የማርያምን መንገድ ፍለጋ. . .

Wednesday, 15 November 2017 12:42

 

በአቤል አዳም

የፊልሙ ርዕስ                - “በእናት መንገድ”

ደራሲና ዳይሬክተር       - በሀይሉ ዋሴ

ፕሮዲዩሰር            - ሜላት ሰለሞን

ኤዲተርና ከለር                - ታምሩ ጥሩዓለም

ዳይሬክተር ኦፍ ፎቶግራፈ   - እውነት አሳሳኸኝ

ተዋንያን               - ደሞዝ ጎሽሜ፣ ሜላት ሰለሞን፣ ለምለም አበራ፣ ብርሃኔ ገብሩ፣ መስፍን ኃ/ኢየሱስ ሰለሞን ተስፋዬ፣ አሸናፊ ዋሴ፣ ቤልሳን ንጋቱ እና ሌሎችም

መጪው ጊዜ አሁን ካለንበት በእጅጉ አስከፊ ነው። ነገር ግን ያኔ ኢትዮጵያ ከጭንቅ ማምለጫ፤ የዓለም ስልጣኔ ማሳያ ትሆናለች፤ ይህም ተፅፏል ይለናል፤ በእውነት ፊልም ፕሮዳክሽን ተዘጋጅቶ፤ በኸርሊ ኤ ኤም መልቲ ሚዲያ ፊልም የቀረበው “በእናት መንገድ”።. . . የፊልሙ ደራሲና ዳይሬክተር በሃይሉ ዋሴ (ዋጄ) ከዚህ ቀደም በፃፋቸው “ሰኔ 30” እና “አይራቅ” ፊልሞቹ እንዲሁም ፅፎ ባዘጋጀው “ዮቶጵያ” ፊልሙ በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ ባለሙያ ነው።

ፍልስፍና አዘል ታሪኮችን በማሳየትና ወዝ ያለው አቀራረብን በመምረጥ የሚታወቀው ደራሲና ዳይሬክተሩ በዚህም ስራው አዲስ መልክ ይዞ ቀርቧል። ሀገርን በእጅጉ ከእናትነት ጋር ከማስተሳሰሩም አልፎ፤ ለመጪው ዘመን ኢትዮጵያ የጭንቅ ጊዜ “የማርያም መንገድ” (የመከራ ጊዜ ማምለጫ/ የመዳኛ መንገድ) እንደምትሆንም ይተርክልናል።

“በእናት መንገድ” ፊልም ውስጥ ያሉት ገፀባህሪያት አብዛኞቹ ወጣቶች ናቸው። የመጪው ዘመን የስልጣኔ ቁልፍ የሚፈታው በኢትዮጵያ ነው የሚለው አቃቢ (ደሞዝ ጎሽሜ)፤ የሚያውቀው ጠፍቶበት የሚደናበረው ታመነ (ብርሃኔ ገብሩ)፤ የከተማው ሩጫ ያታከታትና የልጅነት ዘመኗን የምትናፍቀው እህተ (ሜላት ሰለሞን)፣ ህብረተሰቡ አንባቢ ሳይሆን ጥቅስ ጠቃሽ ነው ሲል የሚተቸው መኖር (መስፍን ሀ/የሱስ) እንዲሁም ተስፋው ሁሉ በባሌም በቦሌም ብሎ ደቡብ አፍሪካ ላይ የወደቀው ዮናስ (አሸናፊ ዋሴ) በድምሩ በህይወት መንገድ ላይ የሚወዛወዙ ባለታሪኮች ናቸው።. . .  የእነዚህን ባለታሪኮች ምስጢር ቋጠሮ የሚፈቱት ደግሞ እማሀሌ (ለምለም አበራ) ናቸው።

