ዝክረ ፍቅር እስከ መቃብር መጽሐፍ የፍቅር ውሃ፤ የፍቅር ግብዣ

Wednesday, 28 March 2018 12:27

 

በይርጋ አበበ

 

ቅር የታሸገ የተፈጥሮ ውሃ ከባህር ጠለል በላይ 2,700 ሜትር ላይ በሆነ ከፍታ ቦታ ላይ በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ ከሚገኘው በደን የተሸፈነ ተራራ ስር ከሚፈልቅ የምንጭ ውሃ የሚመረት ነው። ይህ የመጠጥ ውሃ ፋብሪካ ከአዲስ አበባ 207 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ተመርቶ ወደ ገበያ መቅረብ ከጀመረ ሶስት ወራት ሆኖታል። የፋብሪካው ኃላፊዎች ሰሞኑን ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት ከፍቅር ውሃ ጋር በአርቲስት ወጋየሁ ንጋቱ የተተረከው የፍቅር እስከ መቃብር መጽሐፍ ትረካ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ብሔራዊ አገልግሎት በሳምንት አንድ ቀን እሁድ ምሽት ከ3፡00 በኋላ (የፊታችን ዕሁድ መጋቢት 23 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ) ለአድማጭ እንዲቀርብ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል። የዛሬው መዝናኛ አምዳችንም በዚህ ጉዳይ ላይ የሚያተኩር ሲሆን ጥንቅሩን ለማቅረብም የፋብሪካው ኃላፊዎች የሰጡት መግለጫ እና ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡት ምላሽ፣ ፍቅር እስከ መቃብር መጽሐፍ እና በዚህ በመጽሐፍ መነሻነት ተጽፎ ከሶስት ዓመት በፊት ለንባብ የበቃው ዳሳሽ የጥናት መጽሐፍ ምናብና ገሃድን ተጠቅመናል።

 

መግቢያ የጋዜጣዊ መግለጫው ይዘት በአጭሩ


ከንግድ ዓላማ በዘለለ የምንጭ ውሃው ለዘመናት ወደ ጊቤ ወንዝ በመግባት ከዚያም አልፎ ወደ ጎረቤት አገር የሚፈስበት ሁኔታ ስለነበር ይህንን የተፈጥሮ ሀብት ለአገርና ለአካባቢው ልማት በማዋል የአክሲዮን ማኅበሩ መሥራቾች በአገሪቱ የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ አይነተኛ ተሳትፎ በማድረግ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ የማድረግ ዓላማንም የያዘ ነው።


ኢንቨስትመንቱ በአገር አቀፍ ደረጃ፣ ለክልሉ፣ ለወረዳና ለአካባቢው ኅብረተሰብ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፋይዳ ያለው ሲሆን አሁን ባለበት ደረጃ ለ216 ዜጎች የሥራ እድል ፈጥሯል። በቀጣይ የሚደረጉ ሥራዎችንም ተከትሎ ተጨማሪ የሥራ እድሎች ይኖራሉ ብለንም እናምናለን።


ከንግድ ዓላማ ባሻገር ድርጅቱ ለማኅበራዊ ክንውኖችና ለአካባቢው ኅብረተሰብ ተጠቃሚነት ተግቶ የሚሰራ ሲሆን፤ ይህንንም በተደራጀና በታቀደ ሁኔታ ለመሥራት እንዲቻል የማኅበራዊ ኮርፖሬት ኃላፊነት ፖሊሲና እቅድ ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።


ከዚህ አንጻር አንድ የታሸገ የፍቅር ውሃ ሲሸጥ 2 ሳንቲም ለተፈጥሮ እንክብካቤ እና ለታዳጊ ህፃናት ድጋፍ እንዲውል የሚያደርግ ይሆናል። ይህም ከምንም በላይ ለአክሲዮን ማኅበሩ መሥራቾችና ለባለቤቶቹ ከፍተኛ የመንፈስና የህሊና እርካታ የሚሰጥ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።


በዚህች ምድር የሚኖር ፍጡር ሁሉ በየትኛውም ቦታ በማንኛውም ጊዜ ውሃን ይፈልጋል። የሰው ልጅ ውሃንና ፍቅርን የመፈለጉ ጉዳይ በጊዜና በቦታ የሚገደብ አይደለም። ለዚህም “ፍቅር የተፈጥሮ ምንጭ ውሃ” ስሙን ሆኖ፣ ስሙን አክሎ እንዲገኝ፣ ዘመን ተሻጋሪና ሁሉም የሚወደው እንዲሆን፣ ተጠቃሚዎች የጥም ብቻ ሳይሆን የመንፈስ እርካታም እንዲኖራቸው ማድረግና ይህ ሲፈጸም ማየት ከምንም በላይ የአክሲዮን ባለቤቶቹን የሚያረካ ነው። ለዚህም ተምሳሌት ሲፈልግ ቆይቷል።


