የግርማ ረጅሙ ጉዞ፤ ከክራር እስከ ፒያኖ

Wednesday, 07 June 2017 14:01

በልጅነቱ በኢትዮጵያ የባህል ሙዚቃ መሳሪያ በሆነው “ክራር” እጆቹን ማፍታታት እንደጀመረ ይናገራል። አሁን ላይ ከሀገሩ ይልቅ በዓለም አቀፍ የሙዚቃ አፍቃሪያን ዘንድ በእጅጉ ይታወቃል። የዛሬው እንግዳችን ሙዚቃን በእውቀት ያጎለበተ “ፒያኒስት” ነው። በ16 ዓመቱ አዲስ አበባ በሚገኘው ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ፒያኖ መማር የጀመረው ፒያኒስት ግርማ ይፍራሸዋ፤ በ1989 (እ.ኤ.አ.) ከሶስት ዓመታት የቡልጋሪያ ቆይቶ በኋላ ወደ ኢጣሊያ ስለመሰደዱ የቀደመ ታሪኩ ያስረዳል። በዚያም ካሪታስ በተሰኘው የበጎ አድራጎት ድርጅት ውስጥ በስደተኝነት እያለ የክርስትያን ወንድማማቾች ድርጅትን ተዋወቀ። የሙዚቃ ክህሎቱንና ችሎታውን የተመለከቱት የድርጅቱ አባላት ወደቡልጋሪያ፤ ሶፊያ በ1991 (እ.ኤ.አ) እንዲመለስና እንዲማር በማድረግ ለአራት ተከታታይ ዓመታት በፕሮፌሰር ኩርቴቭ ስር በፒያኖ ዘርፍ በማስትሬት ዲግሪ መመረቅ ችሏል።

የኢትዮጵያን ሙዚቃ በክላሲካል መልክ በአገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ አድናቆትን ያተረፈው ግርማ፤ እንደነቤትሆቨን፣ ሞዛርት፣ ቸቺን፣ ደቡሲ፣ ሃይደን እና ባህ የመሳሰሉ ታዋቂ የሙዚቃ አቀናባሪዎችን ስራ ከመጫወት ባለፈ የእነሱን ስራዎች በመመርኮዝ የኢትዮጵያን ረቂቅ (ክላሲካል) የሙዚቃ ስራዎች በመቀመር ይታወቃል። በአሁኑ ሰዓት ፒያኒስት ግርማ ይፍራሸዋ፤ የረቂቅ ሙዚቃን ባህልና የኢትዮያን ሙዚቃ በረቂቅ የሙዚቃ ዘይቤ ውስጥ በማካተት በሀገሩና በዓለም አቀፍ ደረጃ እራሱን በማስተዋወቅ ላይ የሚገኝ አንጋፋ አቀናባሪ ጭምር ሆኗል።

ፒያኒስትና የሙዚቃ አቀናባሪው ግርማ ይፍራሸዋ የሙዚቃ ስልቱን ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ሊረዱት በሚችሉበት መንገድ በፅሑፍ በመቅረፅ ማስተማሪያ ይሆን ዘንድም ለያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ስለመስጠቱ ይናገራል። “የሙዚቃ ስኮሩን በመፅሐፍ አዘጋጅቼ ለትውልድ እንዲተላለፍ ሰጥቻለሁ። አሁን ላይ የሚሞክሩና ጥረት የሚያሳዩ ወጣቶች እየመጡ ስለሆነ ጥሩ መነሻ ይሆናቸዋል” ይላል።