“መንገድ ሲኖር ነው ጫማ የማደርገው” የሚለው አቃቢ በሚያነሳቸው ጠለቅ ያሉ ሀሳቦች ገና ከመነሻው የተመልካችን ትኩረት ይስባል። “አገራት በሁለት ይከፈላሉ” የሚለው አቃቢ፤ እስራኤልና ሶቬትህብረትን እንደምሳሌ እየጠቀሰ፤ ጠንካራ አስተሳሰብ ያላቸው ህዝቦች አገራቸውን ሲሰሩ በተቃራኒው የሆኑ ደግሞ የተሰራላቸውን አገር ሊያፈርሱ ይችላሉ ሲል ይሞግታል። እናም የመጪውን ዘመን የኢትዮጵያ ስልጣኔ ለማወቅ “አንቀጸ ሰብ” የተሰኘ የጠፋ መጽሐፍን ፍለጋ የታሪኩ አብይ ማጠንጠኛ ይሆናል። እዚህ’ጋ ደራሲና ዳይሬክተሩ በሃይሉ ዋሲ የስራውና ደሞዝ ጎሽሜ በትወና የደመቀቡት “ዮቶጵያ” የተሰኘውም ፊልም ስለሀገራችን መልካምነት እና የተሻለ መሆን በእጅጉ የሚሰብክ ፊልም እንደነበር ለአንባቢ ማስታወስ መልካም ነው።

በሌላ በኩል ወንድማማቾቹ ታመነ እና መኖር አባታቸው ያስቀመጡላቸውን የዕውቀት ሀብት ሳይጠቀሙበት ቀርተው እናታቸውን ገጠር ትተው በከተማው ወጀብ ተወስደው ሲቀሩ እንመለከታለን። በተለይም ታመነ ብዙ ምስጢር እንዲያውቅ ተደርጎ ቢያድግም ነገሩ ሁሉ ሳይገባው ቀርቶ መንከራተቱን ዳይሬክተሩ እንደምልክት (symbol) የማህበረሰባችንን ክፍተት ያሳየበት ይመስላል። አቃቢ የተባለው መሪ ገጸ-ባህሪይ ታመነን ሲገልፀው እንዲህ ይላል፣ “አለም የረሳችው፤ እርሱም አለምን የረሳት ሰው ነው” ይለዋል። አክሎም የኢትዮጰያ እና የልጁ ታሪክ ይመሳሰላል። ድንገት ነው ሁለቱም የሚፈለግ ነገር እንዳላቸው የሚያውቁት” ይለናል።

ከእኛ ዘመን ይልቅ የቀደሙት አባቶቻችን ብዙ ታሪክና ምስጢር እንደሚያውቁ የሚጠቁመው ፊልሙ፤ ዘመናዊነትን ፈልገው ከተማ ከዋጣቸው ወንድማማቾች አንዱ እንዲህ ይለናል። “የቤተሰቦቻችን ታሪክ ከብዶን ነው ከተማ የቀረነው”. . . በአንጻሩ የከተማ ኑሮ የውሸት -የውሸት መሆኑን የሚጠቁሙት የልጆቹ እናት እማ የሁሌ (ለምለም አበራ) “የከተማ መከራ በቅባት ተሸፍኗል” ይሉናል።

“በእናት መንገድ” ፊልም ውስጥ ጊዜያችንና ዘመናችን በስላቅ ተተችቷል። የማህበራዊ ኑሯችን በኑሮ ደረጃ በእጅጉ ተስሎ ቀርቧል። ጫማ እና እግር ከመንገድ ባሻገር ትልቅ ምልክት ሆኖ በፊልሙ ውስጥ ተስሏል። ለምሳሌ ጫማ ሰፊው ዳምጠው (ሰለሞን ተስፋዬ) ለሀገሩ ሲል ተዋግቶ አንድ እግሩን የሰጠ ሰው ነው። ይህ ገፀ ባህሪይ አገሪቷ ብድር መላሽ እንዳልሆነች እያማረረ ጫማዎችን ይሰፋል። በዚህ መሀከል ታዲያ አንድ “ሶሉ” በእጅጉ የተበላ ጫማ ያነሳው አቃቢ የተባለው ገፀ-ባህሪይ “ይሄ ሰው ምን ያህል ቢጓዝ ነው ጫማው እንዲህ ያለቀው?” በሚል ለሰነዘረው ጥያቄ ያገኘው መልስ፣ “ተመርቆ ስራ ሲፈልግ ይሆናል ጫማውን እንዲህ የጨረሰው” የሚል ይሆናል። ይህም የዘመናችንን ምሩቃን ስራ ፈላጊዎች እንክርት በጉልህ የሚያሳይ ነው።

