የጌትሽ ማሞ የአንድነት መዝሙር “ተቀበል ቁጥር 3 ያመኛል”

Wednesday, 14 February 2018 11:44


በይርጋ አበበ

 

ርዕስ ያመኛል (ተቀበል ቁጥር 3)
ድምጻዊ ጌትሽ ማሞ
ዜማና ግጥም ጌትሽ ማሞ
አቀናባሪ አቤል ሳሙኤል
ማስተሪንግ አበጋዝ ክብረወርቅ
ፕሮዳክሽን የአልባብ ምስሎች
ዳይሬክተር ሳምሶን ከበደ
ፕሮዲዩሰር ሎሚ ቲዩብ

ከሰሞኑ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ከተቆጣጠሩት በጣት ከሚቆጠሩ አዲስ ሙዚቃዎች መካከል ጌትሽ ማሞ የለቀቀው አንድ ነጠላ ዜማ ቀዳሚውን ትኩረት የሳበ ሆኗል። የበርካታ ዜማ እና ግጥሞች ደራሲው ጌትሽ ማሞ ከዚህ ቀደም ‹‹ተቀበል›› በሚል ገዥ ርእስ ሁለት ተከታታይ ነጠላ ዜማዎችን ለአድማጭ አቅርቦ ነበር። በተለይ ‹‹እንከባበር/ተቀበል ቁጥር 2›› የተሰኘው ስራው በበርካታ አገራዊ ጉዳዮች የተዋቀረ ‹‹አጽመ ስሪት›› ያለው ነው ሲሉ አድናቂዎቹ ሲገልጹ ቆይተዋል። ቁጥር አንድም ሆነ ቁጥር ሁለት ‹‹ተቀበል›› ሲል ርዕስ የሰጣቸው ሁለቱም ነጠላ ዜማዎች በዩቲዩብ መረጃ መረብ በበርካታ ሚሊዮን ተመልካቾች የተጎበኙ ስራዎቹ ሲሆኑ በቅርቡ (ባሳለፍነው ቅዳሜ ማለዳ) የለቀቀው “ያመኛል” የተሰኘው ተከታዩ ስራ ደግሞ በአንድ ቀን ብቻ ከሶስት መቶ ሺህ በላይ ተመልካች ያገኘ ስራ ሲሆን፤ ሙዚቃውን ለተመልካች ያቀረበው ‹ሎሚ ቲዩብ›› ደግሞ ለዘፋኙ 700 ሺህ ብር ክፍያ ፈጽሞለታል። በዛሬው የመዝናኛ አምዳችንም አዲሱን የጌትሽ ማሞ ነጠላ ዜማ በተመለከተ ዳሰሳ ያደረግን ሲሆን ድምጻዊ ጌትሽ ማሞም ሃሳቡን በስልክ አካፍሎናል።

 

ያመኛል ሲገለጥ
ዘውጉን በኢትዮጵያዊነት አንድነት ላይ አድርጎ የተሰራው ‹‹ያመኛል›› ነጠላ ዜማ ቪዲዮው ሲከፈት ይህን መልእክት በማስተላለፍ ነው የሚጀምረው። ‹‹ኢትዮጵያ ማንነታቸውን በፈቃዳቸው ተቀብለው በጋራ በአንድነት ለመኖር ቃል ኪዳን የገቡና ከፈጣሪያቸው ውጭ ለማንም ተገዥ ከመሆን ነጻ ወጥተው በእኩልነትና በፍትህ በመመራት እየተረዳዱ እንደ አንድ ቤተሰብ የሚኖሩባት ፍጹም ነጻ የሆኑ ህዝቦች የፈጠሯት ምድር ነች። እስኪ ዛሬ በኢትዮጵያ ምድር ወይም በውጭ አህጉር ተበትነው ካሉት የትኛው አትዮጵያዊ ነው በወላጆቹ የትውልድ ግንድ በኩል ጥቂት ወደኋላ ሄድ ብሎ የአያቶቹን፣ ቅድመ አያቶቹን የምንጅላቶቹን የዘር ሃረግ ቢስብ ራሱን የብሔረሰብ ፍሬ ማለትም ጎሳዎች የተዋሃዱበት ቅይጥ ፍጡር ሆኖ የማያገኘው? ይህ ነው ኢትዮጵያዊነት የሚያሰኘው አብይ ባህሪ›› በማለት ጌትሽ ማሞ ለአዲሱ ነጠላ ዜማው መግቢያ ተጠቅሟል።


