አበበ ከፈኒ እና ወንዴ ማክ ለዘመነ ነጠላ ዜማ እንደማሳያነት

Wednesday, 07 February 2018 13:06

 

 

በይርጋ አበበ

 

በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ታሪክ ካለፉት አስር ዓመታት ወዲህ ቁጥራቸው በርከት ያሉ ወጣቶች የመጡበት ጊዜ ነው ብሎ መናገር ይቻላል። ከኢትዮጵያ ሚሊኒየም ጀምሮ ባሉት አስር ተከታታይ ዓመታት ሙዚቃውን በአዲስ ስራ የተቀላቀሉትን ድምጻዊያን ቁጥር በትክክል ይህን ያህል ነው ብሎ መጥቀስ ባይቻልም በርካቶች መሆናቸውን ለመናር ግን አያዳግትም። በተለይ ኢቢኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያ የመገናኛ ብዙሃኑን ዘርፍ መቀላቀሉን ተከትሎ በአሁኑ ሰዓት ወደ 15 የሚጠጉ የመንግስት እና የግል ቴሌቪዥን ጣቢያዎች እና ለ20 የቀረቡ የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች መከፈታቸው ሙዚቀኞች ስራቸውን በስፋት እንዲያቀርቡ ሳይረዳቸው አልቀረም ተብሎ ይታሰባል። ከዚህ በተጓዳኝ ደግሞ ዘመኑ የመረጃ እና የመዝናኛ መሆኑ በራሱ አርቲስቶቹ ስራቸውን ይዘው ለህዝብ እንዲቀርቡ ሳይረዳቸው እንዳልቀረ ይነገራል።


ባለፉት አስር ዓመታት ለህዝብ ከቀረቡ የሙሉ አልበም ስራዎች ይልቅ በነጠላ ዜማ የቀረቡ ስራዎች በርከት ያሉ ናቸው። ለአርቲስቶቹም ቢሆን ከሙሉ አልበም ይልቅ በነጠላ ዜማ መቅረቡ አዋጭ መንገድ ሳይሆን አልቀረም። አንጋፋዎቹና ታዋቂዎቹ ድምጻዊያን ሳይቀሩ በነጠላ ዜማ ከህዝብ ጋር እየተገናኙ ባለበት በዚህ ዘመን ጥቂቶች በመጡበት ፍጥነት ከህዝቡ ጋር ሲገናኙ በርካቶች ደግሞ የህዝቡን ጆሮ ማግኘት ተስኗቸው ይታያል። በዚህ በኩል ድምጻዊ ጌትሽ ማሞ ‹‹ተቀበል›› እያለ ያዜማቸው ሁለት ነጠላ ዜማዎች (ተቀበል እና እንከባበር) ከፍተኛ ተወዳጅነትን ያተረፉለት ስራዎቹ ሲሆኑ ከሙሉ አልበሙ በላይ ገቢ እና እውቅና ያስገቡለት እንደሆኑ ተነግሯል። በቅርቡ ይለቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው ‹‹ተቀበል ቁጥር ሶስት›› ከወዲሁ ረብጣ ገንዘብ ያስገኘለት ስራ እንደሆነ በስፋት ተነግሯል። በዛሬ የመዝናኛ አምድ ዝግጅታችን በነጠላ ዜማዎቻቸው ከህዝብ ጋር መገናኘት ከቻሉት ወጣት ድምጻዊያን መካከል የሁለቱን ወጣቶች ስራዎች እንመለከታን የድምጻዊ አበበ ከፈኒ (ሹሚ) እና ወንድወሰን መኮንን (ወንዴ ማክ)። ሁለቱ ወጣት ድምጻዊያን በኦሮምኛ (አበበ) እና በአማርኛ (ወንዴ ማክ) ከህዝብ ጋር የተዋወቁባቸውን ነጠላ ዜማዎች አቅርበዋል። ወጣቶቹ እስካሁን ሙሉ አልበም ባያወጡም (ወንዴ ማክ ለፋሲካ ያወጣል ተብሎ ይጠበቃል) ለህዝብ ባቀረቧቸው ነጠላ ዜማዎች ተወዳጅነትን አትርፈዋል። ቅኝታችንም በዚሁ ዙሪያ የሚያተኩር ነው።

 

