ኪነ ጥበብን ከፍ ያደረጉት የአድዋ ተጓዦች

Wednesday, 14 March 2018 12:59

 

በይርጋ አበበ

ከአምስት ዓመት በፊት የተጀመረው የጉዞ አድዋ ቡድን በዚህ ዓመት አምስተኛ ጉዞውን አድርጓል። ለ45 ቀናት የፈጀውን ጉዞ ያካሄዱት የጉዞ አድዋ ተጓዦች በዚህ ዓመት ካለፉት ጉዞዎች በተለየ መልኩ አንድ የጉዞ አባል ጨምረዋል። የአጼ ምኒልክ የትውልድ ሰፈር አንጎለላ ሲደርሱ የጉዞ አባላቱን በራሷ ፈቃድ የተቀላቀለች አንዲት እንስት ውሻ ከተጓዦቹ ጋር አስቸጋሪውን ውጣ ውረድ የበዛበት ጉዞ አካሂዳ አዲስ አበባ ገብታለች። ተጓዥ ውሻዋን ጨምሮ ሁሉም የጉዞ አባለት ከትናንት በስቲያ በጣይቱ ሆቴል የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ዛሬ በመዝናኛ አምዳችን ላይ የምንመለከተው በጉዞ አድዋ ዙሪያ የተዘጋጀ ሲሆን ጉዞውንና በጉዞው የነበሩ ክንውኖችን እንዲሁም ከዚሁ ጋር የተያያዙ ክስተቶችን የዳሰሰ ነው። ይህን ጽሁፍ ለማዘጋጀት የጉዞ አድዋ አስተባባሪው ያሬድ ሹመቴ በብሎጉ ያሰፈረውን በዋቢነት ተጠቅመናል።

የጉዞ አድዋ ፭ አብይ ክስተቶች በጨረፍታ

ጉዞ አድዋ የተዘጋጀው በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች አማካኝነት ሲሆን ዓላማውም ኢትዮጵያን ለመውረር ባህር አቋርጦ የመጣውን ወራሪውን የጣሊያን ጦር ለመመከት ወደ ጦር ሜዳው የተጓዙ አባቶችንና እናቶችን ለማሰብ ነው። ጉዞውም ከአዲስ አበባ ተጀምሮ አድዋ ወረዳ በሚገኘው ሶሎዳ ተራራ ድረስ በእግር የሚከናወን ጉዞ ነው።

ጉዞውን የአድዋ ተወላጁ ባለጸጋው አቶ ዳዊት ገብረእግዚአብሔር የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉለት ሲሆን የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ ደግሞ የጉዞው አካል የሆኑበት ነው። (በጉዞው የመጨረሻ ቀን ላይ ተሳታፊ ነበሩ) አሸኛኘቱ በካሌብ ሆቴል የተከናወነ ሲሆን አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮም) በሽኝቱ ላይ ተገኝቶ ‹‹ሰላም ግቡ›› ብሎ አሸኛኘት አድርጎላቸዋል። በዚህ መልኩ የተጀመረው አምስተኛው ዙር ጉዞ አድዋ ከ45 ቀናት በኋላ ከታሪካዊቷ አድዋ ከተማ ደርሰዋል። በዚህ ጉዞ ውስጥም ከአንጎለላ ጀምሯ የጉዞ አባሉን የተቀላቀለችው ውሻ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ ተሳታፊ ሆና ጉዞውን ጨርሳ ተመልሳለች።

የጉዞ አድዋ ፊታውራሪው የፊልም ባለሙያው ያሬድ ሹመቴ የጉዞውን እያንዳንዱን እንቅስቃሴ በግል ብሎጉ ሲከትብ እንደተመለከትነውም ደብረ ብርሃን ሲደርሱ የደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችና ማህበረሰብ አቀባበል አድርገውላቸዋል። ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ በኋላም በወልድያ ዩኒቨርስቲ የመጽሃፍ ማንበብ እና ስለ አድዋ ድል ትምህርት የሰጡበት እንደሆነም ገልጿል። የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ደግሞ ተጓዦቹን በሽለላ እና በፉከራ በደማቅ ስነ ስርዓት የተቀበሏቸው ሲሆን በእግራቸው ሲጓዙ የዋሉትን ተጓዦች እግር አጥበው መስሪያ አቅርበውላዋል። በዚህ የእራት ግብዣ ድግስ ላይ 26ኛዋ ተጓዥ ቡቺ ታዳሚ ነበረች እግሯን አልታጠበችም እንጂ።

