ ፊልም ነው፤ “ፈልጌ አስፈልጌ” በአቡ ቪዲዮ ፊልም ፕሮዳክሽን ተዘጋጅቶ የቀረበው ይህ ፊልም የዘመናት ምስጢርንና የተንኮል ቁልቁለትን በመሳጭ ቅንብር ፍንትው አድርጐ ያሳየናል።

 

ከጋብቻ ውጪ የተወለዱ ልጆች አባቴ የሚሉት ሰውና አባታችሁ ነኝ የሚላቸው ሰው ሲለያይ የሚገጥማቸው ስነ-ልቦናዊ ቀውስን ፊልሙ ይተርካል። በሌላ በኩል ደግሞ ጓደኝነትንና ወዳጅነትን ተገን አድርገው ተንኮልና ሴራ የሚጐነጉኑ መሰሪዎች ራሳቸው በቆፈሩት ጉድጓድ አፋፍ ላይ ሲደርሱ የሚወስኑትን ውሳኔ ያሳየናል።

 

የሙት እናቱን ቃል ለመፈፀም በተሰጠው አድራሻ ፍለጋውን የሚጀምረው የ“ፈልጌ አስፈልጌ” ፊልም መሪ ገፀ-ባህሪይ አቤል (ያየህይራድ ማሞ)፤ አፈላልጐ ያገኛቸው አቶ እንዳሻውን (ዝናህብዙ ፀጋዬ) የነገሩትን ትልቅ ምስጢር ማመን አቅቶት ክፉኛ ከመደናገጡም ባለፈ አምኖ ለመቀበል ሲቸገር እንመለከታለን። ይህን ቀውስ ለመቋቋምም አምሽቶና ጠጥቶ ወደቤት መግባቱን ይደጋግመዋል። ይህም ከባለቤቱ ሶስና (ፍፁም ፀጋዬ) ጋር የግጭት መንስኤ ይሆናል።

 

“ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል” እንዲሉ ቤቱን ጥላ የወጣችው ሶስና በገዛ ጓደኞቿ በመድሐኒት ደንዝዛ የመደፈር ሴራ ውስጥ ትወድቃለች። ቀጥሎ ያለውን የታሪክ ሂደት ተመልካች ይመልከተው።

ባለቤታቸው ካረፈች ገና በአንድ ዓመቱ ከወጣቷ ዛጐል (እየሩሳሌም ደረጀ) ጋር ፍቅር የጀመሩት አቶ ክንፈ (ተዘራ ለማ) ይባስ ብሎ ይህ ግንኙነት በልጅም የደረጀ መሆኑን ስንሰማ በጣም የፈጠነ ቢሆንም “ያዋከቡት ነገር ምዕራፍ አያገኝም፣ ፍቅሬ-ፍቅሬ በዛ እኔ አላማረኝም” የምትለዋን የአርቲስት ጥላሁን ገሰሰን ዘፈን ታስታውሰናለች። እዚህች’ጋ በንፅፅር መነሳት ያለበት ልጃቸው ቴዲ (አማን ታዬ) ከፍቅር ጓደኛው በተደጋጋሚ የሚቀርብለትን የትዳር ጥያቄ ሲሸሽ አባት ግን በፍጥነት ነገሩን የገብስ ያህል ሲያቀሉት ማየት፤ የቴዲ ስነ-ልቦና ምን ያህል በእናቱ ምክንያት ተሰብሮ እንደነበር እንረዳለን።

 

በ“ፈልጌ አስፈልጌ” ፊልም ውስጥ የተሳሉት ገፀ-ባህሪያት ድክመት ስሜታዊነት እንደሆነ ለማሳየት አራት ያህል ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል። የመጀመሪያው አቤል እውነተኛ አባቱን ስለናቱ ሞት አርድቷቸው የቀብር ቦታውን ለማሳየት በሄደበት ጊዜ የምንመለከተው ነው። እዚህ ትዕይንት ላይ እውነተኛ አባቱ በመቃብር ስፍራ ሲያለቅሱ እየተመለከተ እንደሰው ለማፅናናት ከመሞከር ይልቅ ይባስ ብሎ ከሩቅ ቦታ አሳፍሮ ያመጣቸውን ሽማግሌ (አቶ እንዳሻውን) መንገድ ላይ ጥሏቸው ይሄዳል። ይሄ የገፀ-ባህሪውን የበዛ ስሜታዊነት የሚያሳይ ነው።

 

በሁለተኛ ደረጃ ሊታይ የሚችለው የተጋነነ ስሜታዊነት አሁንም (የአቤልና የቴዲ እውነተኛ አባት አቶ እንዳሻው) ማን እንዳሳያቸው አይታወቅም (ነገር ግን ዛጐል ትሆናለች ብለን እንገምታለን) የቤተሰቡ ቤት ድረስ ድንገት ሰተት ብለው ይገባሉ። በዚህም ጊዜ ቴዲ በኃይልና በጉልበት እየገፈታተረ ያስወጣቸዋል። እዚህ’ጋ ምናልባት ቴዲ ቀድሞ የሚያውቀው ነገር ስላለ ይሆን እንዴ ይሄን ያህል የበዛ ስሜታዊነት ያሳየው ልንል እንችላለን። ነገር ግን ተመልካች አያቅም።

 

