ተመስጦና መደመም የነገሰበት የረቂቅ ሙዚቃ ኮንሰርት

Wednesday, 21 June 2017 13:46

 

ከወትሮው በተለየ መልኩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ በውጪ ሀገር ዜጎች፣ ዲፕሎማቶች እና አምባሳደሮች እንዲሁም በጥቂት በማይባሉ ኢትዮጵያውያን ታዳሚዎች ተሞልቷል። በርካቶች ድንገት ያለቀጠሮ የተገናኙ ይመስላል። ሰላምታ መተቃቀፍና ጨዋታው ወደአዳራሹ መግቢያ ይጀምራል። እንግዶች ወደውስጥ ሲዘልቁ ከበሩ ላይ በባህላዊ አልባሳት የደመቁ ቆነጃጂት በፒያኒስትና የሙዚቃ አቀናባሪው ግርማ ይፍራሸዋ የተሰሩትን “Love & peace (ፍቅርና ሰላም)፣ “My strong will” (ጠንካራው መንፈሴ) እና “F. chopin” (የቾፒን) ስራዎቹን በጥምረት የያዘ “ባህሎችን ማገናኘት” (Bridging cultures) የተሰኘ የረቂቅ ሙዚቃዎችን የያዘ እሽግ በስጦታ መልክ ያበረክታሉ።

ይህ የሆነው ባሳለፍነው እሁድ ሰኔ 11 ቀን 2009 ዓ.ም በብሉ ሚዲያ (Blue Media) አስተባባሪነትና በኢትዮጵያ አየር መንገድ ቀዳሚ “ስፐንሰርነት” በተዘጋጀው የረቂቅ ሙዚቃ ኮንሰርት ዝግጅት ላይ ነው። አብዛኞቹ ታዳሚያን የውጪ ዜጎች የመሆናቸውን ያህል በጊዜው ያልጀመረው ይህ ዝግጅት በይቅርታ መሟሸት የጀመረው 10፡40 ደቂቃ ሲል ነበር። በሶስት ምዕራፎች ተዘጋጅቶ የቀረበው ይህ የረቂቅ ሙዚቃ ድግስ በእጅጉ ተመስጦና መደመም የነገሰበት እንደነበር በቦታው ተገኝተን ታዝበናል። በአንጋፋው ፒያኒስትና የሙዚቃ አቀናባሪ ግርማ ይፍራሸዋ የሚመራው ይህ የሙዚቃ ድግስ ከጀርመን፣ ከፈረንሳይ፣ ከአሜሪካ፣ ከቼክ ሪፐብሊክና ከቡልጋሪያ የተውጣጡ ስምንት የሙዚቃ ባለሙያዎችን ያካተተ ነበር።

አስቀድሞ ስለዝግጅቱ ብዙ የተባለለት ይህ የሙዚቃ ኮንሰርት እንዴት እንደነበር የፕሮግራሙን አስተባባሪዎች እና አርቲስቱን ጠይቀናቸዋል። በቅድሚያ የብሉ ሚዲያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር መስራችና ስራ አስኪያጅ የሆነው ወጣት እስክንድር ፋሲል ስለዕለቱ ዝግጅት ሲናገር፣ “ግርማ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ መስራት የቻለ ትልቅ የሙዚቃ ባለሙያ ነው። ይህን እናውቅ ነበር፤ ዝግጅቱም እጅግ የተዋጣለት ነበር ማለት እችላለሁ። እስከዛሬም በአገራችን ከተዘጋጁና በጣት ከሚቆጠሩ የክላሲካል ሙዚቃ ኮንሰርቶች የተሻለና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ነበር” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

በዕለቱ በመድረኩ ላይ በመንገስ ያቀናበራቸውን ሙዚቃዎች በፒያኖው እያጀበ ከሌሎች ሙዚቀኞች ጋር በጋራ ሲያቀርብ ያመሸው ፒያኒስት ግርማ ይፍራሸዋም ከዝግጅቱ በኋላ ስለነበረው መንፈስ፣ “ዝግጅቱ ደረጃውን የጠበቀና ከዚህ ቀደም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሰራቸው መሰል ኮንሰርቶች ከፍ ባለ መልኩ ሰርተናል። በተለይም የታዳሚው በፀጥታ መከታተልና ከሙዚቃው ጋር የነበረው ግንኙነት በጣም የሚያስደስት ነበር” ሲል ይገልጸዋል።