ከዩኒቨርስቲዎች በተጨማሪም ሌሎች አካላት አቀባበል እንዳደረጉላቸው የገለጸው የፊልም ባለሙያው፤ ከእነዚህ መካከል በአላማጣ የኢትዮጵያ ቡና ደጋዎች ያደረጉላቸው አቀባበል አንዱ ነው። ቡናማዎቹ ከሰሜኑ ተወካይ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ ጋር የነበረባቸውን የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ አካሂደው ሲመለሱ ነበር ለጉዞ አድዋ ፭ አባላት አቀባበል ያደረጉላቸው።

ጉዞው እየተካሄደ ባለበት ወቅትም የካቲት 4 ቀን በመድረሱ ማይጨው ላይ አንድ ትልቅ ተግባር ተከናውኗል። ይህም እቴጌ ጣይቱ ብጡል ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ ያረፉበት ዕለት በመሆኑም አራቱ የጉዞው ሴት አባላት ጉዞውን በመሪነት አስጀምረው ያስጨረሱ ሲሆን በማይጨው ከተማም የጧፍ ማብራት ስነ ስርዓት አከናውነዋል። ማይጨው ከመድረሳቸው በፊት ደግሞ ለአድዋ ጦርነት ምክንያት የሆነው የውጫሌ ውል በተፈረመበት ይስማ ንጉስ የሚባው ቦታ ላይ አጼ ምኒልክን የሚዘክርና ለክብራቸው የሚመጥን ዜማ አዘጋጅተው ዘምረዋል። ሌላው የዚህ ጉዞ ትልቁ ገጠመኝ ከአዲስ አበባ ከወጡ በኋላ አማላጣ እስከሚደርሱ ድረስ ኢንተርኔት የሌለ መሆኑ ነው።

ተጓዦቹ ግዳጃቸውን ጨርሰው 25 ሆነው ወጥተው 26 ሆነው አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ ከትናንት በስቲያ ሰኞ አመሻሽ ላይ በጣይቱ ሆቴል የአድዋ ድል በዓል የመዝጊያ ዝግጅት እና ተጓዦቹን የማመስገን ስነ ስርዓት ተከናውኗል። በዕለቱ የተገኙት የፍልስፍና ምሁሩ ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ ‹‹ታሪክ ሻንጣ አይደለም የትም ጥለኸው ሄደህ ስትፈልግ የምታነሳው›› ሲሉ ተናግረዋል። ታሪክን ለማስተማር ላደረጉት ጥረትም የጉዞ አድዋ አባላትን አመስግነዋል። ለጎዙ አድዋ አባላትም የሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

 

 

መደምደሚያ

‹‹አርቲስት ወይም የኪነ ጥበብ ሰው ለአገር እና ለትውልድ ረብ ያለው ስራ ሰርቶ ማለፍ ሙያዊ ግዴታው ነው። የጉዞ አድዋ ተጓዦችም ሙያዊ ግዴታቸውን መወጣት በፈለጉ የኪነ ጥበብ ሰዎች አስተባባሪነት የተሰናዳ ፕሮግራም ሲሆን ይህን በማድረጋቸውም ምስጋና ይገባቸዋል›› ሲሉ አስተያየታቸውን ለዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ የሰጡ ሰዎች ተናግረዋል።

ምንም እንኳን ቦታው ለአዲስ አበባ ሩቅ ቢሆንምና የመንገዱ መልክዓምድራዊ አቀማመጥ አስቸጋሪ ቢሆንም ቡቺን ጨምሮ 26ቱ የጉዞ አድዋ ተጓዦች የማይቻል የሚመስለውን ሰርተው በብቃት ተወጥወተው አሳይተዋልና ክብር ልንሰጣቸው ተገድደናል።

የጉዞው ፊታውራሪ የፊልም ባለሙያ ያሬድ ሹመቴ የጉዟቸውን ማጠቃለያ አስመልክቶ በብሎጉ ‹‹የዳግማዊ ምኒልክን ስም በጉልህ ለማወደስ ያደረግነው ጥረት ተሳክቶልን በድል ተመልሰናል ደስም ብሎናል›› ሲል ጽፏል። የዛሬ ዓመት በፊት በተከበረው የአድዋ ድል በዓል የጉዞ አድዋ አባላትን ወክሎ በበዓሉ ፕሮግራም ላይ ንግግር እንዲያደርግ ሲጋበዝ ‹‹ለድሉ መገኘት ብስለትና ጥበብ የተሞላበት አመራር የሰጡትን አጼ ምኒልክን ልናመሰግን ይገባል›› ብሎ ንግግር ሲያደርግ ከመድረክ መሪዎቹ ወከባ ደርሶበት ሃሳቡን ሳይቋጭ ከመድረክ እንዲወርድ ተደርጎ ነበር። በዚህ ዓመት ግን ከዚያ በተሻለ የድሉን መሪ እውቅና እንዲያገኙ ስለተደረገ የሰጠው አስተያየት ነበር።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
11394 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 980 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us