“ካርቱን ከመልዕክቱ ባሻገር አዝናኝ መሆን ይጠበቅበታል”

Wednesday, 09 April 2014 11:56

ሰዓሊ ቴዎድሮስ መስፍን (ቴዲማን)

ብዙዎች የሚያውቁት “ቴዲማን” በተሰኘውና ከካርቱን ስራዎቹ ግርጌ በሚያስቀምጠው ስሙ ነው። ቀደም ባሉት ጊዜያት በተለይም በ “መዝናኛ” እና በ “አዲስ ነገር” ጋዜጦች ላይ በሚሰራቸው የካርቱን ስራዎችና በሚፅፋቸው ፅሁፎቹ ይታወቃል። አሁንም ድረስ በተለያዩ ጋዜጦችና መፅሄቶች ላይ በካርቱን ስራው እየተሳተፈ የሚገኘው የዛሬው እንግዳችን ቴዎድሮስ መስፍን (ቴዲማን) ሲሆን፤ ከስዕል ሙያው በተጨማሪ የስነ-ልቦና እና የፊልም ባለሙያ ሲሆን በአመራር ደረጃም የአዲስ አበባ ኢንተርናሽናል ቴካንዶ ፌዴሬሽን በመስራት ላይ ይገኛል። ስለስራዎቹ ይህን መሰል ቆይታ አድርገናል።

ሰንደቅ፡- ወደስዕል ሙያ ለመግባት መነሳሳቱን ከየት አገኘኸው?

ቴዎድሮስ፡- ስዕልን የጀመርኩት ቤት ውስጥ ነው። ቤት ውስጥ የመስራቱን አጋጣሚ ያገኘሁት ደግሞ ታላላቆቼ መምህር ተቀጥሮላቸው በቤት ውስጥ ስዕልን ይማሩ በነበረበት ወቅት ነው። ወንድሞቼን ያስተምራቸው የነበረው ሰዓሊ ዕዝራ በልሁ ይባላል፤ አሁንም አለ። ወንድሞቼ ያን ያህል ትኩረት ሰጥተውት አይማሩም ነበር፤ ለምን እንደሆነ አላውቅም። እኔ ግን ስዕል በጣም ደስ ይለኝ ስለነበር አስተማሪያቸው ከሄደ በኋላ ይማሩበት ወደነበረው ክፍል ገብቼ የሰሯቸውን ስዕሎች አያለሁ። ደግሜም ለመስራት እሞክር ነበር። ከጊዜ በኋላ እነርሱ ትምህርቱን ሲተውት እኔ ግን ቀጠልኩ ማለት ነው።

ሰንደቅ፡- ያንተ ሰዓሊነት በተለየ የሚታወቀው በካርቱን ስራዎችህ ነው። ካርቱን ከሌሎች ስዕሎች ምንድነው የሚለየው?

ቴዎድሮስ፡- ካርቱን ከሌሎቹ የስዕል ዓይነቶች የሚለየው በመስመሮቹ ነው። ሁሉም ስዕል በመስመር ነው የሚሰራው። ነገር ግን ረቂቅ መስመሮችን ካርቱን ይፈልጋል። ምክንያቱም ካርቱን ከስዕልነቱና ከቁም ነገር አዘል መልዕክቱ ባሻገር አዝናኝም መሆን ይጠበቅበታል። ስለዚህ አዝናኝ ነገር ለመስራት ዘና ያሉ መስመሮች መጠቀም ይጠበቅብሃል። ወጣ ያሉ ቅርፆችን መጠቀም ይጠበቅብሃል። ሁለተኛው ደግሞ ማስተዋልን በጣም ይጠይቃል። አንድ ሙሉ ስዕል ስትሰራ እና አንድ ሎጎ (ምልክት ወይም አርማ ስትሰራ) ይለያያል። ምክንያቱም በትንሽ ነገር ውስጥ ብዙ ነገር ማሳየት ይጠበቅብሃልና ካርቱንም እንደዛ ነው። ሰፊ መልዕክትን አዝናኝና ቀላል በሆነ መንገድ የማሳየት ችሎታን ይፈልጋል።

ሰንደቅ፡- እንደሚታወቀው ብዙ ጊዜ በጋዜጦችና መፅሔቶች ላይ ነው ስራዎችህ የሚታዩት። መነሻ ሃሳቡ የሚሆንህን ፅሑፍ ታነበዋለህ?

