“አሸናፊዎቹ መፅሐፍት ተተርጉመው ዓለም አቀፍ አንባቢያን ዘንድ እንዲደርሱ ለማድረግ እየሠራን ነው”

Wednesday, 09 August 2017 12:37

 

አቶ ኤፍሬም ብርሃኑ

የሆሄ የሥነ-ፅሁፍ ሽልማት ፕሮግራም ኃላፊ

 

“አንብበው የወደዱትን መፅሐፍ ያሸልሙ!” ይህ ነሐሴ 22 ቀን 2009 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የሚካሄደው “ሆሄ የሥነ-ፅሁፍ ሽልማት” አብይ መልዕክት ነው። ኖርዝ ኢስት ኤቨንትስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ከብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መፅሐፍት ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ያሰናዳው “ሆሄ የሥነ-ፅሁፍ ሽልማት” ለአገራችን ሥነ-ፅሁፍ እድገት የበኩሉን አስተዋፅኦ ከማበርከት ባለፈ፤ ለፀሐፍቱም ሆነ ለአንባቢያኑ መስታወት መሆን የሚችል ፕሮግራም እንደሚሆን በርካቶች ከወዲሁ ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ። አቶ ኤፍሬም ብርሃኑ የፕሮግራሙ ኃላፊ ሲሆኑ፤ በወጣቶች ጤናና ልማት ዘርፍ በርካታ ሥራዎችንም ሰርተዋል። ዛሬ የመዝናኛ አምድ እንግዳ አድርገን ስናቀርባቸው በ“ሆሄ የሥነ-ፅሁፍ ሽልማት” ዙሪያ የሚከተሉትን ሀሳቦች አንስተን ተጨዋውተናል። መልካም ንባብ….

 

ሰንደቅ፡- “ሆሄ” የሚለው የሽልማት ድርጅቱ መጠሪያ በምን መልኩ ሊመረጥ ቻለ?

አቶ ኤፍሬም፡- ኢትዮጵያ ከምትታወቅባቸው ጥንታዊ ሀብቶቿ መካከል አንዱ የራሷ የሆነ ፊደል ያላት መሆኗ ነው። ከዚህም ባሻገር የኢትዮጵያ የሥነ-ፅሁፍ ታሪክም በዓለም ካሉት እጅግ በጣም ቀደምት ነው። እናም የራሳችን ፊደል ባለቤቶች መሆናችንን ለማመልከት ታስቦ ነው “ሆሄ” የሚለው የተመረጠው። የሥነ-ፅሁፍ የሽልማት ፕሮግራም እንደመሆኑ ደግሞ ከፊደል ውጪ አይታሰብምና ዞሮ-ዞሮ ማንነታችን ላይ ከማተኮር የመነጨ ነው ስያሜን ለመጠቀም አስበን ነው “ሆሄ የሥነ-ፅሁፍ ሽልማት” ስንል የሰየምነው።

 

ሰንደቅ፡- ከመነሻው ይህ የሽልማት ፕሮግራም እንዴት ታሰበ? ለአገራችን ሥነ-ፅሁፍስ የሚያበረክተው ፋይዳ ምንድነው?

አቶ ኤፍሬም፡- በዋናነት መነሻ ያደረግነው የንባብ ባህልን ለማነቃቃትና የሥነ-ፅሁፍን ደረጃ ከፍ ለማድረግ በሚል ነው። ሥነ-ፅሁፋችንን ለማበረታታት ምን ይደረግ ስንባባል ሥነ-ፅሁፋችን ላይ ያተኮረ የሽልማት ፕሮግራም ማዘጋጀቱን ተስማማን። መሰል ፕሮግራሞች በተለይ በሥነ-ፅሁፍ ዙሪያ ቀጣይነት ባለው መልኩ ባለመኖሩ ምክንያት እኛ በየዓመቱ የሚወጡትን መፅሐፍት በተቻለ አቅም በዳኞችና በአንባቢያን ፍተሻ ላይ ተመርኩዘን ብንሸልም፤ በአንድ በኩል ሥነ-ፅሁፍን ለማበረታታት ይረዳል። በሌላ በኩል ደግሞ አንባቢያንን በማነቃቃት የንባብ አቅማችንን ማጐልበት እንችላለን በሚል ነው የጀመርነው።

 

ሰንደቅ፡- “ሆሄ የሥነ-ፅሁፍ ሽልማት” ፕሮግራም መፅሐፍትን አወዳድሮ መሸለም ብቻ ነው ዓላማው?