ፒያኒስት ግርማ ይፍራሸዋ በሶስት ሲዲዎች ስራዎቹን ለአድማጮች አድርሷል። ከስራዎቹ መካከልም በ2014 (እ.ኤ.አ) ከአንሲን ወርልድ ሪከርድስ ሌብል ጋር በመሆን “ፍቅር እና ሰላም”  (Love and peace) በሚል መጠሪያ አቀረበ። ይህ የሙዚቃ አልበሙ በዚያው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ በዓለም አቀፍ የክላሲካል (ረቂቅ ሙዚቃ) ሰንጠረዥ ዘርፍ የ23ኛ ደረጃን ይዞ እንደነበር ይታወሳል። እስካሁንም እረኛው ባለዋሽንት (2001 እ.ኤ.አ)፣ መለያ ቀለሜ (2003 እ.ኤ.አ)፣ እልልታ (2005 እ.ኤ.አ)፣ ጠንካራው መንፈሴ (2015 እ.ኤ.አ) የተሰኙ አልበሞቹን ለረቂቅ ሙዚቃ አፍቃሪያን እነሆ በረከት ያላቸው ድንቅ ስራዎቹ እንደሆኑ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችና የሙዚቃ ጠበብት ይመሰክራሉ።

ከዚህ ቀደም በበርካታ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ስራዎቹን በማቅረብ የሚታወቀው ፒያኒስትና የሙዚቃ አቀናባሪው ግርማ ይፍራሸዋ በቅርቡ ደግሞ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ኢትዮጵያዊ የሙዚቃ ስልቶቹ ባቲ፣ ትዝታ፣ አምባሰል እና አንቺሆዬ የተቀመሩባቸውን ስራዎቹን ይዞ እንደሚመጣ ሰምተናል። ከዚህ ቀደም በሀገር ውስጥ በጣሊያን ባህል ማዕከል እና በሸራተን አዲስ ስራዎቹን ያቀረበ ሲሆን፤በ ዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች፤ በጀርመን፤ በእንግሊዝ፣ በፈረንሳይ፣ በፖላንድ፣ እና በአየርላንድ የረቂቅ ሙዚቃ ኮንሰርቱን አቅርቦ አድናቆት ተችሮታል።

እሁድ ሰኔ 11 ቀን 2009 ዓ.ም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የተደገሰው “ባህሎችን ማገናኘት” (Bridging Cultures) የተሰኘው የሙዚቃ ድግስ ላይ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ታዳሚያን ይስተናገዳሉ ተብሎ ይጠበቃል። ፒያኒስት ግርማ ረቂቅ (ክላሲካል) የሙዚቃ ስራዎቹን በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ስለምን አላቀረበም? በሚል ጥያቄ ሲነሳ መልሱ ብዙ ነው። የመጀመሪያው በአገራችን ለረቂቅ ሙዚቃ (ክላሲካል ሙዚቃ) ማቅረቢያነት ምቹ የሆኑ ስፍራዎች በብዛት አለመኖር ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ የረቂቅ ሙዚቃ አድማጮች ወይም አድናቂዎች እምብዛም መሆናቸው ይመስላል። ከዚህም ባለፈ የባሙያዎች አለመኖር እንደሚጠቀስ ሰምተናል። ይህም ባሳለፍነው ሐሙስ ግንቦ 23 ቀን 2009 ዓ.ም በማሪዮት ሆቴል በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ተጠቁሟል። “የክላሲካል ሙዚቃ አፍቃሪያንን ለማበራከት መሰል የሙዚቃ ድግሶች ተደጋግመው መቅረብ ይኖርባቸዋል። ከዚህም ባለፈ በትምህርት የሚደገፍ መሆን አለበት” የሚል አስተያየትም በመግለጫው ወቅት ከመድረኩ ተሰንዝሯል። አክሎም ከማሳያ ቦታዎች እጥረት ባለፈ የመሳሪያዎቹ አቅርቦትና የሙያተኛ ችግር መኖራቸው እንደችግር ሲጠቀሱ ሰምተናል። ይህንን ችግር ለማለፍም በተለይ የውጪ ኢምባሲዎች የጀርመን፣ የቡልጋሪያ፣ ቼክና ሆላንድ ኤምባሲዎች) ትልቅ ድጋፍ እንዳደረጉለት ፒያኒስቱ ተናግሯል።

