የፖርትሬት ካርቱን እና ዝነኞቹ ፊቶች

Thursday, 28 September 2017 14:28

 

የመዝናኛው አለም ሰዎችን፣ ታዋቂና አንጋፋ ስመ ጥር ባለሙያዎችን ያካተተ የሥዕል ሥራዎችን “በፖርትሬት ካርቱን” የአሳሳል ስልት ከፍ ባለ መልክ ያስተዋወቀ ባለሙያ ነው። ሰዓሊ (ካርቱኒስት) ቴዎድሮስ መስፍን (ቴዲማን). . . በያዝነው ወር መጀመሪያ ለአራተኛ ጊዜ የፖርትሬት ካርቱን አውደ ርዕይ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በካፒታል ሆቴል የተከፈተ ሲሆን፤ የ38 ታዋቂ ሰዎችን ፊት የሚያሳዩ የፖርትሬት ካርቱን ስራዎች በ28 ፍሬሞች ተዘጋጅተው ካሳለፍነው መስከረም 7 እስከ 14 ቀን 2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር አርት ጋለሪ ለዕይታ በቅተዋል። በዚህም ከ2ሺህ በላይ የሥዕል አድናቂዎች ተገኝተው ስራዎቹን ተመልክተዋቸዋል።

ግለኝነት እየተስፋፋ በመጣበት በአሁኑ ሰዓት የአውደ-ርዕይውን መጠሪያ “ቤተሰብ ለጥበብ” ሲል ሰይሞ በርካቶችን አሰባስቧል። “ፕሮግራሙን ያሰብኩት አብሮነትን ለመስበክ በሚል ነው” የሚለው ቴዎድሮስ፤ እንደከዚህ ቀደሙም ባይሆን ያሥዕል ተመልካቾች መጥተው በቀረቡት ሥራዎች ተዝናንተው ተመልሰዋል ይላል። ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ምክንያቱን አስቀምጧል።

በመክፈቻው ዕለት አንጋፋና ወጣት አርቲስቶች፣ አትሌቶችና ፀሐፊያን ነበሩ። ከእነዚህም መካከል አርቲስት ፍቃዱ ተ/ማርያም፣ ግሩም ኤርሚያስ፣ ሰለሞን ቦጋለ፣ ፀሐፊና መሃንዲስ ሚካኤል ሽፈራሁ፣ ወግ አዋቂው በኃይሉ ገ/መድህን እና አትሌት ገ/እግዚአብሔር ገ/ማርያም ተጠቃሾች ናቸው።

የፖርትሬት ካርቱን ሥራዎችን ለህዝብ ማቅረብ ከጀመረ ከሰባት ዓመታት በላይ ቢሆንም ዘንድሮ ለዕይታ የበቃው ለአራተኛ ጊዜ መሆኑን ሰምተናል። ለዚህም እንደምክንያት የቀረበው ሰዓሊው በራሱ አቅም ያለአንዳች ድጋፍ እየሰራ መቆየቱ አስታውቆ፤ ሥነ-ጥበቡን የሚደግፉት አካላት ብዙ መስራት ይጠበቅባቸዋል ሲል ምክንያቱን ያስረዳል። በቀጣይም የሥዕል አውደ-ርዕይዎችን የሚደግፉ አካላትና ተቋማት እንደሚያስፈልጉ ሰዓሊ ቴዎድሮስ (ቴዲማን) ይናገራል። “መሰል የሥዕል አውደ-ርዕይዎች ደጋፊ ቢያገኙ በቋሚነት በወር አልያም በዓመት ፌስቲቫል አይነት ዝግጅት ፈጥሮ በርካታ ተመልካቾችን የምንሰበስብበት ይሆናል” ይላል።

ሥራዎቹን በአገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማሳየት ሀሳቡ ያለው አርቲስት ቴዲማን፤ በዚህ ዓመት በአገር ውስጥ ወደመቀሌ ተጉዞ አወደ-ርዕይ ለማሳየት ጥሪ ካደረጉለት አካላት ጋር ተነጋግሮ በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታውቋል። በቀጣይም የተለያዩ ቦታዎችና ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ስራዎቹ ይቀርባሉ ተብሏል።

