እንኳን “ለቢራ ፋብሪካዎች አውደ ዓመት” አደረሳችሁ!!!

Wednesday, 11 April 2018 14:40

 

በይርጋ አበበ

 

ጤና ይስጥልን ውድ የጋዜጣችን አንባቢያን። ሰሞኑን መቼም አገራችን ድርብርብ በዓላትና ዝግጅቶች በዝተውባታል አይደል? በዚህ በኩል የቀድሞውን ጠቅላይ በአዲሱ ጠቅላይ በመተካት ፖለቲካውን አዲስ አየር እንዲነፍስበት ሲደረግ፤ ወዲህ ደግሞ በዓለ ፋሲካን ምክንያት በማድረግ የከተማዋ አየር (በተለይ አዲስ አበባ) በዶሮ እና በከሰል ጭስ ታውዶ ሰንብቷል። እናም የዚህ አምድ አዘጋጅ ለበዓለ ፋሲካውም ሆነ ለበዓለ ፖለቲካው መተካካት እንኳን አደረሳችሁ እያለ ከዚህ በታች የቀረበውን የአውደ ዓመት ልዩ የመዝናኛ ዝግጅት በሚከተለው መልኩ አቅርበነዋል።

በዓላትና የኢትዮጵያ ቴሌቪዥኖች


አውደ ዓመት ሲመጣ መቼም የመገናኛ ብዙሃን በተለይም የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በመዝናኛ ፕሮግራሞቻቸው ተለይተው ይታወቃሉ። ለዘመናት በቆየው የበዓላት ልዩ የመዝናኛ ፕሮግራሞችም የአገራችን ህዝብ ከሊቅ እስከ ደቂቅ በሚያስብል መልኩ የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙሃንን ይከታተላል። ወደዘንድሮው የፋሲካ በዓል የትዝብትና የምልከታ ቅኝት ከማምራቴ በፊት አንድ የቆየ የአውደ ዓመት ታሪክ ላወሳ ወደድሁ።


በኢትዮጵያ አቆጣጠር ጳጉሜ 5 ቀን 1952 ዓ.ም እኩለ ሌሊት ሲሆን የአዲስ ዓመት ልዩ የመዝናኛ እና የሙዚቃ ፕሮግራም በብሔራዊ ቴአትር (ቀድሞ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ቴአትር ቤት) እየተከናወነ ባለበት ሰዓት የአገሪቱ ብሔራዊ ሬዲዮ ጣቢያም የበዓሉን ልዩ ፕሮግራም ለአገሬው ህዝብ እያስተላለፈ ነበር። በዚህ ሰዓት ደግሞ መቶ ዓለቃ አበበ ቢቂላ (በኋላ ሻማበል) በሮም ኦሎምፒክ በልዩ ብቃት 42 ኪሎ ሜትሩን በባዶ እግሩ ሮጦ ሁሉንም ተወዳዳዎች ከኋላው አስከትሎ ገባ። ይህን ዜና እንዳሁኑ የውጭም ሆነ አገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በቀጥታ ያላስተላለፉት በመሆኑ ጄኔራል መንግስቱ ንዋይ ከጣሊያን በቀጥታ በመኖሪያ ቤታቸው ስልክ ተደውሎ ድሉ ነገራቸዋል። ይህን ድል ሲሰሙም በቀጥታ ወደ ብሔራዊ ቴአትር ደውለው የመድረኩን መሪ አስጠርተው ለታዳሚው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት እንዲያስተላልፍ ይነግሩታል።


መድረክ መሪውም የታዘዘውን ፈጽሞ ለታዳሚው እንዲህ ሲል ተናገረ ‹‹የክቡር ዘበኛ አትሌት የሆነው ጀግናው አትሌት የመቶአለቃ አበበ ቢቂላ ዛሬ በሮም ኦሎምፒክ የማራቶን አሸናፊ ሆኗልና እንኳን ደስ አላችሁ›› አለ። በወቅቱ የመድረኩ የሙዚቃ ፈርጦች የነበሩት እነ ጥላሁን ገሰሰ፣ ብዙነሽ በቀለ፣ አሰፋ ማሞ እና የመሳሰሉት ድምጻዊያን በሙሉ ከክብር ዘበኛ የተገኙ ስለነበረ በዓሉ ልዩ ድምቀት እንዲኖረው ደስታቸውን በከፍተኛ መጠን ገለጹ። ይህ ታሪክ ዓመታትን አልፎ መንግስታትን ቀያይሮ ያለፈ ትዝታ ሲሆን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተከበሩ ስላሉት የአውደ ዓመት ልዩ የበዓል ፕሮግራሞች በተመለከተ ደግሞ ከዚህ በታች ያለውን ሃሳብ እንመለከታለን።


