የማንያዘዋል እንደሻው “የመስቀል ወፍ”

Wednesday, 31 January 2018 12:44

 

 

በይርጋ አበበ

 

የቴአትሩ ርዕስ የመስቀል ወፍ
ደራሲ በርናብድ ስሌድ
ተርጓሚ (ውርስ ትርጉም) አንዷለም ውብሸት (አቡቲ)
አዘጋጅ ማንያዘዋል እንደሻው
ረዳት አዘጋጅ ሜሮን ሲሳይ
ተዋንያን አላዛር ሳሙኤል፣ ህሊና ሲሳይ፣ መስከረም አበራ እና ዓለም ሰገድ አሰፋ
አስተባባሪ ኤፍሬም ልሳኑ
የቴአትሩ ዘውግ ትራጄይ ኮሜዲ

ከአስር በላይ ፊልሞችን እና የመድረክ ቴአትሮችን በማዘጋጀት የሚታወቅ ቢሆንም ከሁሉም ዝግጅቶቹ ጀርባ ስሙ ነግሶ ይወጣል እንጂ በሁሉም አልተወነባቸውም። በቅርቡ በእንግሊዝኛ ታትሞ ለንባብ የበቃውን ‹‹እንግዳ›› የተባለውን ቴአትር ጨምሮ የሼክስፒር ድርሰት የሆኑትን ጁሊየስ ቄሳር እና ሃምሌትን በቴአትር ተዘጋጅተው ለህዝብ የቀረቡት በእሱ የዝግጅት ሙያ ነው። ማክቤልን እና ንጉስ አርማህንም አዘጋጅቶ ለመድረክ አብቅቷል። ዴዝዴሞና፣ አባትዬው፣ ሰናይት እና ሌሎች ፊልሞችንም ዳይሬክተር የሆነባቸው ፊልሞች ናቸው። ይህን ሁሉ አዘጋጅቶ ለህዝብ ያቀረበው ማንያዘዋል እንደሻው ነው።


ማንያዘዋል እንደሻው በየሳምንቱ እሁድ አመሻሹ ላይ በአዲስ አበባ ባህልና ቴአትር አዳራሽ (በተለምዶ አዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት) ለእይታ የበቃ አዲስ ቴአትር ይዞ መጥቷል። በአሜሪካዊው በርናብድ ስሌድ ተደርሶ በአንዷለም ውብሸት በውርስ ትርጉም የቀረበ ቴአትር ነው የመስቀል ወፍ። በ1960ዎቹ በአሜሪካዊው ግዙፍ የፊልም ኢንዱስትሪ (ሆሊውድ) ተዋንያን ፊልም የተሰራበትን ድርሰት ወደ አማርኛ ተመልሶ የተዘጋጀው የመስቀል ወፍ ቴአትር በሁለት ሰዎች ድብቅ የፍቅር ህይወት ላይ የሚያተኩር ሲሆን በአራት ትዕይንት የቀረበ ነው። በቴአትሩ ላይ የሚያተኩር የዳሰሳ ዘገባ ከዚህ በታች አቅርበናል።

ቴአትር፣ ቴአትር ቤቶችና ተመልካቾች በአዲስ አበባ


ከአምስት እስከ ሰባት ሚሊዮን ህዝብ ይኖርባታል ተብላ የምትገመተው አዲስ አበባ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የመጠጥ ቤቶችና የጫት መሸጫ ቤቶች ቢኖሯትም የመዝናኛ ማዕከላት ቁጥር አሁንም አነስተኛ ነው። አዲስ አበባ አንጋፋዎቹን አገር ፍቅር እና ብሔራዊ ቴአትር ቤትን ጨምሮ ከአምስት ያልበለጡ ቴአትር ቤቶች ብቻ ነው ያላት። ይህ ለምን ሆነ? ሰፊ ጥናትና በባለጉዳዮቹ (በባለቤቶቹ) ምላሽ የሚሰጠው ጥያቄ ነው። ሆኖም በከተማዋ የሚኖረው የህዝብ ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ስናስብ እንዲሁም የአርቲስቶች ቁጥር ብዙ መሆኑ ከግምት ሲገባ የቴአትር ቤቶች ቁጥር አነስተኛ መሆኑ ግን ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም።