የወንዴ ማክ እና አበበ ከፈኒ ሙዚቃዎች ቅኝት


ጋሻው አዳል ‹‹በምን አወቅሽበት በመመላለሱ›› ሲል የተጫወተውን ተወዳጅ ዜማ ወንድወሰን መኮንን ‹‹ምን ይጥራሽ›› ሲል ከጋሻው አዳል ላይ የራሱን ግጥሞች በማከል አቀነቀነው። ምንም እንኳን የጋሻው አዳልን ዘፈን ዜማ እና ግጥም የሰሩት ድምጻዊ አያሌው መስፍን (በዜግነት አሜሪካዊ) ወንዴ ማክን በአደባባይ ቢዘልፉትም ወጣቱ ድምጻዊ ግን ዘፈኑን የዘፈነው የጋሻው አዳልን ቤተሰቦች አስፈቅዶ እንደሆነ ተናግሯል። ‹‹ምን ይጥራሽ እና አለሁ›› የተባሉትን ሁለት ዘፈኖች ከጋሻው አዳል ዘፈን ላይ የራሱን ግጥም እንደጨመረበት የተናገረው ወንድወሰን መኮንን፤ ከሁለቱ ዘፈኖች በተጨማሪ ሙሉ በሙሉ በራሱ ግጥምና ዜማ የተሰራላቸውን ስምንት ዘፈኖች ለህዝብ በማቅረብ ችሎታውን አሳይቷል።


ወንዴ ማክ በህዝብ ተወዳጅነትን ካተረፉለት ዘፈኖቹ መካከል ‹‹አባ ዳማ›› አንዱ ነው። የሸዋ ኦሮሞ እና የጎጃም ስልተ ምት ያለው ዘፈኑ በሳል ግጥሞችንና ጆሮ ገብ ዜማን የተላበሰ ነው። ከዘፈኑ ላይ ግጥሞችን ስንዘግን፤

‹‹ብርሃን ጠፋፍቶ ቢጋርደን፤
በእኔም ባንቺም ልብ ፍቅር አለን።
ለጊዜው ቀመር እዚህ አድርሶናል፤
መተማመኑን ሽረናል።
ሁሉ በእጅህ ነው የጋጣው ጌታ፤
እስቲ አንድ ፈረስ ስጠኝ ለማታ።
……….
ከአውድማው ላይ የሚያውቁን
ከዳር ሆነው የሚሞቁን።
ቀዩን ከነጭ ከሰርገኛ፤
ቆጥረው ሚለዩን እነሱ መለኛ።
ቂሙን እርሽው ቂሙን ልርሳው፤
ስንለያይ ነው ለእኛ አበሳው።
አዲስ ሆኖ ዛሬ ቀኑ፤
በባለፈው ይቅር መባዘኑ።
እጄን ያዥው አጥብቂና፤
እንድናልፈው የኑሮን ፈተና።›› የሚሉትን እናገኛን።

እነዚህ ስንኞች ሰዎች (ፍቅረኞችም ቢሆኑ) በአንድ ላይ ለመኖር አስፈላጊ የሆኑ ምክረ ሃሳቦች ናቸው። እንደ ድምጻዊው እምነት ተፈጥሯዊ ልዩነቶችን ሰው ሰራሽ ምክንያቶች ተጨምረውበት መተማመን ሲጠፋ ፍቅር እንዴት እንደሚጎዳ የሚናገረው ይኸው ዘፈን፤ ቂምን ረስቶ ቀንን በአዲስ ፍቅር መጀመር የተሻለ እንደሆነ ይገልጻል። በዚህ ላይ መጽሃፍ ቅዱስ ራሱ ‹‹ያለፈውን የመከራ ዘመን አላስብባችሁም›› እንዳለው ዛሬም ኢትዮጵያዊያን በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠሩ የመሪዎችን ወይም የገዥዎችን ስህተት እያነሱ በጅምላ በህዝብ ላይ በመጫን በህዝቦች መካከል መተማመን፣ መፈቃቀር፣ አንድነት እና አብሮ መኖርን እንዲተው ማድረግ ትርፉ መለያየት እንደሆነ ይህ የወንዴ ማክ ዘፈን እየነገረን ነው። ለዚህ ነው ‹የጊዜው ቀመር እዚህ አድርሶናል፤ መተማመኑን ሽረናል›› ያለው።


በኦሮምኛ ቋንቋ እና በኑዌር (ጋምቤላ) ዘፈኖችን አዘጋጅቶ ከምስል ጋር ያቀረበው አበበ ከፈኒ (ሹሚ) ደግሞ የኦሮሚያን ሙዚቃ ኢንደስትሪ እያነቃቃ ያለ ወጣት ነው። አበበ የመጀመሪያ ስራው የሆነው ‹‹መጋል ወረ ቃሉ›› የተባለ ዘፈን ሲሆን መቼቱን ወሎ ላይ ያደረገ ዘፈን ነው። ወሎ የቆንጆ አገር እየተባለ ተደጋግሞ የሚነገርላት አገር ስትሆን እረኛው በዋሽንት፣ አዝማሪው በመሰንቆ፣ ወልይ በድቢ፣ ድምጸ መረዋ እናቶች በወፍጮ ሳይቀር ስለ ወሎ ቁንጅና ደጋግመው ተቀኝተውላታል እንዲህ ሲሉ።