ቴዎድሮስ፡- አዎ! ብዙ ጊዜ ካርቱን የሚያስፈልጋቸውን ፅሁፎች አንብቤ ነው የሆነዋል የምለውን ስራ የምሰራው። በተለይ ደግሞ በጋዜጦች ርዕስ አንቀፅ ከተነሳው ሃሳብ ጋር የሚሄድ ነገር እንድንሰራ ይጠበቃል። እኛ ሀገር ካርቱን ከርዕስ አንቀፅ ውጪ የማይገባ እስኪመስል ድረስ አንድ ቦታ ብቻ ነው ተዘውትሮ የሚሰራው። ነገር ግን ጋዜጦች ለካርቱን ስራዎች አንድ አምድ ቢፈቅዱላቸው ለስራው ማደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረው ነበር። በዚያ ላይ አንባቢያቸውም የሚያርፍበትና ዘና የሚልበት ገፅ ቢያገኝ ጥሩ ይሆን ነበር።

ሰንደቅ፡- ስራችሁ ከገቢ አንፃር ያዋጣል ማለት ይቻላል?

ቴዎድሮስ፡- በጣም ገና ነው። እንዳልኩህ ራስህን የምትገልፅበት መንገድ በጣም ጠባብ ነው። የህትመት ስራዎች ላይ ነው ልንታይ የምንችለው። ባለፈው እኔ እንዳደረኩት አልፈህ ሄደህ ራስህን የምታስተዋውቅበት ኤግዚቪሽን ካላደረግን በስተቀር ገቢው አዋጭ አይደለም።

ሰንደቅ፡- ከሁለት ዓመት በፊት ያቀረብከው አውደ-ርዕይ የመጀመሪያህ ነበር፤ ከታዳሚው ምን ምላሽ አገኘህበት?

ቴዎድሮስ፡- እኔ አንደኛ ነገር ይሄንን ጥበብ ማስረፅና ማስተዋወቅ በጣም እፈልጋለሁ። ሰውን ስዕል አያይም ብሎ ከመንቀፍና ጋዜጦች በቂ ቦታ አልሰጡንም ብሎ ከመቆጨት ይልቅ እኔ ማድረግ የምችለውን ማድረግ ስለነበረብኝ ነው ያን ፕሮግራም ያዘጋጀሁት። በነገራችን ላይ ኤግዚቪሽኑ የታዋቂ ሰዎችን ምስል በካርቱን ማሳየት ወይም ፖርትሬት ካርቱን (Portrait carton) ነው የሚባለው። ይህን በሰው ገፅ የሚሰራ የካርቱን ስዕል በደንብ ለማስተዋወቅና የሚገባውን ትኩረት ለመሳብ ደግሞ ታዋቂ ሰዎችን በመምረጤ ተመልካቹ አስቀድሜ ከገመትኩት በላይ ነበር። ብዙ ሰው ደስተኛና አበረታች ምላሽ ነበረው።

ሰንደቅ፡- ምስላቸውን ያስቀመጥክላቸውን ታዋቂ ሰዎች በምን መስፈርት ነው የመረጥካቸው?

ቴዎድሮስ፡- ምንም የተለየ መስፈርት አልነበረኝም። ሰዎቹ ታዋቂ መሆናቸው ብቻ ነው ያስመረጣቸው። ከዚህ ቀደም ይካሄዱ የነበሩ የስዕል አውደ-ርዕይዎች ያን ያህል ተመልካች የላቸውም። እየተንጠባጠበ የሚመጣ ጥቂት ተመልካችን እንደብርቅ መጠበቅ ተለመዶ ነበር። ሰውን ለምን ስዕል አታይም ስትለው “እኔጃ! አይገባኝም!” ነው የሚሰጥህ መልስ። በብዛት የስዕል ኤግዚቪሽኖች አካባቢ የማይጠፉት የስዕል ባለሙያዎችና ጥቂት የሚባሉ አድናቂዎች ብቻ ናቸው። እኔ ይህን ለመለወጥ ሳስብ አብዛኛው ሰው የሚያውቃቸውን ታዋቂ ሰዎች በመምረጥ ዘና የሚያደርግን መንፈስ መፍጠር አስቤ ነበር ተሳክቶልኛል።

ሰንደቅ፡- በአምስት ቀናት የአውደ-ርዕይው ቆይታ ወቅት የተመልካቹም ሆነ የስዕሎች ባለቤቶች ስሜት ምን ይመስል ነበር?