የቴአትር ቤቶች እጥረት መኖሩን ከላይ ከገለጽን በከተማዋ የቴአትር ተመልካቾችን ሁኔታ ደግሞ ለማየት ስንሞክር ጉራማይሌ መልስ እናገኛለን። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተለምዷዊ የትራጄዲ እና መደበኛ ይዘት ካለው ዘውግ ይልቅ ወደ ኮሜዲ የሚያደሉ ይዘት ያላቸው የጥበብ ስራዎች (ፊልም፣ ድራማ እና ቴአትር) ለህዝቡ የቀረቡለት አማራጮች የሆኑ መስላል። ይህ መሆኑ ደግሞ ተመልካቹ ለአንድ ወቅት በብዛት ወደ ቴአትር ቤቶች ሲጎርፍ ቢታይም እየቆየ ደግሞ ከቴአትር ቤት በራፍ መራቅ ጀመረ።


የመግቢያ ዋጋው አነስተኛ መሆኑ የቴአትሩን ዋና ባለቤቶች (አርቲስቶቹን) ማስከፋቱ የሚነገርለት የኢትዮጵያ ቴአትር ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ደግሞ በየቴአትር ቤቶቹ በራፍ የህዝብ መንጋ ተሰልፎ መታየቱ እየተለመደ መጥቷል። ተመልካቹ በሚፈልገውና እሱን በሚመጥነው ልክ ቴአትሮች እየተሰሩ ነው ወይ? ሁሉም ስራዎች ከደረጃ በታች ናቸው ብሎ መደምደም ባይቻልም ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ የመድረክ ስራዎች ገበያ ተኮር ስለሆኑ ተመልካችን ማሰልቸታቸው አይቀርም። ሆኖም ለኢትዮጵያ ተመልካች ብቻ ሳይሆን የሚሰሩበት አማርኛ ቋንቋ በሌሎች ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ቢሰሩ ዓለም አቀፍ ታዳሚን ማስደሰት የሚችሉ ስራዎችና ብቃት ያላቸው አርቲስቶች መኖራቸው አይካድም። እንደ ወጋየሁ ንጋቱ፣ አበራ ጆሮ እና ደበበ እሸቱን ያፈራው የአገራችን የጥበብ ኢንዱስትሪ በዚህ ዘመንም እንደ ግሩም ዘነበ (እያዩ ፈንገስ)፣ ሽመልስ አበራ ጆሮ፣ አበበ ተምትም፣ ዓለማየሁ ታደሰ እና ሱራፌል ተካን የመሳሰሉ አርቲስቶች፤ እንዲሁም እንደ ስናፍቅሽ ተስፋዬ፣ ባዩሽ አለማየሁ፣ ህንጸተ ታደሰ እና የመሳሰሉትን ኮከብ አርቲስቶችን ማፍራት የቻለ ሙያ ነው። በዚህ ስሌት ስንለካው የአዲስ አበባ ቴአትር እና ተመልካች ደረጃቸው ተቀራራቢ ሆኖ እናገኘዋለን። ቴአትሮቹን በቂ ህዝብ እየተመለከታቸው ነው ወይ? የሚለው ደግሞ ሌላ ጥያቄ ነው። በአዲስ አበባ የቴአትር፣ ቴአትር ቤቶች እና የቴአትር ተመልካቾች ግንኙነት ከዚህ በላይ ባለው መልኩ ነው ብለን ካሰብን ማንያዘዋል እንደሻው ይዞልን የመጣው ‹‹የመስቀል ወፍ›› ምን ይመስላል? የሚለውን ደግሞ ከዚህ በታች እናየዋለን።

 

በገና ማግስት የመጣችው የመስቀል ወፍ

“ማን ያውቃል የመስቀል ወፍ እና የአደይ አበባ፤
ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ

 

ተብሎ ቢቀኝም ማንያዘዋል እንደሻው ግን “በገና ጨዋታ፤ አይቆጡም ጌታ” በሚባልበት ወቅት የመስቀል ወፍ ይዞ ብቅ ብሏል። በዚህ መሰረትም ቴአትሩ ለምን በዚህ ወቅት መጣ ተብሎ ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ለዚህ መልስ የሚሰጠው አዘጋጁ ማንያዘዋል እንደሻው፤ ቴአትሩን አዘጋጅቶ ለማጠናቀቅ ስድስት ወራት እንደፈጀበት ይናገራል። ዝግጅቱ ይህን ያህል ጊዜ እንዴት ሊወስድ ቻለ ለሚለው ጥያቄ መልስ ሲሰጥም “ወጣ ገባ እያልኩ ስለሰራሁት ነው” ሲል መልሳል። ይህም ማለት የገና በዓል ማግስት በልዩ ፕሮግራም ተጀምሮ ባሳለፍነው ሳምንት ለአራተኛ ጊዜ ለዕይታ የበቃው የመስቀል ወፍ፤ ለዝግጅት የወሰደው ጊዜ ባይበዛ ኖሮ የመስቀል ወፍ ቴአትርን ከአደይ አበባ ጋር አብረን እናገኛት ነበር ብሎ ማሰብ ይቻላል።


