ቴዲ አፍሮ - በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ፊት

Wednesday, 17 May 2017 12:12

 

ከአገራችን አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ መነጋገሪያ የሆነ አልበም ነው - በታዋቂውና የኮከብነትን ማዕረግ ከበርካታ የዓለም ሚዲያዎች ባገኘው አርቲስት ድምፃዊው ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) የተሰራው “ኢትዮጵያ” የተሰኘው አልበም። 600 ሺህ ኮፒ ተሰራጭቶ ወደመጠናቀቁ የቀረበው ይህ አነጋጋሪ አልበም ባልተጠበቀ መንገድ በዓለም የሙዚቃ ሽያጭ ሰንጠረዥም (Billboard World Albums) የወቅቱን ቁንጮነት አግኝቶ እንደነበር የሚታወስ ነው። በኢንተርኔት ሽያጩ ይህን የመሰለ አመርቂ ውጤት ያስገኘውና በአድናቂዎች ዘንድ መነቃቃትን የፈጠረው የቴዲ አፍሮ “ኢትዮጵያ” አልበም በይፋ ላልተገለፁ ግለሰቦች በአምስት ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር መሸጡን አርቲስቱ ለአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ጣቢያ ሲናገር ተሰምቷል።

 

የ“ኢትዮጵያ” አልበም መሰራጨትንና በአድማጩ ዘንድ ያገኘውን ተቀባይነትና የሽያጭ ሪከርድ ተከትሎ በርካታ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ቴዲ አፍሮን ለማነጋገር ደጅ ሲጠኑት ማየት የተለመደ ሆኗል። ቴዲን ለማነጋገር ቀዳሚ የሆነው አሶሼትድ ፕሬስ (AP) ሲሆን፤ ቀጥሎም ቪኦኤ (የአማርኛው ክፍል)፣ ቢቢሲ እና ሲሲ ቲቪ ተጠቃሾች ሲሆኑ፤ የእነዚህን ቃለ-መጠይቆች ግብዓት በማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተነባቢነት ያላቸው እንደ ዋሽንግተን ፖስት፣ ዘ ጋርዲያን እና ኒዮርክ ታይምስ፣ ሰፋፊ ዘገባዎችን ሰርተዋል። ከአገር ውስጥ ደግሞ ዘ ሪፖርተር፣ ፎርቹን፣ ዘ ጆርናል ጋዜጣ እና የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት (EBC) ናቸው። ከእነዚህ መካከል ኢቢሲ ባለፈው እሁድ በመዝናኛ ፕሮግራሙ እንደሚተላለፍ ሲጠበቅ የነበረውን የቴዲ አፍሮ ቃለ-መጠይቅ ሳያስተላልፈው በመቅረቱ በአብዛኛው ሰው ዘንድ ቅሬታን ፈጥሮ እንደነበር ከማኅበራዊ ድረ-ገጾች መታዘብ ይቻላል።

በዜማዎቹ እየተወደደ፣ በስራዎቹ እየተደመጠና አድናቆቱ በእጅጉ እየጨመረ የመጣው የ40 ዓመቱ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) በተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘንድ የነበረው ቆይታ እንዴት ነበር? የሚለውን በጥቂቱ እንዳስሳለን።

አርቲስት ቴዲ አፍሮ “ኢትዮጵያ” የተሰኘ አልበሙን ለህዝብ ካደረሰ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደቤቱ ጐራ ያለው የአሶሼትድ ፕሬስ ዘጋቢው ኤልያስ መሠረት ነበር። “አሶሼትድ ፕሬስ” ለአርቲስቱ በርካታ ጥያቄዎችን አንስቶለት ነበር። አልበሙን በተመለከተ ለተነሱለት ሀሳቦች ቴዲ አፍሮ ሲመልስ፤ “አርዕስቱ ‘ኢትዮጵያ’ እንደመሆኑ መጠን ዋናው ዓላማ ኢትዮጵያዊነትን ከአደጋ ማዳን ነው። ይህ አልበም በዚህ ዓይነት ሀሳብ ላይ እንዲያተኩር የፈለኩበት ምክንያት አንድነታችን አስፈላጊ ስለሆነ ነው። ብዙ ዓመት ተደክሞበታል። አሁን እንደሚታወቀው በሀሳብ ከመደራጀት ይልቅ በዘር መደራጀት ይታያል። ያ ደግሞ አዝማሚያው ወደ አደጋ ያመጣው ይመስላል። እናም ከምንም በላይ ኢትዮጵያዊነትን ማዳን ዓላማ አድርጐ የተሰራ ነው” ሲል ተናግሯል።

