ዓመት በዓል እና የጥበብ ባለሙያዎች በኢትዮጵያ

Wednesday, 03 January 2018 16:52

በይርጋ አበበ

 

የፊታችን እሁድ ታህሳስ 29 ቀን 2010 ዓ.ም በመላው የክርስትና ኃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረውን የገና በዓል (የእየሱስ ክርስቶስ ልደት) ጨምሮ በኢትዮጵያ በርከት ያሉ ህዝባዊ እና ኃይማኖታዊ በዓላት ይከበራሉ። እነዚህን ኃይማኖታዊ በዓላት (በክርስትና እና በእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች የሚከበሩትን) ተከትሎ የተለያዩ ክንውኖች ይካሄዳሉ።


አንዳንዶቹ ክንውኖች የአገሪቱ ባህል እና በአላትን የሚያከብሩት አብያተ እምነቶች አስተምህሮት ውጭ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ከወጭ በተለይም ከውጭ ምንዛሬ እና ሥነ-ህብረተሰባዊ ግንኙነት የተቃረኑ ክስተቶች ይከናወናሉ። ዛሬ ግን ትኩረት ሰጥተን ልንመለከተው የወደድነው ዓመት በዓላትን ተከትሎ የአርቲስቶች እና የመገናኛ ብዙሃን ሚና ምን ሊመስል ይገባዋል? የሚለውን ሲሆን ለዚህ ጥያቄ ሃሳቡን እንዲያካፍለን የጋበዝነው የፊልም ባለሙያውን ያሬድ ሹመቴን ነው። የፊልም ባለሙያው ላነሳንለት ጥያቄዎች የሰጠንን ምላሽ ለአንባቢያን በሚመች መልኩ ከዚህ በታች አቅርበነዋል።


ሰንደቅ፡- ዓመት በዓላት እና የኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን ግንኙነት እንዴት ታየዋለህ?


ያሬድ፡- በኢትዮጵያ በዓል እና ባህል ተቆራኝተዋል ብዬ ነው የማስበው። ምክንያቱም አለባበሳችን ብትመለከት ዓመቱን ሙሉ የማንለብሳቸውን የባህል ልብሶቻችንን የምንለብሰው የበዓል ሰሞን ነው፤ መገናኛ ብዙሃንን ስትመለከትም የሚያስተላልፏቸው ሙዚቃዎች የባህል ዘፈኖችን በበዓል ሰሞን ነው፤ ድምፃዊያኑም አልበም የሚያወጡት በዓላትን ተመርኩዘው ነው። ለዚህ ነው በአገራችን በዓላት ባህልን አጣምረው የሚመጡ ናቸው የምለው። ስለዚህ የአንድን ማህበረሰብ ባህል ለማጥናት የበዓል አከባበሩን አውድ ማየት ያስፈልጋል።


በኢትዮጵያ ህዝባዊ እና ኃይማኖታዊ የሚባሉ ሁለት ዓይነት በዓላት አሉ። በእስልምናም ሆነ በክርስትና ኃይማኖት ተከታዮች የሚከበሩትና በካላንደር እውቅና የተሰጣቸው ኃይማኖታዊ ስንላቸው እንደ የካቲት 12 እና የካቲት 23 ያሉትን ደግሞ ህዝባዊ በዓላት ሊባሉ ይችላሉ። ዘመን መለወጫም ቀደም ባሉት ዘመናት ኃይማኖታዊ መልክ ቢኖረውም በዚህ ዘመን ግን ህዝባዊ በዓል ነው።


ከዚህ ጋር በተያያዘ ለምሳሌ ሰሞኑን የምናከብረው የገና በዓል ኃይማኖታዊ በዓል ቢሆንም በቅርስነት ሊታዩ የሚችሉ አገራዊ የባህል ትዕይንቶችና ዜማዎች የሚስተዋሉበት በዓል ነው። ዜማዎቹም ሆነ የገና ጨዋታዎች ከክርስቶስ መወለድ ጋር የሚያገናኛቸው ነገር አይኖርም ምናልባት ሚስጢር ካለ ምስጢሩ እስኪፈታ ድረስ።


