የዬኔስኮ ድጋፍ እና የመላኩ ጥረት በመጥፋት ላይ ያለውን አዝማሪ ይታደገው ይሆን?

Wednesday, 06 December 2017 13:00

 

በይርጋ አበበ

 

እስክስታን በጥምቀት በዓል ላይ የተለማመደው ወጣቱ መላኩ በላይ አሁን የደረሰበትን ስኬት ከማግኘቱ በፊት ረጅም እና አድካሚ አባጣ ጎርባጣ መንገዶችን አልፏል። አሁን ከበሬታን አግኝቶ ዓለም አቀፍ ዝናን ያገኘበትን የባህላዊ ውዝዋዜ (እስክስታ) ሙያዬ ብሎ ከያዘው ወደ 20 ዓመታትን አሳልፏል። በአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ካዛንቺስ “አፓርታማ” ተብለው ከሚጠራው አካባቢ የሚገኘው “ፈንድቃ” የባህል ምሽት ቤት ደግሞ የመላኩ ችሎታ ነጥሮ የሚወጣበት፣ የእስክስታ እና የባህላዊ ሙዚቃ አምሮት ያለበት ታዳሚ ደግሞ አምሮቱን ‘የሚወጣበት’ ቤት ነው። የኑሮ ብዛት እና የእድሳት ማጣት ያጎሳቆላት ፈንድቃ የባህል ምሽት፤ ከውጭ ሆነው ለሚያዩዋት “እዚህ ግባ” የምትባል ባትሆንም ውስጧ ግን ስፍር ቁጥር የሌለው ቱባ ባህል እና ዘርፈ ብዙ ጥበቦችን ይዛለች። የፈንድቃ የባህል ምሽት ቤት ባለቤት እና “የእስክስታው ንጉሥ” አርቲስት መላኩ በላይ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የባህል የሳይንስና የትምህርት ማዕከል (ዩኔስኮ) ጋር በመተባበር እየጠፋ ያለውን የኢትዮጵያ አዝማሪዎችን ወደ ነበረበት ከፍታ ለመመለስ ብሎም ወደ ተሻለ የገቢ ምንጭነት እንዲቀይሩት ለማድረግ እየሰራ ይገኛል። ይህን በተመለከተ ሰሞኑን ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የሰጠውን ጋዜጣዊ መግለጫ እና ከጋዜጠኞች የተነሱ ጥያቄዎችን አቀናጅተን ለንባብ አብቅተነዋል።


ፈንድቃ ማነው? ምንስ ይሰራል?


ፈንድቃ የባህል ምሽት ወይም አዝማሪ ቤት ላለፉት 25 ዓመታት የባህል መዝናኛ አገልግሎት በመስጠት በብቸኝነት የዘለቀ አዝማሪ ቤት ነው። ይህ በአዲስ አበባ በካዛንቺስ አካባቢ የሚገኘውና አገሪቱን ለመጎብኘት የሚመጡ የውጭ ሀገርና የአገር ውስጥ ቱሪስቶች እንዲሁም በአዲስ አበባ ነዋሪ ለሆኑ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብና ለከተማችን ነዋሪዎች ልዩ ልዩ የባህል ውዝዋዜ እና የባህል አዝማሪ ምሽት አገልግሎት በማቅረብ የሚታወቅ አዝማሪ ቤት ሲሆን በስራውም ዓለም አቀፍ እውቅናን ለማግኘት ችሏል።


ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ፈንድቃ “ኢትዮ- ከለር” የተባለ ባንድ በማቋቋም እና በርካታ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ በተለያዩ አገራት የባህል ዝግጅቶችን በማቅረብ የሀገራችንን ባህላዊ ሙዚቃ በማስተዋወቅ ላይ ይገኛል። ከባህላዊ ሙዚቃው ባሻገር በፈንድቃ ባህል ማዕከል ኢትዮ ከለር በሚል የሥዕል -ዓውደ ርዕይ እና የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽን እንዲሁም የግጥም ዝግጅቶችን በቅታቸውን ጠብቀው እንዲቀርቡ ያደርጋል።


የአዝማሪ ሙዚቃ በኢትዮጵያ የ2000 ዓመት በላይ ታሪክ አለው። የአዝማሪ ሙዚቃ ሰዎች ሃይማታዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ በአጠቃላይ የግል አመለካከታቸውን በነፃነት የሚገልፁበት ነው። ይህም የአዝማሪዎች ሙያና የፈጠራ ችሎታቸው ለሀገር እድገትና ታሪክ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርጓል። ለዚህም ይመስላል የድሮ አገር መሪዎች አዝማሪ ምን አለ?” ብለው የሚጠይቁት።