“የፖርትሬት ካርቱን” ባህሪያት ከሚባሉት ውስጥ የታዋቂ ሰዎች የፊት ገጽ ዋነኛ ትኩረቱ መሆኑን የሚያስረዳው ቴዲማን፤ ለዚህም ከጋዜጣ ርዕስ አንቀፅ ውጪ ያሉት ስራዎች በሙሉ ትኩረታቸው የዝነኞች ፊት እንደሆነ በአፅንኦት ያስረዳል። ያም ሆኖ ዘንድሮ በብሔራዊ ቴአትር አርት ጋለሪ ከቀረቡት ሥራዎች መካከል ሃሳብና ትርጉም የሚሰጡ ሥራዎች ተካተው መቅረባቸውንም ያስታውሳል። እንደምሳሌም ሃሳብ ላይ አተኩረው የሚሰሩ የርዕስ አንቀጽ የካርቱን ሥራዎችን ለልዩነቱ ማሳያ አድርጎ ማቅረብ ይቻላል የሚለው ቴዲማን፤ በዚህም ሂደት የፖርትሬት ካርቱን ሥራዎች ወደማዝናናቱ ሲያተኩሩ፤ በአንጻሩ ደግሞ የርዕሰ አንቀጽ የካርቱን ሥራዎች ሃሳብ ላይ ያተኩራሉ ሲል ይገልፃቸዋል።

ሰዓሊ ቴዎድሮስ መስፍን (ቴዲማን) ሥራዎቹን ለአደባባይ ማብቃት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከመቶ አስር ያላነሱ የአገራችንን ታዋቂ ሰዎች ምስል አዝናኝ በሆነው የፖርትሬት ካርቱን ስልት ሰርቶ ለዕይታ ማብቃቱን ይናገራል። በርካቶች የራሳቸውን ምስል ሲመለከቱ የሚሰማቸው የመደነቅ ስሜት እንዳሉ ሁሉ፤ ምናልባት የአሳሳል ስልቱን ካለመረዳት ገጽታችንን አበላሸህብን የሚሉ ሰዎች አላጋጠሙህም ወይ ብለን ጠይቀነው ነበር። “ፊት ለፊት ለምን እንደዚህ አድርገህ ሰራኸኝ ያለኝ ሰው አጋጥሞኝ አያውቅም። ነገር ግን እንደቀልድም ቢሆን “ጉማሬ አስመሰልከኝ፣ የተለየ ፍጥረት አስመሰልከኝ” የሚሉ አስተያየቶች አሉ” ብሎናል።

በፖርትሬት ካርቱን የአሳሳል ስልት ውስጥ የሰዎች የፊት ገጽ ዋናው ማዕከል ነው።  ከፊት ገጻቸውም በጉልህ የሚተኮርበትና የሚጋነን አካል ይኖራል። ይህ አሳሳል ምንን ተመስርቶ የሚሰራ ነው? ያደጉት አገራት ያሉ የፖርትሬት ካርቱን ሰዓሊያን የአንድን ግለሰብ የተለየ ባህሪን መሠረት አድርገው ሁሉ ሊሰሩ ይችላሉ የሚለው ቴዲማን፤ አሁን ላይ እሱ እየሰራ ያለው ግን የሚታየው የፊት ገጽታ (አካላዊ ቅርፅ) ላይ ብቻ መሠረት በማድረግ እንደሆነ ያስረዳል። “እኔ የአንድን ታዋቂ ሰው የፊት ገፅ ለመሳል ስነሳ የመጀመሪያ የምመለከተው ነገር ሰውዬው ፊት ላይ የተለየና በጉልህ የሚታይ ነገር አለው ወይ?” የሚል ይሆናል። ከዚያም በአሳሳል ያንን የሰውዬውን መለያ አጋነን እናቀርበዋለን” ይላል። እንደምሳሌም ሲያስረዳ አንድ ሰው አይኑ ትላልቅ ከሆነ ወይም ጆሮው፣ አልያም አፍንጫው ሊሆን ይችላል በጉልህ የሚታወቅበትን የፊት ክፍል በይበልጥ በማጋነን ስታቀርበው ነው ፖርትሬት ካርቱን የሚባለው ሲል ስለአሰራሩ ይዘረዝራል። በዚህ አሳሳል ስልት ውስጥ ከ50 እስከ 60 በመቶ የሚሆነው የትክክለኛ ሰውነቱ ቅርፅ ቀርቶ፤ ነገር ግን ገኖ የሚወጣው እንዲታይ ያደርጋል ሲል ያስረዳል።