‹‹በእናቷም በአባቷም ወረሂመኖ ናት፤
እንደ በልጅግ ጥይት ትመታለች አናት።
አረጎ አፋፉ ላይ ያገኘናት ልጅ፤
በእጅ አትንኩኝ አለች በከንፈር ነው እንጂ።
ባቄላ ምርቱ እንጂ አያምርም ክምሩ፤
ይምጣ የወሎ ልጅ ከእነምንሽሩ።››

 

የአገራችን ታዋቂ ድምጻዊያንም ቃላት እስኪያጥራቸው ዜማ እስኪጠፋባቸው የወሎን ቁንጅና ሲሹ በመሰንቆ ሲያሻቸው በጊታር አዚመውልናል። ከእነዚህ ድምጻዊያን መካከል አንዱ ሆኖ የቀረበው ደግሞ ወጣቱ አበበ ከፈኒ ነው። ለስለስ ባለ ዜማ እና ጆሮ ገብ በሆነ ድምጹ ያዜመው ‹‹መጋል ወረ ቃሉ›› ዘፈን አበበን ከህዝብ ጋር ያስዋወቀው ሲሆን እየቆየም ሌሎች ስራዎችን ይዞ መምጣት ችሏል። በተለይ በቅርቡ የለቀቀው ‹‹ጅማ›› የተሰኘ ስራው ቋንቋውን በሚችሉት ብቻ ሳይሆን ቋንቋውን ለማያውቁትም ዘፈኑን ሰምተው እንዲወዱት ተደርጎ የተሰራ ስራ ነው።

 

ዓለምን በነጠላ
የኮፒ ራይት ጉዳይ የዘርፉን ዋና ተዋንያን መቅን የሚስፈስስ ፈተና ሆኖ መቅረቡ ድምጻዊያኑ ከሙሉ አልበም ስራቸው ታቅበዋል የሚል ምልከታ እንዲፈጠር አድርጎታል። ዘመኑ ያፈራቸው ቴክኖሎጂ ውጤቶች ደግሞ አንድን ሙዚቃ በቀላሉ ለሌላ ሰው ማስተላለፍና ዘፈኑን በነጻ እንዲጠቀም ማድረጉ ደግሞ ሰዉ አልበም ገዝቶ ሙዚቃ የማዳመጥ ባህሉ እየቀነሰ የመጣ ይመስላል። በዚህ የተነሳም ዘፋኞች የሚጠቀሙት ዘዴ ሙዚቃቸውን በፕሮዲዩሰር እንዲታተም በማድረግ ወጪያቸውን መቀነስ ነው። ይህ ደግሞ ሊሳካ የሚችለው በከፍተኛ ደረጃ ወዳጅነትና ተፈላጊነት ባላቸው ድምጻዊያን ላይ እንጂ በወጣቶችና ልምድ ቢኖራቸውም ተፈላጊነታቸው እዚህ ግባ የማይባሉ ድምጻዊያንን ሙዚቃዎች ፕሮዲዩስ የሚያደርግ ድርጅት ማግኘት ከባድ እየሆነባቸው መጥቷል።


ይህን የተረዱት ወጣት ድምጻዊያን ነጠላ ዜማ ያወጡና ለመገናኛ ብዙሃን በተለይም ለቴሌቪዥን ጣቢዎች ይሰጣሉ። ዘፈኗ በቴሌቪዥን ተደጋግማ ስትታይ ተወዳጅ ከሆነች ተጨማሪ አዱኛዎችን ይዛ ትመጣለች። ይህም ኮንሰርት ይባላል። በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መካከለኛው ምስራቅ ለኢትዮጵያዊያን ወጣት ዘፋኞች ምቹ የኮንሰርት መድረክ የሆነላቸው ይመስላል። አንዳንድ ወጣቶች በአንድ ወይም ሁለት ነጠላ ዜማዎች ብቻ ተወዳጅነትን በማትረፋቸው ኑሯቸውን መቀየር ሲችሉ ታይተዋል።