በአንዱ ቴሌቪዥን ጣቢያ ታዋቂ እና አንጋፋ አርቲስቶች በዕድሜ ከሚያንሳቸው አንድ የሙያ አጋራቸው ጋር ከሀይቅ ዳር ተቀምጠው ስለ ሙያ፣ ህይወት እና ስለ አገር ጉዳይ እየተወያዩ ተመለከትን። ፕሮግራሙ ማለፊያ ነበር። በተለይ ስለ ይቅርታ ያደረጉት ውይይት አስተማሪ ነበር። በዚህ ፕሮግራም ላይ ታዲያ እጅግ አነጋጋሪ የነበረው በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ማስታወቂያ እንዲሰራላቸው ከሚከለክላቸው ምርቶች አንዱ በሆነው በመድሃኒት ፋብሪካ ስፖንሰር መደረጉ ነው። ይህን በተመለከተ የዘርፉ ባለሙያዎችና ምሁራን እንዲሁም መንግስት ምን እንደሚሉ ማወቅ ባልችልም ጥሩ ሆኖ የተዘጋጀውን ፕሮግራም ልክ እንደ ሳሙና፣ ቢራ እና ሌሎች ሸቀጦች መድሃኒት በቴሌቪዥን ሲተዋወቅ ማየት አነጋጋሪ ሆኖብኛል።


በሌላኛው ቴሌቪዥን ጣቢያ ደግሞ ወጣት አርቲስቶች ተሰብስበው በመሮጥና በመጮህ በሚጫወቱት ጨዋታ አሸናፊው በተሸናፊው ገላ ላይ በብርጭቆ የሞላ ውሃ ሲያፈስበት ተመለከትን። የፕሮግራሙ ስፖንሰር የሆነው የአንድ ቢራ ፋብሪካ ምስል ያረፈበት የፕላስቲክ ወረቀት (ባነር) ከአርቲስቶቹ ጎን ተቀምጧል። በእውነቱ የልጆቹን ድርጊት ለተመለከተ ለመሸናነፍ እየተወዳደሩ ሳይሆን ፕሮግራሙን ስፖንሰር ካደረገው ቢራ ፋብሪካ የቀረበላቸውን የነጻ መጠጥ አብዝተው በመጠጣት በደመነፍስ የሚያደርጉ ነበር የሚመስለው።


ይህን ጣቢያ ቀይረን ወደሌላው ስንሸጋገር ደግሞ ቁመተ መለሎ ሴቶች እና በተለያየ ሙያ የተሰማሩ ወንዶች እኩል ቁጥር ኖሯቸው ይደረደሩና ወንዶቹ የመረጧትን ሴት ተሸክመው ሲሮጡ ወይም ውሃ ውስጥ ይዘው ሲያሻግሩ ይታያሉ። ሴቶቹን ሜዳ ላይም ሆነ መዋኛ ገንዳ ውስጥ ተሸክሞ በመሮጥ የሚገኝ መዝናኛ ምን እንደሆነ ግራ ያጋባል። ይህም ፕሮግራም ስፖንሰር የተደረገው እንዲሁ በቢራ ፋብሪካ ነው።


ሌላው ደግሞ ከክልል ቴሌቪዥን ጣቢያዎች አንዱ በሆነው የተላለፈ ፕሮግራም አለ። በአንድ የቢራ ፋብሪካ ስፖንሰር አድራጊነት የተላለፈው ይህ ፕሮግራም ደግሞ ከመጀመሪያው እስከመጨረሻው ከአንድ አርቲስት ቤት ሰዎች ተሰብስበው ምግብ ሲበሉ እና የፕሮግራሙ ስፖንሰር አድራጊን ቢራ ፋብሪካ ምርት ሲጠጡ ይታያሉ። ምግብ መብላት እና ቢራ መጠጣት እንደ አንድ የበዓል ልዩ ዝግጅት ተቆጥሮ በግብር ከፋዩ ህዝብ ቤት መምጣት ደግሞ ሌላው አስተዛዛቢ ፕሮግራም ሆኖ ተገኝቷል።


በየሰፈሩ እየዞሩ የቢራ ጠርሙስ እና አንድ በግ ይዞ ችግረኛ ኢትዮጵያዊያንን የሚጠይቀውና ሌሎችም እንዲሁ የበዓል ፕሮግራም ናቸው ተብለን በየቤታችን የቀረቡ ዝግጅቶች ናቸው።


በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ እና በአማርኛ ቋንቋ ከሚያስተላልፉ ዘጠኝ የመንግስትና የግል ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሙሉ በሙሉ በሚያስብል መልኩ የበዓል ልዩ ዝግጅታቸውን በቢራ ማስታወቂያ ታግዘው ፕሮግራም አስተላልፈዋል። ይህን በተመለከተ የተመለከቱትን ትዝብት እና አስተያየታቸውን እንዲሰጡን ካነጋገርኳቸው ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ‹‹በዓሉ የቢራ ፋብሪካዎች ልደት ይመስላል›› ሲሉ ተናግረዋል። በተለይ በአዲስ አበባ 22 ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ነዋሪ የሆነው ሰለሞን ሀብታሙ የተባለ ወጣት ‹‹በቅድሚያ እንኳን ለቢራ ፋሪካዎች ትንሳዔ በሰላም አደረሳችሁ›› ሲል የአውደ ዓመት ልዩ ዝግጅቶች በቢራ ማስታወቂያ ታጅበው መቅረባው የፈጠረበትን ስሜት አጋርቶኛል።