ስለሙዚቃ ኮንሰርቱ አስፈላጊነት ፒያኒስት ግርማ ይፍራሸዋ ሲናገርም፣ “ይህን የሙዚቃ ስልት ይዤ አገሬን ለማስተዋወቅ ረጅም ጉዞ ተጉዣለሁ። ጥበበኛ ሁልጊዜ አድናቂ ብቻ ሳይሆን ደጋፊም ይፈልጋል። (የተለያዩ ኮንሰርቶችን ) ስሰራ ብዙ ሰዎች ከሀገርም ውስጥ ሆነ ከውጪ ደግፈው እዚህ አድርሰውኛል። አሁን ደግሞ ይህን ከ30 ዓመታት በላይ የደከምኩበትን ስራ በኮንሰርት ደረጃ በማቅረብ ከህዝብ ጋር የማክበር ትልቅ ፍላጎት ነበረኝ። ለኔ ይሄ ዝግጅት እንደልደት ቀኔ ወይም እንደሰርግ ቀኔ ነው የማየው። ስራዎቼን ለሀገሬ ሰዎች ከማቅረብ ባለፈ ለውጪ ሰዎችም ቢሆን የኢትዮጵያን የክላሲካል ሙዚቃ ደረጃ ለማስተዋወቅ የደከምኩበት ነው” ሲል የኮንሰርቱን አስፈላጊነትና ጠቀሜታ አስረድቷል። በዚህም ወቅት ለዝግጅቱ መሳካት ድጋፍ ያደረገለትን የኢትዮጵያ አየር መንገድና “ብሉ” ሚዲያዎችን ጨምሮ ሌሎች ተባባሪዎቹን በእጅጉ አመስግኗል። ይህ ዝግጅት ከኢትዮጵያ ባለፈ በአፍሪካ ደረጃ ሊጠቀስ የሚችል የረቂቅ ሙዚቃ (ክላሲካል) ኮንሰርት እንደሆነም ፒያኒስትና የሙዚቃ አቀናባሪው ግርማ ይፍራሸዋ ያስረዳል።

የሙዚቃ ድግሱ ከፒያኒስት ግርማ ይፍራሸዋ የተወጣጡና በእርሱ የተቀነባበሩ ስራዎች የሚቀርቡበት ሲሆን፤ በመድረኩም ላይ ከቡልጋሪያ፣ ከጀርመን፣ ከፈረንሳይ እና ከቼክ ሪፐብሊክ የተወጣጡ ሙዚቀኞች በዋነኛነት በግርማ የተቀነባበሩ ስራዎችን ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል። በዕለቱ የኮንሰርቱ ቆይታ የአንድ ሰዓት ተኩል እንደሚሆን የተገለፀ ሲሆን፤ በሶስት ምዕራፎች ተከፋፍሎ ይቀርባል ሲባልም ሰምተናል። የመጀመሪያው ምዕራፍ ፒያኒስት ግርማ ይፍራሸዋ ከውጪ ከመጡት የሙዚቃ ባለሙያዎች ጋር በጥምረት የሚያቀርበው ሙዚቃ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ለብቻው የሙዚቃ ቅንብሮቹን የሚያቀርብበት ሲሆን፤ ሶስተኛውና የመጨረሻው የሚሆነው ደግሞ ከጀርመን ሀገር ከምትመጣ የኦፔራ ድምፃዊት ጋር በጋራ የሚያቀርቡት ዝግጅት እንደሚኖር ተነስቷል።

በረቂቅ ሙዚቃ ኮንሰርቱ ላይ ከሶስቱ አልበሞቹ የተውጣጡ ነፀብራቅ ስራዎች እንደሚቀርቡ የተናገረው ፒያኒስት ግርማ፤ በተለይ ግን “ጠንካራው መንፈሴ” (My strong will) የተሰኘው አልበሙ ውስጥ የተካተቱን የኦርኬስትራና የኢትዮጵያዊነት የሚታይባቸው ስራዎቹ እንደሚተኮርባቸውም ከወዲሁ ጠቁሟል። ከዚህም በተጨማሪ ሙዚቃዊ ድራማ ይታይበታል ተብሎ የሚጠበቀውና ከጀርመናዊቷ የኦፔራ ድምፃዊት ጋር የሚጣመርበትንና ራሱ ፅፎ ያዘጋጀውን ስራ እንደሚጫወቱ በማስታወስ “ምናልባትም የኮንሰርቱ ሃይ -ላይት እርሱ ሳይሆን አይቀርም ብዬ እጠረጥራለሁ” ብሏል። ለዚሁም የኦፔራ ዝግጅቱ ላይ አርቲስቷ በአማርኛ መዝፈኗ እና አቀራረቧ ደግሞ አውሮፓዊ መሆኑ ከወዲሁ ጉጉት እንደፈጠረበት ይጠቅሳል።

