“የንጉስ ገፀ-ባህሪን ተላብሼ መተወን እፈልጋሁ”

Wednesday, 16 April 2014 13:18

አርቲስት ተስፉ ብርሃኔ

 

ብዙዎች በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን እሁድ መዝናኛ ላይ በሚተላለፈው “ዳና” ድራማ ውስጥ ባለው ገፀ-ባህሪይው በቀላሉ ያስታውሱታል። ከ48 በላይ የሆኑ የመድረክ ተውኔቶችን እና በርካታ የቲቪና የሬዲዮ ድራማዎችን የሰራው አርቲስት ተስፉ ብርሃኔ የዛሬው የመዝናኛ እንግዳችን ነው።

ሰንደቅ፡- በፕሮፌሽናል መድረክ የመጀመሪያ ስራህና አጀማመርህ ምን ይመስላል ከሚለው ጥያቄ ብንጀምርስ?

ተስፉ፡- ስራዬን የጀመርኩት በዚሁ በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ውስጥ ነው። የመጀመሪያ ስራዬ የነበረውም የፋዘር (ተስፋዬ አበበ) ድርሰትና ዝግጅት በሆነው “ሕይወት በየፈርጁ” የተሰኘ ተውኔት ነው።

ሰንደቅ፡- ከሀገር ፍቅር መድረክስ በፊት የሙከራ ጊዜህን የሰራህባቸው መድረኮች ይታወሳሉ?

ተስፉ፡- ተወልጄ ያደኩት መርካቶ አካባቢ ነው። ይህም በመሆኑ ተ/ሃይማኖት ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ ምከሃ ደናግል መንፈሳዊ ወጣቶች ማህበር በሚባል የሰንበት ትምህርት ቤቱ ክበብ ውስጥ ቴአትር እሰራ ነበር። ከዚያም በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴ ወቅት በከፍተኛ 7 ት/ቤት ሳለሁ ቴአትር እንሰራ ነበር። ያኔ የቀይ መስቀል በዓል ሲከበር ለተማሪው ቴአትር ስንሰራ ለካ ቴአትሩ የጋሽ ተስፋዬ አበበ ነበር። እኛ አላወቅንም። ይህ ለኔ ከመንፈሳዊ ተውኔቶች ወደአለማዊ ስራዎች የተሸጋገርበት ስራዬ ነበር። ከተመልካች ያገኘነው ምላሽ ጥሩ ስለነበር በመቀጠል ወደፋዘር ቤት ገብቼ ቴአትርን መማር ጀመርኩ። የሚገርምህ እዛ ለመግባት 14 ተፈታኞች ተወዳደረን ነው ሁለት ሰዎች ያለፍነው።

ሰንደቅ፡- የሚታወስህ ከሆነ እስከዛሬ በፕሮፌሽናል መድረኮች ላይ ምን ያህል ቴአትሮችን ሰርተሃል?

ተስፉ፡- አሁን በመጨረሻ መድረክ ላይ እየሰራሁት ያለውን “የጉድ ቀን”ን ጨምሮ ወደ 48 ቴአትሮችን ሰርቻለሁ።

ሰንደቅ፡- የመድረክ ቴአትሮችን ትሰራለህ፤ የቲቪ ድራማዎችን ትሰራለህ፤ ፊልሞችንም እንዲሁ ለመሆኑ የጊዜ አጠቃቀምህ እንዴት ነው?

ተስፉ፡- አዎ! ብዙ ጊዜ በተለያየ ምክንያት ሁሉም ሰው ወደራሱ ስራ ነው የሚያተኩረው። እኔ በተቻለኝ መጠን ጊዜዬን በአግባቡ ለመጠቀምና ለመስራት እየሞከርኩ ነው። ያም ሆኖ በጣም ከባድ ጊዜ እንደሆነ ይሰማኛል። ግን ከልጅነቴ ጀምሮ በምወደው ሙያ ውስጥ በመኖሬ እያጣጣምኩ እየሄድኩ ነው ብዬ ማለት እችላለሁ።

ሰንደቅ፡- ከሰራሃቸው ገፀ-ባህሪያት የማትረሳው ይኖራል?

