ለትዳር ችግሮች “የትዳር ክትባት” ምን ይዞ መጣ?

Wednesday, 17 January 2018 13:28

 

በይርጋ አበበ

የመፅሀፉ ርዕስ - የትዳር ክትባት

ደራሲ (ፀሐፊ) - መጋቢ ዳኛቸው ኃይሉ

ህትመት      - ሀብታሙ ህትመትና ኤቨንት

የገጽ ብዛት    - 122

ዘውግ        - የትዳር ሥነልቦና (መንፈሳዊነት ያደላበት)

ዋጋ          - 50 ብር ለኢትዮጵያ፤ 10 ዶላር ከኢትዮጵያ ውጭ

መጋቢ ዳኛቸው ኃይሉ ባለ ትዳርና የልጅ አባት ሲሆኑ በአንድ ቤተአምልኮ ውስጥም መንፈሳዊ አሰተምህሮትን ሰባኪ ናቸው። በዚህ የመንፈሳዊ አገልግሎት ዘመናቸው ውስጥ ደጋግመው ስለቤተሰብ (ሶስት ጉልቻ) ማስተማራቸውን የተመለከቱ የእምነቱ ተካፋዮች “በመጽሐፍ መልክ ብታዘጋጀው ብዙ ህዝብ ታስተምርበታለህ ስላሉኝ ለህትመት አበቃሁት” ሲሉ ስለመጽሀፋቸው ዝግጅት ይገልፃሉ።

የመፅሐፉ አዘጋጅ በዘመናችን ትዳር በተደጋጋሚ እና በስፋት መፍረስ የበዛው ትዳሩ ባለመከተቡ ነው” ሲሉም ይገልጻሉ። የአስተምህሮታቸውን ማዕከላዊ ነጥብ መፅሐፍ ቅዱስ ላይ አድርገው ተጨማሪ የትዳር ስነ-ልቦና መፅሐፎችንም ተጠቅመው ያዘጋጁት መፅሐፍ እንደሆነ ወደ ውስጥ ስንገባ የምናገኘው እውነታ ነው።

“እናም” ይላሉ የመጽሀፉ አዘጋጅ መጋቢ ዳኛቸው፤ “የጋብቻ በረከት የማስተዳደሪያ እውቀት ይፈልጋል። የተሰጠንን በረከት ከእኛ ማንነት በላይ ከሆነ እና የተሰጠንን በረከት በእውቀት መምራት ካልቻልን እኛን ይገዛናል። ጋብቻን በሚያህል ትልቅ የእግዚአብሔር ስርዓት ውስጥ የምናስተዳድርበት እውቀት ያስፈልገናል ማለት ነው” ይላል በገጽ 1 ላይ። አዘጋጁ ሀሳባቸውን ሲያጠናክሩም “አንድ ሰው መኪና ከመንዳቱ በፊት መኪናውን የሚነዳበት እውቀት ወይም መኪናውን የሚነዳበት እውቅና ያስፈልገዋል። ይህንንም ፈቃድ የምናገኘው ከእውቀት በኋላ ነው። በመንጃ ፈቃድ ትምህርት ቤት የምናገኘው እውቀት የሚረዳን መኪናውን እንዴት በአግባቡ መንዳት እንዳለብን ብቻ ሳይሆን፤ በመንገድ ላይ ያሉ የመንገድ ስርዓቶችን፣ ምልክቶችንና የመሳሰሉትን ህጎችን እንድናውቅ ነው። በአሁኑ ሰዓት በአብዛኛው የሚከሰቱት የመኪና አደጋዎች መንስኤያቸው ያለ መንጃ ፈቃድ፣ ወይንም እውቀቱ በሌላቸው አሽከርካሪዎችና ወይንም ህጋዊ የሆነ መንጃ ፈቃድ በሌላቸው አሽከርካሪዎች በሚነዱ መኪናዎች የሚከሰት ነው።” ሲሉ ከጋብቻ በፊት ሊደረግ ስለሚገባው ጥንቃቄ እና ዝግጅት በምሳሌ ያስቀምጣሉ።

የክትባቱ ሂደት

ክትባት ከቃሉ እንደምንረዳው ሊመጣ ከሚችል ወረርሽኝ ወይም ሌላ በሽታ እንዳንጠቃ መከላከያ መድሃኒት መውሰድ ነው። መጋቢ ዳኛቸው ሃይሉ ደግሞ ጋብቻ የማህበረሰብ፣ የህብረተሰብ፣ የህዝብ እና የአገር መሰረት በመሆኑ ክትባት ያስፈልገዋል ሲሉ ያምናሉ። ለዚህ ደግሞ የትዳር ክትባት መፅሐፍ መዘጋጀቱን ገልጸዋል። እናም ወደ ትዳር የሚፈጥኑ እግሮች (ተጋቢዎች) ከጋብቻ በፊት ክትባት ሊወስዱ ይገባል ይላሉ።