አቶ ኤፍሬም፡- ዓላማችን  መሸለም ብቻ አይደለም። ለምሳሌ በቀጣዩ ዓመት ከፈረንሳይ የባህል ማዕከል ጋር በመሆን ዓለም አቀፍ የመፅሐፍት ፌስቲቫል በአዲስ አበባ ለማካሄድ በሚያዚያ ወር ዕቅድ ይዘናል። በሌላም በኩል ከኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ጋር በመነጋገር ቀጣይነት ያለው ሥነ-ጽሁፍ ተኮር የውይይት መድረክ እንዲኖር እየሠራን ነው። የህፃናት የመፅሐፍት ሳምንትም እናዘጋጃለን ብለናል። ስለዚህ ከሽልማት ፕሮግራሙ ጐን-ለጐን ዓመቱን በሙሉ የምንሰራቸው ሥራዎች ይኖራሉ ማለት ነው።

 

ሰንደቅ፡- በግልህ ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮዎችን እንዳገኘህ አውቃለሁ። መሰል ፕሮግራም በእኛ አገር ሲካሄድ ከሌሎቹ አገራት የወሰድናቸው ልምዶች ይኖሩ ይሆን?

አቶ ኤፍሬም፡- ይህንን የሽልማት ፕሮግራም ስናዘጋጅ ከሀገር ውስጥም ሆነ ከዓለም አቀፍ የተመለከትናቸው ቀደምት ተመሳሳይነት ያላቸው ፕሮግራሞች አሉ። ለምሳሌ ከቀደሙት የቀዳማዊ ኃይለስላሴ የሽልማት ድርጅት አንዱ እና በጉልህ ተጠቃሹ ነው። እንደሚታወቀው ይህ ፕሮግራም የተደራጀ ነበር ማለት ይቻላል። እርግጥ እንደ እኛ ሥነ-ፅሁፍ ላይ ብቻ ሳይወሰን በተለያዩ ዘርፎች ላይ ነው የሚያተኩረው። ከዚያም ሌላ ከቅርብ ጊዜው የመገናኛ ብዙሃን ሽልማት ድርጅት የሚባል ተቋቁሞ እንደነበር እናስታውሳለን። ከውጪም የተመለከትናቸው አሉ። በተለይ በመፅሐፍት ዙሪያ በርካታ ፕሮግራሞች ይሰራሉ። ለዛም የሕትመት ኢንዱስትሪው ጠንካራ መሆኑ ማሳያ ነው። ለምሳሌ ከአፍሪካ ኬኒያ፣ ደቡብ አፍሪካና ጋና በመፅሐፍት ዙሪያ አነቃቂ ሥራዎችን ከሚሰሩ ግንባር ቀደምት አገሮች ተርታ የሚመደቡ ናቸው። ወደ እኛ ፕሮግራም ስንመጣ እንግዲህ ደረጃውን ጠብቆ እንዲቀጥል፤ በዋናነትም በዘርፉ ውስጥ ያሉ ተዋንያኖች (ማለትም ፀሐፊያኑ፣ አንባቢያኑ፣ አሳታሚዎቹና በመፅሐፍት ዙሪያ የሚሰሩ ሰዎች በሙሉ) የሚሳተፉበት ለማድረግ እየሰራን ነው። እንደመጀመሪያ እስካሁን ያለው እንቅስቃሴያችን ጥሩ ነው።

 

ሰንደቅ፡- በርካታ ባለሙያዎችን ባቀፈ ኮሚቴ የሚመራ የሽልማት ፕሮግራም አዘጋጅታችሁ፤ በመንቀሳቀስ ላይ እንደምትገኙ ይታወቃል። ምን ያህል ስራዎችን ገምግማችሁ ለመጨረሻ ዙር ዕጩ አደረጋችሁ?

