“ህብረ-ትርዒት” ወርሃዊው የኪነ-ጥበባት ድግስ

Wednesday, 14 June 2017 12:46

ወር በገባ የመጀመሪያውን አርብ ለኪነ-ጥበብ በሰዋው ድግስ ላይ ታድመናል። በማይና ፕሮሞሽን እና ኢንተርቴመንት አሰናጅነትና በኢትዮጵያ ሆቴል ትብብር የሚቀርበው ይህ የኪነ-ጥበባት ድግስ “ህብረ-ትርዒት” ይሰኛል። ባሳለፍነው አርብ ግንቦት 2 ቀን 2009 ዓ.ም ለሰባተኛ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎች እየታዩበት እንደመጣም የዝግጅቱ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ዘካሪያስ ብርሃኑ አስታውቋል። በወርሃዊው “ህብረ-ትርዒት” የኪነ-ጥበባት ድግስ ላይ ከግጥም በጃዝ በተጨማሪ አጫጭር ድራማዎች፣ ወጎችና የሙዚቃ ስራዎችም በጥምረት እንደሚቀርቡበት ታይቷል። “ፕሮግራማችን ከዚህ ቀደም ይቀርቡ ከነበሩት የ‘ግጥምን በጃዝ’ አይነት መድረኮች በአይነቱ ለየት ያለ እንዲሆን ሰርተናል። ከዚህም ውስጥ በዋነኛነት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ ከ20 እስከ 30 ደቂቃ የሚወስዱ አጫጭር ድራማዎችን በየወሩ መስራት መቻላችን አንዱ ማሳያ ነው” ይላል ጋዜጠኛ ዘካሪያስ።

 

በምሽቱ የሚቀርቡ ስራዎች የሚመረጡበት መስፈርት ታዋቂ በመሆን ሳይሆን ታዋቂ የሚያደርጉ ስራዎችን በማቅረብ ላይ ያተኮረ ነበር የሚሉት አዘጋጆቹ፤ ወጣት የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ስራዎቻቸውን ይዘው የሚቀርቡበትን መንገድ ማመቻቸት የመድረኩ ዓላማ ነው ብለዋል። በዋናነት የስነ-ጽሁፍ ስራዎቹ ላይ ትኩረት በማድረግ መረጣው ይካሄዳል ሲሉም ይገልፃሉ። በየወሩ ለሚሰናዳው “ህብረ-ትርዒት” ዝግጅቱ የሚደረገው ወሩን ሙሉ እንደሆነም አስተባባሪዎቹ ይናገራሉ። “ሰውዬው ምንም ይሁን፤ ማንም የእኛ ትኩረት ኪነ-ጥበባዊ ለዛ ያላቸው ስራዎቹ ላይ ነው” የሚለው ዘካሪያስ፤ በምንም አይነት መልኩ የሀሳብ ገደብ አናደርግም ሲልም ያረጋግጣል። ከዚህ ባለፈ አንድ አንጋፋ አርቲስት የታዋቂ ገጣሚያንን ስራ እንዲያቀርብ መድረኩን እናመቻቻለን ይላሉ። ለምሳሌ በዚህ ወር “የቴዎድሮስ ራዕይ” ከተሰኘው የጌትነት እንየው ቴአትር ላይ የቴዎድሮስ ስንብት ከመቅደላን የሚያስታውስ ግጥማዊ መነባንብ በተዋናይ ሱራፌል ተካ ቀርቧል።

 

የህብረ-ትርዒት ወርሃዊ የኪነ-ጥበብ ድግስ ዋና ዓላማው አማራጭ የመዝናኛ መድረክ መፍጠር እንደሆነ የሚገልፀው ዘካሪያስ፤ ወር በገባ በመጀመሪያው አርብ ላይ በሚኖረው የኢትዮጵያ ሆቴል መድረክ ላይ በሁለት ምዕራፍ የተከፈሉ አስር ግጥሞችን ከአምስት ገጣሚያን ጋር ያቀርባል። የሙዚቃ፣ የአጭር ድራማና የወግ መሰናዶም መኖሩን ተመልክተናል። እንደአዘጋጆቹ ገለፃ ከሆነ በመድረኩ በሚቀርቡት ኪነ-ጥበባዊ ስራዎች ሁሉ የተሻለ ደረጃና ከፍታን ለመፍጠር እየሰሩ መሆኑንም ያስረዳሉ።

