ጥልፍልፉን ፈታተን ስናየው

Wednesday, 11 October 2017 13:03

 

የመጽሐፉ ርዕስ - “ጥልፍልፍ”
ደራሲ - ካሳሁን ንጉሴ
አይነቱ - ረጅም ልቦለድ
የገጽ ብዛት - 320
የህትመት ዘመን - 2009 ዓ.ም መጨረሻ
ዋጋው - 95 ብር

 

ሰው በህይወት ጥልፍልፍ መንገድ ውስጥ የሚጓዝ ግዞተኛ እንደሆነ የሚተርክ መጽሐፍ ነው። ይህ “ጥልፍልፍ” የተሰኘውና በአርባ ስድስት ምዕራፎች ተከፋፍሎ ጠቢቡ እና አይናለም በተሠኙ ዋና ገፀ-ባህሪያት በሚኖሩት የታሪክ ሰንሰለት አማካኝነት ተቀጣጥሎ የቀረበልን ረጅም ልቦለድ መጽሐፍ ነው። ጥልፍልፎሹም ሰው ከራሱ፤ ሰው ከወዳጁ፣ ሰው ከኑሮው፣ ሰው ከቤተሰቡና ከማህበረሰቡ ሲነጥለውም ሲያንጠለጥለውም በመሳጭ አተራረክ አብሮን ይዘልቃል።


የ“ጥልፍልፍ” ታሪክ ማግኘትና ማጣትን፣ የአላማ ጽናትን፤ ወዳጅነትና ጠላትነትን፤ በህይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ የወጣትነት ተግዳሮቶችን በባለታሪኮቹ አማካኝነት እያስመለከተን ከገጽ - ወደገጽ የሚሸጋገር በአሳዛኝ ታሪክ የተሞላ ልብ አንጠልጣይ መጽሐፍ ነው።
ደራሲ፣ መምህር እና ዲፕሎማት እንዲሁም ለጠቅላይ ሚኒስትርነት በእጩነት ቀርበው የነበሩት ክቡር ዶክተር ሐዲስ ዓለማየሁ “ፍቅር እስከ መቃብር” በሚለው መጽሐፋቸው የኢትዮጵያን ስነ ጽሁፍ አንድ ደረጃ ከፍ ማድረግ ችለዋል። በ”ትዝታ” መጽሀፋቸው ደግሞ የአገር ፍቅርንና አርበኝነትን ተርከዋል። እኚህ ታላቅ የብዕር ሰው ፍቅር እስከ መቃብርን የመሰለ ስነጽሁፋዊ ይዘቱ የረቀቀ መጽሀፍ ሲጽፉ “በስነ ጽሁፍ ትምህርት” ምን ያህል ርቀት ተጉዘው ቢማሩ ነው ሊያስብል ይችላል። እሳቸው ግን የተማሩት የኬሚስትሪ ትምህርት እንጂ የቋንቋና ስነ ጽሁፍ አልነበረም። “ለስነ ጽሁፍ ይወለዱለታል እንጂ አይማሩለትም” አስብለዋል።


ዛሬ በዚህ አምድ የምንመለከተው ወጣቱ ጸሀፊ ካሳሁን ንጉሴ ‹‹ጥልፍልፍ›› ሲል በሰየመው መጽሀፉ ከአንባቢያን ጋር ተገናኝቷል። ይህ ወጣት ደራሲ ረጅም ልቦለድ መጽሀፉን ለአንባቢያን እንካችሁ ሲል ከየትኛውም የአገራችን ዩኒቨርስቲ በስነጽሁፍ ዘርፍ ተምሮ አይደለም። ወጣቱ ትምህርቱን የተከታተለው በስፖርት ሳይንስ ሲሆን እየሰራ ያለውም በአገራችን ከሚገኙ ሆቴሎች በአንዱ የጂም አሰልጣኝ ሆኖ ነው። እኛም መጽሀፉን አንብበን ያየናቸውን ጥንካሬ እና ድክመቶች ከዚህ በታች ባለው መልኩ ለአንባቢያን በሚመጥን መልኩ እናቀርበዋለን።

