“አመፀኛው ክልስ” ወደፊልም ሲመለስ

Wednesday, 04 October 2017 12:46

 

“ብዙዎች ህይወትን ይኖሯታል እንጂ አይገልጿትም። የኖርኩትን ህይወት ለዚህች መፅሐፌ ለመግለፅ ስሞክር የዝብርቅርቁና ዥንጉርጉሩ የህይወት ማንነት አይነተኛ መስታወት እንደሆነ በማመን ነው።” ይለናል - የአመፀኛው ክልስ መፅሐፍ ደራሲና “The Bastard” የተሰኘው ፊልም ላይ የግል ህይወቱን የተወነው ዳንኤል ሁክ - በመፅሐፉ መግቢያ ላይ ባሰፈረው ሀተታ።

 

“አመፀኛው ክልስ” በ2005 ዓ.ም ለንባብ ከበቃ በኋላ ለስድስተኛ ጊዜ ተደጋግሞ በመታተም በርካቶች ያነበቡት መፅሐፍ ነው። የመፅሐፉን መውጣት ተከትሎ በርካቶች አንብበውት የታሪኩ ፍሰት የፊልም ያህል ነው ሲሉም ከዚህ ቀደም በሚውዚክ ሜይ ደይ የመፅሐፍ ውይይት መድረክ ላይ ሰምተናል። መፅሐፉ የ47 ዓመቱን ጎልማሳ ዳንኤል ሁክ ውጣ ውረድ የሚተርክ መሳጭ ታሪክ ነው። ከአመታት በኋላ ይህንን አስገራሚ የህይወት ጉዞ በፊልም ለመስራት ያቀደው ሆላንዳዊው ዳይሬክተርና ፕሮዲዩሰር ሚስተር ፍሎረንስ ያንስ ቫሊዩ በቅርቡ ለዕይታ ሊያበቃው መዘጋጀቱን ሰምተናል።

 

የመፅሐፉን ይዘት የተመለከተው የኔዘርላንድ መንግስት ምንም እንኳን የኔዘርላንድ “ደም” ያለው ቢሆንም ባለታሪኩ በመፅሐፉ ያሰፈራቸውን ምስጢር ገላጭ ሀሳቦች ተመልክቶ ወደሀገሩ እንዳይገባ በሚል እንዳባረረውም ይገልፃል። በተለይም በደች ቋንቋ ከሚታተመውና ከማሠራጫው “M” የተሠኘ የፋሽን መፅሔት ባልተለመደ መልኩ የዳንኤል ሁክን እና የቤተሰቡን አስገራሚ ታሪክ በፊት ገፁ ጭምር በማውጣት ሽፋን ሰጥቶታል። ከዚህም ባለፈ በበርካታ የመገናኛ ብዙሃን ዘንድ ታሪኩ ትኩረት ስቦም እንደነበር በመፅሐፉ ተገልጿል።

 

በደች እና በቤልጂየም የፊልም ባለሙያዎች የተሠራውና ሙሉ ቀረፃው በኢትዮጵያ የተካሄደው ይህ ፊልም በቅርቡ በዓለም አቀፍ ፊልም ፌስቲቫል ላይ ተሳትፎ ሲያበቃ ለመላው ዓለም ተመልካቾች ለዕይታ እንደሚበቃም፤ ባለፈው ቅዳሜ መስከረም 20 ቀን 2010 ዓ.ም የፊልሙ ዳይሬክተርና ባለታሪኩ ዳንኤል ሁክ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ጠቁመዋል።

 

ሙሉ በሙሉ የባለታሪኩ የዳንኤል ሁክን ትወና ይዞ ያሳለፋቸውን ውጣ ውረዶች የሚያሳየው ይህ ፊልም አንድ ሰዓት ከ38 ደቂቃ እንደሚሸፍን ታውቋል። በሰው መግደል ወንጀል ተይዞ በእስር ቤት ከአስር ዓመታት በላይ ያሳለፈው ዳንኤል ሁክ፤ በይቅርታ ከእስር ወጥቶ ኔዘርላንድ ድረስ አባቱን ፍለጋ የተጓዘበትን ውጣ ውረድ ፊልሙ ይተርካል። በጋዜጣ መግለጫው ወቅትም “ምህረት ያደረጉልኝ የመንግስት አባላትን አመሠግናለሁ” ያለው ዳንኤል፤ “በተለይም በንዴት ተነሳስቼ በኔ ምክንያት በደል ለደረሰባቸው ሰዎች (ቤተሠቦች) ሁሉ በሙሉ ልባዊ ይቅርታን እጠይቃለሁ” ሲል ተደምጧል።