“ክትባት ማለት አንድን በሽታ ለመከላከል ወይንም በበሽታው ሳንጠቃ የሚደረግ ቅድመ ጥንቃቄ ማለት ነው። ይህም ማለት በሽታው ከተፈጠረ በኋላ ሳይሆን ሳይፈጠር በፊት የበሽታውን /Antigen/ በመክተብ ወይም በመውሰድ ሰውነታችን ለበሽታው የሚሆን የመከላከል አቅም /Antibody/ እንዲገነባ ያደርጋል። ይህም ማለት ለበሽታው በምንጋለጥበት ጊዜ ሰውነታችን አስቀድሞ በሽታውን የመከላከል አቅም ስላጎለበተ በበሽታው አይጠቃም። ሁለተኛው የክትባት አይነት ሰውነታችን በበሽታው ቢያዝም ለተጓዳኝ በሽታዎች ሰውነታችን እንዳይጋለጥ የሰውነታችንን በሽታ የመከላከል አቅም /Antibody/ ያዳብራል።” ሲሉ የሚናገሩት መጋቢ ዳኛቸው ሃይሉ፤ ሂደቱን ሲገልፁም “ጋብቻችንን ከሚያሳምሙና መልካም እንዳይሆን ከሚያደርጉ ጉዳቶች በጋብቻ እውቀት ክትባት ቀድመን መከላከል እንችላለን። በክትባት ነገ ሊከሰት ያለውን የጋብቻ ተግዳሮት መከላከል ይቻላል ማለት ነው። ከዚህም ከእግዚአብሔር መንግሥት ስርዓት አንዱ ፀሎት ነው።” ሲሉ በመንፈሳዊ መንገድ የሚሰጥን ክትባት በምክረ ሀሳብነት አቅርበዋል።

የትዳር ክትባት በትዳር ውስጥ

መጋቢ ዳኛቸው በክትባት ዳብሮ ወደ ጋብቻ የገባን ትዳር ችግር ሊገጥመው ቢችል እንኳን ሊደረጉ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች ምክረ ሀሳብ አቅርበዋል። ምክረ ሀሳቡንም “ጋብቻ እና ተሃድሶ” ሲሉ ይገልፁታል። በዚህ ዘመን በፖለቲካው ዓለም ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ የገጠመውን ውስጣዊና ውጫዊ ችግር (ህዝባዊ ተቃውሞ እና ግጭት) ለመፍታት ራሱን ተሃድሶ ውስጥ አስገብቶ መቆየቱን ደጋግሞ ገልጿል። ከዚህ የተነሳም “ተሀድሶ” የሚለው ቃል ፖለቲካዊ መልክ ተላብሶ የሚገኝ ቢመስልም መጋቢ ዳኛቸው ግን “ጥገና” በሚል ትርጉሙ የተመለከቱት ይመስላል።

ለተሃድሶ የሰጡት ትርጉምም “ተሃድሶ የማያስፈልገው የህይወት ክፍል ወይም ስርዓት የለም። ተሃድሶ ማለት አንድን ያረጀ የቀደመ ጉልበቱን፣ ውበቱን፣ ይዘቱን ያጣን ነገር ወደ ቀድሞ ኃይሉና ይዘቱ ወይንም ቀድሞ እንደነበረው ወደ ጥንተ ተፈጥሮ /Original State/ መመለስ ማለት ነው ወይም ደግሞ በመጀመሪያ ሰሪው እንደሰራው ካልሆነ፣ ሰሪው እንዳስቀመጠው ያልተቀመጠ አንድን ስርዓት ወደ መጀመሪያው ሰሪው ወደ ሰራበትና ወደ አስቀመጠው ወደ ተፈጠረበት /ጥንተ ተፈጥሮ/ መመለስ ማለት ነው።” ይላሉ። ገጽ 17