ይህንም ተምሳሌታዊነት ከስነ-ጽሁፍ ዘርፍ እንደሚገኝና ለዚህም በሀገራችን ታዋቂውና ስመ ጥሩው ደራሲ በክቡር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ በፍቅር ተፅፎ፣ በመድረኩ ንጉስ አርቲስት ወጋየሁ ንጋቱ በፍቅር ተተርኮ፤ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ራዲዮ ተደጋግሞ በፍቅር የተደመጠውን “ፍቅር እስከ መቃብር” የተሰኘውን ተወዳጅ የሬዲዮ ትረካ አግኝተናል።


በዚህም መሠረት ይህ ታላቅ የጥበብ ሥራና ድርሰት በወጣቱ ትውልድ እንዲደመጥ “ፍቅር የተፈጥሮ ምንጭ ውሃ” ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር እንደገና በተከታታይ የሬዲዮ ስርጭት እንዲቀርብ መስማማታችንን ይፋ ስናደርግ ከፍተኛ ደስታ ይሰማናል።


የመጽሐፉ ደራሲም ሆነ ተራኪው ዛሬ በህይወት ባይኖሩም ሥራቸው ሁልጊዜ ይታወሳል፣ መጽሐፉና ትረካውም እንደተወደዱ ከዘመን ወደ ዘመን፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር በማየታችን ለፍቅር የተፈጥሮ ምንጭ ውሃም አርአያና ተምሳሌት እንደሚሆን እምነታችን ነው›› ይላል የመግለጫው ይዘት በከፊል።


ይህ የውሃ ፋብሪካው ቀዳሚ መልእክት ሲሆን ድርጅቱ ከትርፍ በተጓዳኝ የማህበራዊ አገልግሎት ግዴታውን ለመወጣት ኪነ ጥበብን ምርጫው ማድረጉንና ለዚህም የምርጫው ተስማሚ ሆኖ ያገኘው ይህ መጽሐፍ እንደሆነ አስታውቋል። ወደፊትም የግጥም ምሽቶችን የመሳሰሉ ፕሮግራሞችንም በገንዘብ ለመደገፍ (በዘመኑ ቋንቋ ስፖንሰር በማድረግ) አብሮ ለመስራት እያሰበ መሆኑን ኃላፊዎቹ ተናግረዋል። ከዚህ መግለጫ በኋላ ለፋብሪካው የሥራ ኃላፊዎች ከመገናኛ ብዙሃን ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል ኢትዮጵያ ሬዲዮን ለምን ምርጫችሁ አደረጋችሁ? የሚል ይገኝበታል።

ዘመቻ ጉዱ ካሳን ፍለጋ


ፍቅር ውሃ ፍቅር እስከ መቃብርን ለአድማጮች እንዲተረክ መዋዕለ ንዋይ ይዞ ኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን ቅጥር ግቢ ሲገባ የመጽሐፉን ዘመን አይሽሬነትና የተራኪውን አይጠገቤነት በመረዳት ብቻ አይደለም። በጋዜጣዊ መግለጫው እንደተገለጸው ‹‹ይህ ትውልድ የዚህን ዘመን ተሻጋሪ መጽሐፍ (ፍቅር እስከ መቃብርን) ትረካ እንዲያዳምጥ እድል ለመፍጠር›› የሚል ሃረግ ተቀምጦበታል። በመሆኑም የዚህ መጣጥፍ አዘጋጅ በፍቅር ውሃ እና በኢትዮጵያ ሬዲዮ ትብብር ከሚቀርበው የክቡር ሀዲስ ዓለማየሁ መጽሐፍ ውስጥ ካሳ ዳምጤን በተለየ መልኩ ፍለጋ ሊደረግበት ይገባል ብሎ ያምናል። ካሳ ዳምጤ ማነው? ምን አይነትስ ሰው ነው? የሚሉትን መጠይቆች ለመመለስ ከፍቅር እስከ መቃብር መጽሐፍ ውስጥ በገጽ 121 እስከ 132 የሰፈረውን ሃሳብ መመልከት ይቻላል። ከዚህ ሰፊ ክፍል ውስጥ ሃሳቦችን ዘግነን እንመልከት።