 

“ዳንኤል በእጅጉ አስደናቂ ሰው ነው” በማለት ንግግሩን የጀመሩት የፊልሙ ዳይሬክተርና ፕሮዲዩሰር ሚስተር ፍሎረንስ፤ ይህን መፅሐፍ ወደፊልም በመቀየር ከሦስት ዓመት በላይ መልፋታቸውንም ይጠቁማሉ። በርግጥም ይህንን ውስብስብ ታሪክ የያዘ መፅሐፍ ለመስራት ፈታኝ እንደነበር የሚናገረው የፊልሙ ፕሮዲዩሰርና ዳይሬክተር፤ ፊልሙን ለመስራት የተነሳሳበትን ምክንያት ሲናገርም “2007 (እ.ኤ.አ) የዳንኤልን ታሪክ በጋዜጣ ላይ ካነበብኩ በኋላ ታሪኩን በፊልም ልሰራው እንደሚገባ አሰብኩ” ይላል። “በመገናኛ ብዙሃን የባለታሪኩ ስም እየገነነ በመጣበት ወቅት እርሱ ግን በእስር ቤት እንደነበርም አስታውሷል። “The Forgotten Netherlands” የተሰኘውን መፅሐፍ ገፅ-በገፅ ባነበብኩ ቁጥር ነገርዬው ፊልም እንጂ የእውነት አይመስለኝም ነበር” የሚለው ሚስተር ፍሎረንስ፤ መደነቄን በፊልም ለሌሎች ለማሳየት ተነሳው ባይ ነው።

 

ፊልሙን ለመስራት ወደ ኢትዮጵያ በመጣበት ወቅት ባለታሪኩ ዳንኤል ደጋግሞ ስለኔዘርላንዳዊው አባቱ ይናገር እንደነበር የሚያስታውሰው ሚስተር ፍሎረንስ፤ በፊልሙ ውስጥ አባትየው መታየት እንዳለበት አምነን ፍለጋውን ጀመርን ይላል። እናም ሆላንድ ውስጥ በሚገኘው በዳንኤል ወንድም በሚካኤል ሁክ አማካኝነት አባትየውን ለማግኘት ሙከራ አደረጉ። ነገር ግን ወንድምየው በመፅሐፉ ጭምር በእጅጉ ተናዶ ስለነበር ፊልሙንም በተመለከተ ምንም አይነት ንክኪ እንዲኖረው እንደማይፈልግ በመግለፅ “ተቃወመን” ይላል። ከዚያም በቀጥታ ለዳንኤል አባት ለሚስተር ሁክ ደብዳቤ መፅፉን የሚናገረው ሚስተር ፍሎረንስ፤ “አንድ የተረዳሁት ምስጢር ግን ልጁን የከዳው ሚስተር ሁክ እርሱም በልጅነቱ በአባቱ የመከዳት አጋጣሚ የነበረው መሆኑን መረዳቴ ነበር” ይላል። “እናም በፊልሙ ውስጥ ማንነታችንን የሚቀበሉን ሰዎች ማግኘት ምን ያህል ዋጋ እንዳለው ለማሳየት ሞክሬያለሁ” ይላል።

 

“በዳንኤል ሁክ መፅሐፍ ላይ ተመስርቶ የተሰራው ፊልም ሲመረቅ ለዓለም የማሳየው የአንድን ኢትዮጵያዊ ታሪክ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም አስቸጋሪ ህይወት ውስጥ ያለ ሰው አንድ ቀን ከችግሩ ተላቆ በነፃነት እንደሚቆም ጭምር ነው። ለዚህም የዳንኤልን ከሞት ፍርድ መትረፍ የሚያሳይ ታሪክ መመልከት በቂ ነው ሲል ምስክርነቱን ሰጥቷል። ይህን ፊልም ለመስራት ተግዳሮት የነበረውን ነገር በተመለከተ ተጠይቆ ሚስተር ፍሎረንስ ሲመልስ፣ ዳንኤል በጣም አስቸግሮኛል” ሲል ብዙዎችን ፈገግ ያሰኘ መላሽ ሰጥቷል። ከዚህ ባለፈ ግን አባትዬው ሚስተር ሁክን አሳምኖ በዘጋቢ ፊልሙ ውስጥ እንዲሳተፉ ለማድረግ ራሱን የቻለ ፈተና እነደነበርም ጠቁመዋል።

