“ታሪክን መፃፍ የምወደው ስራ ነው” የ“ንጉስ አርማህ” እና የ“ህንደኬ” ተውኔቶች ደራሲ መልካሙ ዘርይሁን

Thursday, 03 October 2013 19:38

በአሸናፊ ደምሴ

ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ከታሪካዊ ተውኔቶች ፀሐፍት መካከል ስሙን የማናጣው ፀሐፊ ነው። ቀደም ብሎ “ንጉስ አርማህ” አሁን ደግሞ “ህንደኬ” የተሰኙ ታሪካዊ ተውኔቶችን ለመድረስ አብቅቷል። ከዚህም በተጨማሪ “የእኛ እድር” የተሰኘ ተውኔቱ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች እና በአሁኑ ወቅትም በእንግሊዝና የተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች በመታየት ላይ ይገኛል። የዛሬው እንግዳችን ጋዜጠኛም ነበረ። “አልሆንልህ ብሎኝ ተውኩት” ይላል እንጂ፤ ከደራሲ መልካሙ ዘርይሁን ጋር የነበረንን አጭር ቆይታ እነሆ።

ሰንደቅ፡- እስቲ ለአንባቢያን ራስህን አስተዋውቅ?

መልካሙ፡- መልካሙ ዘርይሁን እባላለሁ። ሁለት ሦስት ቴአትሮች ሰርቻለሁ። ጋዜጠኛም ነበርኩ፤ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የራሴን ድርጅት ከፍቼ እየተንቀሳቀስኩ ነው።

ሰንደቅ፡- ስምህ ተደጋግሞ የሚነሳው ከታሪካዊ ተውኔቶች ጋር ነው። ገንዘብ ተኮር ያልሆነና ለትውልድ ይጠቅማል ያልከውን ታሪካዊ ተውኔቶችን ለመስራት ለምን መረጥክ?

መልካሙ፡- ጥሩ ነው፤ እንግዲህ ዋናው ነገር መስራት የምትችለውን ነው የምትሰራው።መስራት የማትችለውን አትሰራም። አንዱ ይሄ ነው፤ ሁለተኛው ደግሞ ታሪክ ላይ መስራት የምወደው ነገር ስለሆነ ነው። ምናልባት አሁን አንተ ጋዜጠኛ ነህ፤ ጋዜጠኝነት “ኢንተረስትህ” ሊሆን ይችላል። ወይም የመሸጋገሪያ ስራህ ሊሆን ይችላል። ለእኔ ግን ታሪክን መፃፍ በጣም የምወደው ስራ ነው። ለእኔ የሚመቸኝ ስራ ታሪክን አንብቦ መፃፍ ነው። ስለዚህም ታሪካዊ ተውኔቶች ላይ አተኩሪያለሁ። ሌላኛው ምክንያቴ ደግሞ ኢትዮጵያ የምትባለውን ሀገር ወይም ደግሞ ኢትዮጵያዊ ስትሆን፤ እንደ ኢትዮጵያዊ ሆነህ ስታስበው ደግሞ ሀገራችን ታሪክ አላት።

በጣም የሚገርሙና ሊፃፉ የሚቻሉ ዓለም ሊያውቃቸው የሚገባ ታሪኮች ያሏት ሀገር ናት። ይህን ስታስብ በራሱ የሚፈጥርብህ የቁጭት ስሜት አለ። ታሪካችንን ዓለም ቢያውቅልን አልኩህ እንጂ፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ራሳችንም የማናውቃቸው ድንቅ ታሪኮች አሉን። እንደው ዝም ብለን ኢትዮጵያዊ ነን ብለን እንጋበዛለን እንጂ ታሪካችንን በሚገባ የማናውቅበት ሁኔታ አለ። እኔ ይሄን የምልህ በስራዎቼ ላይ የገጠመኝን ተመልክቼ ነው። “ንጉስ አርማህ”ን ኢትዮጵያዊ ታሪክ ሳይሆን ትርጉም ነው ብለው የሚከራከሩኝ ሰዎች ገጥመውኛል። ይህ ነገር ደግሞ አንዳንዴ አፍሬ ምን ውስጥ ልግባ ሁሉ ያሰኛል። ታዝናለህ፤ የታሪክ ትምህርታችን ደካማ ስለሆነም ይሆናል ብለህ ታስባለህ። ይሄ ሁሉ ነው ለእኔ ወደ ታሪካዊ ተውኔት የማተኮር ምክንያቱ።

ሰንደቅ፡- የኢትዮጵያን ታሪክ የማጥናት ዕድሉ ነበረህ?