 

በአሶሼትድ ፕሬስ ዘገባ ላይ ተንተርሶ ሽፋን የሰጠው “ዋሽንግተን ፖስት” በበኩሉ፤ ኢትዮጵያዊው አንፀባራቂ ኮከብ አርቲስት ከሁለት ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ከ600 ሺህ ያላነሱ ኮፒዎችን መሸጡን በማስታወስ ይህንን ከፍታ በማግኘቱም በዓለም አቀፍ የአልበም ሰንጠረዥ ላይ በአንደኝነት መስፈሩን አትቷል።

 

ዘገባው አክሎም፤ ፖለቲካዊ ሀሳቦችን የተላበሱ ስራዎቹን በሬጌና በኢትዮጵያን ሶል ስልት ይዞ መቅረቡን ያስታውሳል። “ፖለቲካዊ ሀሳቦችን ማንሳት ሐጢያት አይደለም” ሲል ለአሶሼትድ ፕሬስ መናገሩን ያስታወሰው ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ፤ በቅርቡ ኢትዮጵያን የጐበኙትን የተባበሩት መንግስታት ሰብዓዊ መብት ኃላፊ ሪፖርት ተንተርሶ በሀገሪቱ ስላለው ሁኔታም በዘገባው አመላክቷል።

 

በ“ኢትዮጵያ” አልበም ውስጥ በበርካቶች ዘንድ ከአንድነት ያለፈ ወቅታዊ ፖለቲካ አንድምታ አላቸው በሚል ትንታኔ ከተሰጠባቸው ስራዎች መካከል የአልበሙ መጠሪያ የሆነው “ኢትዮጵያ”ን ጨምሮ አፄ ቴዎድሮስ፣ ሰምበሬ፣ ሆላን ይዞ፣ አናኛቱም፣ አደይ እና ናትባሮ ተጠቃሾች ናቸው።

በማኅበራዊ ድረ-ገጾች አርቲስቱን በሚመለከት ከሰፈሩ ሀሳቦች በመነሳት፣ “ቴዲ አፍሮ ይህን ያህል ተወዳጅ የሆነው ኮርካሪያችን ስለሆነ ነው” የሚሉ አልታጡም። አርቲስቱ በዘመናችን ከተከሰቱ የሙዚቃ ቀማሪዎች፣ የዜማ ደራሲዎች፣ የግጥምና ድምፅ ስራዎች ውስጥ በጉልህ የሚሰማ ስለመሆኑም በርካቶች ይመሰክራሉ። በተለይም በሬጌ ስልት የሚያቀነቅናቸው ስራዎቹን የተመለከቱ በርካታ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጭምር “የአፍሪካ ሬጌ ሙዚቃ ንጉስ” ሲሉት ተደምጠዋል።

 