በመጽሃፍ ቅዱስ ‹‹ነብር ዥጉርጉርነቱን ኢትዮጵያዊ መልኩን ይቀይር ዘንድ ይቻለዋልን›› እንዲል ድምጻዊ ጌትሽ ማሞም ይህን ሃሳብ በግጥምና ዜማ አዋህዶ ነብስ ሲዘራበት እንዲህ ይላል።

‹‹ከቶ የማይቀይረው ዥጉርጉር ቀለሙ ለነብር ጌጡ ነው
ለሀበሻም መጠሪያው ኢትዮጵያዊነቱ ከአምላክ የጸና ነው››

ይህ ስንኝ ኢትዮጵያዊነት እንዲሁ በአንድ ጀምበር የተገኘ ማንነት ወይም በ‹ቅባት› የሚሰጥ መጠሪያ ሳይሆን ለኢትዮጵያዊያን ኢትዮጵያዊነታቸውን ከአምላክ የተሰጠ ስጦታ ወይም የ‹ተዋህዶ› መገለጫ መጠሪያቸው እንደሆነ በአጽንኦት ይገልጻል። በመሆኑም ይላል ድምጻዊው በዜማና በግጥሙ፤ ኢትዮጵያን የነካ የአምላክን ድንበር ተጋፋ ሲል ኢትዮጵያ ከአምላክ ተራዳኢነት የተቸራት እንደሆነች ይገልጻል።


‹‹እሷን ነክቶ ሰላም አግኝቶ፤
ማንም የለም የሚኖር ከቶ።
ጠባቂዋ አለ ከላይ፤
ዙፋኑ ሁሉን የሚያይ።›› በማለት ፈርጠም እና ጠንከር ብሎ ያዜመዋል። ኢትዮጵያን ከክፉ ለመጠበቅ ፈጣሪ በተጠንቀቅ እንደቆመላት ይናገራል። ‹የእስራኤል ጠባቂ አይተኛም፣ አያንቀላፋም›› እንዲል መጽሃፍ ቀዱስ ጌትሽ ማሞም ‹‹ፈጣሪ ኢትዮጵያን ለመጠበቅ ሁሌም ዝግጁ ነው። ይህን የማያውቁ ብኩናን በኢትዮጵያ ላይ እጃቸውን ቢያነሱ የባሰ ይወርድባቸዋል›› ሲል ይናገራል።

 

ያመኛል እንዴት ተጸነሰ?
ኢትዮጵያን የሚገዛት ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ምሁራን፣ የሀይማኖት መሪዎች፣ የሲቪክ ማህበራት መሪዎች እንዲሁም አብዛኞቹ ኢትዮጵያዊያን በዚህ ወቅት በአንድ ሃሳብ ላይ ይስማማሉ። እሱም ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ በውስጣዊ ችግሮች የተከበበች መሆኗን የሚስማሙበት ጉዳይ ነው። ይህ የሆነው ደግሞ በኢትዮጵያ ታሪክ ዘርን መሰረት ያደረጉ ግጭቶችና ውንጀላዎች መታየታቸው ሲሆን ከኢትዮጵያዊነት ትልቁ ጥላ ይልቅ የዘርና የብሔር ጉዳይ በብዙዎቹ ወጣት ምሁራን ዘንድ የሚቀነቀን ጉዳይ መሆኑ ነው። በዚህ የተነሳም ኢትዮጵያዊነት አደጋ ያንዣበበበት መሆኑ ይታወቃል።