አቶ ኤፍሬም፡- በ2008 ዓ.ም የታተሙ መፅሐፍትን ነው አወዳድረን ለመሸለም የተቀበልነው። እንዳልከው ይህን ፕሮግራም የማያስተባብሩ አስራ አራት አባላት ያሉት ኮሚቴ ተቋቁሞ ስራውን እየሰራ ይገኛል። በረጅም ልቦለድ ዘርፍ ወደሃያ ሦስት መፅሐፍትን ነው ያገኘነው፤ ከዚህም ውስጥ ‘ዝጎራ’፣ ‘የስንብት ቀለማት’፣ ‘መፅሐፉ’፣ ‘ውስብሳቤ’ እና ‘የሱፍ አበባ’ የተሰኙ መፅሐፍት ለመጨረሻው ዙር ቀርበዋል። በግጥም ዘርፍ ደግሞ ወደ ሰላሳ ዘጠኝ የሚደርሱ ሥራዎችን ተመልክተናል፡ ከእነዚህም ውስጥ፤ ‘ኑ ግድግዳ እናፍርስ’፣ ‘የጎደሉ ገጾች’፣ ‘የተስፋ ክትባት’፣ ‘ፍርድ እና እርድ’፣ እንዲሁም ‘እንቅልፍና ሴት’ የተሰኙ ሥራዎች ለመጨረሻው ዙር ቀርበዋል። ሌላው ዘርፍ የልጆች መፅሐፍት የሚል ነው። ከዚህ ዘርፍ ወደ አስራ ሁለት የሚደርሱ መፅሐፍትን አግኝተናል፤ ነገር ግን ለመጨረሻው ዙር የቀረቡት ‘የቤዛ ቡችላ’፣ ‘የአይጦችና የድመቶች ሰርግ’ እና ‘ዋናተኛዋ ሶሊያና’ የተሰኙ ሦስት መፅሐፍት ናቸው። በዋነኛነት ለውድድር የቀረቡት መፅሐፍት በሙሉ በኢትዮጵያውያን ፀሐፍት የተፃፉና ወጥ ታሪኮችን የያዙ በሚል ነው የመረጥናቸው። በመሆኑም በተለይ የልጆች መፅሐፍት አብዛኞቹ ትርጉም ስራዎች ሆነው ስለመጡልን ሳንቀበላቸው ቀርተናል።

 

ሰንደቅ፡- የመወዳደሪያ ዘርፎች ለምን አነሱ?... በኢትዮጵያ የሥነ-ፅሁፍ ታሪክ ውስጥ የትርጉም ሥራዎችም የራሳቸው ድርሻ አላቸው የሚሉ ባለሙያዎች አሉና ወደፊት ዘርፎቹን በማስፋት እንዲካተቱ የማድረግ ሀሳብስ ይኖራል?

አቶ ኤፍሬም፡- እውነት ነው። እንግዲህ በዚህ ዓመት በሦስቱ ዘርፎች በመጀመር በቀጣይ እያሳደግን ለመምጣት ሀሳቡ አለን። በቀጣይ ዓመት እናካትታለን ብለን ካሰብናቸው መካከል የአጫጭር ልቦለድ ሥራዎችን፤ የትርጉም ሥራዎችን፤ እንዲሁም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚያሳትማቸውን የምርምር ሥራዎችንም የሚዳሰሱበትና የሚተዋወቁበትን መንገድ እንፈልጋለን ብለናል። ስለዚህ ዘርፎቹ በቀጣይ ሰፋ ማለታቸው አይቀርም።

 

ሰንደቅ፡- ነሐሴ 22 ቀን 2009 ዓ.ም በብሔራዊ ቴአትር ለሚካሄደው የሽልማት ፕሮግራም ከዳኞች በተጨማሪ የአንባቢያን ድምፅ በምን መልኩ ይካተታል?

አቶ ኤፍሬም፡- ስንጀምር ምንድነው ያደረግነው፤ የተለያዩ የሽልማት ፕሮግራሞችን ተሞክሮ በመውሰድ ሦስት-ሦስት ዳኞችን በእያንዳንዱ ዘርፍ እንዲኖሩ አድርገናል። እነዚህ ዳኞች በስፋት በሥነ-ፅሁፍ ዙሪያ የሚታወቁ ደራሲያን፣ የሥነ-ፅሁፍ ተመራማሪዎች እና የሚታመኑ ባለሙያዎች የተካተቱባቸው ናቸው። ከዳኞቹ ባሻገር አሁን የመጨረሻዎቹ ዕጩዎች ታውቀዋል። እኛ የምንሸልመው አንደኛ የወጡትን ሥራዎች ነው። ይህ የተሳካ እንዲሆንም አንባቢያን የራሳቸውን ድምፅ እንዲሰጡ በተለያዩ መንገዶች መፅሐፍቱን በማስተዋወቅ እንዲመርጧቸው ከሐምሌ 20 እስከ ነሐሴ 20 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ እያስተዋወቅን እንገኛለን። በነገራችን ላይ የአንባቢው ድምፅ ከአጠቃላዩ 20 በመቶ የሚሆነውን ይይዛል። የዳኞቹ 80 በመቶ ሲሆን፤ የድምር ውጤቱ በሽልማቱ ዕለት ይታወቃል። ስለሆነም አንባቢያን አንብበው የወደዱትን መፅሐፍ ለመሸለም በስልክ 0988-12 12 12 በአጭር የፅሁፍ መልዕክት ወይም ደግሞ በፌስ ቡክ እና በሽልማቱ የትዊተር አድራሻ በኩል ለመጨረሻዎቹ ዕጩ መፅሐፍት ደረጃ መስጠት ይችላሉ ማለት ነው።

