“ማስታወቂያ ውሸትን ሳይሆን ግነትን ይፈልጋል”

Wednesday, 23 April 2014 11:30

ይህ ሰው ባለወርቃማ ድምፅ ነው ይባልለታል። በርካቶች የሚያውቁት በሚሰራቸው ማስታወቂያዎቹ ሲሆን፤ በተለይ ከአርቲስት ሙሉዓለም ታደሰ ጋር የሰራው “ግብዣ ያለአንቦ ውሃ” በምትለው ማስታወቂያው አይረሱትም። በአሁኑ ወቅት የግሉን የማስታወቂያ ድርጅት ዘ ጎልደን ቮይስ (The golden voice) ሲል ከፍቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። ብዙዎቹ በማስታወቂያ ሥራዎቹ ይወቁት እንጂ ጎበዝ ተዋንያንም እንደሆነ የሚመሰክሩለት ጥቂቶች አይደሉም። ሰማያዊ ፈረስ፣ ጆከር፣ 3ኛ ወገን፤ ትዝታህ፣ ሰምና ወርቅን ጨምሮ በዚህ ሳምንት ተመርቆ የሚታየውን “ሊነጋሲል” ፊልሞችን በብቃት ተውኖባቸዋል። የምድር ጦር ኦርኬስትራ መድረክ መሪ የነበረው ይህ የዛሬው የመዝናኛ አምድ እንግዳችን አርቲስት ቢኒያም በቀለ ነው፤ መልካም ቆይታ፤

ሰንደቅ፡- ብዙ ሰዎች በማስታወቂያ ስራዎችህ ነው የሚያስታውስህ፤ ለመጀመር ያህል ወደማስታወቂያ ስራ እንዴታ ገባህ?

ቢኒያም፡- ወደሚያስታወቂያ ስራ የገባሁበትን ትክክለኛ ጊዜ አላስታውሰውም። ግን በፍቅር ነው የገባሁት፤ ልጅ እያለሁ በትምህርት ቤት ውስጥ ለተማሪዎች ቀልድ ማውራት እወድ ነበር። አንድ ጎረቤቴ የነበረ ልጅ አለ አባቱ አየር መንገድ ይሰሩ ስለነበር መፅሔት ያመጣልኛል። ከእዚያ ላይ ብዙ ቀልዶችን እየተረጎመ ያወራልኛል። እኔ ደግሞ እሱን ገልብጬ ት/ቤት ሄጄ ተማሪ አስቅበታለሁ። ያኔ ነው ሰው ፊት ማውራትንና መደመጥን ያዳበርኩት ይመስለኛል።

ሰንደቅ፡- በአገር አቀፍ ሚዲያዎች መስራቱንስ መቼና እንዴት ጀመርከው?

ቢኒያም፡- ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን መጎርጎር እወድ ነበር። አንድ ጊዜ ወደመርካቶ ዕቃ ልገዛ ሄጄ አንድ ሱቅ በር ላይ የዘፈን ማስታወቂያዎችን ሰማሁ። “እገሌ የሚባል ዘፋኝ እንትን የተሰኘ ዘፈን ይዞላችሁ ቀርቧል፤ እገሌ የተባለ ሙዚቃ ቤት ታገኙታላችሁ” ምናምን የሚል ማለት ነው። ታዲያ ስሰማ ለኔ አልጣፈጠኝም፤ ቤት ገብቼ ራሴን በካሴት እየቀረፅኩ እኔ ካሴቱን ባስተዋውቀውስ እያልኩ ለራሴ መሞከር ጀመርኩ። ከዚያ ለመጀመሪያ ጊዜ የአሰፉ ደባልቄን ዘፈን ከኢትዮ-ሙዚቃ ቤት ጋር አስተዋውቄ ድምፄ በይፋ መሰማት የጀመረው ያኔ ነው። ባይገርምህ አቶ ውብሸት ወርቃለማሁም ድምፄን የወደዱትና የተዋወቅነው ያኔ ነበር። ከዚያ ከሳቸው ጋር ሆኜ የሎተሪ ማስታወቂያ ሰራሁ፤ በዚያው ቀጠልኩ። ለመጀመሪያ ጊዜ ድምፄ በሬዲዮ የተሰማ ጊዜ ግን ደስታዬ ወደር አልነበረውም።

ሰንደቅ፡- ማስታወቂያ መልዕክቶችና አዝናኝነት እስቲ ንገረኝ?