የተደበቀው መጽሐፍ ፍለጋ የሚኳትነው አቃቢ፤ የጠበቀ ፍልስፍና የሚመስል ሀሳብ ይሰነዝራል። “ሴት ልጅ እናትነቷ ሲበዛ ጻዲቅ ትሆናለች” ይለናል። በዚህ ጊዜ ደግሞ ሴቶች ጥያቄም መልስም እየሰጡ የተደበቀውን ይፈታሉ።  ለምሳሌ እህተ፣ (ሜላት ሰለሞን)  “ለምንድው ኢትዮጵያ ውስጥ ምስጢር የሚበዛው?” ስትል ላነሳችው ጥያቄ እማ ሁሌ ሲመልሱ፣ “ፆም ላይ ስለሆነች ይሆናል። በፆም ወቅት ደግሞ ብዙ አይወራም” ሲሉ ምስጢር የሚበዛበትን ምክንያት ያመስጥራሉ።

“አንዳንድ እውነቶች የሚገለፁት በጊዜያቸው ነው” የሚለው አቃቢ፤ የጠፋብን ምስጢር ከትውልድ ወደትውልድ በዘር ተላልፎ እኛ ጋር የደረሰ በመሆኑ እኛም ለቀጣዩ ማሳወቅ አለብን ባይ ነው። እናም የኢትዮጵያን “የማርያም መንገድ”ነት በባለታሪኮቹ አማካኝነት “በእናት መንገድ” ፊልም ውስጥ እንድናይ እንገደዳለን። ያለውን ሀብት የማያውቅ ህዝብ ለራሱ የሚሰጠው ዋጋ ይወርዳል። ያንን ምስጢር የፈታንለት ጊዜ ግን ልክ በፊልሙ ፖስተር ላይ እንደምናያት “የአስፓልት” መሀል አደይ አበባ ማስደነቁ አይቀርም።

በፊልሙ ውስጥ የአቃቤ እና የእህተ ታሪክ ወደኋላ ተመልሶ ይተረካል። ነገር ግን ዳይሬክተሩ የተጠቀመው ቴክኒክ የፊልሙን አቅም የሚጎትት ባለመሆኑ ታሪካቸው አይሰለችም። ያም ሆኖ በፊልሙ ውስጥ ሊጠቀሱ የሚገባው ግድፈት የለም ማለት አይደለም። በተለይም በሁለቱ ወንድማማቾች ዘንድ የቋንቋ አጠቃቀም ከዘዬ አንጻር በሚገባ መቃኘት ነበረበት። ምክንያቱም በገጠር አካባቢ ተወልደው አድገው ፍፁም ቃናው የጠፋ የቋንቋ አጠቃቀም (አነጋገር) መከተላቸው ለተመልካች ጥያቄን የሚፈጥር ነው። ያም ሆኖ ፊልሙ ያለንበትን ዘመን በፍልስፍና፣ በታሪክ፣ በተስፋና ባልተቋጨ ምስጢር እያፍታታ ያሳየናል።

አስቀድሜ ለመጠቆም እንደሞከርኩት እግርና ጫማ በፊልሙ ውስጥ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ አጽንኦት ተሰጥቷቸዋል። የጫማ ሰፊውን ታሪክ፤ የአቃቢን ባዶ እግርነት፣ የእህተን እግር መቁሰል፤ የእማ ሁሌን እግር አጣቢነት ስንገጣጥመው ደራሲና ዳይሬክተሩ በእግር እና በጫማ በኩል ሊነግረን የፈለገው ምስጢር እንዳለ ግልጽ ነው። ፊልሙን ስትመለከቱ የተቋጠረውንም ምስጢር አብራችሁ ፍቱ።

በፍልስፍና፣ በታሪክ፣ በማንነትን ፍለጋና በወጣትነት መውተርተር ውስጥ የሚታጠፍና የሚዘረጋው “በእናት መንገድ” የተሰኘው አዲስ ፊልም የሚከተለውን ቅኔ አስታቅፎን የታሪኩን ምህዋር ይዘውረዋል።

አባሮ ያዥ በዛ፣ ሁሉም ባለወጥመድ

እንደው ወዴት ገባ የማርያምስ መንገድ።

መልካም የመዝናኛ ስምንት ይሁንላችሁ!   

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
15882 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1028 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us