መልካሙ፡- እውነቱን ለመናገር እኔ የተማርኩት ጋዜጠኝነት ነው። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ “Press Journalism” የሕትመት ሚዲያውን ነበር በዲፕሎማ ያጠናሁት። ቀጥዬ ደግሞ ለሬዲዮ ጋዜጠኝነት የመጀመሪያ ዲግሪዬን አግኝቻለሁ። ለተወሰነ ጊዜ ጋዜጠኝነቱን ሞክሬ ስላልቻልኩት ትቼዋለሁ። ስለዚህ የተማርኩት ጋዜጠኝነት ነው፤ ነገር ግን ታሪክን የማወቅ ከፍተኛ ጉጉቱ ስለነበረኝ በራሴ ጥረት ነው ያነበብኩት። በእኛ ጊዜ ደግሞ የተመደብክበትን ትምህርት ነው የምታጠናው። ሲጀመር ጥሩ ጋዜጠኛ ይወጣኛል ብዬ አስቤ ነበር። ግን አልሆነም። በተቻለኝ ሁሉ ግን ስለኢትዮጵያ ታሪክ ለማንበብ፣ ለማጥናትና ለመመርመር እሞክራለሁ።

ሰንደቅ፡- እስቲ ስለ “ንጉስ አርማህ” እና ስለ “ህንደኬ” ቴአትሮችን አጫውተኝ። በተለይ ግጭትን ለመፍታት ከተጠቀምክባቸው “ዲፕሎማት” ገፀ-ባህሪያቶች አንፃር ብናወራ ደስ ይለኛል።

መልካሙ፡- እንግዲህ እዛ ላይ ምንድነው መሰለህ?... እኔ እንደማስበው አብዛኛው የኢትዮጵያ ታሪክ የጦርነት ታሪክ ነው። ሁሉም ኢትዮጵያ ውስጥ የተደረጉት ጦርነቶች ፍትሐዊ ወይም ተገቢ ጦርነቶች ናቸው ብዬ አላምንም። አንዳንዱን ታሪክ አገላብጠህ ወደኋላ ስታይ የሚያስቁ አይነቶች የጦርነት ምክንያቶችን ታገኛለህ። እንዲያው ከመሬት ተነስቶ “ሄደን እንያዘው፤ ሄደን እንውጋው” የሚል አይነት ቀልድ መሰል ምክንያቶች የተከሰቱ ጦርነቶች አሉ። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የግድ መሆን ያለባቸው የክብር እና የሀገር ጉዳይ የሆኑ ጦርነቶች አሉ። አንዳንድ ጊዜም ሀገርን ምክንያት አድርገህ በቀላሉ በዲፕሎማሲና በንግግር መፍታት የሚቻሉ ጦርነቶች ይገጥሙሃል። ብዙ ጊዜ ጦርነቶች ወይም ግጭቶች ያለመግባባት ውጤቶች ናቸው። ያ ስለሆነ ንጉስ አርማህም ላይ በተለይም ህንደኬ ላይ የምታየው የጦርነት መነሻ ምክንያቱ ተራና ልል አይደለም። ጦርነት በጣም አሰቃቂ ነገር ነው። ለእኛ ደግሞ ምስክር አንሻም አይተነዋል፤ እናውቀዋለን። እኔ እርግጠኛ ነኝ ከዚህ በኋላ ያሉ መሪዎች ስለጦርነት አይቀልዱም። ከዚህ በፊት ግን ሆኗል። አንዳንድ ጦርነቶች ከሀገር ክብር ይልቅ የመሪና የግለሰብ ክብር ከፊት የቆሙና በቀላሉ በመነጋገር ልትፈታው የሚቻልህ ነገር ሆኖ ሳለ፤ የጦርነት መንስኤ ሆኖ ሲመጣ ታየዋለህ። የሚገርመው ነገር ብዙዎችም አሉ ጦርነትን አመቻምቸው በብልሃት ያለፉ መሪዎች። በአንፃሩ ደግሞ ጦርነት አለ በተባለበት ሁሉ እንደ እሣት እራት ጥልቅ የሚሉ መሪዎችም በታሪካችን ውስጥ አሉ።