ዘርፉ ያን የመሠለ ታሪክና ክብር እንዲሁም ቁምነገር ቢኖረውም በአሁኑ ጊዜ ግን የአዝማሪ ሙዚቃ ተጫዎቾች ቁጥር እየቀነሰ መጥቷል። ለዚህም ምክንያቱ በርካታ ቢሆንም ለጥበቡ በማኅበረሰቡ የሚሰጠው ቦታ፣ የውጭ ወይም የምዕራብያዊያን ሙዚቃ ተጽዕኖ፣ ወደ ዕድገት ወይም ዘመናዊነት በሚደረገው ጉዞ አዝማሪ ቤቶች መፍረሳቸው ጥቂቶቹ ምክንያቶች ናቸው።


የዩኔስኮ ውድድርና የመላኩ ሃሳብ


የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሳይንስ፣ የባህልና የትምህርት ድርጅት (ዩኔስኮ) በየዓመቱ ባህል እና ቅርስ ላይ ውድድሮችን ያዘጋጃል። ድርጅቱ በሚያዘጋጀው ውድድር ላይ በዓለም ላይ ያሉ ተወዳዳሪዎች “አሸንፍበታለሁ” ብለው የሚያምኑትን ሥራ “ንድፈ ሃሳብ (Proposal)” አቅርበው ይወዳደራሉ። በለስ የቀናቸው የአዱኛው አሸናፊ ሲሆኑ ያልቀናቸው ደግሞ አጃቢ ሆነው ይመለሳሉ። በ2016/17 ዓመት ድርጅቱ በዘርፉ ባወጣው ውድድር ላይ 900 ተወዳዳሪዎች ተሳታፊ ቢሆኑም 899ኙ የኢትዮጵያዊው የእስክስታ “ጌታ” መላኩ በላይ አጃቢ ሆነው ተመልሰዋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየቱን የሚሰጠው አርቲስት መላኩ “በውድድሩ አሸናፊ የሆንኩት ድርጅቱ በምን ላይ እንደምሰራ ሲጠይቀኝ በአዝማሪዎች ላይ መሥራት እንደምፈልግ ተናገርኩ። ምክንያቱም አዝማሪነት የተከበረ ሙያ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ሙያው እየደከመ ነው። ባለሙያዎችም ሥራውን እየተውት መጥተዋል። ለዚህ ምክንያቱ ብዙ ቢሆንም ተገቢውን ክብር እና ጥቅም አለማግኘት፤ እንዲሁም የዘመናዊነት ተፅዕኖ የሚሉት ይገኙበታል። እኔም ዓላማዬ ይህን የተከበረ ሙያ ወደ ቦታው መመለስ ነው” ብሏል። ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በሚፈልገው በዚህ ፕሮጀክት ምን ሊሰራ እንዳሰበ ተጠይቆ ሲመለስም ፕሮጀክቱን ዩኔስኮና አርቲስት መላኩ በላይ በጋራ የሚሰሩት ሲሆን እድሜያቸው ከ18-30 የሆኑ ወጣት የአዝማሪ ሙዚቀኞችን እና የባህል ተወዛዋዦችን ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በማምጣት ልምድ ካላቸው አርቲስቶች ጋር ልምድ እንዲቀስሙ በማድረግ ኮንሰርቶችን በተለያዩ ቦታዎች እንዲያሳዩ ይደረጋል።


ወጣቶቹ ከኢትዮ- ከለር ባንድ ጋር በመሆን አራት ፌስቲቫሎችን በሁለት ዙር የሚያቀርቡ ሲሆን ይሄውም የመጀመሪያው ዙር በፈረንሳይ የባህል ማዕከል እና በጁፒተር ሆቴል ይቀርባል። ሁለተኛው ዙር ደግሞ የአደባባይ ፌስቲቫል ሲሆን በሀገራችን በታላቅ ድምቀት በሚከበረው የጥምቀት በዓል ላይ በተመረጡ ቦታዎች ይቀርባሉ።


ይህ ዝግጅት ወጣት አዝማሪዎችን ሙያቸውን ለማሳደግና ለማሳየት እንዲሁም በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ዕድል ይፈጥርላቸዋል። በዚህም ከሚያገኙት ልምድና እውቅና በተጨማሪ ለውደፊቱ በሙያቸው ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ ማድረግ ይቻላል። በዚህ ዩኒስኮ ድጋፍ ባደረገበት የአዝማሪ ፌስቲቫል ላይ ፍላጎቱ ያላቸው ወጣቶች መሳተፍ ይችላሉ።


