“64 የሎሬት ተሸላሚ መነሩ ይበዛል ብለን አናስብም”

Wednesday, 27 December 2017 12:30

 

አቶ ግርማ በቀለ

የአቢሲኒያ የሽልማት ድርጅት ፕሬዝደንት

በይርጋ አበበ

ሎሬት የሚለው የሽልማት ስም ይህ ነው የሚባል ወጥ ትርጉም የለውም ሲሉ ሰዎች ይናገራሉ። በሌላ በኩል ደግሞ UNESCO ቃሉን “ተሸላሚ” ሲል ይገልጸዋል። ከ17 በላይ መጻህፍት በመፃፋቸው የሚታወቁትና በካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ እና ሌሎች ትላልቅ ዩኒቨርስቲ በማስተማርና በመመራመር የሚታወቁት ፕሮፌሰር ዎልፍ ሌስላው English-Amharic Context Dictionary በተሰኘው መጽሀፋቸው ገፅ 700 ላይ Laureate የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል በኪነ-ጥበብና በሳይንስ ችሎታው የተመሠከረለትና ሽልማት ወይም ክብር የተሰጠው ሰው ብለው ተርጉመውታል።

የቀዳማዊ ኃለስላሴና እቴጌ መነን ሽልማት ድርጅት ከ1955 ዓ.ም ጀምሮ ሽልማትና ክብር ሲሰጥ በቆየበት ጊዜ ተሸላሚዎች የሚለውን ቃል ለመተካት Laureates እያለ ተጠቅመዋል። ይሁንና ከተሸላሚዎች ደረጃ፣ ከሽልማቱ ደረጃና ከኮሚቴው አመራረጥ ስርዓት ተሸላሚዎቹ የከፍተኛ ክብር ሽልማት ወይም ሎሬት ተሸልሟል ብሎ መረዳት ይቻላል። በሽልማት ድርጅቱ ከተሸለሙት መሀከል ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህንና ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ “ሎሬት” በሚለው መጠሪያ ሲጠቀሙ፣ አቶ ከበደ ሚካኤል፣ ደራሲ ሀዲስ አለማየሁ፣ አብዬ መንግስቱ ለማ፣ አቶ ተካ ኤገኖ፣ ሰዓሊ ገ/ክርስቶስ ደስታና ሌሎችም በርካቶች የንጉሱን ሽልማት የወሰዱ በመጠሪያው አልተጠቀሙበትም።

በሀገራችን የከፍተኛ ክብር ሽልማት ወይም ሎሬት አሰጣጥ ታሪክ ተመስርቶ በይፋ የተደራጀ የሽልማት ታሪክ የለንም። በዚህ የተነሳ በተለያዩ ተቋማት ስር የተለያዩ ሽልማቶች ሲሰጡ ቆይተዋል። የከፍተኛ ክብር ሽልማት የየድርጅቱ ነው። ለምሳሌ የኖቤል ድርጅት መንግስታዊ ያልሆነ የሽልማት ድርጅት ነው። ይህ ድርጅት ከተለያዩ ተቋማት ጋር የስራ ትስስር በመፍጠር የሽልማት ስራውን ይሰራል። ስራው ሲጠናቀቅም በመጨረሻ ስርዓቱ ላይ የስዊድን ንጉስ በተገኙበት ሽልማት ይሰጣል። በነገራችን ላይ የኖቤል ሽልማት ድርጅት የ1957 የእቴጌ መመን ሽልማትን አዲስ አበባ ቤተ-መንግስት ተገኝተው ወስደዋል። በወቅቱ የተገኙት የድርጅቱ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ቲሲሲየስ ይባላሉ። ይህን መሰረት በማድረግ አቢሲኒያ ሽልማት በህግ ተቋቁሞ የሚሰራ የሽልማት ድርጅት ነው። የራሱን ተሸላሚዎች ይሰይማል። ድርጅቱ በ1986 ዓ.ም ቢቋቋምም በሁለት እግሩ ቆሞ ሽልማቶችን ማከናወን የጀመረው ግን በቅርቡ ነው። አርቲስት አስናቀች ወርቁን በመሸለም ስራ የጀመረው አቢሲኒያ የሽልማት ድርጅት በዚህ ዓመት ጥቅምት 19 ቀን እና ታህሳስ 15 ቀን 2010 ዓ.ም በሁለት ዘርፎች ሽልማት አበርክቷል። በዚህ ሙያ ከድርጅቱ ፕሬዝዳንት አቶ ግርማ በቀለ ከምሲ ጋር አጠር ያለ ቃለ ምልልስ አካሂደናል የቃለ ምልልሱን ሙሉ ክፍል ከዚህ በታች አቅርበነዋል።