 

የቋንቋ ክህሎት


የደራሲ ካሳሁን ንጉሴ መጽሀፍ ምናልባትም ትልቁ ችሎታው ሊባል የሚችለው ጠንካራ ጎኑ የቋንቋ ችሎታው ነው። ደራሲው ተወልዶ ያደገው በጎጃም ክፍለሃገር መሆኑ እና የአካባቢው ህዝብ ትልቅ ሀብት የሆነውን የቅኔ ችሎታ ደራሲ ካሳሁን ተክኖበታል። መጽሀፉን ገጽ በገጽ በተመለከትንበት ሁሉ የልጁን የቋንቋ ክህሎት በሚገባ መመልከት እንችላለን።


ምጥን እና ጉልበት ያላቸው ቃላት በትክክል ሰድሮ የጻፈው ደራሲ ካሳሁን ንጉሴ መጽሀፉን ለማንበብ የሚፈልጉ አንባቢያንን እንዳይጎረብጥ አድርጎ ነው የሰራው። ከዚህ ጋር አብሮ ሊነሳ የሚገባው ደግሞ በበርካታ የህትመት ስራዎች ላይ በብዛት የሚታየው የፊደላት ግድፈትና የስርዓተ ነጥብ አጠቃቀም ችግር በ‹‹ጥልፍልፍ›› ውስጥ በብዛት አይታይም። ይህ የሆነው ደግሞ ከአንድም ሁለት ጊዜ የአርትኦትና ፊደል ለቀማ ስራ የተሰራ መሆኑን መጽሀፉ መግቢያ ላይ ተገልጿል። ይህ ማለት ግን ፍፁም ከግድፈት የነፃ ነው ለማለት እንዳልሆነ አንባቢ ልብ ሊለው ይገባል።

 

የመቼትና የሀሳብ አቀማመጥ


‘ጥልፍልፍ’ ውስጥ ዋና ገጸ-ባህሪዎቹን አይናለምንና ጠቢቡን ጨምሮ ሌሎች አጃቢ ገጸ ባህሪያት ያለቦታቸው የገቡበት አጋጣሚ የለም። ጊዜውንና ወቅቱን በጠበቀ መልኩ ተሰድሮ የተቀመጠ የታሪክ ፍሰት የተላበሰ መጽሀፍ ነው ማለት ይቻላል። ምናልባት በዚህ መጽሃፍ የታሪክ ፍሰት ላይ ሊነሳ የሚችለው ጉድለት ቢኖር ጥድፊያ የበዛበት መሆኑ ነው። ደራሲው ለምን እንደዛ በጥድፊያ ነገሮች እንዲከናወኑ ማድረግ እንደፈለገ ግልጽ ባይሆንም ጥድፊያ ግን በብዛት ይታይበታል። በጥድፊያው ውስጥም ቢሆን እንኳን ፍሰቱ ሂደቱን ጠብቆ የሚሄድ ነው።

 

ልብ ሰቀላ


ታሪኩ እንደ ርዕሱ ውስብስብነትና ጥልፍልፎች የበዛበት ቢሆንም ለአንባቢ አይጎረብጥም ወይም በጥልፍልፉ አይሳቀቅም። አይናለም የመጀመሪያ ፈተና የደረሰባት በጥበበ እና በጓደኛው በደረሰባት መደፈር ነው። ጥበበ በመጠጥ ተነሳስቶ በሚወዳትና በሚያከብራት አይናለም ላይ ወሲብ ቢፈጽምም በማግስቱ ግን ጸጸት ሲያንገላታው እናያለን። በዚህ ብቻ ያልቆመው የጥበቡ ጸጸት ትምህርቱን ለማቋረጥ እንዳደረገውም ይገልጻል።