ሁለት ባለትዳር ወጣቶች በድንገት ከለትዳር አጋሮቻቸው ተለይተው ለስራ ወደ አንዱ የአገራችን ክፍል (ባህር ዳር) ሄደው ይገናኛሉ። በመጀመሪያ ግንኙነታቸውም የወይን ጠጅ ብርጭቆ ሰውነታቸውን አሙቆት አዕምሯቸውን ሲቆጣጠረው ሳምሶን ከያዘው ክፍል አብረው ያድራሉ። ያ የመጀመሪያ ቀን ውስልትናቸው ለ30 ዓመታት በዓመት አንድ ጊዜ በተመሳሳይ ቀን እና ቦታ እየተገናኙ የሚከውኑት ድብቅ የፍቅር ጊዜያቸውን ያሳየናል የመስቀል ወፍ። ልክ እንደ አምልኮተ ፈጣሪ፤ ቀጠሮ ቀን ሳያዛንፉ እና ቦታ ሳይስቱ በየዓመቱ እየተገናኙ የዓመት ቆይታቸውን ሪፖርት አድምጠው የቀጣዩን ዓመት እቅዳቸውን አሰምተው ወደ ተለመደ ተግባራቸው ያቀናሉ።

 

የመስቀል ወፍ በተዋንያኑ ልኬት


አንጋፋው ተዋናይ አላዛር ሳሙኤል ጨምሮ አራቱም ተዋንያን ለቴአትሩ ተወዳጅነት ያሳዩት የትወና ብቃት ቢያስወድሳቸው እንጂ የሚያስተቻቸው አይደለም። ወጣቶቹ መስከረም አበራ እና ዓለምሰገድ አሰፋም ሆኑ አናጋፋዎቹ አላዛር ሳሙኤል እና ህሊና ሲሳይ የቴአትሩ ልዩ ድምቀት ያጎናጸፉ የመድረክ ፈርጦች ሆነው አይቻቸዋለሁ። ቴአትሩ ሲጀመር ከይዘትም ከቀልድም (ኮሜዲም) አንዱንም ያልያዘ መስሎ ቢታይም ጥቂት እንደተጓዙ ግን ከትዕይንት ትዕይንት የሚደረገው ሽግግር ሳይታወቅና ተመልካች ሳይሰለቸው እንዲታይ ያደርጋሉ።


ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ አርቲስቶቹ መድረክ ላይ እንዲሰሩት የታዘዙትን ሁሉ ለመስራት የሚያስችል ተጨማሪ ችሎታ (ክህሎት) የታደሉ መሆናቸው ደግሞ በተመልካች እንዲወደድ አድርገውታል። ለአብነት ያህልም ቴአትሩ ላይ ከአንድም ሁለት ሶስቴ እና ከዚያም በላይ ተዋንያኑ እንዲዘፍኑ የሚጠይቅ ክፍል አለ። የጥላሁን ገሰሰንም ሆነ የመሀሙድ አህመድ፣ አስቴር አወቀ እና ማንነቱን የዘነጋሁት ድምጻዊን ዘፈን ተዋንያኑ ለተመልካች ጆሮ በሚመች መልኩ ነበር የዘፈኗቸው። ይህን ችሎታቸውን ለተመለከተ የቴአትሩ ታዳሚ ቤቱ ሲገባ ቴአትሩን በጥሩ ትዝታ እንዲያስታውስ የሚያደርግ ይሆናል።


ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ከተዋንያኑ አንዱ (ወጣቱ ሳሚ) ከወጣቷ ራሄል ጋር በነበረው የመጀመሪያዎቹ አስር ዓመታት ከሚያደርጓቸው ውይይቶች ተነስቶ ነብሰ ጡር ሆና የቀረበችውን ራሄልን ሲያገኛት እንደለመደው ወደ አልጋ ሊጋዛት ሲል የማይሆን ይሆንበታል። ስሜቱ ደግሞ ይፈታተነዋል። በዚህ የተነሳም ለወሲብ የተነሳ ስሜቱን ለማለዘብ ሰውነቱን በስፖርት ለማድከም ወስኖ መድረኩ ላይ ፑሽአፕ ይሰራል። ይህን ክፍል እንዲሰራ ሲመረጥ ስፖርት የመስራት ልምድ እና ብቃት እንዳለው በሚያመለክት መልኩ ነበር ስፖርቱን ለተመልካች ያቀረበው። እነዚህ ሁለት ተሰጥኦዎች የአርቲስቶቹን ሁሉንቻይነት አመላካች ሲሆኑ፤ የቴአትሩን ተመልክችም ቴአትሩን በደስታ እንዲመለከት የሚያደርጉ ቅመሞች ሆነው አግኝቻቸዋለሁ።