‹‹ካሳ ዳምጤ ከእነማይ ባላባት ከፊታውራሪ ዳምጤ ብሩና ከወይዘሮ ጥሩወርቅ ታላቅ እህት ከወይዘሮ አስቴር ተሰማ የተወለደ በሁለት እጅ የማይነሳ ከባድ የጌታ ዘር ነበር። በመኳንንት ልጆች ወግ የቤተ መንግስት ስርዓት እያጠና ቢያድግ ኖሮ ቢያንስ ቢያንስ የአባቱን ግዛት ባላጣ ነበር። ነገር ግን አባቱ በህጻንነቱ ስለሞቱ እና ምቀኞች ዘመዶቹ እንኳን ይህን እድል እንዲያገኝ ሊያደፋፍሩትና ወደፊት ሊገፉት ቀድሞ እፊት ቢያገኙትም ወደኋላ ለመጎተት የማይመለሱ ስለነበሩ ከቤተ መንግስት ርቆ ከእናቱ ዘንድ አደገ›› ሲል ስለ ካሳ ዳምጤ (ጉዱ ካሳ) አስተዳደግና የዘር ሃረግ ይገልጻል።


የፍቅር እስከ መቃብር መጽሐፍ ዋና ገጸ ባህሪ የሆኑት ፊታውራሪ መሸሻ ባለቤት የወይዘሮ ጥሩወርቅ ተሰማ የእህት ልጅ የሆነው ጉዱ ካሳ ትውልድ እና እድገቱ ይህን ሲመስል ትምህርቱን በተመለከተ ደግሞ ‹‹ባገሩ ትምህርት እውቀቱ የጠለቀ ከመሆኑም በላይ የባላባት ልጅ በመሆኑ የቤተ ክህነት ሹመት ፈላጊ ቢሆን ኖሮ ከታላላቁ አድባራት የአንዱን አለቅነት ቢያንስ ሊቀጠበብትነት ሊያገኝ እንደሚችል የማይጠረጠር ነበር። ነገር ግን አስተያየቱ ከቤተክርስቲያ መሪዎችና ካህናት በጣም የተለየ ስለነበረና ስራቸውን አጥብቆ ይጠላ ስለነበረ ቤተክርስቲያንን በእነሱ ዐይን እያየ ከቤተክርስቲያም ይርቅ ጀመር። በኋላ እንዲያውም የሚኖርበት ምህበር የተመሰረተበት ስርዓት፣ ልማዱ፣ ደንቡ፣ ወጉ እና ህጉ የማይረባ ከመሆኑም በላይ የሚጎዳ መሆኑን ይሰብክና ይህ አሮጌ ስርዓት ሳይሻሻል እንደ እግዚአብሔር ቃል ተከብሮ እንዲኖር የሚጣጣሩትን የልማድ ባሮች ‹ከብቶች፤ ድንጋዮች እያለ ልዩ ልዩ ስም እየሰጠ ይዘልፍ ነበር›› ይላል።


እዚህ ላይ የምንረዳው ጉዱ ካሳ በወቅቱ ከነበረው ማህበረሰብ አንድ እርምጃ የፈጠነ ሲሆን ስህተትን አይቶ እንዳላየ ወይም ደግሞ አዲስ ትምህርትን እና ለውጥን ለመቀበል በሩን ዘግቶ የተቀመጠ ሳይሆን ለውጥ ፈላጊ አብዮተኛ እንደነበረ ነው። ይህ ተናጋሪ የወቅቱ ምሁር (በዚህ ዘመን የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞች ይሉታል ዶክተር ዘካሪያስ አምደብርሃን በምናብና ገሃድ መጽሐፋቸው) አስተዳደጉ ከእኩዮቹ ጋር ተመሳሳይ ቢሆንም የተማረው ትምህርት ግን አዱኛን እና ስልጣንን እንዲመኝ ሳይሆን መጥፎውን በመንቀፍ ለውጥ እንዲመጣና ማስተካከያ እንዲደረግ ይታገል የነበረ መሆኑን በፍቅር እስከ መቃብር እንመለከታለን።