ሰንደቅ፡- ለውይይት መጀመሪያ እንዲሆነን እስቲ የድርጅታችሁን ዝርዝር መግለጫ (Profile) ይንገሩን?

አቶ ግርማ፡- አቢሲኒያ የሽልማት ድርጅት ቀደም ባለው ጊዜ በዶክተር ካርል የተመሰረተ ድርጅት ነው። ከ1996 እስከ 1998 ዓ.ም በዶ/ር ካርል ስም ሽልማቶችን ስንሰጥ ነበር። ያኔ ረዳት ፕ/ር ሃይማኖት ዓለሙ እና እኔ ነበርን ስራውን የምንሰራው። ሽልማት የምንሰጠው ግን ከተለያዩ ድርጅቶች የተውጣጡ የቦርድ አባላት ተካተውበት ነው ሽልማቱን የምንሰጥ የነበረው። ከዚያ በኋላ ድርጅታችን የሽልማትን ሥራ በስፋት ለመስራት የሚያስችል ዓለም አቀፍ ተሞክሮን ለመውሰድ ጥረት አድርገን በጀማሪዎች የተሰጥኦ ውድድር፣ በልህቀት ሽልማት፣ የከፍተኛ ክብር ሽልማት እና በተለያዩ ዘርፎች በተደራጀ የሽልማት ቅርፅ ለመሸለም ሥራ ጀምረናል። በዚህ መሠረት የዘንድሮው ሁለት ሽልማቶችን ለመስጠት አስችሎናል። (የከፍተኛ የክብር ሽልማት እና የተሰጥኦ ሽልማት)

ሰንደቅ፡- ድርጅታችሁ መርህ አድርጎ የቀረፀው “ዓለምንና ህዝቦቿን የሚታደግ ሥራ ለሰሩ ትጉሃን እንሸልማለን” በሚል ነው። በዚህ ዓመት ባካሄዳችሁት የኖቤል ሽልማት የሽልማችኋቸው ኢትዮጵያዊያን በትክክል የሚገባቸው ናቸው?