ሌላው የአዘጋጁ እና የቴአትሩ ባለቤቶች (አርቲስቶችን ጨምሮ የቴአትሩ ክሩ) ልዩ ብቃት የሚገለጸው የተጠቀሙት የአርቲስቶች ቁጥር ነው። ቴአትሩ በሁለት ሰዎች ተጀምሮ በሁለት ሰዎች የሚያልቅ ቢሆንም በዚህ መሃል የዕድሜ ልዩነት ስለሚከሰት ይህን የዕድሜ ዥረት በሚገልጽ መልኩ አርቲስቶቹን በሜካፕ (ገጽ ቅብ) ተጠቅመው እንዲሰሩ ማድረግ የሚቻል ቢሆንም አዘጋጁ ማንያዘዋል እንደሻው ግን ልቦናው ያዘዘው የዕድሜ ልዩነቱን የሚገልጹ አራት አርቲስቶችን መጠቀም ሆኗል። ለምን እንዲህ አደረክ? ተብሎ ከሰንደቅ ጋዜጣ የተጠየቀው አዘጋጁ ‹‹በገጽ ቅብ የሚያልቀውን ጊዜ ስንመለከት ሁለቱን ወጣት ተዋንያን ሁለት ጎልማሳ ተዋንያን እንዲተኳቸው ማድረጉ ጥሩ ሆኖ ስላገኘነው ነው›› ብሏል። ይህ ደግሞ የአዘጋጁን ብቃት እና የአርቲስቶቹን ክህሎት አመላካች ችሎታ በመሆኑ ቴአትሩ ሲጠናቀቅ ከተመልካች የቀረበላቸው አድናቆት የበረታ እንዲሆን አድርጎታል።

ዘመኑን ያልዋጀ ቴአትር?


የመስቀል ወፍ ቴአትር ላይ ከተመለከትኳቸው ሰህተቶች/ድክመቶች መካከል አንዱ ዘመኑን የማይወክሉ ምልልሶች ማየቴ ነው። በ1966 ዓ.ም ተጀምሮ በ2006 ዓ.ም ፍጻሜ የሚገኘው የቴአትሩ መቼት ተዋያኑ የሚመላለሷቸው አብዛኞቹ የቃላት ልውውጦችና የጊዜ መጠቁሞች ወቅቱን የሚገልጹ አይደሉም።


ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ተዋንያኑ በየዓመቱ እየተገናኙ በዓቸውን የሚከብሩ ቢሆንም የቴአትሩ ትኩረት ግን የአስር ዓመት ሪፖርት ብቻ ነበር የሚመስለው። ለአብነት ያህልም ጎልማሳው ሳምሰን የበኩር ልጁ እና ባለቤቱ መሞታውን ለራሄል ሲነግራት የአስር ዓመት ሪፖርት እንጂ በአንድ ዓመት ውስጥ የተከወነ ድርጊት አይመስልም ነበር። በተለይ ከ1996 ዓ.ም በኋላ ባላቸው ግንኙነቶች ዘመኑ የፈጠራቸውን የግንኙነት አውታሮች መጠቀም ሲኖርባቸው እነሱ ግን በዓመቱ ያገኙትን በረከትም ሆነ የወረደባቸውን መቅሰፍት የሚነጋገሩት በግንኙነታቸው ቀን ብቻ ነው። ለዚህም የድብቅ ፍቅረኛዋ ልጅ እና ባለቤቱ መሞታቸውን የሰማችው ራሔልም ሆነች የራሔል ባለቤት መታመሙን የሰማው ሳምሶን ድንጋጤያቸውን መቆጣጠር ሲሳናቸው ይታያሉ።
ከእነዚህ ጥቃቅን ስህተቶች በስተቀር በመድረክ ስራ፣ በዝግጅት፣ በትወና እና በድምጽ ግብአት የተስተካከለ ቴአትር ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
15706 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 893 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us