የአገራችን አርቲስቶች በተለይም ድምጻዊኑ ከበዓላት ጋር ጠንካራ ቁርኝት አላቸው። በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ የሙዚቃ ቅኝቶች በስፋት የምንሰማውም በበአላት ወቅት ነው። ከዚያ ውጭ ደግሞ በአላት በኢትዮጵያ በሚከበሩበት ጊዜ ከህዝቡ አእምሮ ጋር የተቆራኙ ሙዚቃዎች አሉ። ለምሳሌ አዲስ ዓመት ሲመጣ ድምፃዊት ዘሪቱ.. “እንቁጣጣሽ” በሚለው ዜማ፣ ገና ሲመጣ ፍሬው ኃይሉ እንዲሁም ፋሲካ ሲመጣ ታደሰ አለሙ (ሚሻሚሾ) አብረው የሚነሱ ድምፃዊያን ናቸው። ይህ አጋጣሚ ግን በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በውጭው ዓለምም ይታያል። ለምሳሌ ልደት ሲከበር “መልካም ልደት (Happy birthday)” የሚለው ዜማ መቶ ዓመታትን የተሻገረ ዜማ ነው። የገና በዓልን የሚያከብሩበት ዜማም እንዲሁ ዘመናትን የተሻገረ ነው።


ሰንደቅ፡- በዓላት እና ባህል ግንኙነት አላቸው ብለሃል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የኢትዮጵያ ባህል ያልሆኑ የውጭ ባህሎች ለምሳሌ የገናዛፍ የሚባለው የበዓል ማድመቂያ ሆኖ መቅረቡን የኃይማኖት መሪዎችም ሆኑ ምሁራን ይገልጻሉ። ይህን የመሰለ አወዛጋቢ የበዓል አከባበርን ለማስወገድ የአርቲስቶቹም ሆነ የመገናኛ ብዙሃኑ ሚና ምን መሆን አለበት?


ያሬድ፡- በኢትዮጵያ የሚከበሩ ኃይማኖታዊ በዓላት ከዋናዎቹ በዓላት ቀደም ብሎ የበአላቱ ድባብ አድማቂ ሁኔታዎች አሉ። ለምሳሌ የፋሲካ በዓልን ብንመለከት ከጉልባን፣ ሚሻሚሾ እና ዘንባባ ማሰር ጀምሮ ያሉት ቅድመ በዓላት ድባቦች ስለ ፋሲካ በዓል እንድናስብ የሚያደርጉ ናቸው። በገና በዓል ግን ይህ ቅድመ በዓል ድባብ የለም። በመሆኑም በዓሉን ለማክበር አንዳንድ ሰሞን በዓላቱ ከውጭ የተቀዱ ይመስለኛል። የውጮቹ ደግሞ የገና በዓለን የሚያከብሩት እኛ ፋሲካን እንደምናከብረው በከፍተኛ ድምቀት ነው። ስጦታዎችን የሚቀያየሩበትም ሆነ ዘመድ አዝማድ የሚጠያየቁት በገና በዓል ነው። በዚህ የተነሳም የበዓሉ ድባብ የደመቀ ይሆናል።


ወደኛ ስንመጣ ደግሞ እንደ ሌሎቹ ኃይማኖታዊ በዓላት የገናን በዓል በሰሞነ በዓል ድባብ አድምቀን አክብረን እንድናልፍ የሚያደርግ ትውፊት የለንም። ይህንን ስል ግን ቀድሞ አልነበረም እያልኩ አይደለም። ቀድሞ እንደነበረ የሚያመላክተው ርዝራዥ መኖሩ ነው። ለምሳሌ የገና በዓል ጨዋታ እና የገና በዓለ ዜማ ቀደም ባሉት ዘመናት የገና በዓለ ማድመቂያ ሰሞነ በአላት ነበሩ። አሁን ጠፉ እንጂ። እነዛ ከጠፉ በአሉን በቅድመ በዓል ድባብ ለማድመቅ ከሌላ ቦታ አምጥቶ ለመሙላት ሲባል ነው የገና ዛፍ የመጣው።


ሰንደቅ፡- የጎደለንን ለመሙላት ከበአድ መዋሱን በአገር በቀል ለመተካት የመገናኛ ብዙሃንና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ያልሰሩት የቤት ስራ እንዳለ አትመለከትም?


ያሬድ፡- የገና ዛፍን በተመለከተ አሁን አሁን በፕላስቲክ ዛፍ ከመተካቱ በፊት ትክክለኛው የጽድ ዛፍ እየተቆረጠ ነበር የሚከበረው። ለምሳሌ አሁን ከኔ ቤት የገና ዛፍ ባይኖርም ልጅ እያለሁ ግን ከመኖሪያ ሰፈሬ ሀብተጊዮርጊስ ድልድይ እስከ ዘነበ ወርቅ ድረስ ሄደን ዛፍ ቆርጠን ነበር በአልን የምናከብረው። አሁን ግን በአሉን የማይገልፅ መሆኑ ስለገባኝ ከቤቴ የገና ዛፍ የለም። ዛፉ የውጭ በአል ማክበሪያ እንጂ የእኛ አይደለም ካልን የእኛ እንዲሆን ብናደርገው ምን ይጠቅመናል ስንል ጥቅም የለውም። መጥቀም አይደለም ጭራሽ ጎጂ ነው። ምክንያቱም እውነተኛውን ዛፍ ከቆረጥን በደን ሀብት ላይ አሉታዊ አስተዋፅኦ (የደን መመናመን) ሲያመጣ አርተፊሻሉን እንጠቀም ካለን ደግሞ የውጭ ምንዛሬን ጭምር በመጋፋት በኢኮኖሚው ላይ ጫና ያሳድራል። ለምሳሌ ባለፈው ዓመት በተካሄደ አንድ ጥናት በኢትዮጵያ በአላትን ለማክበር ብቻ ከውጭ የገቡ ሸቀጦች ዋጋ 28 ሚሊዮን ዶላር የወጣባቸው መሆኑን አመልክቷል።