ቢኒያም፡- ማስታወቂያ መልዕክቱን ሳይስት ትኩረት ሳቢና አዝናኝ ሆኖ መቅረብ አለበት ብዬ አምናለሁ። በማስታወቂያ ድርቅ ብለህ ይህንን ሳሙና ግዙ ብትል አይሆንም። “አረፋው ይኩረፈረፋል፤ አያልቅም፤ ሽታው አይረሳም” ማለትና ጆሮ ገብ ቃላትን መጠቀም ይኖርብሃል። ማስታወቂያን በአዝናኝና በማይሰለች መልኩ ማቅረብ ተገቢ ነው።

ሰንደቅ፡- ስለአንድ ዕቃ ለማስተዋወቅ ሲባል ምርቱን ከሚገባው በላይ ማጋነን ውሸት አይሆንም?

ቢኒያም፡- በሌለ ነገር ላይማ አለ ብሎ መጮህ ነውር ነው። እርግጥ ነው ማስታወቂያ ግነት ይፈልጋል። ታዲያ ያም ሲባል መጠኑን ያለፈ መሆን የለበትም። ብልጥ ግነት ነው መሆን ያለበት፤ እውነቱን ለመናገር በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ ማስታወቂያዎችን ስሰማ ከግነትም አልፈው ወደስድብ ደረጃ የገቡም አጋጥመውኛል።

ሰንደቅ፡- ከሰራሃቸው በርካታ ማስታወቂያዎች መካከል አሁን ድረስ የማትረሳው የትኞቹን ነው?

ቢኒያም፡- በማስታወቂያ ስራዬ የኔ “ማስተር ፒስ” ነው የምለው ስራ ከአርቲስት ሙሉዓለም ታደሰ ጋር የሰራሁት የአምቦ ውሃ ማስታወቂያ ነው። “ግብዣ ያለ አምቦ ውሃ” የምትል አሁን ድረስ ብዙዎች ያስታውሱታል። ሌላው የመኪና ነው። ባይገርምህ ከሀገራችን ማስታወቂያዎች በተጨማሪ የሌላ አገራትንም ማስታወቂያዎች በደንብ አያለሁ። በሀገራችን ስለመኪና ሲተዋወቅ “ለሀገራችን መንገድ ተስማሚ፣ ለሀገራችን አየር ተስማሚ” ምናምን እየተባለ የጎማ ይሁን የመኪና ማስታወቂያ ያለየ ሆኖ ታየዋለህ። አሁን ለምሳሌ “ቮላሬ” የሚል መኪና እንዳስተዋውቅ ተጠራሁ። የመኪናውን እንቅስቃሴ የበር፣ የመሪና የማርሽ ሁኔታ በቴሌቭዥን (በምስል) ካሳየሁ በኋላ በድምፅ ተናገርኩት አንድ ቃል ብቻ ነው፤ “ቮላሬ!” አለቀ። እኔ ከምናገረው በላይ ስለመኪናው ምስሉ አሳይቷል። አሁን የቀረው ይሄ መኪና ማን መሆኑን ብቻ መናገር ነበር፤ እርሱን ተናግሬ ዘጋው።

ሌላው ብዙዎቹ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተሳፋሪዎች የሚያውቁት ስራዬን ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁን ድረስ ለብዙ ዓመታት የሚጠቀምበትን የአውሮፕላን ውስጥ ማስታወቂያ የሰራሁት እኔ ነኝ። በዚህ ማስታወቂያ ላይ የሚሰማው ድምፅ እንኳን ሌላውን ሰው ቀርቶ እኔንም ይማርከኛል። ባይገርም ያ ልጅ እያለን መፅሄት እያመጣልኝ “ጆኮችን” ይተረጉምልኛል፤ ያልኩህ ልጅ አሁን ይህን ማስታወቂያ የሰማ ጊዜ ለሆስተሶቹና አብረውት ለሚሰሩት ሁሉ “ቢኒያም የሚባል ጓደኛዬ ነው የሰራው” ሲላቸው አያምኑትም። ማስታወቂያውን ስሰራ ያኔ ወጣት ነበርኩ። ከዚያም ከሆስተሶቹና ከፓይለቶቹ ጋር ላስተዋውቅህ አለኝና፤ ሄድኩ። እዛ ክበብ አላቸው ዳር ላይ ቁጭ ብዬ አስር የሚሆኑ ሰዎች መጡ። እኔን ሲያሳያቸው ከጠበቁት በታች ሆንኩባቸው መሰለኝ ወዲያው ነበር የቀዘቀዙት። ሁሉም “ሃይ!” ብለውኝ ሄዱ። አየህ እነርሱ የጠበቁት ሽክ ያለ ሰው ምናምን ነበር። እኔ ደግሞ እንደምታየኝ ቀለል ያለ ነገር ነው የሚመቸኝ። በነገራችን ላይ በዚህ ማስታወቂያ የረባ ጥቅም አላገኘሁበትም። አየር መንገዱም አንድም ቀን ጠርቶ አላመሰገነኝም።

ሰንደቅ፡- እስቲ ከማስታወቂያ ባለሙያው ከአቶ ውብሸት ወርቃለማሁ ጋር የነበራችሁን ትውውቅ አስታውሰኝ?

