“ፊልም ራሴን የምገልፅበት ጥበብ ነው”

Wednesday, 20 September 2017 14:01

“ፊልም ራሴን የምገልፅበት ጥበብ ነው”

ሰውመሆን ይስማው (ሶሚክ)

ዳይሬክተርና ሲኒማቶግራፈር

 

 

Entertanmentወጣት የፊልም ባለሙያ ሰውመሆን ይስማው በዳይሬክቲንግ የሠራቸው ፊልሞች፣ የፀሐይ መውጫ ልጆች፣ ዓለሜ፣ እንዲሁም “8፡62”ን ጨምሮ ሦስት ለዕይታ ያልበቁ ሥራዎቹ ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ ያ-ልጅ፣ ፔንዱለም፣ ሲቲ ቦይዝ፣ ኦፕሬሽን አክሱም፣ ባለገሩ፣ አዲናስ፣ ቀሚስ የለበስኩ’ለት፣ የፀሐይ መውጫ ልጆችና ዓለሜ የተሰኙትን ፊልሞች ጨምሮ በኦሮምኛ ቋንቋ የተሰራውን “ዋዳ” የሲኒማቶግራፊ ችሎታውን ይሳየባቸው ስራዎቹ ናቸው። በሙዚቃ ክሊፕ ደግሞ “ጥቁር ሰው” እና  “ማር እስከጧፍ” በተሠኙት የቴዲ አፍሮ ሥራዎች ላይ በረዳት ዳይሬክተርነት እና በሁለተኛው ደግሞ በሲኒማቶግራፊው ዘርፍ አቅሙን አሳይቶባቸዋል። እዚህ ላይ “ቀሚስ የለበስኩ’ለት” እና “ዓለሜ” በተሰኙት ፊልሞች ለተከታታይ ሁለት ዓመታት የጉማ ፊልም ፌስቲቫል በሲኒማቶግራፊው ዘርፍ ባሳየው ድንቅ ችሎታ ተሸላሚ መሆኑም ይታወሳል።

 

 

አሁን ደግሞ በቅርቡ ለዕይታ የሚበቃውንና በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረተውን “እውር አሞራ ቀላቢ” የተሠኘ ፊልም ዳይሬክት አድርጐ አቅርቧል። ከወጣቱ ዳይሬክተርና ሲኒማቶግራፈር ሰውመሆን ይስማው (ሶሚክ) ጋር ያደረግነውን አጭር ቆይታ እነሆ፡-

 

ሰንደቅ፡- እስካሁን ከሰራሃቸው ፊልሞች ጋር ሲነፃፀር በቅርቡ ለዕይታ የሚበቃውና በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተው “እውር አሞራ ቀላቢ” የተሠኘው ፊልም በምን ይለያል?

ሰውመሆን፡- የመጀመሪያው ነገር በዘውጉ የተለየ ነው። “ዶክመንተሪ ድራማ” የተሠኘ ለኔ አዲስ የሆነ ዘውግ የሞከርኩበት ሥራ ነው። እውነተኛ ክስተቶችና የፈጠራ ድራማዎች በፊልሙ ውስጥ በውህደት ለማሳየት ሞክረናል። በፊልሙ ውስጥ ዋናው ባለታሪክ ያለፈበትን የህይወት ውጣ ውረድ በምልሰት መልክ የሚተርክበትን አካሄድ ተከትለን የሰራነው ፊልም ነው።

 

ሰንደቅ፡-በ“እውር አሞራ ቀላቢ” ፊልም ውስጥ የተጠቀምከው የሲኒማቶግራፊ በእጅጉ መሳጭ ነው። እንደባለሙያ አንዳንድ ትዕይንቶችን (Scene) ለመቅረፅ ያስቀመጣችሁት የቆየ ፊልም ነበረ ማለት ይቻላል?

ሰውመሆን፡-­­ እውነቱን ለመናገር የሳሲሳ ፊልም ፕሮዳክሽን በአጠቃላይ ለፍቶበታል። በተለይ ረዳት “ካሜራ ማኔ” በጣም ብዙ ነገር አግዞኛል ማለት እችላለሁ። ከዚያ ውጪ በምናብህ የምትስለውን ነገር ወደሚታይ ነገር ለማምጣት ብዙ ተጉዘናል። በረሃውን ማንሳት እንችላለን። በፊልሙ ውስጥ ያለውን ባቡር ለመቅረፅ እስከ ጅቡቲ ሄደናል። ባለታሪኩ የረገጣቸውን ቦታዎችና የተጓዘባቸውን መስመሮች እንደነበሩ ለማሳየት ብዙ መስዋዕትነት ከፍለናል ማለት እችላለሁ።

 

ሰንደቅ፡- ይህ አዲሱ ፊልምህ በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረተ እንደመሆኑ መጠን፤ ወደ ፊቸር ፊልም የሰዓት ገደብ ለማምጣት ሲባል ብዙ ቀርፃችሁ በኋላ ቆርጣችሁ ያስቀራችሁት ትዕይንት ይኖራል ማለት እንችላለን?