አቶ ግርማ፡- እኛ ያደረግነው በየዘርፋቸው ዓለምና ህዝቦቿን የሚታደግ ስራ የሰሩ ናቸው ያልናቸውን ሸልመናል። ለእያንዳንዱ የሽልማት ቅርፅ አደረጃጀት አለው። በመጀመሪያ ደረጃ ወደ ሽልማቱ ከመምጣታችን በፊት እጩ የምንሰበስብበት ሥርዓት አለን። ለከፍተኛ የክብር ሽልማት ደብዳቤ ይላክልናል እገሌ ይሸለም የሚል። ወይም በመገናኛ ብዙሃንና በተለያዩ መልክ በምናስተዋውቀው ላይ ሰዎች በሚሰጡን ጥቆማ ተነስተን እጩ እንመርጣለን። ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ የራሳችን ዲሲፕሊን አለን። በእጩነት የቀረቡ ሰዎች የእጩነት ደብዳቤ እንሰጣቸዋለን። ደብዳቤውን ተቀብለው ምላሽ ካልሰጡ ሽልማት አንሰጥም ምክንያቱም እጩዎቹ ደብዳቤ ስንሰጣቸው ደብዳቤውን ተቀብለው ወደ ቢሯችን መጥተው ፎርም መሙላት እና የህይወት ታሪካቸውንና ስራቸውን ዘርዝረው ወደ ድረገፃችን እንድናስገባ በተለያየ ኮፒ ማቅረብ የሚሉትን ጥያቄዎች ማሟላት አለባቸው። ከዚህ በተጨማሪም የምንሰራውን ስራ አምነው እና አክብረው መቀበል አለባቸው። ይህንን ስርዓት ላላሟሉ ድርጅታችን ሽልማቱን አይሰጥም። ለአትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ እና ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ሽልማቱን ያልሰጠነው የፃፍንላቸውን የእጩነት ደብዳቤ ተቀብለው መልስ ስላልሰጡ እና ተገቢውን የድርጅታችንን ዲሲፕሊን ስላልፈፀሙ ነው። ከዚህ በተረፈ ደግሞ ረዳት ፕ/ር ዘሪሁን አስፋው በሥነ ፅሁፍ ዘርፍ ላበረከተው አስተዋፅኦ ልንሸልመው ደብዳቤ ስንልክለት እኔ መሸለም የምፈልገው በሥነፅሁፍ ሳይሆን በአስተማሪነት ዘርፍ ነው ብሎ ደብዳቤያችንን መልሶልናል። ከዚህ ውጭ ግን እንደነገርኩህ ዓለምንና ህዝቦቿን የሚታደግ ስራ ለሰሩ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ እንሸልማለን። ዓለምንና ህዝቦቿን የሚታደግ ስራ ሲባል ምንድን ነው? ለሚለው አንተማማ፣ እንፈቃቀር፣ እንከባበር፣ አብረን እንኑር፣ በፍቅር በሰላም እንዋደድ የሚል ድርሰት ጽፈው ድምፃቸውን ተጠቅመው እያቀነቀኑ ህዝብን ሰላም የሚያደርጉ፣ ትዳርን በሰላም የሚያኖሩ፣ ልጆችን የሚያበረታቱ እና ማህበረሰብን የሚያንፁ ኢትዮጵያዊያን ይሸለማሉ።

በዚህ መሠረት የድርጅታችንን ሥርዓት የፈፀሙ እንደ ድምፃዊ አስቴር አወቀ፣ መሀሙድ አህመድ፣ ሙላቱ አስታጥቄ፣ እና ጤፍ አንድ ጊዜ ተዘርቶ አራት ጊዜ መብቀል እንደሚችል ያሳዩት አቶ ታለ ጌታ የከፍተኛ የክብር ሽልማት ተቀብለዋል። ሌሎቹም እንዲሁ።

በዚህ ሂደት ውስጥ የሚፈለገውን ያህል አልሰሩም ብለው የሚያምኑ ይኖራሉ። ይህ ደግሞ ሊፈጠር የሚችል ነው። እኛም ራሳችን በቦርድ ውስጥ ሽልማቱ አይገባቸውም ብለን የተከራከርንባቸው ሁለት ሰዎች ነበሩ።

ሰንደቅ፡- ድርጅታችሁ የከፍተኛ ክብር ሽልማት ሲያበረከት የተሸላሚዎችን ስራ (ሙያ) እና ማንነት (Personality) መሠረት አድርጎ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። ነገር ግን ከተሸለሙት መካከል ለታዳጊዎች አርአያ ሊሆን የማይችል ሰው እንደሸለማችሁ ይነገራል። ይህ ተገቢ ነው?

አቶ ግርማ፡- በነገራችን ላይ ሥራ እና ማንነት (Personal identity) መለየት መቻል አለብን። ሰዎች የራሳቸው ባህሪ (Identity) ሊኖራቸው ይችላል። እኛ ግን ትኩረት የምናደርገው በሥራቸው ላይ ነው። አንድ ሰው ዲሲፕሊኑ ጥሩ ካልሆነ እኛም ውስጥ በተወሰነ ደረጃ አንድ ሁለት ሰዎች አለመግባባት ላይ ደርሰን ነበር። አንዳንዶቹ ለዚህ ሽልማት ብቁ አይደሉም ብለን ተሟግተናል። የሆኖ ሆኖ ግን የሚፀድቀው የጋራ ድምፅ ስለሆነ ሰዎቹ ሊሸለሙ ችለዋል። እንደ መጀመሪያ ስህተት ሊገኝብን ይችላል ወደፊት ለምናከናውነው ተመሳሳይ ሽልማት የአሁኑ ትምህርት ይሆነናል።

ሰንደቅ፡- በአንድ ዓመት 64 ሰዎችን ሎሬት ብሎ መሸለም አልበዛም?