ቴዎድሮስ፡- በጣም የሚገርም ነበር። ብዙዎቹ ደስተኞች ነበሩ። በአምስቱ ቀናት ውስጥ የተመለከተውን ተመልካች ቁጥር ሪከርድ መዝጋቢ ቢኖር በስዕል አውደ-ርዕይ ታሪክ ትልቅ ይመስለኛል። ትዝ ይለኛል በሰልፍ ሁሉ የምናስገባበት ጊዜ ነበር። በተመለከቱት ነገር ተደንቀው የት ነበርክ እስካሁን የሚሉ ነበሩ። ቀጣይነቱ እንዳይቋረጥ የሚጠይቅህ ሰው አለ። ኤግዚቪሽኑን በተመለከተ ለታዋቂዎቹ ሰዎች አዲስ እንዳይሆን አስቀድሜ በአካል እያገኘሁ ሁሉንም አስረድቻቸው ነበር። ምክንያቱም ስዕል ኤግዚቪሽን አለ ኑ! ቢባል ማንም ሰው ላይመጣ ይችላል። ልዩ መሆኑንና አዲስ ነገር እንዳለው የውጪ ሰዎችን “ሳምፕል” እያሳየሁ አስረድቼያቸው ነበር። ስለዚህ የሆነ ነገር ጠብቀው እንዲመጡ አድርጌያቸዋለሁ። ነገር ግን ደግሞ የፈለገ ጠብቀኸውም ብትመጣ የራስህን ምስል ከአሁኑ በፊት አይተኸው በማታውቀው መልኩ እንደዛ ሆኖ ስታየው የሚሰማህ ስሜትህ በራሱ ጉጉትን ይፈጥር ነበር። የማልረሳው ሁሉም የራሱን ምስል በተመልካች መሀል ቆሞ አንድ በአንድ ሲከፍተው የሚፈነዳ ሳቅ ነበር። እሱ ስሜት አዲስ ነገር ነበር። ግን ሁሉም ተዝናንተውበታል፤ አድንቀዋልም። ምናልባት የውጪ ሀገር ልምድ ያላቸው ሰዎች ለምሳሌ እንደጋሽ ሙላቱ አስታጥቄ አይነት፣ “ፈረንጆች ሰርተው ያሳዩኝ ስራ ነበር። በሀገሬ ሰው እንዲህ አይነት ነገር ማየቴ በጣም ደስ ይለኛል” ብሎ እንደነበር አስታውሳለሁ። ከሁሉም ደግሞ የማልረሳው ኮሜዲያን ክበበው ገዳ ምስሉን ካየ በኋላ ተደንቆ ብዙ አጥንቶት ሲያበቃ ያኔ ወላቃ ጥርስ ነበረውና፣ ወደኔ ጠጋ ብሎ ወላቃውን ጥርሴን አለዋውጠኸዋል ቦታው ትክክል አይደለም በሚል አስቆኛል። (ሳቅ). . . ግን በአጠቃላይ ሁሉም ተመልካቹም ሆነ ታዋቂዎቹ ሰዎች ተዝናንተውበታል ማለት ይቻላል።

ሰንደቅ፡- ፕሮግራሙን ዓመታዊ ለማድረግ አስቸጋሪ የሆነው ለምንድነው?

ቴዎድሮስ፡- ሲጀመር በቋሚነት በዓመቱ ለማካሄድ ነበር በመሀል ሌሎች ስራዎች ስለነበሩ ሳይታሰብ ጊዜው ሄዶብኛል። አሁንም ግን ካሰብኩ ትንሽ ቆይቻለሁ፤ ካለፈው ኤግዚቪሽን በተሻለ መልኩ ለመስራት አስባለሁ። የሚመለከታቸው አካላት፤ የመንግስት ባለስልጣናትና ሚዲያው በደንብ የሚሳተፍበት እንዲሆን እፈልጋለሁ እንጂ አንድ ኤግዚቭሽን ተከፈተ፤ ተዘጋ እንዲባል ብቻ አልፈልግም። ይህን ለማድረግ ደግሞ ተባባሪዎች ያስፈልጋሉ፤ ጊዜ በጣም ይፈልጋል። በኛ ሀገር ለስዕል ሲባል ማንም መተባበር አይፈልግም። ተመልካች የለውም ተብሎ ስለሚታሰብ ደጋፊ ማግኘት ቀላል አይደለም። በርግጥ ደግሞ ከአራት ወራት በኋላ ከመጀመሪያው በደረጃ ከፍ ያለና አለማቀፋዊ ይዘት ያለው አውደ-ርዕይ ለማዘጋጀት እየሰራሁ ነው። ስለዚህ ሰፋ ብሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን ምስል ለሌላው ዓለም ማሳየት በሚችል መልኩ እየሰራን ነው። በዚህ ፕሮግራም ላይ ኤምባሲዎች ይሰተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ያም ሆኖ ግን ከዚህ በኋላ አመታዊነቱን በጠበቀ መልኩ እንዲካሄድ ነው ሃሳቤ።

