“የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቀን”

Wednesday, 28 June 2017 11:45

 

አልባብ የቴአትርና ሙዚቃ ፕሮሞሽን ለአምስተኛ ጊዜ የሚያዘጋጀው “የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቀን” በባህርዳር ከተማ ሊካሄድ መሆኑን ባሳለፍነው ሳምንት በካፒታል ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ37ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለአምስተኛ ጊዜ የሚካሄደው ይህ ፕሮግራም፤ የኢትዮጵያውያንን የሙዚቃ ቅኝቶች ከማስተዋወቅ ባለፈ የእርስ - በእርስ ግንኙነታችንን እንደሚያጠነክረው አዘጋጆቹ ሲናገሩ ሰምተናል። ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ (2004ዓ.ም)፣ በሀዋሳ (2005ዓ.ም)፣ በድጋሚ በአዲስ አበባ (2007ዓ.ም)፣ እንዲሁም በትግራይ ክልል አክሱም፣ አዲግራትና መቀሌ ደግሞ (2008 ዓ.ም) በደመቀ መልኩ መከበሩን ያስታወሰው የአልባብ የቴአትርና የሙዚቃ ፕሮሞሽን ዋና ስራ አስኪያጅ አርቲስት ተስፋዓለም ታምራት፤ በዚህም ዓመት ከባህርዳር ከተማ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር የተሻለ ዝግጅት መደረጉን አስታውቋል።


“ይህን ፕሮግራም ለማሰናዳት የመጀመሪያው ሰው መሆን በራሱ ከታሪክ ባለፈ ዕድለኛም ያሰኛል” የሚለው አርቲስት ተስፋዓለም ታምራት፤ የሙዚቃ ቀንን በኢትዮጵያ ደረጃ ለማክበር በሄደበት መንገድ የደገፉትን አንጋፋውን ድምጻዊ አረጋኸኝ ወራሽ እና የሙዚቃ ባለሙያውን ሰርፀ ፍሬ ስብሃትን በመድረኩ መክፈቻ ላይ አመስግኗል።


ይህንን ፕሮግራም ለመጀመር የተለያዩ ፈተናዎች እንደነበሩ ያስታወሰው አርቲስት ተስፋዓለም ታምራት፤ “ሙዚቃ የተለያዩ በብሔራዊ ደረጃ ታሳቢው የሚከበሩ ቀኖችንና ባህላትን ሲያደምቅ እንደኖረ ሁሉ ይህ ቀን ራሱን ሙዚቃን ማድመቂያ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል ብዬ በማሰብ ጀመርኩት ፕሮጀክት ነው” ይላል። እንደተግዳሮት ከሚጠቀሱት ክስተቶች መካከል ፕሮጀክቱን ለባለሙያዎች ይፋ ባደረገበት ወቅት “ይህ ጉዳይ ነው፤ አንተን አይመለከትህም” መባሉ እንደሆነ አስታውሶ፤ የሀሳብ “ኮፒ ራይት” ነገር ያኔ እንደጀመረው በፈገግታ ያስታውሰዋል። ያም ሆኖ አሁን ላይ የሙዚቃ ባለሙያዎችን በማስተባበር በሀገር አቀፍ ደረጃ ለአምስተኛ ጊዜ ቀኑን ለማክበር በዝግጅት ላይ እንገኛለን ብሏል።


በዓለም አቀፍ ደረጃ የሙዚቃ ቀን መከበር የጀመረው በአሜሪካዊው አርቲስት ጆኤል ኮሄል (በ1976) እንደነበር በማስታወስ የተናገሩት ደግሞ የአልባብ የቴአትርና ሙዚቃ ፕሮጀክት አማካሪው አቶ ዘመዱ ደምስስ ናቸው። የተቀናጀ የሙዚቃ ቀን ለሙያተኞች በሚል ለመጀመሪያ ጊዜ በፈረንሳይ ሀገር መከበር የጀመረው ይህ ፕሮግራም፤ ከ32 በላይ በሆኑ የዓለማችን አገራት በአንድ ቀን እንደሚከበርም አስታውቀዋል።


የሙዚቃ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲከበር ሁለት መሠረታዊ አላማዎች እንዳሉት ያስታወሱት የፕሮጀክቱ አማካሪ፤ “አንደኛው ጀማሪና የበቁ ሙያተኛ ሙዚቀኞች ስራዎቻቸውን በየጎዳናው እንዲያቀርቡና እንዲበረታቱ ለማድረግ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ከክፍያ ነፃ የሆነ የሙዚቃ ኮንሰርት ለህዝብ እንዲቀርብ ማመቻቸትን ያለመ” እንደሆነ አስረድተዋል። ይህንንም ሀሳብ የዓለም አቀፉ የሙዚቃ ምክር ቤት (1975 እ.ኤ.አ.) በአባላቱ አማካኝነት በዩኔስኮ ደብዳቤ በመፃፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲከበር ማድረጉንም ከታሪካዊ ዳራው መገንዘብ ተችሏል። በአገራችንም በተመሳሳይ ያልተዳሰሱ ባህላዊና ዘመናዊ መሳሪያዎችን ለማስተዋወቅ ለጀማሪ ሙዚቀኞች ዕድል ከመስጠቱም ባለፈ የሀገራችን ሙዚቃና ዕድገቱ የት ደረጃ ላይ እንዳለ ለመገምገም ምቹ መድረክ መሆን ይችላል ሲሉ “የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቀን” የሚከበርበትን ፋይዳ ያስረዳሉ።


“የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቀን” በሚል ከሰኔ 28 እስከ 30 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ በባህርዳር ከተማ የሚካሄደው በዚህ ዝግጅት ላይ የክልሉ መንግስት ያሳየውን ባለድርሻነት በተመለከተ የከተማዋ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ዘለቀ ይህን ብለዋል። “ባህርዳር የባህልና የኪነ-ጥበብ ማዕከል እንድትሆን ተግተን እየሰራን እንገኛለን” ያሉት ኃላፊው፤ ስመጥር የሆኑ ከያኒያንን ከማፍለቅ ባለፈ በተለይም ለፊልም ስራ ምቹ የሆነ ምስል የሚገኝባት ከተማ መሆኗን አስታውሰዋል። “የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቀን በባህርዳር ከተማ እንዲከበር በመጠየቃችን በደስታ ተቀብለነዋል። ወደፕሮግራሙ የሚመጡ እንግዶችን ሠላማዊና አስደሳች በሆነ መልኩ እንዲስተናገዱ ለማድረግ ከተማችን የተቻላትን ታደርጋለች” ብለዋል።


ዘንድሮ ለአምስተኛ ጊዜ የአማራ ክልል መዲና በሆነችው ባህርዳር የሚከበረው “የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቀን” ምን የተለየ ነገር ይኖረዋል ከተባለ፤ መገናኛ ብዙሃን ለፕሮግራሙ ሽፋን እንዲሰጡት በማድረግ የሙዚቃ ቀንን በማህበረሰቡ ልብ ውስጥ በማስረፅ በባለቤትነት እንዲንከባከበው ግንዛቤ መፍጠርን ታሳቢ አድርጓል። ከዚህም ባለፈ በክልሉ ስለሚገኙ የሙዚቃ መሳሪያዎች፣ ተፈጥሯዊ፣ ቁሳዊና መንፈሳዊ ቦታዎች በማስተዋወቅ እንዲጎበኙ ማበረታታት እና በክልሉ የሙዚቃ ዕድገት ዙሪያ ጥናት ላይ የተመረኮዘ የዳሰሳ ስራ፤ የፓናል ውይይት ማካሄድ ይኖራል ሲባል ሰምተናል። በተመረጡ ቦታዎች ተጋባዥ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች በስማቸው ችግኝ እንዲተከል የሚደረግ ሲሆን፤ በክልሉ የሙዚቃ ስራ ላይ አሻራቸውን ላሳረፉ ባለሙያዎችም ዕውቅና የሚሰጥበት ፕሮግራም መሠናዳቱ ተነግሯል። ባህርዳርን ሊገልጽ የሚችል የሙዚቃ ቪዲዮ እንዲሰራ በማድረግ አወዳድሮ ለመሸለም ዝግጅት መደረጉም ተሰምቷል። በአጠቃላይም አምስተኛውን “የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቀን” የሚያትት ጥናትና ዳሰሳን ያካተተ በማሳተም ይሰራጫል ተብሏል።


የአልባብ የቴአትርና ሙዚቃ ፕሮሞሽን የፕሮጀክት አማካሪ የሆኑት አቶ ዘመዱ ደምስስ በአገር አቀፍ ደረጃ ስለሚከበረው የሙዚቃ ቀን አስፈላጊነት ሲያስረዱ፤ “ኢትዮጵያ ሙዚቃን ለዓለም ካበረከቱ አገራት ተርታ ትመደባለች ቢባል ምንም ውሸታም አያሰኘንም” በማለት ማስረጃዎች እንዳሉን ይጠቅሳሉ። ነገር ግን በጥናትና ምርምር የተደገፉ ስራዎችን ለዓለም ማስተዋወቅ አለመቻላችን እንደትልቅ ችግር ሊጠቀስ ይችላል ባይም ናቸው። ለዚህም ከ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ዓመታት ያስቆጠሩ የሙዚቃ ቅኝቶች እንዳሉን አስታውሰው፤ ቤተ ክህነት አካባቢ ቅዱስ ያሬድ የፃፋቸው ጥንታዊ የሙዚቃ ቀመሮች (ኖታዎች) አሁን ድረስ እየተሰራባቸው ይገኛል ብለዋል። የሙዚቃ ቀን በኢትዮጵያ መከበሩም እርስ - በእርሳችን ያለንን የሙዚቃ መሳሪያና ስልት ከመተዋወቅ ባለፈ ለአለምም የምናሳየው ነገር እንዲኖረን ዕድሉን ይፈጥራል የሚሉት አማካሪው፤ አክለውም፣ “አልባብ ያሰናዳው ይህ ዝግጅት ያልተተጋበትን የሙዚቃ መንደር በትጋት በመስራት፤ የሙዚቃን ፋይዳ ከፍ አድርጎ በማሳየትና የእርስ - በእርስ ትውውቅን መፍጠር ያስችላል” ብለዋል።