የፍቅር ውሃ ግብዣ የሆነው ይህ ትረካም ይህን ታሪክ ለአድማጮች እንዲያደርስ ማድረጉ ይበል ያሰኛል ይላሉ ለዚህ ጽሁፍ አቅራቢ አስተያየታቸውን የሰጡ ሰዎች። እንደ አስተያየት ሰጪዎች አረዳድ በልብወለዱ ፊታውራሪ መሸሻ ማለት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሲሆኑ እሳቸውን ይመክሩ የነበሩት ሀዲስ ዓለማየሁን ጨምሮ ሌሎች ለአገር አሳቢ ምሁራን ደግሞ በጉዱ ካሳ ተመስለዋል። ነገር ግን እንደ ቄስ ሞገሴ ያሉ አድር ባይ የሀይማኖት መሪዎችና ፍርፋሪ አዱኛ ፍለጋ ከፊታውራሪ መሸሻ እግር ስር (ከንጉሱ ደጅ) የማይጠፉ ምሁራን ተብዬዎች ፊታውራሪም ሆኑ ንጉሰ ነግስቱ ሳይማሩና ሳይስተካከሉ አወዳደቃቸው ሲከፋ ተመልክተናል። (ፊታውራሪ መሸሻ በገበሬዎች አመጽ አስተባባሪው አበጀ በለው፤ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ደግሞ በቮልስ ዋገን ተጭነው ከቤተመንግስት በውርደት በደርግ እንዲወድቁ መዳረጉን ልብ ይሏል)


ይህ ተሞክሮ ደግሞ በዚህ ዘመንም መኖሩን የሚጠቅሱት የስነ ጽሁፍ ምሁራን፤ ኢህአዴግም የዘመኑን ጉዱ ካሳዎች (የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞችና የአደባባይ ምሁራንን) ከማሳደድ ይልቅ ቢያዳምጣቸው ለአገርም ለስርዓቱም እንደሚበጀው ይመክራሉ። ለዚህ ደግሞ ፍቅር እስከ መቃብር በአርቲስት ወጋየሁ ንጋቱ ድምጽ በኢትዮጵያ ሬዲዮ እንዲተረክ መቅረቡ ጉዱ ካሳን ለማዳመጥና ምክሩን ለመውሰድ ትክክለኛ ጊዜ እና ወቅት መሆኑን ይናገራሉ።

ለምን ኢትዮጵያ ሬዲዮ?


ፍቅር ውሃ በኢትዮጵያ ሬዲዮ አማካይነት ትረካው እንዲቀርብ መጠኑ ያልተገለጸ ግን ደግሞ ዳጎስ ያለ እንደሆነ የሚጠበቅ ገንዘብ መክፈሉን በተመለከተ በዚህ ዘመን በተለይም በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ ላሉ የሬዲዮ አድማጮች ኢትዮጵያ ሬዲዮ ተቀዳሚ ምርጫ አለመሆኑን ጋዜጠኞች አንስተው ለምን ጣቢያውን ሊመርጡ እንደቻሉ ተጠይቀው ነበር። ለዚህ ጥያቄ መልስ ሲሰጡም ኢትዮጵያ ሬዲዮ በመላው አገሪቱ የሚሰማ በመሆኑ እና በአዲስ አበባ እና አካባቢዋ ላሉ አድማጮች ደግሞ በኤፍ ኤም 93 ነጥብ 1 አማካይነት እንዲያዳምጡ የቀረበበት አማራጭ እንደሆነ (ሊንክ የተደረገ መሆኑን) ተናግረዋል።


በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየቱን የሰጠው የኢትዮጵያ ሬዲዮ ጋዜጠኛ ብርሃኑ ገብረማሪያም በበኩሉ ‹‹ስለ ሬዲዮ ጣቢያው እና በየትኞቹ ፍሪኩየንሲዮች ሊገኝ እንደሚችል ማስታወቂያ አለመስራታችን ችግሩ የእኛ ነው›› ሲል ተናግሯል። ከዚህ በኋላም አድማጮች እንዲመርጡት ጣቢያው ላይ ማስታወቂያ እና የፕሮግራም ማሻሻያዎች ጭምር እንደሚካሄድበት በመናገር የፍቅር ውሃ ምርጫ የተሳሳተ እንዳልሆነ ተናግሯል።


ፍቅር ውሃ ፍቅር እስከ መቃብርን በፍቅር ስም ማቅረቡን የሚጀምረው ዕሁድ ምሽት ከ3፡00 በኋላ ሲሆን በድጋሚ ሰኞ ጠዋት ከ1፡00 ዜና በኋላ ይቀርባል። ለአድማጮችማ ሆነ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መልካም ጊዜ!! የአዘጋጁ መልእክት ነው።


ፍቅር እስከ መቃብርን በፍቅር ውሃ!! ወደ ፍቅር ይምራን።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
9166 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 973 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us