ቢኒያም፡- ባይገርምህ ይህ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ማስታወቂያ ውድድሩ የመጣው በእርሳቸው ድርጅት በኩል ነበር። እኔ ያኔ በርሳቸው ስር ነበር የምሰራው። ተወዳድሬ ድምፄ ስለተመረጠ ነው ዕድሉን ያገኘሁት። በነገራችን ላይ አንበሳ ማስታወቂያ ድርጅት ከመግባቴ በፊትም ቢሆን ማስታወቂያን እሰራ ነበር። ትዝ ይለኛል ከአቶ ውብሸት ወርቃለማሁ ጋር የተገናኘነው የድምፃዊት አሰፉ ደባልቄን ዘፈን ማስታወቂያ ሰርቼ፤ ከአቶ አስራት ዋሬ (የኢትዮ ሙዚቃ ቤት ባለቤት) ገንዘብ ልቀበል ሄጄ ነው። አቶ ውብሸትን እዛ መጥተው ማስታወቂያዬን ሲሰሙ በአድናቆት “የዚህ ልጅ ድምፅ ጥሩ ነው” አሉ ያኔ ነው የተዋወቅነው፤ ከዚያም አብሬያቸው እንድሰራ ጋብዘውኝ ደስ እያለኝ አብሬያቸው መስራት ጀመርኩ።

ሰንደቅ፡- ማስታወቂያ በጥቂት ሰከንዶች ጊዜ ውስጥ የተገደበ ነው። ላንተ ፈተና ሆኖህ ያስቸገረህ አጋጣሚ የለም?

ቢኒያም፡- አንድ ጊዜ የሆነ ኤሌክትሮኒክስ መደብር ለሽያጭ ያቀረባቸውን ምርቶች እንዳስተዋውቅለት ጋብዘኝ። ባለቤቱ ሱቁን አስጎበኘኝ የሌለ የቲቪ አይነት የለም። የሌለ ሬዲዮ አይነት የለም። የሌለ የፍሪጅ አይነት የለም። ሰውየው ሁሉንም በስም እየጠራሁ እንዳስተዋውቅለት ፈለገ። እኔ ደግሞ ሁሉንም መጥራት አልችልም አልኩት፡፤ በተመጣጣኝ ዋጋ፣ ኦሪጅናሉን ዕቃ እዚህ አካባቢ በሚገኘው እገሌ ሱቅ ውስጥ ያገኙታል የሚለውን ብቻ ነው መናገር የሚጠበቅብኝ አልኩ። ሰውዬው ግን ሁሉም ዕቃዬ በስም ካልተጠራ አይሆንም አለ። በዚህ ሳልሰራው ተለያየን ማለት ነው።

ሰንደቅ፡- እስቲ ደግሞ ስለፊልም ስራዎችህ እንጨዋወት፤ እንዴት ነው ተዋናይነት?