እንደ ፀሀፊው እምነትም ለጋብቻ በየጊዜው ተሃድሶ ማድረግ ትዳርን ከመፍረስ መታደግ ይችላል። በዚህ ጉዳይ ሃሳባቸውን ሲያጠናክሩም “ከላይ በመግቢያችን ላይ ተሃድሶ የማያስፈልገው የህይወት ክፍል ወይም ስርዓት እንደሌለ ለመጥቀስ ሞክረናል። ይህም ማለት በማንኛውም ዘርፍ ማለትም ኢኮኖሚው፣ ፖለቲካውና ማህበራዊው ህይወቱ በሙሉ ተሃድሶ ያስፈልገዋል። ምክንያቱም እኛ በእያንዳንዱ የህይወት እንቅስቃሴያችን ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የኢኮኖሚው፣ የፖለቲካውና የማህበራዊው ህይወት ድምር ውጤቶች ስለሆንን ነው። ነገር ግን ከእነዚህ መካከል በተለየ መልኩ ተሃድሶ የሚያስፈልገው ክፍል ማህበራዊ ህይወታችን ነው። በዚህ ማህበራዊ ህይወት ውስጥ ዋና መሠረት የሆነው ደግሞ ቤተሰብ ነው። ስለዚህ ሌሎቹን ማደስ የምንችለው ቤተሰብን ስናድስ ነው። ቤተሰብ ደግሞ የሚታደሰው የቤተሰቡ መሠረት የሆነው ጋብቻ ሲታደስ ነው። ቤተሰብ ሲታደስ ህብረተሰብ ይታደሳል፣ ህብረተሰብ ሲታደስ ደግሞ ሀገር ይታደሳል። ስለሆነም የጋብቻ መታደስ የማያድሰው ስርዓትና ክፍል የለም።” ሲሉ በጋብቻ ውስጥ ስለሚደረግ ግንኙነት ይናገራሉ። ይህ አስተምህሮታቸው ግን ዋና መሳሪያው መፅሐፍ ቅዱስ እንደሆነ መፅሀፋቸው ላይ ተገልጿል።

የትዳር ክትባት እንከኖች

መፅሀፉ ገፁ አነስተኛ ዋጋውም ዳጎስ ያለ ቢሆንም፤ ይዘቱ ጎላ ያለ ጠቀሜታውም ላቅ ያለ ነው። ሆኖም በመፅሐፉ ውስጥ የተመለከትናቸው ችግሮች ስላሉ በእነዚያ ክፍሎች ላይ የተወሰኑትን ከዚህ በታች እንመለከታለን።

የመፅሀፉ የመጀመሪያ ድክመት መግቢያው እና ምስጋና የተቸራቸው አካላትን የያዙት ክፍሎች ከማውጫው ቀድመው መቀመጣቸው ነው። ይህ መሆን አልነበረበትም። ምክንያቱም ምስጋናውም ሆነ መግቢያው የመፅሐፉ ክፍሎች በመሆናቸው ከማውጫው ቀድመው መቀመጣቸው “ከግንዱ የተገነጠለ ቅርንጫፍ” ያስመስላቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ከሥነ-ፅሁፍ እና ከቋንቋ አኳያ ካየነው በተለይ የፊደላት ግድፈት እና የሀሳብ ፍሰቱ ጥሩ አይደለም። በርካታ ቦታዎች ላይ የፊደላት ግድፈት እና የፊደላት አጠቃቀም ችግር (ለምሳሌ ጅ፣ ጂ፣ ኃ፣ ሀ፣ ሼ፣ሸ…) የተቀመጡበት መንገድ በተገቢው ድምጸታቸው ሳይሆን ፀሐፊው በተመቻቸው መንገድ ነው ያስቀመጧቸው።

ከዚህም ሁሉ በላይ የባሰው የመፅሀፉ ችግር ሆኖ ያገኘሁት መላው የቋንቋው አንባቢ (አማርኛ) ኢትዮጵያዊያን በሙሉ በፈለጉት መፅሀፍት መደብሮች ገዝተው እንዳያነቡት መጋቢ ዳኛቸው በሩን ዘግተውባቸዋል። ቤተሰብ፣ ማህበረሰብ፣ ህዝብ፣ አገር እያለ በሚያድገው የሰዎች ስብስብ ውስጥ ጋብቻ ቁልፍ ሚና ይጫወታል። ይህ ተቋም ደግሞ ሃይማኖታዊ አጥር ሳይደረግበት ለሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ምክረ ሃሳብ ሊሰጥበት የሚገባ ቢሆንም መጋቢ ዳኛቸው ኃይሉ ግን መፅሃፋቸውንም ሆነ የመጽሀፉን ሃሳብ ለእምነቱ ተከታዮች ብቻ ማበርከታቸው ተገቢ ነው ብዬ አላምንም።

ሁለተኛው እትም የሚቀጥል ከሆነ የበዛውን መንፈሳዊነት ወደማህበራዊነት በማድላት እና የተጠቀሱ አብይ ድክመቶች ታርመው ቢቀርቡ መልካም ነው። ከዚህ በተረፈ ግን መፅሐፉ በርካታ ምክረ ሰናይ ሃሳቦችን የያዘ መጽሀፍ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።   

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
15804 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 884 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us