ሰንደቅ፡- አሁን በብሔራዊ ቴአትር በመታየት ላይ የሚገኘው “ህንደኬ” የተሰኘው ቴአትርን የተመለከቱ ሰዎች የቤተሰቡ የስልጣን ሽኩቻ በዝቷል ይላሉ አንተስ?

መልካሙ፡- አዎ! የስልጣን ሽኩቻው ከውስጥም ከውጪም ሊሆን ይችላል። ስልጣን ትልቅ ነገር ነው። በብልሃትና በዘዴ ከተጠቀምክበት ልማትና ብልፅግናን የምታመጣበት ሲሆን፤ አይ ብለህ ስልጣንን በሌላኛው መንገድ ከወሰድከው ደግሞ ጥፋትን የሚያመጣ ነው። የኢትዮጵያን ታሪክ ደግሞ መለስ ብለህ ስታየው አንድም በሰለሞናዊ ዘርነት ተብሎ የስልጣን ጉዳይ የዘር ሽኩቻ ነበር። ወንድምና እህት እርስ በእርሱ የሚፋጭበት ነው። ይሄ “ሲምቦሊክ” (ተምሳሌታዊ) ነው። ምን ለማለት ነው መሰለህ ያው ግጭት አሁንም አለ። እንደው ፖለቲካችንን እንፈትሸው ብንል አሁንም ያው የስልጣን ሽኩቻው አሉ። የግድ እኮ ከአንድ አባት ስለተወለድክ ብቻ አይደለም። ኢትዮጵያዊ ስለሆንክም ቢሆን ስልጣንን እስከፈለክ ጊዜ ድረስ ኩዴታ ወይም ሰውን አጥፍተህ ስልጣን የምትይዝ ከሆነ ይህ ምክንያታዊ አይደለም። አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ግን ይሄ የኢትዮጵያ ብቻ ታሪክ አይደለም። በሌላው ዓለም ያለ ነው። ግን ስልጣንን ያህል ኃይል በብልሃትና በሰለጠነ ዲፕሎማሲ ለሀገር ልማት እንዲውል ማድረግ መልካም ታሪክ ይመስለኛል።

ሰንደቅ፡- ወደ ቴአትሩ ዓለም እንዴት ገባህ?

መልካሙ፡- የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለሁ የፃፍኩት “ንጉስ አርማህ” በ1993 ወይም 94 ዓ.ም አካባቢ ይመስለኛል ቴአትር ቤት አልፎ መታየት ጀመረ። ቴአትር ሲፃፍ አንዳንድ ጊዜ በአጭር ቀናት ትጨርሰዋለህ፤ አንዳንዴ ደግሞ ብዙ ዓመታትን ሊወስድብህ ይችላል። ይሄ ግን ያው እንደምታውቀው ታሪካዊ ተውኔቶች ናቸው። ጊዜ በጣም ይፈልጋሉ። ለምን መሰለህ ተመልካቹ ሊመረምረው የሚችል የተፃፈ ታሪክ ስላለ ተጠንቅቀህ ነው መስራት ያለብህ። መፋለስ የሌለባቸው ታሪካዊ እውነቶች አሉ። ከዚያ በተረፈ ደግሞ ስታቀርበው ለቴአትር ተመልካቹና ለታሪኩ ሚዛናዊ የሆነ ነገር መስራት አለብህ። ታሪክን ሳታዛባ ነገር ግን አዝናኝ በሆነ መልኩ ተጠቅመህ ማሳየት መቻል አለብህ። ይህንን ከቀደምት የሀገራችን ስራዎችና ከሌሎች ስራዎች አይቼ ስለነበር መፃፉ ብዙም አልቸገረኝም። ታስታውስ ከሆነ “ንጉስ አርማህ” ሦስት አመት አካባቢ ታይቷል። አሁን ደግሞ “ህንደኬ” ሦስት ዓመት አልፎትም እየታየ ነው። “ህንደኬ” ብዙ የደከምኩበት ስራ ነው። በቴአትር ቤቱ ሂደት ውስጥ ከ3 ዓመት በላይ ቆይቶ ነው ለተመልካች የደረሰው። እውነቱን ለመናገር አዘጋጁ ጌትነት እንየውም ብዙ ደክሞበታል ማለት እችላለሁ።

