እጅ ያልሰጠው የጥበብ ኮከብ

Wednesday, 21 March 2018 12:56

 

በይርጋ አበበ

 

አርቲስት ፍቃዱ ተክለማሪያም ላለፉት 40 ዓመታትና ከዚያም በላይ በኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ላይ የነገሰ ኮከብ የጥበብ ሰው ነው። አንጋፋው ከያኒ ፍቃዱ ተክለማሪያም ከሰራቸው ቁጥር ስፍር የሌላቸው ድራማዎች፣ ፊልሞችና ቴአትሮች በተጓዳኝ ተተኪዎችን በማፍራት በኩል የሚጫወተው ሚናም ከፍተኛ መሆኑ ይነገርለታል። በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዐይንና ጆሮ ተስለው ወይም ተቀርጸው የተቀመጡ የተዋናዩን ምትሃታዊ ችሎታ የሚያሳብቁ የጥበብ ስራዎች ቤት ይቁጠራቸው። ይህ አርቲስት ግን በዚህ ወቅት በከባድ የጤና ችግር ውስጥ ወድቋል። ቀደም ሲል የስኳር በሽታ እንዳለበት ያወቀው አርቲስት ፍቃዱ፤ በቅርቡ ደግሞ ሁለቱም ኩላሊቶቹ ስራቸውን እንዳቆሙ በሐኪሞች ተነግሮታል። በዚህ የተነሳም የተሻለ ህክምና እንዲያገኝ በሙያ አጋሮቹ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ተዘጋጅቶለታል። ምንም እንኳን አርቲስቱ ‹‹ክብሬን ጠብቄ እንድሞት ፍቀዱልኝ›› ቢልም ቅሉ። የዛሬ የመዝናኛ አምድ ዝግጅታችንም በዚህ ዙሪያ የሚያጠነጥን ሲሆን የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴው እያካሄደ ያለውን እንቅስቃሴ፣ ከህዝቡ ያገኘውን ምላሽ እና የአርቲስቱን ታሪክ በወፍ በረር እንመለከታለን።

አካሉን ለመስጠት የተዘጋጀ ህዝብ


አርቲስት ፍቃዱ ተክለማሪያም (ጋሽ ፍቄ) ሁለቱ ኩላሊቶቹ ስራ ማቆማቸውን (ፌል ማድረጋቸውን) ተከትሎ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና ማከናወን ግድ ይለው ነበር። ይህን ጉዳይም ወደ አደባባይ ሳያወጣ በቤተሰብና በወዳጅ ዘመዶቹ እርዳታ ብቻ ለማከናወን ሃሳብ ይዞ የነበረ ቢሆንም ለአርቲስቱ የቀረቡለት ኩላሊት ለጋሾች ተስማሚ እንዳልሆኑ በሐኪም ተገለፀላቸው። ይህ ደግሞ የችግሩን አሳሳቢነት ከፍ አደረገው። በዚህ ዙሪያ አስተያየታቸውን ለሰንደቅ ጋዜጣ የሰጡት የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴው ሰብሳቢ ደራሲ ውድነህ ክፍሌ ‹‹ከቤተሰብ የቀረበለት የኩላሊት ልገሳ በአንድ በኩል የደም አለመገጣጠም (የደም አይነት ተመሳሳይ አለመሆን) ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የጤና ሁኔታ ነበሩ ኩላሊቱን ከቤተሰብ እንዳያገኝ ያደረገው›› ብለዋል።


አርቲስት ፍቃዱ ተክለማሪያም እርዳታ እንዳይጠየቅለት ሲከላከላቸው መቆየቱን የገለጹት ደራሲ ውድነህ፤ ‹‹ክብሬን ጠብቄ እንድሞት ፍቀዱልኝ፣ ሰውንም አታስቸግሩብኝ›› ይላቸው እንደነበር ገልጸው ሆኖም በጓደኞቹ የበረታ ጫና ሃሳቡን ሊቀበል እንደቻለ ተናግረዋል። አርቲስቱ በዚህ ሃሳብ ከተስማማ በኋላ ጉዳዩ ለመገናኛ ብዙሃን እንዲገለጽ ተደረገ። ባሳለፍነው ሃሙስ ረፋዱ ላይ (መጋቢት 6 ቀን 2010 ዓ.ም) ጋዜጣዊ መግለጫው ከተሰጠ በኋላ የፍቃዱን ጤንነት ለመመለስ በየአቅጣጫው ድጋፍ ይጎርፍ ጀመር።