ቢኒያም፡- ወደፊልሙ ዓለም ከመግባቴ በፊት ብዙ መድረኮችን እመራ ነበር። በነገራችን ላይ የምድር -ጦር መድረክ መሪም ነበርኩ። ባይገርምህ መድረክ ስመራ እቀልዳለሁ፤ የምቀልደው ደግሞ በራሴ ጭምር ነው። ታዲያ ቀልዶችን ሳወራ “አክት” አደርግ ስለነበር ትወናው ከዚያ ጋር ተያይዞ የመጣ ይመስለኛል። በነገራችን ላይ ልመንህን ኩምክና ያስተማርኩት እኔ ነኝ። እኔ ከፍተኛ 15 ስሰራ እርሱ የኔን ልብስ ይዞ ይከተለኝ ነበር። ከዚያ በኋላ ነው አለባቸውና ልመንህ ገጥመው ጥሩ ኮሜዲያን የሆኑት። ወደጠየከኝ ስመለስ የመጀመሪያ ፊልሜ የሰራዊት ፍቅሬ “ሰማያዊ ፈረስ” ነው። ጥሩ ስራ ነበር፤ ከሰራዊት ጋር በድጋሚ “ጃዊሳሮ” የተሰኘ ፊልም ሰርቻለሁ። ከዚያ በኋላ ብዙ ፊልሞች መጡ፤ ድራማዎች መጡ፤ ትናንሽ ጭውውቶችም ነበሩ። መቼም በኛ ሀገር የፊልም ስራ አንድ ጊዜ ዘበኛ ሆነህ ከሰራህ ሁልጊዜ ዘበኛ ነው የምትሆነው፤ ሰራተኛ ሆነህ ከሰራህ ሰራተኛ ሆነህ ትቀራለህ፤ አባት ሆነህ መስራት ከጀመርኩ ሌላውም አባት ሆነህ እንድትሰራለት ይፈልጋል። እኔም እንደ አጋጣሚ “ገመና” ላይ ፖሊስ ሆኜ ተጫወትኩ። ከባህሪው ወጣ ያለ ፖሊስ ነበር የሰራሁት፤ ከዚያ አንድ ሰው ፊልም ይዞ መጣና ፖሊስ ሆነህ ተጫወትልኝ አለኝ። ኖ እኔ ሌላ ገፀ-ባህሪይ መሞከር እፈልጋሁ ብየ ሳልሰራው ቀረ።

ሰንደቅ፡- በፊልም አሁን በቅርቡ ለዕይታ ከሚበቃ “ሊነጋ ሲል” በፊትና ከሰማያዊ ፈረስ በኋላ የምታስታውሰኝ የለም?

ቢኒያም፡- የማልረሳውን ልንገርህ፤ ከግሩም ኤርሚያስ ጋር “ትዝታህ” የሚል አሪፍ ፊልም ሰርቻለሁ። ከዚያ “ሰምና ወርቅ”ን ከፍቃዱ ተ/ማርያም ጋር ሰርቻለሁ። ከዚያ “ጆከር”፣ “አንድ ቀን” ፣ “3ኛ ወገን” ፣ “አማረኝ” የተሰኙ ፊልሞች ሰርቻለሁ። ሌሎችም አሉ ለጊዜው አላስታወስኳቸውም።

ሰንደቅ፡- አዲሱ ፊልም “ሊነጋ ሲል” ምን የተለየ ነገር አለው?

ቢኒያም፡- ፊልሙ በጣም የፈጠራ ሃሳብ የታየበት ነው። ኢትዮጵያ ወደፊት መንኩራኩር አምጥቃ የሚከሰተውን ለውጥና ፍጥጫ መነሻ አድርጎ የተሰራ ፊልም ነው። ሰራዊት ፍቅሬ በ“ሰማያዊ ፈረስ” ፊልም አባይን የማዝነብ ሀሳብ እንዳነሳ ሁሉ ይህም በመንኩራኩር ሳይነሳ ላይ ተመስርቶ ተሰፋን የሚያሳይ ፊልም መሆኑ ይለየዋል።

ሰንደቅ፡- በሰራሃቸው ፊልሞች የሚገባኝን በቂ ክፍያ አግኝቻለሁ ብለህ ታስባለህ?

ቢኒያም፡- አይደለም በፊልም በማስታወቂያ እንኳን በቂ ክፍያ አይከፈለኝም። ችግሩ ደግሞ የራሴ ይመስለኛል። ገንዘብ ስጠይቅ እፈራለሁ። እኔ የምጨነቀው ስለምሰራው ስራ ነው፤ ሰው አስቦ ይከፍለኛል ብልም አሁን ድረስ የሚገባኝን ተከፍሎኛል የምለው ዋጋ የለም።

ሰንደቅ፡- በምን ትዝናናለህ?                

ቢኒያም፡- ይገርምሃል ለኔ እፎይታ የማገኘውና የምዝናና ከቤተሰቦቼ ጋር ስሆን ነው። በተለይ ባለቤቴና ትንሹ ልጄ ለኔ ጥሩ መዝናኛዎቼ ናቸው። ለኔ እነሱ መንፈሴን ዘና የማደርግባቸው መድሃኒቶቼ ናቸው (ሳቅ). . . ይህን ስልህ ግን ሌሎቹ ልጆቼንም በጣም እንደምወዳቸው ልነግርህ እወዳለሁ።

ሰንደቅ፡- በጣም አመሰግናለሁ?

ቢኒያም፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ። እናንተንም በጣም እወዳችኋለሁ በርቱ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
15780 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us