አቶ ግርማ፡- በመጀመሪያ ደረጃ ሎሬት ማለት ምን ማለት ነው? የሚለውን እንይ። ቀደም ባለው ዘመን ሎሬት የሚለው ቃል ትርጉም ጭንቅላታችን ላይ ገዝፎ ህዝባችንን በጣም ያስጨንቅ ስለነበር አሁንም በዛው ትርጉም ውስጥ ነው እየተሽከረከርን ያለነው እንጂ ኢትዮጵያ ከ96 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላት አገር ነች። በዚህ ሁሉ ህዝብ ውስጥ በተለያዬ ሙያ አንድ አንድ ሰው ቢሸለም ከ500 እና 600 በላይ ሎሬቶች ይኖረናል ማለት ነው። ነገር ግን ቀደም ባለው ዘመን ሽልማቱ ለጥበቡ ሰዎች ብቻ የሚሰጥ መስሎ ይታይ ስለነበር እና እነዛ ሶስት አራት ሰዎች ስሙን ሲጠሩበት ስለኖሩ ነው አሁን የበዛ የመሰለው። በእኛ እምነት ግን 64 የከፍተኛ ክብር ተሸላሚ (ሎሬት) መኖሩ ይበዛል ብለን አናስብም። ምክንያቱም አለማችን አርአያዎችን የመፍጠር ጉዳይ ስለሆነ ተሸላሚዎች ብዙ ተከታዮችን ማፍራት ያስችላቸዋል። ለምሳሌ ሩጫ ላይ ቀነኒሳን ስትሸልም፣ በጄኔቲክ ምህንድስና አቶ ታለ ጌታን ስትሸልም፣ ስዕል ላይ ሰዓሊ አፈወርቅ ተክሌን ስትሸልም እነሱ ከደረሱበት የክብር ልክ ላይ ለመድረስ የሚጥሩ ወጣቶችን ማብዛት ነው። ሌላው ችግር ሆኖ የታየው ለብዙ ዓመታት ሲሸለሙ የቆዩ ሰዎች አሁን እኛ ከላይ ወጣንና እኒህን ሰዎች መሸለም አለብን ብለን ስንሸልም መተውና መምረጥ እስኪያቅተን ድረስ በጣም ብዙ ነበሩ። የተከማቸ የተሸላሚ ብዛት ስለነበረ ነው የበዛ የመሰለው እንጂ ተሸላሚዎቹ በዝተው አይደለም። በሚቀጥለው ዓመት አስርም ላንሸልም እንችላለን። ነገር ግን ፊልም ውስጥ የምንሸልመው አጥተናል። ይህንን ሳትፅፈው ብትቀር ቅረ ይለኛል። ከዚያ በኋላ ነው ተጠርቶ እና ተጣርቶም ለውጥ አምጭ የፊልም ኢንዱስትሪ ባለሙያ እና ሲኒማ ቶግራፈር በሚሉ መስኮች የሸለምነው። ከዚያ ውጭ በፊልም ትወና፣ ድርስት እና በፊልም ጥራት ደረጃ የምንሸልመው አጣን።

ሰንደቅ፡- በፊልም ዘርፍ የምንሸልመው አጣን ብለው መቸገራችሁን ነግረውናል። ፕሮፌሰር ሀይሌ ገሪማ ባሉበት አገር ተሸላሚ አጣን ሲሉ መናገር አይከብድም?