በዓለም አቀፍ ደረጃ ስሙና ስራው የገነነው ቴዲ አፍሮ ባለፈው ሳምንት በቢልቦርድ ሰንጠረዥ አናት ላይ መቆናጠጡን የሚያስታውሰው የአሜሪካ ድምፅ የአማርኛው ክፍል በዩቲዩብ የጫነው ስራው ከ3 ሚሊዮን በላይ አድማጭ እንዳገኘ አስታውሶ፤ ከአርቲስቱ ጋር የግማሽ ሰዓት ቆይታ አድርጓል። እንደክስተት የተቆጠረው ይህ አርቲስት፣ “ይህ የትውልዱ ድምፅ ነው” ሲል ተሰምቷል። በአዲስ አልበም ውስጥ ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ማቀንቀኑን ተከትሎ ስለኢትዮጵያ የሚያስበውን ተጠይቆ ሲመልስ፣ “በጣም ትላልቅ አባቶች የነበሩን ተከታታይ ህዝቦች ነን እዚህ የደረሰ ነው። ብዙ የተለፋበት ሀገር ነው። ለብዙዎች ምሳሌ የሚሆን ነው። በነፃነት ድልም ይሁን፣ በዲፕሎማሲውም ዘርፍ፤ የመንግስታቱን ማኅበር እስከሚያስጨንቀው ድረስ የኛ አባቶች በጨዋነት የዘለቁ፣ የለፉ፣ በቅንነት አገራቸውን ያገለገሉ ሰዎች አንከባለው እዚህ ያደረሱት አገር ነው። ሲቀደምም ከዚያም በፊት እንደአጋጣሚ ሆኖ በተፈጠሩ አለመግባባቶች ያለው ብዥታ በእውነት የአገር ህልውና የራስ ህልውና ነው። አገራችን መዳን የምትችለው ኢትዮጵያን እንደቀደመው መንፈስ በአንድነት ሆነን በፍፁም ቅንነት ለመቀጠልና ለማስቀጠል በጋራ ስንጥር ነው። ምክንያቱም ይሄ ቢሆን ደስ ይለኛል የሚባል አይደለም። መሆን ያለበትና የህልውናችን መሠረት ነው” ሲል ተደምጧል።

 

በቀዳሚ አልበሙ “ግርማዊነትዎ” በሚል ለቀዳማዊ ኃ/ስላሴ የዘፈነው ቴዲ አፍሮ፤ በመቀጠል “ጥቁር ሰው” ባለው አልበሙ ውስጥ ስለምኒልክ ከፍ አድርጐ ተጫውቷል። አሁን ላይ ደግሞ አፄ ቴዎድሮስን ማንሳቱን ተከትሎ ለነገስታቱ የሰጠውን ትኩረት በተመለከተ ተጠይቆ በሰጠው መልስ፤ እንዲህ ብሏል።

 

“ነገስታት የህዝብ ምልክቶች ናቸው። በሁሉም ውስጥ የኛ መልክ አለ። ለአድዋ ድል ምኒልክን የሚያህል አስተዋይና ኃይልን አሰባስቦ ጠላትን ለመመከት የሚያስተባብር፤ ጣይቱን የመሰለ ብልህ ሴት ያስፈልጉ ነበር። ንብም እኮ ያለንግስት አልተፈጠረም። ስለዚህ እኛም ደግሞ ነገስታቶቻችን የሰሩትን ትልቅ ነገር ማየት ሳንችል [እነዚህ ሰዎች በጊዜያቸው ብዙ ደክመዋል] እንደ አፄ ቴዎድሮስ ደግሞ ከወገንም ከሩቅም፤ ከውጪም ከእርሱ ህልም ጋር የተግባባና የታረቀ ህዝብ አጥቶ ያለግዜው ተፈጥሮ ተሰቃይቶ የሞተ ሰውዬ ነው። ይህ ሃቅ ሊጮህለት ይገባል። አላማውና ህልሙ ደግሞ እስካሁን ድረስ እኛ ተመልሰን እዛው ዘመነ መሳፍንት አይነት ዘመናዊ ነገር ውስጥ ያለን ነው የሚመስለው። በዚህ ጊዜ ደግሞ በትክክል የሚያስፈልገው የሱ ህልም ነው። ሊጋባብን ይገባል። አሁን አንቺ የምትኖሪው “ዮናይትድ ስቴት ኦፍ አሜሪካ ነው” ሰዎች ተባብረው ያገዘፉት ሃገር ነው። ለሌላው ከሩቅ ለማመጣም የሚተርፍ ትልቅ በረከት የፈጠሩበት ጥበበኞች ናቸው። እኛ ደግሞ በአንድ ወቅት አይደለም ኢትዮጵያን አልፈን አፍሪካን ያነቃቃን፤ በአንድነት አፍሪካነትን ለመመስረት የሞከርን ባለህልመኞች ነበርን። አሁን ግን አገር ማከል ደግሞ አቃተን። ይሄ ደግሞ ተንደባሎ እዚህ የደረሰ ነገር ረቂቅ ነው። ሄዶ ውጤት ላይ ብቻ መነጋገር አንዳንዴ ለውጤቱ መሰረት በጋራ ጉዟችን ውስጥ የነበሩ ሁኔታዎች የተፈጠሩ ናቸው። መጀመሪያ ችግሩን ፊት ለፊት ማየት ያስፈልጋል። ከምንም በላይ ታላላቆቻችን ተግባብተው ለኛ ለታናናሾቻቸው መንገድ አሳይተው ነው፤ በኖሩበት አገር አርጅተው፤ ተከብረው ነው መሄድ ያለባቸው። እኛ ጋር መተላለፍ የለበትም ያ ጉዞ። ለዚህ ደግሞ እኛ ምልክት ስናጣ እኮ ነው ተመልሰን ወደነዚያ የምንሄደው ምልክት የሌለው ህዝብ ይጠፋል። ራዕይ የሌለውም ህዝብ ይጠፋል። ለዚህ ነው እዚህ ጫፍ የደረሰ ነው። ስለዚህ እንደዚህ የጐሉ መልክቶቻችንን ከነተግባራቸው ለወደሱና ሊጋቡብን ይገባል።” ሲል በአፅንኦት ተናግሯል።

