ሥላቅ እና ቅኔ - “የወንበር ፍቅር” ስር

Wednesday, 08 November 2017 19:11

 

የመጽሐፉ ርዕስ  -    “የወንበር ፍቅር”
ገጣሚው  -            ሙሉቀን ሰለሞን
የታተመበት ዘመን  - 2010 ዓ.ም
የገፅ ብዛት  -          111
ዋጋው  -             50 ብር ከ60 ሳንቲም

 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች እና ሥነ-ፅሁፍ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት መምህር ዘሪሁን አስፋው “የሥነ-ፅሁፍ መሠረታዊያን” የተሰኘው መፅሐፋቸው ውስጥ ስለሥነ- ግጥም እንዲህ ይላሉ። “ሥነ-ግጥም አንድን ነገር ወይም ድርጊት አድምቆና አጉልቶ የማሳየት፣ ሀሳብን አክርሮና አግዝፎ የማቅረብ ችሎታ ያለው፤ በጥቂት ምርጥ ቃላት ብዙ ነገሮችን አምቆ የሚይዝና በሙዚቃዊ ቃናው የስሜት ህዋሳትን በቶሎ የሚነካ ለስሜት ቅርብነት ያለው ኪነ-ጥበብ ነው”።


ዛሬ ዳሰሳ የምናቀርብበት የገጣሚ ሙሉቀን ሰለሞን “የወንበር ፍቅር” የተሰኘችው መድብልም ይህንን ሀሳብ በወጉ ታሟላለች። “የመፅሀፏ ሙሉ ቢሮች (ገጾች) ለእርስዎ የተከፈቱ ናቸው” በሚል ቀላል መግቢያ ገጣሚው ይንደረደራል። “የወንበር ፍቅር” የግጥም መድብል ለወጣቱ ገጣሚ የበኩር ስራው ይሁን እንጂ ያነሳቸው ሀሳቦችና ሀሳቦቹን የገለፀባቸው ሥነ-ግጥማዊ ለዛዎች ግን የልጁን ባለተሰጥኦነት የሚያመለክቱ ናቸው። እኛም ለዛሬ ዳሰሳችን በተለይም “ሀገር ተኮር” በሆኑት ግጥሞቹ ላይ አተኩረን መድብሉን እናጣጥማለን።


አንድ ብሎ በስላቅ የተሞላ፤ በቅኔ የታመሰ የግጥም “አረቄውን” ማስቀመስ ሲጀምር “ርምጃ” ሲል እንዲህ ይኮረኩረናል።

 

ሰው
ካለበት ቦታ ተነስቶ
ሩቅ ለመሄድ ቢመኝ
ሩቅ ለመጓዝ ቢያምረው
ያንን የተስፋ ’ርምጃውን
አንድ ብሎ ነው የሚጀምረው።
አንድ አልኩ. . .


     ይለናል። (ገፅ ፥ 9)


“በወንበር ፍቅር” ስብስብ ግጥሞች ውስጥ ፍቅር ተዘርዝሯል፤ ስልጣን ተበርብሯል፤ ማንነትና ማህበራዊ ትዝብቶች ተቀምረዋል፤ ማጣትና ማግኘት፤ ፍቅርና ጥላቻ፤ ከፍታና ዝቅታ ሁሉ በስላቅ በተሞሉ ቅኔዎችም ተዘርፈውባቸዋል።


ዘመናችንን በዘመኑ ተማሪ መነፅር ሊያሳየን የተጠበበው ገጣሚ ሙሉቀን ሰለሞን “የዘመኑ ተማሪ” በተሰኘውና ሶስት ገፅ በሚሸፍነው ዘለግ ያለ ስራው ዘመናችን ላይ ያለውን የዘር ነገር እያነሳ እንዲህ ይሳለቃል።


“ግን ያልገባኝ ነገር
ይህች ተዓምረኛ - ሉሲ ’ምትባለው
የሰው ዘር ሁሉ እናት፤
የኢትዮጵያ ኩራት፤
የዓለም ልዩ ፍጡር፤
የእኛነት ምስክር፤
ወዘተ -ወዘተ. . .
ተብላ እየተጠራች የምትወደሰው
የኛዋ ድንቅነሽ
ብሔሯ ምንድነው???”
               (ገፅ ፥ 12)


ሁሉም ነገር በአገር እንዳለ የሚጠቅሰው ገጣሚው፤ ነገር ግን ከሁሉም ነገር ምንም ነገር እንደሌለው ሲሳለቅ “የሌለኝ” ይለናል። እነሆ ቅምሻ . . .