 

በቀጣይም ከደቡብ ኮርያ አካባቢ የተነሳና በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረተ ፊልም ለመስራት በዝግጅት ላይ መሆኑን የሚናገረው ሚስተር ፍሎረንስ፤ አሁን ላይ ከአስራ ስምንት ያላነሱ ፊልሞችን የሰራው ፕሮዲዩሰርና ዳይሬክተር ሚስተር ፍሎረንስ ቀደም ብሎ በጋዜጠኝነት ሙያ ላይ ተሰማርቶ ይሰራ እንደነበርም ሰምተናል። የፊልሙ ፕሮዲዩሰርና ዳይሬክተር ሚስተር ፍሎሬስ ያንስ ቫን የሚከተለው ማስታወሻ በ“አመፀኛው ክልስ” መፅሐፍ ድህረ-ታሪክ ውስጥ እንደሚከተለው ሰፍሮ ይነበባል፤ “ፍሎሬስ ወደፊልም ስራ የገባው በውስጡ ያለውን የፊልም ስራ ጥበብ ፍቅር ምላሽ በመስጠት በሚገጥሙት ምርጥ ታሪኮች ላይ ተንተርሶ ጥልቀት ያለው ስራ ለመስራት ለጥናቶቹ ሰፊ ግዜ መስጠት እንደሚያስፈልገው ስለተገነዘበ ነበር። በዚህም ቁርጠኝነቱ የተነሳ በአጭር ግዜ ውስጥ በፊልም ስራዎቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተዋጣለት የፊልም ባለሙያ ለመሆን በቃ። የፊልም ት/ቤቶችን ደጅ ረግጦ የማያውቀው ፍሎሬስ የፊልም ስራን ከጀመረበት ከ2004 ጀምሮ አራት የሲኒማቲክ ዶክመንተሪዎችን፤ አንድ አጭር ልቦለድ፤ በርከት ያሉ ተከታታይ የቴሌቪዥን ፊልሞችን ጨምሮ አስራ ሰባት (17) ፊልሞችን መስራት ችሏል። በ2010 የሰራው እና “Rainmakers” የተሰኘው ፊልሙ ከሁሉ በላይ የስኬት ማማ ላይ እንዲወጣ ያደረገው ሲሆን፤ ፊልሙ አምስት ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን በሮም፤ በጄኔቫ፤ በሼፍልድ እና በሊዩቨን ጠራርጎ ከመውሰዱም በላይ በሃያ አምስት ሀገሮች ዓለም አቀፍ ፌስቲቫሎች ላይ የመታየት እድል አግኝቷል። ፍሎሬስ ከፊልም ስራዎቹ ጎን ለጎን በርካታ መፃህፍቶችንም ለንባብ ያበቃ ምርጥ ደራሲ እና ታሪክ ተራኪ ነው።”

 

በምን አይነት የሠነ-ጽሁፍ ችሎታ ይህን “አመፀኛው ክልስ” የተሰኘ ባለታሪክ እንደፃፈው የተጠየቀው ዳንኤል ሁክ፤ “በእስር ቤት ቆይታዬ ምንም እንኳን የሞት ፍርድ ቢፈረድብኝም አንድ ቀን ተፈትቼ እንደምወጣ አምን ነበር” ይላል። ለዚህም ሥነ-ልቦናዊ ጥንካሬ ያበቁትን አስተሳሰቦች ያዳበረው ደጋግሞ ከሚያነባቸው መፅሐፍ ቅዱስና የሥነ-ልቦና መፅሐፍት እንደነበር ይገልፃል።

 

በአሁኑ ወቅት ምንም አይነት ቤተሰብ ያልመሠረተ እንደሆነ የሚናገረው ዳንኤል ሁክ፤ “የተዋጣልኝ አማካሪና ቢዝነስ ማን እሆናለሁ” ሲል በህይወቱ የተሳካለት ሰው እንደሆነም አስረድቷል። በቀጣይ ከኑሮ የተረፈ ጊዜ ካለው ለመፃፍ የሚያስባቸው ታሪኮች እንዳሉም ጠቁሟል። በህይወቱ ለመዝናናት ሲያስብ ፊልሞችን (በተለይም የቻይና ካራቴ ፊልሞችን) መመልከት እንደሚማርከው ገልጾ፤ አሁንም ድረስ በአቋሙ ለመጠንከር አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚያዘወትርም ተናግሯል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
15742 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 887 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us