ሰንደቅ፡- ታሪካዊ ተውኔት መፃፍ ከገቢ አንፃር ያዋጣል? የልፋትህን አግኝተህበታል?

መልካሙ፡- ከገቢ አንፃር ስታየው የሚያዋጣ ስራ አይደለም። ከገቢም ብቻ ሳይሆን ከጊዜም አንፃር ቢሆን የሚያዋጣ አይደለም። የለፋህበትን ያህል አታገኝበትም። ነገር ግን ለእኔ ስሜቴን የውስጤን የምፅፍበት ስለሆነ አልከፋም። የምፅፈው ልኖርበት ሳይሆን የማውቀውን ላሳይበት እስከሆነ ድረስ ገቢው አያሳስበኝም፡፡

ሰንደቅ፡- ሁለቱን ታሪካዊ ተውኔቶች ከሰራህ በኋላ “የእኛ ዕድር” የተሰኘ ሌላ በማኅበራዊ ህይወት ላይ የሚያጠነጥን ተውኔት ፅፈሃል ምን ልዩነት አገኘህበት?

መልካሙ፡- “የእኛ ዕድር” ተውኔት ሳታየር ኮሜዲ የምትለው አይነት ነው። ኮሜዲም ሆኖ አንድ አካባቢ ላይ ስላለ ስለ አንድ እድር እና በውስጡ ያሉትን አባላት ማዕከል አድርጐ ነው የተፃፈው። በቴአትሩ ላይ ሸዋፈራው ደሳለኝ፣ ሰብለ ተፈራ፣ ሰለሞን ሙሄ፣ ሰብስቤ ዘርጋውና መቅደስ የሚጫወቱበት ተውኔት ነው። በአጋጣሚ አዲስ አበባ ላይ አላሳየነውም። ክፍለ ሀገር ላይ ወደ 44 አካባቢ መድረኮችን ሰርተነዋል።

ሰንደቅ፡- በአዲስ አበባ ያልታየው መድረክ ጠፍቶ ነው?

መልካሙ፡- አይደለም። ብዙ አልሞከርንም፤ በስፖንሰር ነው የሰራነው። መርቀን የከፈትነው በባህርዳር ነው። በእውነቱ የክልሉ መንግስት በእጅጉ ነው የተባበረን። አንድ ጊዜ ለምስጋና በማዘጋጃ ቤት መድረክ ላይ ሰርተነዋል። ጥሩ ምላሽ አግኝተንበታል። የሚገርመው ደግሞ በአጋጣሚ ካሳለፍነው እሁድ (መስከረም 12 ቀን 2006 ዓ.ም) ጀምሮ በለንደን እና በተለያዩ ከተሞች ለማሳየት ዝግጅታቸውን ጨርሰዋል። ቴአትሩን ያዩት ተመልካቾች በፌስ ቡክ ጥሩ ምላሾች እየደረሱኝ ነው።

ሰንደቅ፡- ለአዲስ አበባ ተመልካች ምን የታሰበ ነገር አለ? እንደሰማሁት ቴአትሩን ወደፊልም ልትቀይረው ነው፤ ይሄ ነገር እውነት ነው?