 

ምን ጉልበት ቢጣጥር - ቢለካ በፈረስ
ሙሉ አካል ታቅፈው - ቁጭ እስካሉ ድረስ
ሆድ እየተራበ - አረቄ ይጠጣል
የሚበላው አጥቶ - ጨጓራ ይላጣል
ሺህ ዳቦ ቤት ቢኖር
ዳቦ ከየት ይመጣል???
               (ገፅ ፥ 19)


“የወንበር ፍቅር” የግጥም መድብልን በእጃችሁ ስትይዙ በዋጋ መጠቆሚያው ገፅ (የኋላ ሽፋን) ላይ አስተያየት አታገኙም። የምታገኙት የሚከተለውን ጉልበታም ግጥም ነው። ታላቁ መፅሐፍ “መታዘዝ ከመስዋትነት ይበልጣል” ይላል። እነሆ የመታዘዝን ያህል መስዋትነት የሚከፍል ህዝብ ሲቀጣም እንዲያው የመረረ እንደሚሆን ገጣሚው ሲያመላክተን እንዲህ ይለናል።

 

የትዕዛዝ ቅኔ
(1)
እዚህ በ’ኛ መንደር
እያደር እያደር
ያዛዥና ታዛዥ - መራራቁ ሰፋ
ያም ‘አዞ’፣ ያም አዞ - የሚታዘዝ ጠፋ።


(2)
ያም አዞ ያም አዞ - መታዘዝ ከሞተ
‘አዳኙን’ ይበላል - ህዝብ እየሸፈተ።
             (ገፅ ፥ 23)

 

በእጃችን ያለውን - ዛሬን በሚገባ እንዳልሰራንበት እና በአባቶቻችን ታሪክ ላይ ብቻ ተንጠልጥለን እንደቀረን የሚያስታውሰን የሙሉቀን ግጥም “የኔ ነገር” ይላል። ይህ ግጥም በአንደኛ መደብ ይፃፍ እንጂ፤ ለሁላችንም ይሆናል። የአባቶቻችንን ታሪክና ብርታት ለኛ ብርታትና አቅም ካላደረግነው፤ “በትናንት በሬ ያረሰ የለምና” የማንቂያ ደወሉን እንዲህ ሲል ያንቃጭለዋል። ለቅምሻ ያህል ልቆንጥር. . .


ወይ የደረቀ አጥንት - ጋሻ ላይሰራልኝ
የሻገተ ስጋ ምግብ ላይሆንልኝ፣
ስጋዬን ስመትር፣
አጥንቴን ስቆጥር፣
ተቆጠሩ ዓመታት - ነጎዱ ዘመናት ለራሴ ሳላድር፤
በሙታን ሳቅራራ - በሙታን ስፎክር።
                (ገጽ ፥ 30)


“የወንበር ፍቅር” መድብል ውስጥ ሌላው በስላቅ የቀረበው የዘመናችን አካሄድ ወሲብን የተንተራሰ ነው። ሰው የራሱን ብቻ ይዞ መኖር ሲገባው፤ የሌላውን ሲመኝ የሚሰራውን ስህተት ለመሸፈን ሲል ፌስታል (ኮንዶም ማለቱ ነው) ፈጥሮ ዘር እየጨረሰ ነው የሚል ስላቅን ያስነብበናል።

 

የዛሬ ዘመን ሰው


የዛሬ ዘመን ሰው - ከድሮው ይቀላል
እራሱ እየዘራ - ’ራሱ ይነቅላል።
የዛሬ ዘመን ሰው፤
የሰው ሰው ሳይፈልግ - ልክ እንደትላንቱ
ራሱ የወለደውን - አምጦ ካንጀቱ፣
በፌስታል ጠቅልሎ ምንም ሳይጸየፍ
ከሔሮድስ ብሷል - ልጆች በመጨፋጨፍ።
                (ገጽ ፥ 36)


ከነጠላነት ይልቅ አንድነት፤ ከብሔረሰብነት ይልቅ ብሔርተኝነት፤ ከእኔነት ይልቅ “እኛነት” በእጅጉ እንደሚያስፈልገን ደግሞ “ተይማነሽ - ተይማነሽ!” በተሰኘው የፍቅር ቃና ባለው ግጥሙ ይመካከረናል። ይህ በፍቅር መወደስ የታሸ ግጥም መልዕክቱ ለዘመናችን በእጅጉ አስፈላጊ ነው። ለቅምሻ ያህል. . .