“ሙዚቃ የቃል ትምህርት መሆን የለበትም” የሚለው ፒያኒስት ግርማ፤ በሌላው ዓለም ትውልዱ ሙዚቃን በተግባር እንዲማር መደረጉና በጽሁፍም ተዘጋጅቶ ለትውልድ እንዲተላለፍ መሆኑ ሙዚቃ (በተለይም ረቂቅ ሙዚቃ) ከፍ ያለ ደረጃ ሊደርስ ችሏል ባይ ነው። ለዚህም እንደአብይ ምሳሌ የሚጠቅሰው የነሾፓን እና የእነቤትሆቨን ሙዚቃዎች በዓለም የተዳረሱት ተጽፈው በመተላለፋቸው ነው ሲል ያስረዳል።

በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ያለፈው ፒያኒስት ግርማ፤ በተለይም ከሚጫወትበት የሙዚቃ መሳሪያ (ፒያኖ)ውድነትና ትልቅነት አንፃር በቀላሉ የሚገኝ አለመሆኑን ይናገራል። በትምህርት በቆየባቸውም ጊዜያት የፒያኖ ጨዋታ የሀብታሞች ብቻ ተደርጎ በመታሰቡ ትምህርቱን ፍለጋ እስከመሰደድ መደረሱን ያስታውሳል። በተለይም ልጅነቱን ከክራር ጋር አሳልፎ ድንገት ወደ ፒያኖ ስልጠና መሄዱን በበርካታ ወዳጆቹ (በተለይም በፈረንጆቹ) ዘንድ መገረምን የፈጠረ እንደነበረም ያስታውሳል። ፒያኒስቱ ውድ የሆነውን የሙዚቃ መሳሪያ ለመግዛት ከገጠመው ችግር የተነሳ “ኮንትሮባንድ” እስከመስራት የደረሰ ሲሆን፤ አሁን ላይ የደረሰበት ደረጃ በብዙ ፈተናዎችና ችግሮች ውስጥ የተለፋበት እንደሆነም ይናገራል።

ከዋነኛውና “ባህሎችን ማገናኘት” (Bridging Cultures) ከተሰኘው ኮንሰርት ባሻገር ማክሰኞ ሰኔ 13 ቀን 2009 ዓ.ም በዚያው በብሔራዊ ቴአትር ለታዳጊ የሙዚቃ አፍቃሪያንና ለተማሪዎች በሚል የተዘጋጀ ፕሮግራም እንዳለ ተሰምቷል። ከተለያዩ የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ተማሪዎች የሚታደሙበት ይህ ኮንሰርት ትኩረቱን ለታዳጊዎቹ እድል በመስጠት ላይ እንደሚያደርግም አዘጋጆቹ ተናግረዋል።

እሁድ ሰኔ 11 ቀን 2009 ዓ.ም የሚካሄደው የረቂቅ ሙዚቃ ኮንሰርት የኢትዮጵያን ሙዚቃ በከፍተኛ ደረጃ የሚያስተዋውቅ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ ነው። የመግቢያ ዋጋውን በሚመለከት 1000 ብር ሲሆን፤ ለልዩ መስተንግዶ (VIP) ደግሞ 1300 ብር መሆኑ ተገልጿል። በኮንሰርቱ ላይ 1200 ሰዎች ይታደማሉ ተብለው የሚጠበቅ ሲሆን፤ የሚቀርቡት የረቂቅ ሙዚቃዎች “ስኮር” በፅሁፍ ተዘጋጅቶ የሚሰጣቸው ከመሆኑም ባሻገር የፒያኒስት ግርማ ይፍራሸዋ ሶስት አልበሞችን በነፃ የማግኘት ዕድል እንዳለም አዘጋጆቹ በመግለጫው ወቅት ተናግረዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
15918 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1068 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us