መልካሙ፡- ከዚህ በኋላ ወደ አዲስ አበባ መድረክ እናመጣዋለን የሚል ሀሳብ የለንም። ካለው ሁኔታ አንፃር አሁን በከፊል ወደፊልም ቀይረነው ጽሁፉን ጨርሰናል። ቀረፃም ጀምረን ነበር። ተዋንያኑ ለሾው ወደውጪ ስለሄዱ ነገሮች እስኪስተካከሉ በሚል ነው ያዘገየነው። ጊዜው ከፈቀደ በዚህ ዓመት ወደፊልም ቀይረነው ለተመልካች እናደርሰዋለን ብዬ አስባለሁ።

ሰንደቅ፡- ወደፊልም መቀየሩ ለምን አስፈለገ?

መልካሙ፡- ፊልም ለማድረግ ለምን ተፈለገ ላልከው፤ እንደምታየው ነው፤ ፊልም በብዛት እየተሰራ ነው። ይሄ ታሪክ ደግሞ በፊልም ቢመጣ የተሻለ ይሆናል በሚልና መሞከሩ አይከፋም በሚል ነው። የቴአትሩንና የፊልሙን አቅምም የቱ ድረስ እንደሆነም ለመለካት የጠቅመናል በሚል ነው።

ሰንደቅ፡- ወደፊትስ ምን የመስራት ሀሳብ አለ? በተለይም ከታሪካዊ ተውኔቶች አንፃር በአንተ በኩል ምን የታሰበ ነገር አለ?

መልካሙ፡- ምን መሰለህ፤ ለእኔ “ህንደኬ” ትንሽ ፈታኝ ነበረ። ከመፃፉ ጀምሮ፣ ቴአትር ቤቱ የወሰደው ጊዜ፣ አሁንም ቢሆን የረካሁበትም ስራ አይደለም። የምጠብቀውን ያህል ተመልካች አይቶታል ብዬ አላስብም። ሦስት ዓመት መቆየቱ ስም ብቻ ነው፤ ምን ያህል ተመልካች አየው ብትል ምናልባት አንድ ኮሜዲ ፊልም ካየው ህዝብ በታች ይሆናል “ህንደኬ” የታየው።

ሰንደቅ፡- ይሄ ታዲያ ለታሪክ ያለን ዝቅተኛ አመለካከት ውጤት ነው ወይስ እንደዚህ ጠንከር ያለና ከባድ ሀሳብን ማስተናገድ የሚችል ተመልካች ማጣት፤ የቱ ይመስልሃል?

መልካሙ፡- እዚህ ድምዳሜ ላይ መድረሱ ትንሽ ይከብዳል። ለምሳሌ ስለ “ንጉስ አርማህ” ብትጠይቀኝ ብዙ ሰው አይቶታል። እና አሁን ያ ነገር ለምን በ“ህንደኬ” አልተደገመም ብለህ ስታስብ ብዙ ነገር ልታነሣ ትችላለህ። አንዱ ያልከው ሊሆን ይችላል፤ ተመልካቹ ከበድ ያሉ ነገሮችን ማጣጣም አይችልም ወይ የሚለውን ነገር ታነሳለህ። በሌላ በኩል ደግሞ ስታየው ውጪ ሀገር የተሰሩ ቢሆንም፤ እንከን የሆሊውድን ታሪካዊ ፊልሞች በደንብ አጣጥሞ የሚያይ ተመልካች አለን። ግን እኔ እንደሚመስለኝ የጊዜ ጉዳይ ነው። “ህንደኬ” ቀደም ብሎ ታይቶ ቢሆን ወይም ደግሞ ከዓመታት በኋላ ቢታይ ተመልካቹ ጥሩ ይሆን ነበር ብዬ አስባለሁ። አልረካሁበትም ያልኩህ ከዚህ እንፃር ነው እንጂ ስራው ጥሩ አይደለም ለማለት ፈልጌ አይደለም።

ሰንደቅ፡- አሁን ወደፊልሙ እየመጣህ ነው፤ ታሪካዊ ስራዎችህንስ ወደፊልም ለመስራት ኀሳቡ አለህ?