ተስፉ፡- ምን አስባለሁ መሰለህ፤ ይህን ገፀ-ባህሪይ በዚህ ምክንያት አልረሳውም ወይም ለኔ ልዩ ነው ለማለት መስራት ማቆም ያለብኝ ይመስለኛል። እስካሁን ባለውም ቢሆን የሚመጡት ከዚህ ቀደም ያልተጫወትኳቸው አዳዲስ ገፀ-ባህሪያት በመሆናቸው አንዱን ብቻ መምረጥ ይከብደኛል። ለኔ የመጨረሻው ስራ የመጨረሻው ፈተናዬ ነው። ግን አዲስ ስራ ሲመጣ ደግሞ እርሱ አዲሱ የመጨረሻ ፈተናዬ ይሆናል ማለት ነው።

ሰንደቅ፡- መልካም! እስካሁን በተለያዩ መድረኮች ላይ ከተለያዩ ዕውቅ ተዋንያን ጋር ተውነሃል። ወደፊት ከእገሌ ጋር ብሰራ ብለህ የምትናፍቀው ሰው አለ?

ተስፉ፡- አይገርምህም እኔ በጣም እድለኛ ልጅ ነኝ። ማለት ልጅ ሆኜ በቲቪ አያቸው ከነበሩ ሰዎች ጋር የመተወን አጋጣሚውን አግኝቻለሁ። ቴአትር ጀምሬም ትልቅ ከሆኑ ተዋንያን ጋር አብሬ የመተወን አጋጣሚውን አግኝቻለሁ። ከአብራር አብዶ ፣ እነሙናዬ መንበሩ፣ እነሃይማኖት አለሙ፣ ፍቃዱ ተ/ማርያም እነወለላ አሰፋ፣ ከእነ ኩንዬ ሁሉ ጋር መስራቴ እድለኛ መሆኔን የሚያሳዩ ናቸው። ግን በጣም የሚቆጨንና የምናፍቀው ከተፈሪ አለሙ እና ከኤልሳቤጥ መላኩ ጋር እስካሁን አለመስራቴ ነው። አንድ ቀን ተሳክቶ ከነዚህ ትላልቅ ተዋንያን ጎን እንደምቆም ተስፋ አለኝ።

ሰንደቅ፡- ከትወናውና ከዝግጅቱ በተጨማሪ ድርሰት መፃፉስ ላይ እንዴት ነህ?

ተስፉ፡- የሚገርምህ ነገር የፅሁፍ ስራዎች እጄ ላይ አሉ። ነገር ግን አንድ ፅሁፍ ተሰርቶ ቶሎ ከእጅህ መውጣት አለበት። በተለይ አጫጭር የመድረክ ስራዎችና የቲቪ ስራዎችን ሰርቻለሁ። ከዚህ ውጪ ግን የመድረክና የፊልም ያለቁ ፅሁፎች በእጄ ላይ አሉ። ነገር ግን ቆይ ዛሬ ቆይ ነገ እያልኩ ጊዜ አጣሁ በዚህ መሃል ታናሽ ወንድሜ ሚሊዮን ብርሃኔ “የፈጣሪ ያለህ” የተሰኘ ድርሰቱን በፊልም ይዞ ሲመጣ ለእርሱ ቅድሚ ሰጥቻለሁ። ተስፋ አለኝ በሚቀጥሉት አንድና ሁለት አመታት ውስጥ የራሴን ስራ ፕሮዲዩስ አደርጋለሁ።

ሰንደቅ፡- እስቲ ደግሞ ስለ “ዳና” ድራማ እናውራ፤ “ዳና” ላይ የዘዉዱን ገፀ-ባህሪይ እንደተመልካች ስታየው ምን ይሰማሃል?

ተስፉ፡- እውነቱን ለመናገር አሁን -አሁን ብዙ ጊዜዬን እየወሰደብኝ ነው። የዘውዱን አይነት ገፀ-ባህሪይ ተጫውቼ አላውቅም። ግን ገና ፅሁፉ ሲሰጠኝ ነው ብዙዎቹ ተመልካቾች ስለገፅባህሪው የሚሰማቸው ስሜት የሚሰማኝ። በጣም የሚያሳዝነኝ ገፀባህሪይ ነው። ባይገርምህ ቀጣይ ክፍል ከመቅረፃችን በፊት ያለፉትን ክፍሎች ማየት አዘወትራለሁ። ለምን? መሰረታዊ የሆነውን ባህሪይ ላለመልቀቅ ነው። ዘውዱ በቤተሰብና በሚስት መካከል የቆመ ምስኪን ሰው ነው ለኔ።

ሰንደቅ፡- ድራማውን በተመለከተ የተመልካቹ ምላሽ እንዴት ነው?