 

ቴዲ አፍሮ በውዝግብ ከተሞላውና ብዙም ከማይታወቅለት የመጀመሪያ አልበሙ በኋላ በህዝብ ዘንድ በአያሌው የታወቀበትን “አቦጊዳ” (1993) ከናሆም ሪከርድስ ጋር ይዞ መጥቷል። በመቀጠልም በበርካቶች ልብ ውስጥ የተሰነቀረበትንና የ1997ቱን ፖለቲካዊ ግለት ተከትሎ የሚታወስለትን “ጃ ያስተሰርያል” የተሰኘ ምርጥ አልበሙን ለአድማጩ አድርሷል። ከዓመታት በኋላም የምኒልክን ጀግንነትና የኢትዮጵያዊንን ኅብረት ያሳየበትን “ጥቁር ሰው” የተሰኘ አልበም በ2004 ዓ.ም ከአዲካ ሪከርድስ ጋር አቅርቧል። እነሆ ከአምስት ዓመታት በኋላ ደግሞ “ኢትዮጵያ” የተሰኘ ጥልቅና ሰፊ ትንታኔ የሚሻ ስራውን ይዞ መጥቷል። በበርካቶች ዘንድም ተወዶና ተመርጦ እየተደመጠ ይገኛል። እዚህ’ጋ በበርካቶች ዘንድ ተወዳጅነት ያላቸውን እንደ ታሪክ ተሰራ፣ ወገኔ፣ ሰባ ደረጃና የመሳሰሉትን ነጠላ ዜማዎች ለአድናቂዎቹ ማድረሱን ማስታወስ ያስፈልጋል።  

 

አርቲስቱን እንዲህ ተወዳጅ ያደረገው ስራዎቹ ብቻ አለመሆናቸውን የሚናገሩ ሰዎች አሉ። በበጐ ምግባር ስራው ልታይ-ልታይ አለማለቱ። በንግግር ብስለቱና በስብዕናው ጭምር እርሱንና የእርሱን የሆነ ነገር ማየትና መስማት የሚፈልጉ አድናቂዎቹ ስፍር ቁጥር እንደሌላቸው ከሰሞኑ። ከዚህም ባሻገር ወቅትን ተከትሎ ታሪክን አስታኮና ወቅታዊነትን ተላብሶ የሚሰራቸው ስራዎቹ በህዝብ ልብ ውስጥ ተደላድሎ ይቀመጥ ዘንድ ስፍራ አሰጥተውታል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
15999 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 977 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us