ድምጻዊ ጌትሽ ማሞም ‹‹ያመኛል›› ሲል ርእስ የሰጠውን ነጠላ ዜማ ከስድስት ወራት በፊት ጀምሮ ሲያዘጋጅ መነሻ የሆነው ይሄው አገራዊ ጉዳይ እንደሆነ ለሰንደቅ ጋዜጣ ተናግሯል። ድምጻዊው ሃሳቡን ሲገልጽ ‹‹ዜማውም ግጥሙም ታስቦበትና ጊዜ ተወስዶበት የተሰራ ስራ ነው። ለአገሬ ወቅታዊ ሁኔታ ያዘጋጀሁት ስራ ነው›› ሲል ተናግሯል። ከድምጻዊው ንግግርም ሆነ ከዘፈኑ ዜማ እና ግጥም ተነስተን ስንመለከተው ‹‹ያመኛል›› ነጠላ ዜማ ከመለያየት ይልቅ አንድነትን የመስበክ አላማ አድርጎ የተሰራ ስራ ሆኖ እናገኘዋለን። ይህንም ከዘፈኑ ላይ የተወሰኑ ስንኞችን በመጥቀስ ሃሳቡን እናዳብረው።

 

‹‹እምም እምም እምም፤ እምም ያደርገኛል፤
እንዴት ስለፍቅር ሰው አንሶ ይገኛል።
ኧረ አንድ አይደለም ዘጠኝ ሞት ይምጣ
በአገር በወገን ገፍቶ ከመጣ።
እኔ እሚያጓጓኝ በቃ ይሄ ነው
ኢትዮጵያዊነት ከዘር በላይ ነው››

እነዚህ ስንኞች በግልጽ እንደሚነግሩን ኢትዮጵያዊነት ከዘር እና ከሀይማኖትም በላይ መሆኑን ሲሆን፤ ኢትዮጵያዊነትን በዘር መንዝሮ ዝቅ ሲያደርጉት እንደማንኛውም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ድምጸዊ ጌትሽ ማሞም ‹‹እምም ያደርገኛል›› ይላል። ይህን አቋሙንም እንዲህ ሲል ያጠናክረዋል።

 

‹‹በነጻነት ሰንደቅ በከፍታ ማማ
ትኑር አትንኩብኝ ያመኛል ህመሟ።››

ያመኛል የተጸነሰውም ሆነ ጽንሱ አድጎ ለፍሬ የበቃው አደጋ ላይ የወደቀውን ኢትዮጵያዊነትን ለመመለስ እንደሆነ ከዘፋኙ አንደበትም ሆነ ከዘፈኑ ስንኞች ላይ መረዳት ይቻላል።

ኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያ በጌትሽ ዜማ
ብዙዎች ኢትዮጵያ የሶስት ሺህ ዘመናት ዕድሜ እና ታሪክ እንዳላት ሲገልጹ፤ አንዳንዶች ደግሞ ‹‹ኢትዮጵያን ጠፍጥፎ የሰራት የምኒልክ ጦር ነው ዕድሜዋም ከመቶ እልፍ አይልም›› ሲሉ በአደባባይ ይናገራሉ። ሃሳብ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ምሁራን እና አፍቅሮተ ኢትዮጵያ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን ሁለተኛውን አምርረው ሲኮንኑ ይታያሉ። ለሃሳባቸው ማጠንከሪያ የሚያቀርቡት ስነ አመክንዮ ደግሞ ‹‹ኢትዮጵያ በመጽሃፍ ቅዱስ ሳይቀር ለ41 ጊዜ ስሟ የተጠቀሰች ምድር መሆኗን፣ ከንግስት ሳባ እስከ አጼ ቴዎድሮስ በዘለቀው ዕድሜዋ በርካታ ውጣ ውረዶችን ማለፏን እንዲሁም በርካታ ዓለም አቀፍ ምሁራንና የታሪክ ተመራማሪዎች በምርምር ስራዎቻቸው ኢትዮጵያን ደጋግመው መግለጻቸውን›› በማውሳት ነው።