አቶ ግርማ፡- በእርግጥ ጋሽ ሃይሌ በጣም የምናከብረው ጥሩ ፊልም ሰሪ ነው። ነገር ግን ጋሽ ሃይሌ ዜግነቱ አሜሪካዊ እንጂ ኢትዮጵያዊ አይደለም። እኛ ደግሞ ኢትዮጵያ ዜግነት ያላቸውን ሰዎች ለመሸለም ነው የተነሳነው። ኢትዮጵያዊ ዜግነት የሌለውን ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ አንሸልምም። ስለዚህ የሽልማት ደረጃችንን ከአገር አቀፍ ወደ አህጉር እና ዓለም አቀፍ ስናሳድግ ያን ጊዜ ጋሽ ሃይሌን ልንሸልም እንችላለን።

ሰንደቅ፡- ሽልማት ለመስጠት የሙያ መስክ እና የባለሙያ መረጃ እጥረት እንደገጠማችሁ ይነገራል። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትስ ይህን ችግር ለመቅረፍ አልተባበሯችሁም?

አቶ ግርማ፡- የእኛ ሀገር እኮ አስገራሚ ነው። በቀላሉ መረጃቸውን ከድረ-ገፅና ከመፅሀፍ ማግኘት የቻልነው የጥቂቶቹን ነው። ለምሳሌ እንደ ሙላቱ አስታጥቄ ያሉትን ሰዎች መረጃ ማግኘት አልተቸገርንም። በሌሎቹ ብዙ ተሸላሚዎች የገጠመን ችግር የግለሰቦቹን ታሪክ የያዘ መረጃ ከነፃ ኢንሳይክሎፒዲያ (free encyclopedia) ላይም ማግኘት አይቻልም።

ከዚህ በባሰ መልኩ ደግሞ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ውስጥ እኮ የግዕዝ ትምህርት ክፍል የሚያስተምረው ጀርመናዊ ፕሮፌሰር ነው። ይታይህ የራሳችንን ቋንቋ የባዕድ አገር ሰው አጥንቶ እኛኑ ያስተምረናል።

ድሮ እኛ የተማርንበት ISL ክፍል የነበረውን ሰነድ ሙሉ በሙሉ አስወጥቶ ውስጡን በቻይና ቋንቋ እና መረጃ ነው የሞላው። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንደዚህ ናቸው።

ሰንደቅ፡- ከኖቤል ሽልማቱ ማግስት ሰሞኑን በታዳጊዎች የሰጣችሁት የተሰጥኦ ውድድር ሽልማት ነበር። በዚህ ዘርፍ ስንት ሰው ቀርቦ ስንቶቹ ተሸለሙ?

አቶ ግርማ፡- በመጀመሪያ በ20 ዘርፎች 280 ተወዳዳሪዎች ቀርበው ከብዙ ማጣራት በኋላ 20ዎቹ ተሸልመዋል። ለምሳሌ በየተቋማቱ የሚገኘው የአስተያየት መስጫ ሳጥን አይነ ስውራንን እና ማንበብና መፃፍ የማይችሉ ሰዎችን ያገለለ ነበር። ይህን የተረዳው ታምሩ ካሳ የተባለ ወጣት አስተያየት መስጫን በድምፅ ቀይሮ ተግባራዊ የሚያደርግ ፈጠራ ይዞ መጥቶ ተሸልሟል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ “የኦሮሞ እና የአማራ ህዝብ አንድነት” የሚለውን የፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳን መፅሀፍ ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ የመለሱት መምህር አብርሃም በዝብዜ ሌላው ተሸላሚ ናቸው። ሌሎቹም እንዲሁ የፈጠራ ችሎታ እና ብቃት የተሸለሙ ናቸው።

እስካሁን ከሸለምናቸው ሽልማቶች በተጨማሪም በየክልሎቹ በአካባቢያቸው ላሉ ትውፊቶች ህልውና መቆየት አስተዋፅኦ ያደረጉ ሰዎችን የምንሸልምበት ፕሮግራም አዘጋጅተናል። በቅርቡ ወደ ሥራ የምንገባ ይሆናል።         

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
15729 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1081 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us