በዚህ ዙሪያ አስተያየታቸውን ለዝግጅት ክፍላችን የሰጡት ደራሲ ውድነህ ክፍሌ፤ የገንዘቡን መጠን ከመግለጽ ቢቆጠቡም (በቅርቡ በጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል) የኢትዮጵያ ህዝብ ለባለውለታው አርቲስት አካሉን በነጻ ለመስጠት ምዝገባ መጀመሩን ተናግረዋል። እንደ ደራሲው መግለጫ ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት (ትናንት ማክሰኞ ረፋድ) ድረስ በአገር ቤትም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ከ80 በላይ ኢትጵያዊያን ፈቃደኝነታቸውን ገልጸዋል። ይህን ድጋፍ ለማበርከት ሲሉም ኩላሊት ለጋሾቹ የደም አይነታቸው ከአርቲስቱ የደም አይነት ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ለማረጋገጥ በራሳቸው ወጭ የደም አይነት ምርመራ ማካሄዳቸውን ተናግረዋል። ይህን የተመለከተው አርቲስት ፈቃዱ ተክለማሪያምም ለአገሩ ህዝብ የበረታ ውለታ ምስጋና ማቅረቡን ደራሲ ውድነህ ተናግረዋል።


ደራሲ ውድነህ “አርቲስቶች ሀብታችን የኢትዮጵያ ህዝብ ነው” ሲሉ ደጋግመው መናገራቸውን አስታውሰው፤ “ይህ አባባል በፍቃዱ ልብ ውስጥ እውነት መሆኑን ተመልክተናል። ፍቃዱ ከ40 ዓመታት በላይ ለአገሩ እና ለወገኑ ሲሰራ መኖሩን የተመለከተው የአገሩ ህዝብም ይህን ውለታውን ለመመለስ አካሉን አሳልፎ ለመስጠት ቁርጠኛ ሲሆን ታይቷል” ብለዋል። ይህን የህዝብ ድጋፍ የተመለከቱት አቶ ወድነህ ክፍሌ ሲናገሩም “በዚህ አጭር ጊዜ በዚህ ፍጥነት ይህን ያህል ድጋፍ እናገኛለን ብለን አልጠበቅንም ነበር። ሆኖ ስናየው ግን በጣም ተገርመናል” ብለዋል።


እውነትም የኢትዮጵያ ህዝብ ያከበረውን የሚያከብር ኩሩ ህዝብ መሆኑን በዚህ ወቅት አስመስክሯል። ይህን የህዝብ ውለታ መላሽነት በተመለከተ ደራሲ ውድነህ ሲናገሩ ‹‹ይህን ለመግለጽ በእውነት ይከብዳል። ገንዘብ አስፈላጊ ቢሆንም ይኽኛው (ኩላሊት ለመለገስ ፈቃደኛ መሆንን) ግን ቃላትም፣ ዋጋም የማይገልጹት ትልቅ ስጦታ ነው›› ብለዋል።

 

40 ዓመታትን የተሻገረ የሙያ ፍቅር


ከሬዲዮ ድራማ እና ከቴሌቪዥን ማስታወቂያ ጀምሮ በመጽሐፍት ትረካ (ወንጀለኛው ዳኛ፣ ጥቁር ደም፣ ሞገደኛው ነውጤ እና ሌሎችም)፣ በቴአትር፣ በፊልም እና በቴሌቪዥን ድራማ ለቁጥር የሚያታክቱ ስራዎችን አከናውኗል። ይህ አርቲስት ከዚህ በተጨማሪም የሙያው ተተኪዎችን ወደ እውቅና ማማው ለማምጣት እየሰራ ሲሆን ቴአትር ግምገማ እና ወጣቶችን ማስተማር ደግሞ ሌሎቹ ተሰጥኦዎቹ ናቸው። ይህን ሁሉን አቀፍና ስኬታማ የጥበብ ጉዞ በተመለከተ አስተያየታቸውን የሚሰጡት አቶ ውድነህ ክፍሌ “ለሙያው የተሰጠ እና ሁሉም የተሰጠው” በማለት ነው።


እውነት ነው ፍቃዱ ከላይ ከተጠቀሱት ሙያዎች በተጨማሪም በአጠቃላይ በዘጠኝ የኪነ ጥበብ ዘርፎች ተሳትፎ አድርጎ በሁሉም ነጥሮ የወጣ ብርቅዬ የጥበብ ፈርጥ ነው። የእስካሁኑ ጉዞ በቂ ነው ብሎ መውሰድ ያልፈለገው አርቲስት ፍቃዱ በዚህ ወቅት በስኳር ህመም እየተሰቃየ እና ሁለቱም ኩላሊቶቹ መስራት አቁመዋል ተብሎ ተነግሮትም በአንድ የቴሌቪዥን እና አንድ የሬዲዮ ድራማዎች ላይ ቀረጻ ያካሂዳል። ሙያን ማፍቀር እና ለሙያ መታመን ይሏል ይህ አይደል!!