በተለይ ከመኖሪያ ቀየው ርቆ ለጸበል ከሄደና በዚያው የቤተ ክህነት ትምህርት መማር ሲጀምር ዘመናዊውን ትምህርት እስከመጨረሻው ይሰናበታል ወይስ ይመለሳል? የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ ጋር የመዘበሩትን ገንዘብ አስተዳድርልኝ ሲሉ እምቢ በማለቱ ሊደርስበት የሚችል መጥፎ እጣ ይኖራል ወይስ በምን መንገድ ያልፈዋል? የሚሉት እንዲሁም አይናለም ልጇን የተገላገለችበት መንገድ፣ ከሆስፒታል ስትወታ የገጠማት ነገር፣ ከባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተዘዋውራ የገጠማት የፍቅር ህይወትና ሌሎች ታኮች በደራሲው የተሳሉ ልብ ሰቃይ ታሪኮች ናቸው። ታኮቹ ልብ ሰቃይነት ቢታይባቸውም ከጥድፊያ የጸዱ አለመሆናቸው ግን አንዱ ችግር ነው። አንዳንዴ ለማመን በሚከብድ መንገድ የተገኙ ድሎች የተካተቱበት በመሆኑም ከእውነታው የራቁ መስለው ይታያሉ።

 

በመጨረሻም የ“ጥልፍልፍ” ክፍተት ምንድነው?


ወጣቱ ደራሲ ካሳሁን ንጉሴ አለኝ ያለውን የሥነ-ጽሁፍ ትሩፋት አበርክቶልናል። ነገር ግን ከሰው ስህተት ከብረትም ዝገት አይጠፋምና በቀጣይ ስራዎቹ ትኩረት ያደርግ ዘንድ ማስታወሻ የሚሆኑ እንከኖችን ለመጠቆም እንወዳለን።


በ“ጥልፍልፍ” ረጅም ልቦለድ መፅሐፍ ውስጥ የመጀመሪያውና ዋነኛው ግድፈት ሆኖ የሚቀርበው የሥርዓት ስህተት ነው። እንደሚታወቀው በቤተክርስትን (በተለይም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን) ዘንድ አንድ ሰው በገዛ እጁ ህይወቱን ካጠፋ “ሥርዓተ- ፍትሃት” አይደረግለትም። በመጽሐፍ ውስጥ በልጃቸው ትልቅ ተስፋና እምነት የነበራቸው ወ/ሮ ይሻሙሽ ራሳቸውን ስለማጥፋታቸው ይተርክልናል። “የሚወዷትን ልጅ ጉንጭ ሳይሰሙ እንደናፈቀቻቸውና በእሷ እንደተራቡ፣ ናፍቆታቸውን ሳይወጡ ረሃባቸውን ሳያስታግሉ አንገታቸውን ለገመድ ሰጡ። “ይለናል (ገፅ፥ 180) ቀጥሎ በሚቀርበው ታሪክ ውስጥም በካህናት ፍትሃት እንደተደረገላቸው መገለፁ ከሃይማኖቱ ስርዓት ጋር ፍፁም የሚጋጭ ነው።


ሌላው በታሪኩ ውስጥ ያለው ተቃርኖ የጠቢቡ አንባቢነት አስተዋይነትና አርአያነት ያለው ሆኖ መሳሉ አንባቢው ትልቅ ቦታ እንዲሰጠው ተደርጓል። ሆኖም ግን ከተሳለበት የገፀ ባህሪይ አውታር አንፃር የሚወዳትን ልጅ ከጓደኛው ጋር አስገድዶ እስከመድፈር መድረሱ ትልቅ ተቃርኖ ነው። (እዚህ’ጋ ደራሲው በመጠጥ አስክሮት ስህተቱን ሊሸፍንለት የሄደበት መንገድ ደካማ ምክንያት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል) የገፀ- ባህሪውን ጠንካራነትና የፍቅሩንም ጽናት ልናይ ቢገባም ይህንን እንዳናይና የጥልፍልፉ ጅማሮ እንዲሆን ሁለቱን በነፍሳቸው የሚፈላለጉ ሰዎች በስጋቸው እንዲለያዩ አድርጎ አስቀምጧቸዋል።