ሌላኛው ቤተሰባዊ መፍረስን ያስከተለው ስሜታዊነት በእነሶስና እና አቤል ቤት የተፈጠረው ግለት ነው። በተደጋጋሚ ውጪ በማምሸትና በመጠጣቱ ስትበሳጭ የምንመለከታት ሶስና አስቀድማ “ለልጆቼ ስል ነው” በማለት የቻለችውን ነገር ሁሉ ድንገት በገነፈለ ስሜታዊነት ተነስታ ቤተሰቡን ጥላ ስትሄድ እንመለከታለን። ይህም የባለቤቷን ችግር ለመረዳትና ለመፍታት ከሄደችበት ርቀት አንፃር የፈጠነ ውሳኔ ነው ያስብላል። ለምን ቢባል በፊልሙ ውስጥ ጠንካራ ሴት አድርጎ ተመልካች የሚጠብቃት እርሷን ነውና።

 

የመጨረሻው ጐልቶ የሚወጣውና ዋጋም የሚያስከፍለው ስሜታዊነት አቶ ክንፈ (ተዘራ ለማ) ቤታቸው ድረስ በመምጣት እውነቱን ያፍረጠረጡት አቶ እንዳሻውን ለመግደል አስበው የተኮሱት ጥይት መድረሻዋ ያልታሰበ መሆኑና በመጨረሻም ለራሳቸው ያተረፈላቸውን ችግር መመልከት እንችላለን።

“በተንኮል የምትቆፍረውን ጉድጓድ አታርቀው ምክንያቱም ማን እንደሚገባበት አይታወቅምና” ይሉት አባባልን የሚያስታውሰው የጓደኛሞቹ የተንኮል ሴራ አስተዛዛቢ ሆኖ ተጠናቋል። የሰው ልጅ ለማንነቱ፣ ለሀብቱና ለቀጣይ ህይወቱ ዋስትና ሲል በሰው ላይ ምን ያህል እንደሚጨክንም እንመለከታለን።

 

“ፈልጌ አስፈልጌ” ፊልም የእውነት ፍለጋን፣ የማንነት ፍለጋን፣ የተሰወረ ፍለጋን የምናይበት ልብ አንጠልጣይና የቤተሰብ ድራማ ዘውግ ያለው ፊልም ነው። የብርሃንና የድምፅ አጠቃቀሙም ዘመኑን የሚመጥን ነው ማለት ይቻላል።

“ፈልጌ አስፈልጌ” ፊልም ውስጥ በተመልካች ዘንድ ጥያቄን የሚያጭሩ ክፍተቶች የምንላቸውን እዚህ’ጋ መጠቋቆም ይኖርብናል። የመጀመሪያው አቤል ከስራ ሲወጣ በጐረምሶች ሲደበደብ ተመልክተናል። በቀጣይም አባቱ በጠሩት ግብዣ ላይ ስንመለከተው መደብደቡን እናያለን። ነገር ግን የለበሰው ልብስ የተለያየ ሆኖ ሳለ እንዴት ሶስና ሳታየው ቤት ገብቶ ልብስ ቀይሮ ወጣ? የሚለውን ጥያቄ ይፈጥራል።

 

በከተማ ውስጥ ያሉት መጠጥ ቤቶች ቁጥር ስፍር የሌላቸው ሆነው ሳለ ስለምን ሁሉም ገፀ-ባህሪያት ሳይቀጣጠሩ የሚገናኙበት አንድ ቡና ቤት ብቻ እንድንመለከት የተገደድነው? ይህ ክስተት በቂ ምላሽ ያልተሰጠው ምክንያት አልባ ትዕይንት ፈጥሯል ማለት ይቻላል።

 

በሌላ በኩል ጥያቄን ከሚያጭሩ ነገሮች መካከል የሐውልቱ ጉዳይ ነው። አቤል አቶ እንዳሻውን ወደ እናቱ የመቃብር ስፍራ ሲወስዳቸው ያየነው ሐውልት በጣም ያረጀ ነው። ከሞቱ ዓመት የሆናቸውና ከዚያ ቤተሰብ (ከሀብታም ቤተሰብ መሆኑን ለማመልከት ነው) የወጡት እናት ሐውልታቸው ምን ሊመስል እንደሚችል መገመት ቀላል ነው። ዳይሬክተሩ ተመሳሳይ እና ደረጃውን የጠበቀ የሌላ ሰው ሐውልት ማሳየት እየቻለ በገደምዳሜ ያረጀ ሀውልት ብቻ አሳይቶ ማለፉ ጥያቄን የሚያጭር ሆኗል።

 

“ፈልጌ አስፈልጌ” ፊልም አፈላልጐ የሚያሳየን እውነትና ውስብስብ ሴራ ልብን የሚያንጠለጥል ነው። የመወለድን ቋንቋ መሆን፤ የመካን ወላድነትን፤ የጽኑ ቤተሰባዊ ፍቅርን መሠረት በአንድ በኩል ያሳየናል። በሌላ በኩል ደግሞ የተንኮል ቋትን፣ ለይስሙላ የቆመ ጓደኝነትንና ብር አምላኪነትን በሚዛኑ አስቀምጦ ተመልካችን ለፍርድ ይጋብዛል።

 

በዚህ አጋጣሚ ከ20 ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ፊልም ስራ ውስጥ ያሳለፈው አቡ ቪዲዮ ፊልም ፕሮዳክሽን ወደሲኒማው መምጣቱ ይበል የሚያሰኝ ነው። ከዚያም በኋላ ገና ብዙ ስራዎችን የምንጠብቅበት ይሆናል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
15986 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 881 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us