ለምሳሌ ህዳር 12 ቀን የሚከበረው ህዳር ሲታጠን የሚባለው ባህል ንጽህናን ለማምጣት ግንዛቤ ስለሚፈጥር ሊበረታታ ይገባል። ነገር ግን ቆሻሻን ማቃጠሉ በአካባቢ ብክለት ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ ስለሆነ ዘመኑ ባፈራው የቆሻሻ ማስወገድ መንገድ (waste management) እንዲስማማ አድርጎ ባህሉን ማክበር ተገቢ ነው። ይህ ግን በዘመን ልክ የመስፋት የቤት ስራ ይጠይቃል።


በምንም ሆነ በምን መንገድ ከውጭ ተፅዕኖ መውጣት አልቻልንም እንጂ የገና በአል አከባበርንም በሚስማማን መንገድ ለማክበር ከገና ዛፍ የተሻለ ነገር ማምጣት ካልተቻለ በማውገዝ ብቻ ልታጠፋው አትችልም። ስለዚህ በተስማሚ ነገር ወደመቀየር ነው መሄድ ያለብን። ለምሳሌ የገና ጨዋታ ባህላዊ ስፖርት ስለሆነ የገና ዛፍን ሊተካ ይችላል ወይ? የሚለው ራሱ ብዙ ጥያቄዎች አሉ። ሰው በሚያየውና በሚወደው ልክ እንዲካሄድ ምን መደረግ አለበት የሚለው ትልቅ የቤት ሥራ ነው።


ሰንደቅ፡- የውጭ አገራት የበአላት አከባበር ድባቦች ወደ አገራችን ከገቡ ቆይተዋል። እነዚህ ቅድመ እና ድህረ በዓል አከባበር ሂደቶች ግን አመሰራረታቸውም ጥያቄ ይነሳባቸዋል። በዚህ ላይ ያንተ አረዳድ ምንድን ነው?


ያሬድ፡- በፈረንጆቹ አቆጣጠር 2010 የበዓል ሰሞን ለስራ ጉዳይ አሜሪካ ሄጄ ነበር። በዚያ ቆይታዬ ያስተዋልኩት ነገር ብዙዎቹ በአላትና የበዓል አከባበር ስርዓቶች የተፈጠሩት እና እውቅና ተሰጥቷቸው ሲተዋወቁ የምናቸው በስራ ፈጣሪዎች (Entrepreneurs) ነው። ምክንያቱ ደግሞ በአላቱ የገቢ ምንጭነት ስላላቸው ነው። ለምሳሌ ቫላንታይን ቀን ብለው ቀይ ልብስ እና አበባ ሲሸጡ ይውላሉ። ልደት ስታከብርም የሚገዛው እቃ በሙሉ ከውጭ አገር የሚመጣ ነው። ስለዚህ በአገራችን በአላትን ስናከብር የሰው አገር ባህልን ብቻ ሳይሆን የእነሱን ኢኮኖሚም እያሳደግን እንደሆነ ነው የማስበው። እነሱ በበአሉ ውስጥ የኢኮኖሚ ጥቅማቸውን አስተሳስረው ነው የሚሄዱት። እኛ ደግሞ በአላትን ስናከብር ሁሉንም እቃ የምንገዛው ከውጭ በመሆኑ ብዙ ገንዘብ ከኢትዮጵያ የሚወጣበት ስለሆነ ኢኮኖሚውን (የአገርን ኢኮኖሚ) ቁልቁለት ነው የሚወስደው። ስለዚህ ማወቅ ያለብን በአልን ስናከብር ይህን ሁሉ ታሳቢ እያደረግን መሆን አለብን። ለዚህ ደግሞ የሚዲያው እና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ሚና ላቅ ያለ እንደሚሆን ግልጽ ነው። በተረፈ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መልካም የገና በዓል እንዲሆንልን እመኛለሁ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
15760 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 977 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us