ሰውመሆን፡- እውነትህን ነው። በጣም የሚገርሙ ጠንካራ ትዕይንቶችን (Scene) ቆርጠን ለማውጣት ተገደናል። ፊልም ስትሰራ ማለት የምትፈልገውን ነገር መድረሱ ላይ ታተኩራለህ። ከዚያ ውጪ ግን ብዙ ገንዘብ ያወጣህበት ትዕይንት ቢሆን እንኳን ቆርጠህ ልታስወጣ የምትችልበት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል። በዚህም ፊልም ብዙም ባይሆን ቆርጠን ያወጣናቸው ትዕይንቶች አሉ። ያ ማለት ግን ፊልሙ ሙሉ  ለማለት አይደለም።

 

ሰንደቅ፡- በስራዎችህ ውስጥ ደጋግመን የምንመለከታቸው ነገሮች አሉ። ለምሳሌ የቀደመ (ቆየት) ያለ ታሪክ ያለው ፊልም እና ወታደር ገፀ-ባህሪያት ትደጋግማለህ። ለምን ይሆን?

ሰውመሆን፡- (ሳቅ) ወታደር በጣም ነው የምወደው። ግን “የፀሐይ መውጫ ልጆች”፣ “ዓለሜ” እና በቅርቡ የሚወጣ ፊልሜም ውስጥ ባይገርምህ ወታደር ገፀ-ባህሪ አለበት። ወደኋላ ብዙም ርቄ የሠራሁት ፊልም የለም፤ ነገር ግን እንዳልከው “ታሪክ ተናጋሪ” ነኝ ብዬ አስባለሁ። እንደፊልም ባለሙያነቴ በምሰራው ፊልም ውስጥ አንዳች ታሪክ ለተመልካቹ ቢደርስ እመርጣለሁ።  

 

ሰንደቅ፡- እስካሁን በዳይሬክቲንግም ሆነ በሲኒማቶግራፊው ዘርፍ ከሰራሃቸው ሥራዎች በመነሳት ፊልም ላንተ ምንድነው?

ሰውመሆን፡- ፊልም ለኔ ራሴን የምገልፅበት ጥበብ ነው። ሀሳቤን፣ ፍልስፍናዬን የምገልፅበት መሣሪያ ነው ብዬ አምናለሁ። እኔ በግሌ የምመኛቸው ነገሮች በሰራዋቸው ፊልሞች ውስጥ አሉ ብዬ አምናለሁ። ፊልም ሰሪ የሆንኩትም በጣም መናገር የምፈልጋቸውን ታሪኮችን ለማጉላት ነው። ገና ያልተናገርኳቸውም ብዙ ነገሮች አሉ።

 

ሰንደቅ፡-የፊልም ባለሙያነትህን ብቻ ሳይሆን ያለህን እምቅ አቅም ጭምር ሰዎች ተረድተውልኛል ብለህ ታስባለህ?

ሰውመሆን፡- እሱን የሚመሠክሩት ሥራዎቼ ናቸው። እኔ ያንን በእርግጠኝነት መናገር አልችልም። ነገር ግን ፊልም መሥራት የሚፈልጉ ሰዎች ሥራዎቻቸውን ይዘው ወደኔ ሲመጡ ሳይ በተወሰነ መልኩም ሰዎች አቅሜን እየተረዱት መጥተዋል ብዬ አስባለሁ። ለምሳሌ በ“እውር አሞራ ቀላቢ” ፊልም ምክንያት ሁለት ሰዎች ታሪካቸውን በፊልም መልክ እንድሰራላቸው ፍላጐታቸውን ገልፀውልኛል። አንደኛው ኒውዮርክ ላይ ፊልሙ ሲመረቅ አይቶ የራሱን የጉዲፈቻ ታሪክ በፊልም እንድሰራለት ጠይቆኛል። ሌላውም እንዲሁ አሜሪካን አገር የሚኖር ነው የእሱም ታሪክ ወደፊልም እንዲቀየር ተነጋግረናል። ይህ ማለት ሰዎች አቅሜን እያዩ መምጣት ጀምረዋል ማለት ይመስለኛል።

 

ሰንደቅ፡- ከ“እውር አሞራ ቀላቢ” ፊልም ደራሲና ባለታሪኩ ከዘካሪያስ ጥበቡ መስፍን ጋር እንዴት ተገናኛችሁ?