ፌስቲቫሉ በርካታ የሀገርና የውጭ ታዳሚዎችን የሚያሰባስብ ሲሆን የአዝማሪ ሙዚቃን እና ቱባውን የኢትዮጵያ ባህላዊ ሙዚቃ ከማስተዋወቁ ባሻገር የሀገራችን ወጣቶች ባህላዊ አርት ላይ እንዲሳቡ፣ እንዲሳተፉ እንዲሁም የአዝማሪነት ባህል እንድንኮራበትና ከትውልድ ትውልድ ለማስተላለፍ የሚረዳ ፕሮጀክት ነው ተብሎለታል።


በሞት አፋፍ ላይ ያለው አዝማሪነት


ከኢትዮጵያ ቱባ ባህሎች አንዱ አዝማሪነት ቢሆንም አደጋ ላይ መውደቁን ቀደም ባሉት ክፍሎች አይተናል። ባለሙያዎቹ ስራውን ወደ መተው እና ልጆቻቸውን የእነሱን ፈለግ እንዲከተሉ የማይፈልጉ መሆናቸውን አርቲስት መላኩ ይናገራል። “ለዚህ ፕሮጀክት ወጣት እና ሥራውን ለመስራት ፍላጎት ያላቸውን አዝማሪዎች ለማግኘት ወደ ላሊበላ፣ ጎንደር አለፋ ጣቋሳ እና ባህር ዳር ሄጄ ነበር። በጉዞዬ የታዘብኩት ግን አዝማሪነት አደጋ ላይ መሆኑን ነው” ይላል። ምድር ላይ ያሉ ድምፆች ሁሉ እስክስታ ለመምታት በቂዎቹ የሆኑት ዳይሬክተር መላኩ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን ባህል የሚያስተዋውቁ ሁለት የሲዲ ሙዚቃዎችን ቢያሳትምም፤ ለዓለም ያስተዋወቀው የአገሩ ባህል ግን አደጋ ላይ መውደቁን ይናገራል።


የኦሮሞ፣ ወላይታ፣ ትግራይ እና አማራ አዝማሪዎች ተዝቆ የማያልቅ የጥበብ አውድማዎች መሆናቸውን የሚገልጸው መላኩ በላይ፤ ነገር ግን እነዚህን ተንቀሳቃሽ የቱሪስት መሥህብ እና ውድ ሃብቶች የኔ ብሎ የሚጠብቃቸው አካል ባለመኖሩ እየጠፉ እንደሆነ ተናግሯል። ለዚህ ደግሞ መፍትሄ ያለውን ሲያስቀምጥ “የአንባሳውን ድርሻ” መንግሥት መውሰድ እንዳለበት ይገልጻል። መንግሥት ባህልን የመጠበቅና የማሳደግ ሞራላዊ እና ህዝባዊ አደራ እንዳለበት አርቲስቱ ይናገራል። የአገሪቱ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከጎንህ ሆኖ እንዲሰራ ጠይቀኸው ነበር ወይ? ተብሎ ተጠይቆ ነበር። አርቲስት መላኩ ሲመልስ “የሚያሳዝን ምላሽ ነው የሰጡኝ። ቢሮክራሲያቸው ተስፋ አስቆራጭ ነው” ብሏል።


ከዩኔስኮ ጋር በመተባበር ለሚያዘጋጀው የአዝማሪዎች ፌስቲቫል ከመላው አገሪቱ የተመረጡ ስድስት እንስት እና ስድስት ተባዕት አዝማሪዎች ወደ አዲስ አበባ መጥተው በፈንድቃ የባህል ምሽት ለአንድ ወር ስልጠና ይወስዳሉ። ሥልጠናው የሚሰጠው በሙያው አባቶችና እናቶች (አንጋፋ አዝማሪዎች) ሲሆን የሥልጠናው ትኩረት ማዕከሉ ደግሞ ወጣቶቹ ባለሙያዎች በራሳቸው እንዲተማመኑ የሚያደርግ እንደሆነ በአንድ ወቅት በሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ የእስክስታ ትምህርት (ኮርስ) ያስተማረው አርቲስት መላኩ ተናግሯል። አርቲስቱ አክሎም አደጋ ላይ ያለውን አዝማሪነት ማዳን የሚቻለው በዩኔስኮ ድጋፍ ወይም በውጭ አገራት ሰዎች ሳይሆን በራሳችን እንደሆነ አስምሮ ተናግሯል።

 