 

“ተመልካቹ ምርጥ የሚባል የኪነ-ጥበብ ፕሮግራሞችን ብናዘጋጅለት ማጣጣም ይችላል” በሚል መንፈስ የተነሱት “የህብረ-ትርዒት” አዘጋጆች፤ ይህንንም ከተመልካቹ ባገኙት ምላሽ ማረጋገጣቸውን ይናገራሉ። በርግጥ መሰል መድረኮችን አዘጋጅቶ ቀጣይነት ባለው መልኩ ማቅረብ እና የተመልካቹንም ትኩረት በአንድ ጊዜ ማግኘት ቀላል አለመሆኑን የሚናገረው ዘካሪያስ፤ እስካሁንም ሰውን የማስለመድ ስራ እየሰራን ነው ይላል። ለዚህም እንደማስረጃ አንዴ የመጣ ሰው በቀጣይም ሲደግም ይታያል፤ ይህም የዝግጅቱን ጣዕም የሚያሳይ ምልክት እንደሆነ አዘጋጆቹ እምነት ጥለዋል። በተለይም ከሌላ መደበኛ የቴአትር አዳራሽ በተለየ መልኩ ታዳሚው እየበላና እየጠጣ ዘና ብሎ የሚታደምበት መሆኑ ተመራጭም አማራጭም መሆን እንዳስቻለው የአዘጋጆቹ እምነት ነው።

 

የተለያዩ የኪነ-ጥበብ ዝግጅቶች ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ይታመናል። የፈጠራ ባለሙያዎቹ የተሻለና አስተሳሰብ ላይ ለውጥን ሊያመጣ የሚችል ስራ ይዘው ይቀርቡ ዘንድ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። ለመሆኑ ከኢትዮጵያ ሆቴል ጋር በመተባበር ዘወትር በወሩ የመጀመሪያ አርብ ላይ የሚሰናዳውን “ህብረ-ትርዒት” የተሰኘ የኪነ-ጥበባት ድግስ ማን እየደገፈው ነው ስንል ላነሳነው ጥያቄ ዘካሪያስ ይመልሳል።

 

“የመጀመሪያው ነገር ከእኛ የሚጠበቀውን ነገር መስራታችን ነው። እኛ ደግሞ የምንችለውን ሁሉ ሰርተናል። ለምሳሌ በወር አንዴ ለሚቀርበው ተውኔት፣ ሙዚቃ፣ ግጥምና ወግ ኃላፊነት ወስዶ በጥልቀት በማየት መርጦ የሚያዘጋጅ አካል አለን። ይህ በባለሙያዎች የተዋቀረ ነው” ሲል ማይና ፕሮሞሽን እና ኢንተርቴንመንት ስራዎቹን መርጦ በማቅረብ ሂደት የተቻለውን እየሰራ እንደሚገኝ ይገልፃል። ድጋፍ ከሚያደርጉ አባላት አንፃር ደግሞ በዋናነት መገናኛ ብዙሃን ዝግጅቱን ከማስተዋወቅ አንፃር እየሰሩት ያለው ስራ የሚያስመሰግን እንደሆነ በቅድሚያ ያነሳው ዘካሪያስ፤ ከዚህ በዘለለ ግን የተለየ ድጋፍ እንደሌላቸውና ወርሃዊው የ“ህብረ-ትርዒት” ፕሮግራም ፍላጐቱና ፍቅሩ ባላቸው አካላት ወር ሙሉ ተለፍቶበት የሚቀርብ መሆኑን አስረድቷል።

 

በሥነ-ግጥም፣ በሙዚቃ፣ በቴአትርና በወግ ስራዎች ዙሪያ መስራት የሚፈልጉ ፀሐፍት በሙሉ ወደማይና ፕሮሞሽን እና ኢንተርቴንመንት ስራዎቻቸውን “በኢ-ሜይል” መላክ እንደሚችሉ የተገለፀ ሲሆን፤ ይህም ወጣት ፀሐፍትን ለማነቃቃት እንደሚያግዝ አስተባባሪዎቹ ይናገራሉ። ፀሐፍቱ ስነ-ጽሁፋዊ ለዛቸውን የጠበቁ ስራዎች ያቅርቡ እንጂ በፅሁፎቻቸው ላይ ምንም አይነት የሀሳብ “ማዕቀብ” እንደሌለ የሚናገሩት አዘጋጆቹ፤ “ስነ-ጽሁፋዊ ብስለቱ ግን የማንደራደርበት ሚዛናችን ነው” ይላሉ።