 

ሰንደቅ፡- ከሽልማትና ከዕውቅናው ባለፈ ሆሄ የሥነ-ፅሁፍ ሽልማትን ያሸነፉ ደራሲያን ምን የተለየ ጠቀሜታ ይኖራቸዋል?

አቶ ኤፍሬም፡- በዋናነት ከመነሻው ያሰብነው የምንሰጠው ሽልማት እንዳለ ሆኖ የሚያገኙት ዕውቅና ትልቅ እንዲሆን ለማድረግ ነው። የሽልማቱ ነገር በዕለቱ በአዳራሽ ውስጥ ብቻ የሚያልቅ አይደለም። ለምሳሌ አንድ ጥሩ ነገር ያደረግነው ከፈረንሳይ የባህል ተቋም ጋር በመነጋገር ከሆሄ የሥነ-ፅሁፍ ሽልማት አሸናፊ የሆኑትን መፅሐፍት ወደ ውጪ ቋንቋ በመተርጐም በፈረንሳይ አገር እንዲታተም ለማድረግ እየሠራን ነው። ይህም አሸናፊዎቹ መፅሐፍት ተተርጉመው ዓለም አቀፍ አንባቢያን ዘንድ እንዲደርሱ ለማድረግ እየሠራን ነው። ከዚያም ባሻገር በተለያዩ አገራት አጫጭር ሥልጠናዎችን የሚያገኙበት መንገድ ይመቻቻል። በውጪ ሀገር የሚካሄዱ መሰል የመፅሐፍት ፌስቲቫሎች ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ እስከማመቻቸት የሚደርስ ሥራ ለመሥራት እየተዘጋጀን እንገኛለን።

 

ሰንደቅ፡- እስካሁን በሄዳችሁበት ሂደት እንደተግዳሮት የሚጠቀሱ ነገሮች አሉ?

አቶ ኤፍሬም፡- በዋናነት መፅሐፍቱን የማግኘት ፈተና ገጥሞን ነበር። በተለይም የቤተ-መዛግብት እና ቤተ-መፅሐፍት ኤጀንሲ በአገሪቱ ውስጥ የሚታተሙ ሕትመቶች በሙሉ ይኖሩታል ተብሎ ስለሚታሰብ በአንድ ላይ ይገኛሉ የሚል ሀሳብ ነበረን። ነገር ግን በ2008 ዓ.ም የወጡትን መፅሐፍት በሙሉ ማግኘት አልተቻለም። በዓመቱ ለሕትመት የበቁ መፅሐፍትን ለማግኘት ሁለት ሦስት መንገዶችን ተጠቅመናል። ከዛም ባሻገር የሚጠቀስ ጉልህ ችግር የለም። ግን ይሄ የመጀመሪያ ሥራችን እንደመሆኑ ለቀጣይ መማሪያችንም ጭምር ሆኖ አልፏል።

 

ሰንደቅ፡- አሸናፊዎቹ የሚያገኙት ሽልማት ምን-ምን ያካትታል?

አቶ ኤፍሬም፡- ለአሸናፊዎቹ የሆሄ የሥነ-ፅሁፍ ሽልማት ዓርማ ያለበትን ሽልማት ከማበርከት ባለፈ፤ የገንዘብ ሽልማት እንዲኖረው አስበናል። ከዚያ ውጪ ግን በዚህ የሽልማት ፕሮግራም “ሒደት” ውስጥ ያለፉ መፅሐፍትን እንዴት ነው በትልቁ የምናስተዋውቃቸው የሚለው ነገር በጥልቀት አስበን እየሰራንበት ነው። ከተቻለም መፅሐፍቱን ወደፊልም የመቀየር ሀሳብም ይዘናል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
15747 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 877 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us