ከእነዚህ ወጣቶች መካከል አንዱ ወንዴ ማክ ነው። ወጣቱ ድምጻዊ ሁሉንም ዘፈኖቹን ሙሉ በሙሉ የዜማ እና የግጥም ስራዎች ራሱ የሚሰራቸው ሲሆን ጆሮ ገብ በሆነ ድምጹ የተነሳም ስራዎቹ ተወዳጅ ሆነውለታል። ‹‹ምን ይጥራሽ፣ ሺ ሰማኒያ፣ ሽርሽር፣ ኢትዮጵያ የማናት፣ የኔ ማር፣ አለሁ፣ ይምጣ ያማረው፣ ታገቢኛለሽ ወይ፣ አባ ዳማ እና በቅርቡ ለህዝብ የቀረበው ‘አንድነት’›› የተሰኙ ለአንድ ሙሉ አልበም የቀረቡ ነጠላ ዜማዎቹ ወጣቱን ድምጻዊ በህዝብ እንዲወደድ አድርገውታል። በዚህ የተነሳም በዓለም ዙሪያ እየተንቀሳቀሰ ስራዎቹን ለህዝብ ያቀርባል። ዓለምን በነጠላ ይዞራል ማለት ነው።


ከዓሊ ቢራ እስከ አቡሽ ዘለቀ ድረስ በዘለቀው የኦሮምኛ ሙዚቃ ታሪክ እንደ ታደለ ገመቹ፣ ጃምቦ ጆቴ፣ አጫሉ ሁንዴሳ፣ ጌታቸው ኃይለማሪያም እና ሰለሞን ደነቀ በድንቅ ስራዎቻቸው ተደንቀው ያለፉ እና አሁንም እያስደነቁና እየተደነቁ ያሉ ድምጻዊያን ናቸው። መጋል ወረ ቃሉን ይዞ ብቅ ብሎ ሌሎች ስራዎችን እየጨማመረ የመጣው ወጣቱ አበበ ከፈኒ ወደ ፊት በኦሮምኛ ሙዚቃ አብቦ የሚታይ እንደሆነ ሙዚቃዎቹን ያዳመጡ ሁሉ ይናገሩለታል።

 

መደምደሚያ


ቀደም ባለው ክፍል በተቀመጡ ምክንያቶች አርቲስቶች ሙሉ አልበም መስራቱን ትተው በነጠላ ዜማ ብቅ ማለትን እንደመፍትሔ ወስደውታል። በተለይ ወጣት ድምጻዊያን ነጠላ ዜማን ሰርተው በዩቲዩብ መረጃ መረብ መልቀቅና በዚያ ላይ እውቅናን እያገኙ መምጣት እንደ ስኬት ያዩት ይመስላል። በእርግጥ በነጠላ ዜማ ከህዝብ ጋር ተዋውቆ ተወዳጅነትንና ተቀባይነትን ካገኙ ሙሉ አልበምን ይዞ መምጣት ጥሩ መፍትሔ ነው። ይህን ሳያደርጉ በቀጥታ ሙሉ አልበምን ይዘው በመቅረብ ቶሎ ወደ ህዝቡ መግባት ካልቻሉት ተወዳጅ አርቲስቶች መካከል አሁን በህይወት የሌሉት እዮብ መኮንን እና ሚኪያ በኃይሉ ይጠቀሳሉ። ሁለቱ ድምጻዊያን በሁሉም መመዘኛ ለአድማጭ ተስማሚ አልበም ሰርተው ቢያቀርቡም ቶሎ ወደ ህዝብ ጆሮ ሊገቡ አልቻሉም ነበር። ይህ የሆነው ደግሞ ምናልባትም ከአልበሙ በፊት ህዝብ ሊያውቃቸው ስላልቻለ ዘፈናቸውን ለማድመጥ እንደተቸገረ ይታመናል።


የእነ እዮብን ችግር የተመለከቱ መፍትሔ ብለው የሚስቀምጡት ከአልበም በፊት በነጠላ ዜማ ከህዝብ ጋር መተዋወቅ ጥሩ እንደሆነ የሚመክሩ አሉ። ሆኖም ዕድሜ ልክን በነጠላ ዜማ ብቻ ከህዝብ ጋር መኖር ስለማይቻል ለሙያው ተፈጥረናል የሚሉ ወጣቶች ከተወሰኑ የነጠላ ዜማ ስራዎቻቸው በኋላ በሙሉ የአልበም ስራ ከህዝብ ጋር ቢገናኙ መልካም ሳይሆን አይቀርም።


በዚህ ዝግጅት የተመለከትናቸው አበበ ከፈኒ እና ወንዴ ማክም ሆነ ሌሎች የዘመናችን ወጣት የነጠላ ዜማ ዘመን አቀንቃኞች ከህዝቡ ያገኙትን አቀባበል (ጥሩ ሆኖ ካገኙት) አይተው ለህዝብ ይመጥናል ያሉትን የሙሉ አልበም ስራ ይዘው ቢመጡ መልካም ነው የሚሉ አድማጮች ቁጥር ቀላል አይደለም።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
15720 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1071 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us