የረቂቅ ሙዚቃ ድግሱን በአዳራሹ ተገኝተው የታደሙት ከ600 በላይ የሙዚቃ አፍቃሪያን እንደሚሆኑ የገለፀው እስክንድር፤ ከረቂቅ ሙዚቃ አንፃር ለአገራችን ትንሽ የሚባል የተመልካች ቁጥር አይደለም ይላል። ፒያኒስትና ሙዚቃ አቀናባሪው ግርማ በበኩሉ በዕለቱ ስለመጣው ታዳሚ ሲገልጽ፣ “እንደውም ከዚህም በላይ ታዳሚ ይኖራል ብዬ ጠብቄ ነበር” ይላል።

የተመልካቹን ምላሽ በተመለከተ ከእሁድ ምሽት ጀምሮ እስካነጋገርኩት ጊዜ (ማለትም ሰኞ ከሰዓት በኋላ ድረስ) የአድናቆትና የምስጋና የስልክ ጥሪዎች እየደረሱት እንደነበር የገለፀው ፒያኒስት ግርማ፤ “ሰው በጣም ከመደሰቱ ባለፈ ለሙዚቃው ያላቸውን ትልቅ ክብር ስለገለፁልኝ እኔም በጣም ደስተኛ ነኝ” ይላል።

“የትም ቦታ በክብር ልንናገርለት የምንችለው አይነት የሙዚቃ ኮንስርት ነው” በማለት የሚገልፀው የብሉሚዲያ መስራች ስራ አስኪያጅ እስክንድር፤ ከዝግጅቱ በኋላ ከበርካታ እንግዶች ጋር በመገናኘት ስለዝግጅቱ መጠየቁን አስታውሶ፤ “ሁሉም ሰው ከጠበቀው በላይ ረክቶ እንደወጣ ነግሮኛል” ይላል።

በፕሮግራሙ ላይ ግንቦት 5 ቀን 2009 ዓ.ም ድንገት ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩት በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ለነበሩት ለዶ/ር ጆአሺም ሺችሚት የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት እንዲደረግ የጋበዘው አርቲስቱ ለአምባሳደሩ ያለውን ክብር በመግለፅ አብረውት ስራዎቻቸውን ላቀረቡትና በስፍራው ለታደሙት ጀርመናዊያን ከልብ የመነጨ መፅናናቱን ተመኝቷል። በረቂቅ የሙዚቃ ድግስ ላይ በርካቶችን ያስደመመችው ጀርመናዊቷ የኦፔራ አቀንቃኝ ፍሬደሪካ ሃርሞሰን በፒያኒስት ግርማ የተፃፈውን የአማርኛ ግጥም ያካተተ ሙዚቃ ተጫውታለች። የእርሷ በማይመስል ተስረቅራቂና የመደመጥ ለዛን በተቸረው ድምጽ “የት ነው መነሻችሁ፣ የት ነው መድረሻችሁ?” ስትል ትጠይቃለች። በአዘፋፈን ስልቷና በአስገራሚው ድምጿ በተመልካቹ ዘንድ የተለየ መደመም ፈጥራ ነበር ማለትም ይቻላል። በአገሯ አንጋፋ ሙዚቀኛ መሆኗን የሚናገረው ፒያኒስት ግርማ ይፍራሸዋ ስለጀርመናዊቷ የኦፔራ አቀንቃኝ የተሰማውን እንዲህ ይገልጻል። “አስቀድማ ይህን ዝግጅት ለመስራት ከፍተኛ ፍቅርና ጉጉት ነበራት። ከልቧ የተዘጋጀችበት በመሆኑ እኔንም አስገርማኛለች። ለኛም ቢሆን ለቋንቋችንና ለሙዚቃችን ትልቅ ኩራት ነው” ብሏል። የኦፔራ ሙዚቃን በመጫወት በሀገሯ ትልቅ ስምና ዝናን እንዳላት የተነገረላት ይህቺ አርቲስት፤ ከሶስት በላይ ስራዎችን ለታዳሚው ፊት አቅርባ አድናቆትን አግኝታለች።