የዚህ ሃሳብ አራማጆች ታዲያ ስለ ኢትዮጵያ አገርነትና የግዛት ወሰን ሲናገሩ ‹‹እንደ ሰንበቴ ማህበር ወይም እቁብ ስብስብ›› በቀላሉ የተገኘች ሳይሆን ብዙ ደምና አጥንት የተከፈለባት እንደሆነች በማውሳት ጭምር ነው። እንደ ድምጻዊት እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ያሉ ድምጸ መረዋ ዘፋኞችም ይህን ሃሳብ ያጠናክሩታል።

 

‹‹አድዋ ዛሬ ነው አድዋ ትናንት
መቼ ተነሱና የወዳደቁት።
የምኖረው ህይወት ዛሬ በነጻነት ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት›› በማለት የኢትጵያ ታሪክ የመንደር ቡድን ታሪክ ሳይሆን የደምና አጥንት ድምር ውጤት መሆኑን ትናገራለች በዜማዋ። 

ከጂጂ ሃሳብ ጋር የሚስማማው ድምጻዊ ጌትሽ ማሞም በ‹‹ያመኛል›› ዘፈኑ

 

‹‹በብዙ ደም አጥንት ተበጅታ የኖረች
በዘመን ስንክሳር ተፈትና ያለፈች።
በቀደመው ፍቅር በማይነጥፍ ማንነት
ቀድማ የታጠቀች በአትንኩኝ ባይነት›› ሲል የትናንቷን ኢትዮጵያ ስሪት ይናገራል። ስለዛሬዋ ኢትዮጵያ ልጆች ሲናገርም ‹‹ኖረው የሚያስጠሯት ሞተው እሚያኖሯት ልጆች አሏት ዛሬም ልክ እንደትናንት›› ሲል ለዚህች አገር ህልውና ራሳቸውን አሳልፈው ለመስጠት የተዘጋጁ ልጆች እንዳሏት ይገልጻል። ኢትዮጵያዊነት ዛሬ እንዲህ በዘርና በጎሳ ከመከፋፈሉ በፊት ለኢትዮጵያ ህልውና መስዋዕት የከፈሉትን ዜጎች ሲጠቅስም አንድ ከሰሜን አንድ ከምዕራብ የተወለዱ ጀግኖች ያነሳል።

‹‹ዘርአይ ደረስ ሲሞት ሰንደቅ ተሸክሞ
ጃጋማ ተተካ ከመብረቅ ፍም ቀድሞ››

ዛሬ ኤርትራ ከእናት አገሯ ኢትዮጵያ ተገንጥላ (መሪዎቿ ነጻነቷን ተጎናጽፋ ይሉታል) ራሷን ችላ አገር ከመሆኗ በፊት ዘርአይ ደረስ ለኢትዮጵያ አንድነት የከፈለውን ጀግንነት ከኦሮሞው ጃጋማ ኬሎ ጋር አዋህዶ ያቀርበዋል ጌትሽ ማሞ። በእርግጥ በጌትሽ ማሞ እይታ ኢትዮጵያዊነትን ወዶ እና ፈቅዶ መቀበል ሲባል ማንነትን ረስቶ ስርን ዘንግቶ እንዳልሆነ በአጽንኦት እንዲህ ሲል ይናገራል።

 

‹‹ማንነትን ማወቅ ስርን ማየት ጥሩ
የአንድነቱ ገመድ ሳይበጠስ ክሩ››

ይህን ተፈጥሯዊ ማንነት ማወቅና መመርመር ሲባል የራስን አወድሶ የሌሎችን አውግዞ ወይም አሳንሶ በማየት የታላቁን ዛፍ ፍሬ (ኢትዮጵያዊነትን) በማጥፋት መሆን እንደሌለበት ስንኙ ላይ የገባው ሀረግ ይገልጻል። ይህን የአንድነት ገመድ ሳይበጠስ ለማስቀጠል ደግሞ ሁሉም በየጎጡ ማሰቡን ትቶ ስለ ታላቁ ምስል መጨነቅ ይኖርበታል ሲል የጌትሽ ማሞ ዘፈን ምክረ ሃሳቡን ይለግሰናል።