ይህ የፖርትሬት ካርቱን የአሳሳል ዘይቤ በስነ ጥበብ ትምህርት ቤቶች አካባቢ ያን ያህል ትኩረት የተሰጠው አይደለም የሚለው ቴዲማን፤ በርካታ ፍላጎት ያላቸው ወጣቶች ቢኖሩም የሚያስተምራቸውና የሚያበረታታቸው አካባቢን ግን የለም ሲል በቁጭት ይናገራል። ይህንን የአሳሳል ስልት በማስተዋወቅና የመገናኛ ብዙሃንም ትኩረት እንደሰጡት በማድረግ የዛሬ ሰባት አመት ሲጀምረው ለብዙዎች መነቃቃት እንዲፈጠርም ያስታውሳል። በዚህም መነሻነት ትምህርቱን ለመማር የሚፈልጉ ወጣቶች መበራከታቸውን ተከትሎ ተፈሪ መኮንን ሙያና ቴክኒክ ትምህርት ቤት የሥነ-ጥበብ ክፍሉ አንድ ዘርፍ አድርጎ ጀምሮት እንደነበረ የሚያስታውሰው ቴዲማን፤ በኃይሉ ከተባለ የካርቱን አሳሳል መምህር ጋር አንድ ሁለቴም ተማሪዎቹ ፊት ቀርቦ “ስለ ፖርትሬት ካርቱን” ገለፃ አድርጎ እንደነበር ይናገራል። ከዚያ በኋላ መቀዛቀዞች መታያታቸውን በመጠቆም አሁን ላይ የአሳሳል ስልቱን የሚያስተምር ትምህርት ቤት አለመኖሩን ይናገራል።

የፖርትሬት ካርቱን ስራዎችን መማር የሚፈልጉ ወጣቶች መኖራቸውን ከአሁን አውደ-ርዕይ በኋላም ጥያቄ የሚያቀርቡለትና እየመጡ እንደሚያናግሩት የገለፀው ቴዲማን፤ ሁኔታዎች ከተመቻቹ በግሉ ያለውን ልምድ ለማካፈልና ለማስተማር ዝግጁ መሆኑንም ይገልጻል። ያም ሆኖ ግን ለጥበቡ የሚሰጠው ግምትና ዋጋ ዝቅተኛ መሆኑ እንዲሁም የአሳሳል ዘዴውን የቀሰሙ ወጣቶችም በቀጣይ የሚገጥማቸው የሥራ አካባቢ በግልጽ አለመኖሩ ተስፋ የሚያስቆርጣቸው ይመስለኛል ሲል ተግዳሮቶቹን ያመለክታል። ይህ የፖርትሬት ካርቱን አውደ-ርዕይ ደጋፊ አካላትን አግኝቶ ቢቻል ወርሃዊ የመመልከቻ አጋጣሚዎች አሊያም ደግሞ በቋሚነት ከአንድ አመት ውስጥ አንድ ሳምንቱን ለሥዕል ጥበቡ አፍቃሪያን ዕይታ የማቅረብ አጋጣሚው ቢመቻች ከማዝናኛነቱም ባለፈ የሥራውን ዋጋ እንድናይ ያግዘናልና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ያድርጉበት እንላለን።   

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
15740 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 886 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us