ሌላኛው እንዴት የሚያስብል ጥያቄን በአንባቢ ዘንድ የሚፈጥረው የህግ ጉዳይ ነው። አይናለምን ይወዳት የነበረው መምህር ክብረት የፈፀመው የወንጀል አይነት እና ደረጃ በሚገባ ሳይገለፅ ጥድፊያ በተሞላበት መንገድ የአስራ አምስት ዓመታት ፅኑ እስራት እንደተወሰነበት ይተርክልናል። “መምህር ክብረት ነገሰ አይናለም በቀጠራት ቀን ስላልመጣችለት በመንገድ ላይ ጠብቆ ሊበቀላት ሲል በህዝብ ትብብር በፖሊስ በቁጥጥር ስር ውሎ የ15 ዓመት ፅኑ እስራት ተወስኖበት በወህኒ ቤት ይገኛል”ይለናል። (ገጽ፥60) . . . ደራሲው “መንገድ ላይ ጠብቆ ሊበቀላት” በሚል አንቀጽ ብቻ ሰውን 15 ዓመት ማሰር ቀላል የህግ ስህተት አይደለም።


ደራሲው በተለይ መሪ ገፀ-ባህሪያቱን “ትልቅ” ለማድረግ የሄደበት ርቀት ከተዓማኒነት አንጻር ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነው ማለት ይቻላል። ለምሳሌ ከመነሻው ጠቢቡ የተባለውን ገፀ ባህሪይ ተማሪና ተመራማሪ፤ የመፅሐፍ ቀበኛ አንባቢ በማድረግ አግዝፎ ስሎታል። በሌላ በኩል አይናለም ገና የመጀመሪያ ዓመት የዩኒቨርስቲ ተማሪ ሆና እና በዚያ ሁሉ የህይወት ጥልፍልፍ ውስጥ አልፋ በዓለማቀፍ ደረጃ የሚያገለግል ፈጠራ መፍጠሯን ይተርክልናል። (በገፅ፥ 248) እዚህ ላይ መጠቀስ ያለበትና ቢቀር የሚያሰኘው ነገር ደግሞ የሰራችውን “ሶፍት ዌር” ለማሳየት ሁለት ገጽ ሙሉ በእንግሊዝኛ የተዘጋጀ ምሳሌ ቅፅ ማሳየቱ ነው። ይህ ነገር ከስነፅሁፍ ውበት አንፃር አስፈላጊ አልነበረም።


ሌላው በመጽሐፍ ውስጥ መፅሐፉን የማስተዋወቅ ያህል ዋናው ገፀ-ባህሪይ ጠቢቡ “ብርቅርቅታ” የተሰኘው የዳኔል ስቲል መጽሐፍ ያስተዋውቀናል። በተለይም የታሪክ ተመሳስሎሽ ለማሳየት ሲባል በገጽ 31፣ 32 እና 33 መፅሀፉን አንባቢ እንዲያነበው መደረጉ አላስፈላጊ ነው። ከሆነም በገፀ-ባህሪው ምናብ ውስጥ የሚመላለሰውን ሃሳብ በትርክት መልክ ቢነገረን ይሻል ነበር።


እዚህ’ጋ በአፅንኦት ሊገለፅ የሚገባው ሌላው ነገር የመፅሐፉ የሽፋን ስዕል ሳቢ ያለመሆኑ ጉዳይ ነው። አበው “ከፊትፍቱ ፊቱ” ማለታቸው ቀላል አይደለም። መፅሐፍ በርካታ ቁምነገሮች ያሉት ቢሆንም ከሽፋኑ አንጻር ግን በእጅጉ ሳቢነት ይጎድለዋል ማለት ይቻላል። እናም ደራሲው በቀጣዮቹ ስራዎቹ መሰል ስህተቶችን እንደማይደግም ተስፋ በማድረግ ዳሰሳችንን እናጠናቅቃለን።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
15818 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 883 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us