‹‹ከዚህም ከዚያም ሆኖ ስሙ ሀይማኖቱ
ከዘር ይሻገራል ኢትዮጵያዊነቱ።
ቆጥረህ ላትጨርሰው የዘር ሀረጌን
ማነህ? አትበለኝ ማን ልበል? አንተን።
እንዲያው ሌላው ቢቀር ስትመለከተኝ
ምን አይተኽብኛል ካንተ የሚለየኝ?
በታመመ ብዕሩ በከንቱ ሙገሳ
የአንድ እናት ልጆች ነን ይህንን አንርሳ።››

ይህን ብሎ ማለፍ በቂ መስሎ ያልታየው ድምጻዊው ስለ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን ሲቆረቆር ይህን ብሏል።

‹‹አላጊጥ ይቅርብኝ ወርቄንም እንካችሁ
ነገም ከማገኘው ሰርቼ ልስጣችሁ
ብቻ በወገኔ በአገሬ መጣችሁ
እንዳታሳምሙኝ እናንተም ታማችሁ።
ጀግንነት መከታው ከአያት ቅድመ አያቱ
ቋንቋው ጉራማይሌ ፍቅሩ ሀይማኖቱ።
ጠፍቶ ከገበያው ዋጋ ቢያጣ ብሩ
ዘር በሰው ልጅ ሆነ የሚለካው ክብሩ።
ሰው በጎጥ አበደ ልቡን ሞላው ክፋት
አምላኬ አደራህን ኢትዮጵያን ጠብቃት።
እንደ ዐይኑ ብሌን የሚጠብቃት
አገሬ አገሬ እሱ አምላክ አላት።
በሰላም ውሎ በቸር ይደር
የእምዬ ጓዳ የእናቴ ምድር›› ሲል ተቆርቋሪነቱን ሲገልጽ እንመለከታለን።

ያመኛል ከአዱኛ እና ከትወና አንጻር ያመኛል (ተቀበል ቁጥር 3) የተሰኘውን ነጠላ ዜማ ‹‹ሎሚ ቲዩብ›› የተባለ የማህበራዊ ትስስር ገጽ በ700 ሺህ ብር ከጌትሽ ማሞ ላይ ገዝቶታል። ለአንድ ነጠላ ዜማ ይህን ያህል ገንዘብ አልበዛም ወይ? የሚል ጥያቄ ከሰንደቅ ጋዜጣ የቀረበለት ጌትሽ ማሞ ሲመልስ ‹‹አልበዛም፤ የተከፈለኝ ክፍያ የተጋነነ ሳይሆን የሚገባኝን ነው። እንዲያውም የኢትዮጵያ ሙዚቃ ከዚህ በላይም ሊከፈለው ይገባል›› ብሏል።
‹‹ያመኛል›› ካለፉት ተከታታይ ነጠላ ዜማዎች በምን ይለያል? የሚል ጥያቄ ለጌትሽ ቀርቦለት ነበር። ድምጻዊው ሲመልስም “ያመኛል”፣ ከእንከባበርም ሆነ ከተቀበል በዜማ፣ በመቼት፣ በቪዲዮ ቀረጻ እና በይዘትም የተለየ መሆኑን ተናግሯል። ለዚህም ኢትዮጵያዊነትን ሊገልጹ በሚችሉ አልባሳት፣ አባት እና እናት አርበኞች እንዲሁም ቁሳቁሶች ታጅቦ የተቀረጸ ስራ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም በነበሩት ሁለት ስራዎች ላይ የዘፈኖቹ ‹‹ክስተት›› የነበረው ተዋናይ ሳሙኤል ለገሰ እንዳለፉት ሁሉ በዚህ ዘፈንም የአጋፋሪነቱን ሚና በአግባቡ የተወጣበት ሆኖ ቀርቧል። ከጌትሽ ጋር በአጋፋሪነት (ፈረንጆች ባክ ሲንገር የሚሉት ሊሆን ይችላል) ሁለት ስራዎች ላይ የታየው አርቲስት ሳሙኤል ለገሰ በቅርቡ የራሱን ስራ ‹‹ፍቺኝ›› ሲል ይዞ መቅረቡ የሚታወስ ነው።