በአገራችን የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ የሚታዩ ክፍተቶች መኖራቸውን የጠቆሙት አማካሪው፤ በተለይም የሙዚቃ ባለሙያዎች በተቀናጀ ህብረት ውስጥ አለመኖራቸው እንደቅርብ ጊዜ ምሳሌ ተጠቅሷል። ሙዚቀኛውንና የሙዚቃ ባለድርሻውን በሚገባው መጠን ተጠቃሚ አለማድረጉም ሌላው በአገሪቱ የሙዚቃ ሂደት ውስጥ የሚጠቀስ ክፍተት ነው ተብሏል። በተለይ ከፊት የሚገኙ ድምፃዊያን (አርቲስቶች) ተጠቃሚ ሲሆኑ፤ ከኋላ ያሉት የግጥምና ዜማ ደራሲዎች፣ የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋቾች፣ የሙዚቃ አቀናባሪዎችና ሙዚቃውን የሚያስተዋውቁ ሁሉ በሚገባቸው መጠን ተጠቃሚ አለመሆናቸው ለነበረው ክፍተት እንደማሳያ ተጠቅሷል። ሌላውና አንገብጋቢው ነገር ኢትዮጵያን አጠቃሎ መግለፅ የሚችል የሙዚቃ ሙዚየም አለመኖሩ ተነግሯል። ይህም በተለይ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ላሉ ተመራማሪዎች እንደግብዓት የሚጠቀሙበት ማጣቀሻ እንዲያጡ አድርጓል ብለዋል። በአንፃሩ ደግሞ “ከአባይ ማዶ” ያሉ ሙዚቃዎች ብቻ ለረጅም ዓመታት ተቆጣጥረውን መቆየታቸው፤ ወደተቀሩት የአገራችን ክልሎች መድረስ የሚገባንና ማየት ያለብንን እንዳናይ ሆነናል ብለዋል። በቀጣይም ሁሉም የአገራችን የሙዚቃ መሳሪያዎችና ስልቶች በሚገባ እንዲተዋወቁ “የሙዚቃ ቀን” የድርሻውን ይወጣል ሲሉ ተደምጠዋል።


የኢትዮጵያ ሙዚቃ ቀን አጥብቆ ከሚሰራባቸው ጉዳዮች መካከል በተለይም በሙዚቃ ቪዲዮዎቻችን ውስጥ የሚታዩ ጉራማይሌ የሆኑ አለባበሶችና ጭፈራዎች ወጥነት እንዲኖራቸው መሆኑን አስታውሰው፤ ከሙዚቃዎች ጋር የሚቀርቡ ባህላዊ አልባሳትና ጭፈራዎች ወጉን የጠበቁ እንዲሆኑ ለማስቻል እንደሚተጉ አማካሪው አቶ ዘመዱ ተናግረዋል።


የሙዚቃ ቀንን በኢትዮጵያ የምናከብረው ለማክበር ብቻ በሚል የአንድ ሰሞን ግርግር አይሆንም ያሉት አዘጋጆቹ፤ በቀጣይም ሳይቆራረጥ እየተከበረ የሚገኘውን የሙዚቃ ቀን ወደዓለም አቀፍ ደረጃ ለማድረስ እየተሰራ እንደሚገኝ በመድረኩ ሲነገር ሰምተናል። ለዚህም የኢትዮጵያን የሙዚቃ ቀን የዓለም አቀፍ የሙዚቃ ቀን አካል ማድረግ፤ እንዲሁም በኢትዮጵያ ሙዚዎች ላይ በዓለም አቀፍ ዩኒቨርስቲዎች ሳይቀር ጥልቅ የሆነ ጥናትና ምርምር እንዲካሄድ በማስቻል፤ በተለይም የተዘነጉ የሙዚቃ መሳሪያዎችንና ጭፈራዎች ተጠንተው እንዲታወቁ በጀት እናፈላልጋለን ብለዋል።
አልባብ የቴአትርና የሙዚቃ ፕሮሞሽን “የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቀን” ሲከበር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የሚሰራ መሆኑን ያስታወሰው ሀሳብ አመንጪው የፕሮግራሙ ዋና አዘጋጅ አርቲስት ተስፋለም ታምራት፤ የበጀት ክፍተት መኖሩ ከዚህም በላይ እንዳይሰሩ ተግዳሮት እንደሆነባቸውም ተናግሯል። እስካሁንም አብረዋቸው ለሰሩት እና ለደገፏቸው አካላት ምስጋና አቅርቦ በቀጣይም ባለሙያውና የሚመለከተው አካል ተባብሮ የኢትዮጵያን ሙዚቃ በአለም አቀፍ ደረጃ የበለጠ ማስተዋወቅ እንደሚገባ ተናግሯል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
15940 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 977 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us