ሰንደቅ፡- ከአንገት በላይ በሚሳል ምስል ውስጥ የግለሰብን ባህሪይ ማሳየት ይቻላል?ፈታኙ ነገርስ ምንድነው?

ቴዎድሮስ፡- ለምስል ካርቱን (Portrait Carton) የሰውን ባህሪይ መግለፅ በጣም ከባድ ነገር ነው። ብዙ ተማሪዎች ከስዕል ትምህርት ቤት የሚሸሹበት አንዱ ምክንያት ይህ ይመስለኛል። አንድን ሰው ከአንገት በላይ ምስል ተጠቅመህ ክፉ ሰው ወይም የዋህ ሰው አድርገህ ሳል ልትባል ትችላለህ። ይህ ለብዙዎች በጣም ፈታኝ ነው። ካርቱን ሲሆን እንደውም ትንሽ ይቀላል። ምክንያቱም ለፈጠራ ክፍት ስለሆነ ማለቴ ነው። ሌላው ፈታኙ ነገር የታዋቂ ሰዎችን ምስል በካርቱን ፖርትሬት ስታስቀምጥ ተመልካቹ ምስላቸውን አይቶ በቀላሉ “እገሌ ነው” ሊልህ መቻል አለበት። ይህ ካልሆነ ግን በትክክል አላመጣኸውም ማለት ይሆናል።

ሰንደቅ፡- ከሰዓሊነትህ በተጨማሪ የምትሰራቸው ስራዎች እንዳሉ ሰምቻለሁ እስቲ አጫውተኝ?

ቴዎድሮስ፡- በስዕል ሙያ “ማስተር” ላድርግ እንጂ ሌሎች ስራዎችንም እሰራለሁ። ለምሳሌ በፊልም ዳይሬክቲንግ ተምሬ እየሰራሁ ነው። በስነ-ልቦና ማማከር ረገድ ስልጠናዎችን እየሰጠሁ ነው። ስፖርት ላይ በማርሻል አርት ስፖርት አመራር ነኝ። ከነዚህ ስራዎች ጋር እንግዲህ በጋዜጣና በመፅሄት ያለን ተሳትፎም ይቀጥላል ማለት ነው።

ሰንደቅ፡- ከስራህ ውጪ በምን ትዝናናለህ?

ቴዎድሮስ፡- አነባለሁ፤ ብዙ ጊዜ ፊልም አያለሁ፤ የፊልም ባለሙያም እንደመሆኔ ፊልም ያዝናናኛል። በነገራችን ላይ ብዙም አልታየም እንጂ “በራድ ፍም” የተሰኘ ፊልም ሰርተን ነበር። አሁንም በመሰራት ላይ ያለ ፊልም አለ።

ሰንደቅ፡- ከአራት ወር በኋላ ለዕይታ ከሚበቃው የስዕል ዓውደ ርዕይ በተጨማሪ ወደፊት ምን ልትሰራ አስበሃል?

ቴዎድሮስ፡- እንደነገርኩህ ከስዕል ስራዬ ጎን ለጎን ልሰራው እየተዘጋጀሁበት ያለ ፊልም አለ። እርሱን እሰራለሁ። በግራፊክስ ዲዛይን ስራም መበርታት እፈልጋለሁ። በቀጣይ ደግሞ ለህፃናት ማስተማሪያ ይሆናሉ ብዬ ያዘጋጀኋቸው መፅሀፍት አሉ፤ አጠር አጠር ያሉ ታሪኮችና ስዕሎች ያሉባቸው መፅሐፍት ናቸው። ከሞላ ጎደል አንድ ሁለቱ አልቀዋል ተከታታይ ክፍሎች ናቸው፤ ሶስት ያህል ይቀራሉ። በሚቀጥለው አመት ላይ ታትመው አንድ ጊዜ የሚወጡ ይሆናል።

ሰንደቅ፡- ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።

ቴዎድሮስ፡- እኔም ስለተሰጠኝ እድል አመሰግናለሁ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
11253 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us