የሰው ልጅ ውድቀቱ የሰው ልጅ በሽታ
‘እኛ’ ማለት ትተው ‘እኔ’ ያሉ ለታ፡፤
በሰፊ ምድር ላይ በጠባብ መሄጃ
‘እኔ - እኔ’ ማለትሽ ማዋጣቱን እንጃ።
                    (ገፅ ፥ 56)


እስቲ አሁን ደግሞ የመፅሐፉ ርዕስ የሆነውን ግጥም እንመልከት። የወንበር ፍቅር በብዙ የህይወታችን መስመር መመንዘር የሚችል የታመቀ መልዕክት ያለው ግጥም ነው። ስጋ እንዳየ ጉንዳን አንድ ወንበር ላይ ስንጋደል ህሊናችን ምን ያህል እንደሚጎድል ገጣሚው ያስታውሰናል።


ስንት ወንበር ክፍት እያለ - ለሚያስብ ሰው የሚስማማ
ለሰውነት ማይጎረብጥ - ለህሊናም የማይገማ፤
አንድ ወንበር ላይ ሙጭጭ ብለን - ለመቀመጥ ስንጋፋ፤
ሰው በሰው ላይ ተመርኩዞ - ቦታ እያለ ምቾት ጠፋ።
                        (ገጽ ፥ 70)


ገጣሚው ህሊና ሰርሳሪና ሞጋች ጥያቄዎቹን አሁንም ማቅረቡን አልተወም። እናም ያልገባውን “ያልገባኝ” እያለ ጥያቄውን ወደ አንባቢው እንዲህ ሲል አንከባለለ።


ለምድራዊ ስልጣን - ከሞት ለሚያስጥል
ለማያጠግብ ንዋይ - ከምስጥ ለማይከልል፣
ውል በሌለው ምኞት - እየተደለለ
እንዴት ሰው ይኖራል - ሰው እየገደለ!!!???
              (ገፅ ፥ 75)


“የወንበር ፍቅር” ስብስብ ግጥሞችን የያዘው ይህ መፅሐፍ በሽፋን ገዙ እጅግ ኮስታራ ቢመስልም የሚያነሳቸው ሀሳቦች ግን ከቁጭት ይልቅ ጠያቂ እና ኮርኳሪዎች ናቸው ማለት ይችላል። በፊት ገጹ የቀረበውን ዙፋንና ባንዲራ የተመለከተ ሰው ሀገር -ሀገር የሚሸቱ ብዙ ስራዎችን ጠብቆ ንባቡን ቢጀምር ይሻለዋል። እናም የአገር ነገር ከተነሳ ላይቀር “ነገር ጦቢያ” ከተሰኘው ግጥም እንቀንጭብ፡-


ከ13 ወር ፀሐይ፣
የ13 ወር ሌሊት ገዝፎ ሚታይባት
የቀኗ ብርሃን፤
በሌሊት ጨለማ የተሸፈነባት
ሰሚያዊው ሰማይ
በአመዳም ደመና የተጋረደባት
አረንጓዴ ምድሯ
በስንፍና አረም የደራረቀባት
አገሬ ናት እሷ
ሰዎች የበደሏት
ትውልድ ያከሰራት።  (ገፅ ፥ 78)


አብዝቶ ስለአገሩ የሚጮኸው ገጣሚው፤ ድሮና ዘንድሮን አነፃፅሮ ይጠይቃል። ድሮ ወንድሙ ስለአገሩ ባነሳው ጥያቄ ምክንያት ፀረ -አብዮተኛ ተብሎ በደርግ እንደተገረፈ አስታውሶ፤ አሁን ላይ ስሚወዳት አገር የሚጠይቅ ሰው “አሸባሪነህ” ከሚባልም አልፎ ለስደት እየተዳረገ መሆኑን ይገልጽና “የአገር ያለህ!?” የተሰኘ ግጥሙን እንዲህ ሲል ይቋጨዋል።


“አገሬ? ለሚል ጥያቄ - ስደት አይሁን መልሱ
በአገራችን እንኑር አገራችንን መልሱ” (ገፅ - 67)


“የወንበር ፍቅር” መጽ ሐፍ ገጣሚ በስልጣን ወንበር ላይ፤ በፍቅር መንበር ላይ፤ በእኛነት ክብር ላይ፤ በህይወት ውስጥና ላይ ሁሉ ፍልስፍና አዘል ሀሳቦቹን እነሆ ብሏል። የፍቅር ጉዳይን ሲተርክ በአንደኛ መደብ (ራሱን ባለታሪክ እያደረገ) መሆኑን እና ደጋግሞ ጥያቄ ማንሳቱን እናስተውላለን። የስብስብ ግጥሞቹ ውበትና የአገላለፅ አቅም ይበል የሚያሰኝ መሆኑ ባይካድም፤ አልፎ - አልፎ የሚያጋጥሙን የፊደል ግድፈቶች የአርትኢት ስራው በሚገባ እንዳልተሰራ ያመለክታል። ያም ሆኖ “የወንበር ፍቅር” የት ድረስ እንደሚመነዘር የገጣሚውን ስላቅና ቅኔ እየፈቱ ማየት መንፈስን ዘና ያደርጋል።

 

ይምረጡ
(11 ሰዎች መርጠዋል)
17117 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 958 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us