ሰውመሆን፡- ከዘካሪያስ ጋር ያገናኘችን ብርቱካን በፍቃዱ ናት። ከእርሷ ጋር “አዲናስ” እና “ሲቲ ቦይዝ” የተሰኘ ፊልም ሰርተናል። ዘካሪያስ ታሪኩን ፊልም ማድረግ እንደሚፈልግ ሲነግራት ቀጥታ ወደኔ ነበር የላከችው። ያለችው ቀን ደወለልኝ፤ ተገናኝተን አወራን፤ ታሪኩ መሳጭ ስለነበር ለመስራት ሙሉ ፍቃዴን ገለፅኩለት፤ መስራት ጀመርን ማለት ነው።

 

ሰንደቅ፡- በተቀነጨበው ፊልም ውስጥ የምናየው የዘካሪያስ ገፀ-ባህሪይ ህይወቱ አሳዛኝ ነው። ገፀ-ባህሪውን እና ዘካሪያስን እንዴት መግለፅ ይቻላል - እንደ ዳይሬክተር ስታየው?

Entertanment2ሰውመሆን፡- ዘካሪያስ የሚገርምና ጠንካራ ልጅ ነው። የፅሁፍ ችሎታና ልምድ ባይኖረውም ሀሳቡን በትክክል መግለፅ የሚችል ሰው ሆኖ አግኝቼዋለሁ። በስራ ሂደት ብዙ ጊዜ ተጋጭተናል። እሱ የሚፈልገው ነገር አለ፤ እኔም የምፈልገው ነገር አለ ስለዚህ ግጭት አይጠፋም። ከቀረፃ በኋላም ይሄ ይቆረጥ፣ ይሄኛው ይቀጥል ስንባባል ብዙ ተጨቃጭቀናል። ግን ለጥሩ ስራ ሲባል የሆነ ነገር እንጂ በፀባይ ለክፉ የሚሰጥ ልጅ አይደለም። በስራው ሂደት ያሳየውን ትዕግስትና ውጣ ውረድ በተመለከተ በጣም ነው የማደንቀው።

 

ሰንደቅ፡- እስቲ ደግሞ ስለ ቴዲ አፍሮ “ጥቁር ሰው” እና በቅርቡ ስለወጣው “ማር እስከ ጧፍ” ስራዎች ላይ ስለነበረህ ሚና ንገረኝ።

ሰውመሆን፡- የመጀመሪያው ማለትም “ጥቁር ሰው” ላይ ረዳት ዳይሬክተር ነበርኩ። የተሰራው በሳቢሳ ፊልም ፕሮዳክሽን ነበር። ብዙ ትግልና ብዙ ፈተና የነበረበት ስራ ነው። ግን ደግሞ አሪፍ ፕሮዳክሽን ያሳየንበት ስራ ነበር ማለት እችላለሁ። አሁን በቅርብ በወጣው “ማር እስከ ጧፍ” ስራ ላይ ግን የተሰራው በአምለሰት ፊልም ፕሮዳክሽን በኩል ስለነበር እኔ እንደ ሲኒማቶግራፈር ነው የተቀላቀልኩት። ካሜራውን የሰራሁት እኔ ነኝ። ደብረማርቆስና ደብረሊባኖስ አካባቢ ተገኝተን ለክሊፑ የሚሆን ቀረፃ ሰርተናል። በስተመጨረሻ ሥራው ወጥቶ ሳየው የቴዲ፣ የአምለሰት፣ የያሬድ ሹመቴ እና የቡድኑ ጥምረት በአሪፍ መልኩ የታየበት ነው ማለት እችላለሁ። ተመልካቹም በጣም የተረዳን ይመስለኛል። አስተያየቶቹን ለማህበራዊ ሚዲያዎች ስመለከት በጥልቀት የሚመለከቱ ሰዎች እንዳሉ አይቼ ተገርሜያለሁ።

 

ሰንደቅ፡- በምታገኘው ክፍት ጊዜ ውስጥ ምን ያዝናናሃል?

ሰውመሆን፡- እኔን የሚያዝናናኝ ፊልም ማየትም መስራትም ነው። ወደፊትም ቢሆን ፊልምን በመስራት፤ ታሪክ በመናገርና የሰዎችን የፊልም ስራ በማየት መስራቴንም መዝናናቴንም እንደምቀጥል ነው የማስበው።¾

Last modified on Wednesday, 20 September 2017 17:28
ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
15765 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 914 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us