ተስፉ፡- በጣም የሚገርም ነው። አሁን ላይ አብዝቼ ማህበራዊ ድረ-ገፆችን አያለሁ። የመጀመሪውን ምዕራፍ አጠናቀን ስናቆም ብዙ መልዕክት ከተለያዩ ቦታዎች ደርሰውኛል። በተለይ ደግሞ በአረብ አገራት፣ በአውሮፓና በአሜሪካ ያሉ ተመልካቾች በትኩረት ነው የሚከታተሉት፤ ይህንንም ከሚያደርሱኝ መልዕክት መመልከት ትችላለህ። በርካታ አበረታች አስተያየቶች ይደርሱናል ሁሉንም አመሰግናለሁ።

ሰንደቅ፡- ከስራህ አንፃር አሁን ጥሩ ተከፋይ ነኝ ብለህ ታስባለህ?

ተስፉ፡- ክፍያ አንፃራዊ ነው። ለምሳሌ ገና ስጀምር ምናለ አንድ ቀን እንኳን ድምፄን በሬዲዮ ብሰማው ብለህ ታስባለህ። ከዚያ በኋላ ድምፅህ ሲሰማ ደግሞ ትንሽ ቢከፍሉኝ ትላለህ። ትንሽ ሲከፍሉህ ደግሞ እንዲጨመርልህ ትሻለህ። ፍላጎትህና የአኗኗር ዘይቤህ በተለወጠ ቁጥር የሚከፈልህ ጥሩ የሚባል ክፍያ ሁሉ ላይበቃህ ይችላል። ለምሳሌ አሁን በቅርቡ ለኦስካር እጩነት የቀረበውን ሱማሌያዊውን ተዋናይ ተመልከተው “በካፒቴን ፊሊፕስ” ፊልሙ ላይ ተውኖ ያገኘው 67 ሺህ ዶላር ነው። ነገር ግን በኦስካር ምሽት ክፍያው በቂ እንዳልነበር ሲያማርር ትሰማዋለህ፡ አየህ መጀመሪያ በስክሪን መታየቱ ብቻ ላንተ እንደክፍያ ሊታይህ ይችላል። በሂደት ግን ያም በቂ የማይሆንበት አጋጣሚ ይመጣል ማለት ነው። ስለዚህ ስጀምር በተከፈለንና አሁን በሚከፈለኝ መካከል በጣም ሰፊ ልዩነት አለ። ነገር ግን አሁንም የአርቲስቱ ክፍያ በቂ ነው ብዬ አላስብም።

ሰንደቅ፡- በምን ትዝናናለህ?

ተስፉ፡- እርስ በእርሱ ነው። ጓደኞቼ የሰሯቸውን ፊልሞችና ቴአትሮች በማየት እዝናናለሁ። ልጄን ዳግማዊትን ሳገኛት ደስ ይለኛል። ባለቤቴ ድምፃዊት ሰብለ ግርማ ትባላለች። አውስትራሊያ ነው ያለችው። እነርሱን በስልክ ሳገኛቸው በጣም ነው የምደሰተው። ብዙ ሰዓት እናወራለን። ከዚያ ውጪ ከጓደኞቼ ጋር ሀሳብ በመለዋወጥና ኳስ በመመልከት እዝናናለሁ።

ሰንደቅ፡- ኳስ የማን ደጋፊ ነህ?

ተስፉ፡- ከውጪው የአርሰናል ከሀገር ውስጥ ደግሞ የጊዮርጊስ ደጋፊ ነኝ። አርሰናሎች ሲያቃጥሉን በጊዮርጊሶች ደግሞ እደሰታለሁ (ሳቅ)

ሰንደቅ፡- ወደፊት ብሰራው ብለህ የምትመኘው ገፀ-ባሀሪይ አለ?

ተስፉ፡- አዎ! የንጉስ ገፀ-ባህሪን መጫወት በጣም ነው የምናፍቀው።

ሰንደቅ፡- የምታመሰግነው ሰው አለ?

    ተስፉ፡- አዎ በቅርቡ የሃይሉ ፀጋዬ ድርሰት የሆነ “ከራስ በላይ ራስ” የተሰኘ ተውኔት አዘጋጅቻለሁ። ፕሮዲዩሰሩ ሙሉ ቀን ተሾመ ይባላል በጣም ጥሩ ሰው ነው። አመሰግነዋለሁ። በተረፈ ግን በህይወቴ የማመሰግናቸው ብዙ ሰዎች አሉ በተለይ ግን የልሄን እናት ድምፃዊት ሰብለ ግርማን፤ ጓደኛዬ ዮሃንስ ፈለቀንና ደረጃ ፍቅሩን፣ እንዲሁም ታምሩ ብርሃኑንም በጣም አመሰግናቸኋለሁ በልልኝ። ከሁሉም በላይ ግን አምላኬን አመሰግናለሁ።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
11333 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us