የፈንድቃ ቀጣይ ጉዞ


ፈንድቃ የባህል ምሽት በአርቲስት መላኩ በላይ የበላይነት መተዳደር ከጀመረ ከአስር ዓመታት በላይ ሆኖታል። አካባቢው በመልሶ ማልማት እንደሚፈለግ ሲገለፅ የቤቱ ባለንብረት በአምስት ሚሊዮን ብር ለአርቲስቱ ሸጠውለታል። የንብረቱ ባለቤት መሆን የቻለው አርቲስት መላኩም መንግሥት ለአካባቢው ይመጥናል ብሎ በደነገገው የህንጻ ደረጃ ቤቱን ለመገንባት እየተንቀሳቀሰ ነው። 75 ሚሊዮን ብር ይፈጃል የተባለለትን ባለ ስምንት ፎቅ ህንፃ ለመገንባትም የህንጻውን ዲዛይን አሰርቷል።


አርቲስቱ ሲናገር “ቤቱን ለመገንባት አቶ ፋሲል ጊዮርጊስ የተባሉ ባለሙያ የአርክቴክቱንና የዲዛይኑን ሥራ በነፃ ሰርተውልኛል። ግንባታው ሲጠናቀቅ አገልግሎት የሚሰጠው ሙሉ በሙሉ የባህል ማዕከል ሆኖ ነው። ብዙ ሙዚቃዎቻችን ገጠር ላይ እንዲሁ የሚቀሩ ናቸው። የእኛ ባህል ማዕከል ሲገነባ ይህንን ለመታደግ የሪከርድ ስቱዲዮ ይኖረዋል” ሲል የባህል ሙዚቃዎችን በስቱዲዮ ቀርፆ በአርካይቭ ለማስቀመጥ እንደሚሰራ ተናግሯል። “ፈንድቃ ይህን የመሰለ ኃላፊነት ይዟል። ነገር ግን የመንግሥት እርዳታ ያስፈልገዋል” የሚለው አርቲስት መላኩ አያይዞም “ይህን ህንጻ ለመገንባት ወደ 75 ሚሊዮን ብር ይጠይቃል። ይህን ገንዘብ ደግሞ እኔ እስክስታ ወርጄ የማገኘው ገንዘብ ይገነባዋል ተብሎ አይገመትም። ውጭ አገር ሄጄ ሰርቼ የማመጣውን ገንዘብም ለአንጋፋ እና ወጣት ድምፃዊያንን (ለምሳሌ አርቲስት ፉንቱ ማንዶዬ) ጨምሮ ወደ 70 የሚጠጉ ኢትዮጵያዊያንን ቀጥሬ የማሰራበት ነው” ይላል። በዚህም መሠረት ባህልን ከመጠበቅና ቱሪዝምን ከማስፋት አኳያ መንግሥት ከጎኑ እንዲሆን ጠይቋል።


ፈንድቃ የባህል ማዕከል በአሁኑ ሰዓት ከባህል ምሽት ቤቱ በተጨማሪ ለ12 ወጣት እና አንጋፋ ሰዓሊያን እንዲሁም የቅርፃ ቅርፅ ባለሙያዎች ስራቸውን እንዲያቀርቡ የምልከታ አዳራሽ (ጋላሪ) ከፍቶ ሥራዎቻቸውን በነፃ እንዲያቀርቡ እየደረገ ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪም በእውቅ እና አዋቂ ምሁራን መሪነት በየወሩ የፓናል ወይይት ይካሄዳል። እስካሁን ከተካሄዱ ውይይቶች መካከልም የታሪክ ተመራማሪው አቶ ስሜነህ አያሌው የመሩት what is modernity in Ethiopian context በሚል ርዕስ የተካሄደው ውይይት ይገኝበታል። “በዲንካ የባህል ሙዚቃ” እና አጠቃላይ በአርክቴክት ላይም ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት የተካሄደባቸው በዚሁ የፈንድቃ የባህል ማዕከል ውስጥ ነው።


እውን አዝማሪነት ከተደቀነበት የሞት (የመጥፋት) አደጋ ዩኔስኮ እና መላኩ በላይ ይታደጉት ይሆን? የሚለውን ጥያቄ መልሱን ለማግኘት ጊዜ ይፈልጋል። እስካሁን ባለው ሂደት ግን አርቲስቱን የሚመለከታቸው አካላት የሚደግፉት ከሆነ የታሰበው ባህልን የመታደግ ተግባር እውን ሊሆን እንደሚችል ተስፋ ሰጭ ምልክቶች ታተዋል።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
15744 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1031 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us