መልካሙ፡- ይሄ ትልቁ ነገር ነው። “ንጉስ አርማህ” እና “ህንደኬ” ብቻ አይደሉም የእኔ ታሪካዊ ተውኔቶች ሌሎችም የፃፍኳቸው አሉ። ግን ከዚህ በኋላ ቴአትር ቤት አላወጣቸውም። ለምን መሰለህ ያለፍኩትን መጐዳት እንደገና አልደግመውም። ስለዚህ ያለኝ ብቸኛ ዕድል ፊልም መስራት ነው። ፊልም ደግሞ አቅም ይጠይቃል፤ ገንዘብ ይጠይቃል። አቅሜን አዳብሬ የፈጀውን ፈጅቼ ወደፊልም ብለውጣቸው እመርጣለሁ። ይህንንም ለማድረግ እየተዘጋጀው ነው። በመሆኑም ከዚህ በኋላ ታሪካዊ ፊልሞችን እሰራ ይሆናል እንጂ ታሪካዊ ተውኔቶችን የምሰራ አይመስለኝም።

ሰንደቅ፡- መፃፍ ችለሃል፣ ማዘጋጀት እየሞከርክ ነው ወደትውናውስ የመምጣት ሀሳቡ አለህ?

መልካሙ፡- (ሣቅ) አልችልበትም። እኔ ጋዜጠኝነትና ትወናውን አልችልበትም። ዝግጅቱንም ቢሆን በድፍረት ሳይሆን በዕውቀት ለመስራት ነው የማስበው።

ሰንደቅ፡- የሬዲዮና የቴቪ ተከታታይ ድራማዎችን የመፃፍ ሀሳቡ አለህ?

መልካሙ፡- አስባለሁ። ነገር ግን እንዳጋጣሚ ሆኖ የምሰራቸው ብዙ የግል ስራዎች አሉኝ። አሁን ባለው ሁኔታ የጀመርኳቸውን ስራዎች ማጠናቀቅ አለብኝ። ለምን ቴአትር አያኖረኝምና። ከዚያ በኋላ ነው ስለጥበቡ ማሰብ የምፈልገው። ከዚያ ውጪ ግን በስፋት የምሰራበት ጊዜ ሳገኝ በፊልሙም በሬዲዮኑም ሆነ በቴቪው ስራ እመጣለሁ ብዬ አስባለሁ።

ሰንደቅ፡- መልካሙ በምን ትዝናናለህ?

መልካሙ፡- በንባብ ልምዴ ጥሩ ነኝ ብዬ አስባለሁ። ልጅ እያለሁ ጀምሮ ለንባብ ቅርብ ነበርኩ። ምክንያቱ ደግሞ አባቴ ስራ ሲጀምር “ላይብረሪያን” ሆኖ ነው ስራ የጀመረው። በመሆኑም ቤታችን ውስጥ መፃሃፍ አይጠፋም ነበርና ንባብ ብቸኛው መደበቂያዬ ነበር። በተለይ ከአባቴ ጋር ባነበብናቸው መፅሐፍት ዙሪያ ስናወራ ደስ ይለው ነበር። ያኔ ነው የመፅሐፍትን ጥቅም ያወኩት። ከዚያም በኋላ አባቴ ወመዘክር ሲሰራ ቴአትር ደጋግሞ የማየት ዕድሉ ነበረኝ። በማንበብ እዝናናለሁ፡፡ አሁን አሁን ግን ብዙ አንባቢ ነኝ ብዬ አልልም። መዝናናቱን በተመለከተ ከልጆቼና ከቤተሰቤ ጋር ስሆን እዝናናለሁ። ከከተማ ወጣ ስልም ደስ ይለኛል። በተረፈ ግን ፊልሞችን አያለሁ። የሀገር ውስጥ ስራዎችን እምብዛም ነኝ ካልተጋበዝኩ በስተቀር አላይም፡፡ የውጪዎቹን ግን ጥሩ ተመልካች ነኝ ብዬ አስባለሁ።

ሰንደቅ፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ?

መልካሙ፡- እኔም ለተሰጠኝ ጊዜ በጣም አመሰግናለሁ።

Last modified on Monday, 07 October 2013 09:59
ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
12362 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us