“ያመኛል” በጌትሽ ማሞ የቀረበ ድንቅ ስራ ሲሆን ግጥሞቹን አዳምጦ ለመረዳት ትንሽ አስቸጋሪ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ድምጻዊው ከዚህ ቀደም በሙሉ አልበምም ሆነ በነጠላ ዜማዎችና በፊልም ማጀቢያ ሙዚቃዎች ላይ ብቃቱን ያሳየ ድንቅ ዘፋኝ መሆኑ ይታወቃል። (የሶስት ማዕዘን ፊልም ማጀቢያ ሙዚቃ በአፍሪካ ደረጃ ሽልማት የተቸረው ስራ መሆኑን ልብ ይሏል) ይህ የአሁኑ ስራውም በከፍተኛ ጥንቃቄ የተሰራ እና የብዙ ባለሙያዎች እገዛ የታየበት ስራ ቢሆንም ታስቦበት ይሆን ወይም በስህተት የተፈጠረ ማወቅ ባይቻልም ዘፈኑ ሲጀምር ጌትሽ ማሞ የሚገባበት ድምጽ ዜማው የራሱ ሳይሆን ቀደም ብሎ ከተሰሩ ስራዎች የተቀዳ ይመስላል። በተለይ ‹‹ከቶ እማይቀይረው….›› ብሎ ሲገባ ስሙን ከዘነጋሁት ምዕራብ አፍሪካዊ የሬጌ ሙዚቃ ተጫዋች ላይ ቴዲ አፍሮ ወስዶ ‹‹ኮርኩም አፍሪካ›› ሲል ከተጫወተው ዜማ ጋር ይመሳሰላል።


ከዚህ በተረፈ ግን በመልዕክት፣ በዜማ፣ በግጥም፣ በቀረጻ፣ በትወና እና በቁሳቁስ አጠቃቀም እጅግ የተዋጣለት ስራ ሆኖ አግኝቼዋለሁ ‹‹ያመኛል››ን። ዝግጅት ላይ ካለው ሙሉ አልበሙ እና ከአልበሙ በፊት ለህዝብ ይቀርባል ተብሎ የሚጠበቀውን የጌትሽ ማሞ ነጠላ ዜማ እስኪወጣ ድረስ ከያመኛል ዘፈን ስንኞች ላይ ጥቂት ዘግነን እንሰናበት።


‹‹በብዙ ደም አጥንት ተበጅታ የኖረች
በዘመን ስንክሳር ተፈትና ያለፈች።
በቀደመው ፍቅር በማይነጥፍ ማንነት
ቀድማ የታጠቀች በአትንኩኝ ባይነት።
ከዚህም ከዚያም ሆኖ ስሙ ሀይማኖቱ
ከዘር ይሻገራል ኢትዮጵያዊነቱ።
ቆጥረህ ላትጨርሰው የዘር ሀረጌን
ማነህ? አትበለኝ ማን ልበል? አንተን።
እንዲያው ሌላው ቢቀር ስትመለከተኝ
ምን አይተኽብኛል ካንተ የሚለየኝ?
በታመመ ብዕሩ በከንቱ ሙገሳ
የአንድ እናት ልጆች ነን ይህንን አንርሳ።
ሰው በጎጥ አበደ ልቡን ሞላው ክፋት
አምላኬ አደራህን ኢትዮጵያን ጠብቃት።
እንደ ዐይኑ ብሌን የሚጠብቃት
አገሬ አገሬ እሱ አምላክ አላት።
በሰላም ውሎ በቸር ይደር
የእምዬ ጓዳ የእናቴ ምድር።››

በሰላም ውለን ቸር እንደር። ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!! የአዘጋጁ የመሰናበቻ መልእክት ነው።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
15329 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1039 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us