 

የፍቃዱ ሌላው ገጽታ


በኢትዮጵያም ሆነ በሌላው ዓለም በአንድም ይሁን በሌላ በየትኛውም መንገድ የእውቅና ጥግ የደረሱ ሰዎች በበጎ አድራጎት ማህበራዊ አገልግሎቶች ሲሳተፉ ማየት የተለመደ ነው። ይህ የሚሆነው ደግሞ ታዋቂዎቹ ግለሰቦች በስራ ዘመን ካካበቱት ዳጎስ ያለ ገንዘብ ላይ ዘግነው ወይም እውቅናቸውን ተጠቅመው ለበጎ ዓላማ ተባባሪ የሆኑ ተቋማትን ወይም ግለሰቦችን ደጅ በመጥናት ገንዘብ በመሰብሰብ ነው።


በአርቲስት ፍቃዱ እምነት ግን ከላይ በተጠቀሰው መንገድ በጎነትን ማካሄድ አያምንም ወይም አይፈልግም። ዳጎስ ያለ ገንዘብ የለውም ወይም ደግሞ ሰውንም ማስቸገር አይፈልግም። ስለዚህ ያለው አማራጭ “ሁለት ልብስ ያለው አንዱን ምንም ለሌለው ይስጥ” በሚለው ከኢየሱስ ክርስቶስ የደግነት አስተምህሮ በመነሳት ነው። የቤተሰቦቹን ጓዳ እና ቁም ሳጥን እያራገፈ በደብረ ብርሃን ከተማ አንድ የበጎ አድራጎት ድርጅት መስርቷል። ይህ ድርጅት አረጋዊያንን እና አቅመ ደካሞችን ሰብስቦ የሚረዳ ድርጅት ነው። ሙያውን እና እውቀቱን ሰጥቶ በቃኝ ማለት ያልፈለገው አርቲስት ገንዘቡን (ሳይኖረውም ጭምር) በመስጠት ለአገሩ ያገለገለ አርቲስት ነው። ይህ አርቲስት በጠና ታሞ ህይወቱ አደጋ ላይ መሆኑን የህክምና ባለሙያዎች ሲነግሩት “ወገኔን ላስቸግር ውለታዬን ይመልስልኝ” ማለት አልፈለገም። ፈጣሪ ፍቃዱ ከሆነ እንዲፈውሰው ወይም ደግሞ በቃህ ካለውም በክብር እንዲወስደው መፀለይን መርጦ መቆየቱን ደራሲ ውድነህ ክፍሌ ተናግረዋል። ስለ ፍቃዱ ሲናገሩ “ለመርዳት የማይመች ሰው ነው” የሚሉት ደራሲ ውድነህ፤ “በጣም ይሉኝታ የሚያጠቃው ሲሆን ከመቀበል ይልቅ መስጠትን የህይወቱ መርህ አድርጎ የያዘ ሰው ነው። ለዚህ ነው እርዳታ ስናሰባስብ የተቃወመን” ሲሉ ተናግረዋል።


ባለ ብዙ ሙያውና ብዙ ልምዱ አርቲስት ፍቃዱ፤ ወገኖቹን ለመጠየቅ እጅ ባይሰጥም እጆች በስፋት ተዘርግተውለት ለዓመታት የሥራውን ውለታ ሊከፍሉት ተዘጋጅተዋል። በመድረክ ያጨበጨቡለት የአድናቂዎቹ እጆች አሁንም በችግሩ ሊደርሱለት ቁርጠኝነታቸውን አሳይተዋል። በቅርቡም በሐኪሞችና በአርቲስቱ ምርጫ ለህክምና ተስማሚ ወደሆነ አገር ሄዶ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምናውን አካሂዶ ወደሚወደው ሙያው ይመለሳል።

 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
10271 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1152 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us