የሙዚቃ ዝግጅቱ በከፍተኛ ጥናት የቀረበ መሆኑንም የሚናገረው ግርማ፤ ምንም እንኳን ለሙዚቃ ባለሙያዎቹ ስራዎቹ ቀድመው የደረሷቸው ቢሆንም ያለፈውን አንድ ሳምንት ግን በጋራ ዝግጅት ማሳለፋቸውንም ያስታውሳል። በዕለቱ ሲነገር እንደሰማነው በተለይ ፒያኒስት ግርማ ይፍራሸዋ ለዝግጅቱ መሳካት ከነበረው ጉጉት የመነጨ የእንቅልፍ ማጣትም አጋጥሞት እንደነበር ሰምተናል። “እንደአዘጋጅም እንደባለሙያም ስለነበር የማስበው “ይህ ኮንሰርት በመልካም ይጠናቀቅ ይሆን?” በሚል ትንሽ መጨናነቁ አይጠፋም። ያም ሆኖ እግዚአብሔር ይመስገን በጥሩ ሁኔታ አልፏል” ብሏል።

በዕለቱ በርካታ ግለሰቦችና ተቋማት የምስጋና ስጦታ የተበረከተላቸው ሲሆን፤ በተለይም አንጋፋው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በፒያኒስት ግርም ይፍራሸዋ የተፃፈ የረቂቅ ሙዚቃዎችን የያዘ “ስኮር” ሲበረከትለት አይተናል። “ይህ ስራ ለትውልድም እንዲተላለፍ በሚል ለቴአትር ቤቱ ማበርከቴ ለኔ ትልቅ ክብር ነው” ብሏል። ከዚህ ባለፈም ከአዳማ ድረስ በውሰት የመጣለትን የረቂቅ ሙዚቃ መጫወጫ ትልቅ ፒያኖ በተመለከተ ያዋሱትን ዶ/ር አማካለች ከልብ የመነጨ ምስጋናውን በይፋ አቅርቧል።

የሙዚቃን ዓለምቀፋዊ ቋንቋነት ማጉላት የቻለው ይህ የረቂቅ ሙዚቃ ድግስ የባቲ፣ የአንቺ ሆዬ፣ የትዝታና የአምባሰል ስልት በጉልህ የሚታይባቸው ስራዎች ቀርበውበታል። በተለይ ግን “እሩቅ ምስራቅ ሳለሁ ጃፓኗን ወድጄ”፣ የተሰኘውን የአንጋፋውን የጥላሁን ገሰሰ ስራ በረቂቅ የሙዚቃ ስናዳምጥ የሚሰጠው ጣዕም የተለየ ነበር። የጋብቻና የትዳርን ከፍታ የሚያሳዩ ስራዎች ቀርበዋል። በተለይም “ለጥበበኛው” (To the master) የተሰኘውን ስራ በጋራ ሲያቀርቡት የነበራቸው መናበብና የሙዚቃ ውህደት የታዳሚውን ነፍሴ በሀሴት የሞላ እንደነበር አዳራሹን ካናጋው ጭብጨባ መገመት ይቻላል።

ፒያኒስትና የሙዚቃ አቀናባሪው ግርማ ይፍራሸዋ በቀጣይም በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ባህላዊና ታሪካዊ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች ላይ ደማቅ የረቂቅ ሙዚቃ ኮንሰርት የማዘጋጀት ሃሳብ እንዳለው ገልጿል። ይህን ለማድረግ ብዙ ደጋፊዎች ከጎን እንደሚያስፈልጉ ያስታወሰው ግርማ፤ “በኔ በኩል ስራዎቼን ለማቅረብ ዝግጁ ነኝ። አቅሙ ያለው ኃይል ይህን ማመቻቸትና ማስተባበር ከቻለ በስድስት ወራት ውስጥ ሊሆን የሚችል ነው” ሲል የሚመለከታቸው አባላት ትኩረት እንዲያደርጉበት ጠይቋል።

ይህን በተመለከተ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ፌስቲቫሎችና የሙዚቃ ኮንሰርቶች በመስራት የሚታወቀው “ብሉ ሚዲያ” ልክ እንደዚኛው ኮንሰርት ሁሉ የግርማን ሃሳብ በመደገፍ አብረውት መሠራት እንደሚፈለጉም ገልጸዋል። ከዚህም ባለፈ የጃዝ ሙዚቃ ኮንሰርት የማሰናዳት ፍላጎት እንዳላቸው አስረድተዋል።

እስካሁን በአልበም ደረጃ ሶስት ስራዎችን ለአድማጩ ያደረሰው ግርማ፤ አሁን ላይ በአልበም ደረጃ የሚወጡ አዳዲስ ስራዎችን እየሰራ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ተናግሯል። የፒያኒስትና ሙዚቃ አቀናባሪው ግርማ ይፍራሸዋ ስራዎች በተመስጦ፣ በፅሞናና በመደነቅ ተጀምሮ ሳይሰለች ተጠናቋል።    

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
15861 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1030 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us