 

ለሰባተኛ ጊዜ ባሳለፍነው አርብ ግንቦት 2 ቀን 2009 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሆቴል በቀረበው “የህብረ-ትርዒት” መሰናዶ ላይ አምስት ወጣት ገጣሚያን ስራዎቻቸውን በሁለት ምዕራፍ ከፍለው አቅርበዋል። በስራዎቹ ውስጥ ፍቅር፣ ቁጭት፣ ፀፀትና ሽሙጥ መሳጭ በሆነ አቀራረብ ለታዳሚው ደርሰዋል ማለት ይቻላል።

 

እስቲ በምሽቱ ካቀረቡት የግጥም ስራዎች መካከል ስንኞችን እንቁጠር፤

 

ሄዳለው ከጎኑ ወገቤን ታቅፌ

ከሌላዋ ምስኪን

የሰረቅኩትን ባል ከጎኔ አንከርፍፌ

እኔ የረገጥኩት የራሴ ‘ግር ዱካ

አንዴ ይሰፋኛል፤

አንዴ ይጠበኛል፣

በእሷ እየተለካ።

 

 

ገጣሚዋ በአብሮነት ውስጥ ያለውን ብቸኝነት በቁጭትና በፀፀት ተሞልታ ትወርደዋለች። ይቀጥላል ደግሞ ሌላው፤ የህይወት ድግግሞሽና አሰልቺነትን ለማሳየት እንዲህ ይላል።

 

እልፍ እግር አቁሞ

ህይወት መተረቻ፣

ህይወት መዘበቻ፣

በየመንገዱ ላይ ጫማ ሰፊ ብቻ፣

ልብስ ሰፊ ብቻ

***    ***    ***

ምን ያለ ህይወት ነው እንዴት ያለ መኖር

ለማይበሉት ነገር እህል ይዞ መዞር።

 

እያለ ይቀኛል። በልዩነቶችና ባለመግባባቶች መካከል የተዘረጉ የግጥም መሰላሎችና ድልድዮች በወጣትነት መንፈስ ሲገነባ ይሰማል። ተማፅኖና ምህረት፤ ይቅርታና ጥፋት፣ ፍቅር እና ጥላቻ፣ ይሁንታና ዛቻ የገጣሚያኑ ምሰሶዎች ይመስላሉ።

 

ይቀጥላል ሌላው ገጣሚ፤ በመምህርነት የንግስና መንበር ላይ በፍቅር የተቀመጠችውን ሴት የወደደው ተማሪ እንደሚከተለው ግጥም ይመትራል፡-

 

“እንደምን አደራችሁ ተማሪዎች” ካልሻቸው መካከል

“እግዚአብሔር ይመስገን” ብዬ የማልለው

“ውሸትን መናገር ሃጢያት ነው” ስላልሺኝ እኮ ነው።

***    ***    ***

በእንደኔ አይነቱ የመሀይም ህይወት ታዛ ሲጠለሉ

ንጉስን ማፍቀር ነው የባሪያ በደሉ።

***    ***    ***

በመሀይም ህይወት ያልገባኝን ስሌት አካፋይ ደማሪ

የምቀምሰው ያጣሁ ቆሎ የቸገረኝ የቆሎ ተማሪ

***    ***    ***

በመሀይም ህይወት ለዕውቀት፣

የሚሆን ልብን እንደማጣት፣

አዎ አውቃለሁኝ መምህርን ማፍቀር ነው የተማሪ ሃጢያት።

 

ይህ አፍቃሪ ደህና በመምህሩ ፍቅር ሲብሰለሰል በደህናው አለማደሩን፣ ሰላም ማጣቱን፤ መናገርም አለመቻሉን ያስረዳበት መንገድ በታዳሚው ዘንድ የመዝናናት መንፈስን የፈጠረ ነበር።

 

በምሽቱ ቀርበው ወንበር ከነቀነቁ ግጥሞች መካከል ለመሰነባበቻ የሚሆን ስንኝ እንመዛለን።

 

በዚህች ምስኪን ሀገር

ጐጆ ሲያበቃ ነው የሚሰራው ማገር።

የወሩ ሰው ይበለን፤ መልካም የመዝናኛ ሳምንት!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
15844 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 879 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us