ወጣት ሰለሞን አክሎም ‹‹ህጻናት ከወላጆቻቸው ጋር ቤት ውስጥ ከሚያሳልፉባቸው ቀናት አንዱ አውደ ዓመት ቢሆንም ልጆች ቀኑን ሙሉ በቢራ ማስታወቂያ ደንዝዘው እንዲውሉ መደረጉ አገሪቱ ወዴት እየሄደች ነው?›› ሲል የተሰማውን ስጋት ገልጿል።

 

መልካሙን ፍለጋ


ቀደም ባለው ንዑስ ርዕስ ስር በዓላት በቢራ ማስታወቂያ ብቻ ታጅበው መቅረባቸው እና የዝግጅቶቹን ከደረጃ በታች ሆኖ መገኘት ያለውን አሉታዊ ጎን ተመልክተናል። አሁን ደግሞ በቢራ ማስታወቂያ ስፖንሰር ተደርጎ በአንድ ቴሌቪዥን ጣቢያ የቀረበን ልዩ የበዓል ዝግጅት በአዎንታዊነት መመልከቴን ለመግለጽ ነው ‹‹መልካሙን ፍለጋ›› በሚል ንዑስ ርዕስ የመጣሁት።


ስምንት ስመ ጥር እና ወጣት አርቲስቶች በጾታ ስብጥር ቡድን ሰርተው ለቡድናቸውም ስያሜ ሰጥተው የሚወዳደሩበት አንድ ውድድር አለ። ይህ ውድድር ለአሸናፊው ቡድን 300 ሺህ ብር የሚያሸልም መሆኑን የውድድሩ አስተዋዋቂ ቀድሞ በመግለጹ ውድድሩ ፈታኝ ሆነ። ከአዲስ አበባ ተነስተው አክሱም፣ ጎንደር፣ ጂማ እና ሀዋሳ በመሄድ እንዲያመጡ የታዘዙትን እቃ ፍለጋ ይማስናሉ። ከብዙ መማሰን እና መንከራተት በኋላ ስምንቱም አርቲስቶች (አራቱም ቡድኖች) ይገናኙና የሚፈልጉትን እቃ ያቀርባሉ። ሁሉም ያገኙት አንድ አንድ ፊደል ሲሆን ‹‹ኢ›› ‹‹ት›› ‹‹ጵ›› እና ‹‹ያ›› የሚሉ ፊደላትን ሲሆን የመጨረሻ ፍለጋቸው ‹‹ዮ››ን ፍለጋ ሆነ። ‹‹ዮ››ን በጋራ ፈልገው ሲያገኙ የተሟላ ምስል ‹‹ኢትዮጵያ›› የሚል ሆነ። (ምስሉ ከላይ ተቀምጧል)
ውድድሩ በዚህ መልኩ ከተጠናቀቀ በኋላ የውድድሩ አስተዋዋቂ አርቲስት እንዲህ አለ ‹‹በዚህ ውድድር ማንም ተሸናፊ የለም፤ ሁሉም አሸናፊ ነው። አንድነት፣ ሰላም፣ ፍቅር እና መተባበር ካለ ማሸነፍ እንችላለን። ኢትዮጵያዊነት ያሸንፋል›› በማለት ለሽልማት የቀረበው መጠኑ ዳጎስ ያለ ገንዘብም ለአራቱም ቡድኖች የሚከፋፈል መሆኑን አበሰረ።


ይህን ፕሮግራም የተመለከተ አንድ እድሜው ከ15 ዓመት የማይበልጥ ታዳጊ ለዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ‹‹ከተመለከትኳቸው ፕሮግራሞች ሁሉ የተሻለ ዝግጅት ይህ ነው›› ሲል ተናገረ። ቀደም ሲል ‹‹እንኳን ለቢራ ፋብሪካዎች አውደ ዓመት አደረሳችሁ›› ሲል ተናግሮ የነበረው ወጣት ሰለሞን ሀብታሙ በበኩሉ ‹‹መልካምነትን እና ኢትዮጵያዊነትን ያስተማረ ልዩ ዝግጅት›› በማለት ይህኛውን ፕሮግራም አወድሶታል። (ይህ የበዓል ልዩ ዝግጅት የቀረበበት ቴሌቪዥን ጣያ ከወራት በፊት በተከበረው የገና በዓል ለአንድ አካባቢ ነዋሪዎች ጥልቅ ጉድጓድ ቆፍሮ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ማቅረቡን ተመልክተናል)

 

ለምን ቢራ ብቻ?


በዓላት ሲቀርቡ መልካምነትን ማበርከትና በጎነትን ማድረግ የንግድ ተቋማት ማህበራዊ ኃላፊነት ነው። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባለ ስር የሰደደ የኢኮኖሚ ድህነትና የፖለቲካ መልከ ጥፉነት የተነሳ የዜጎች ኑሮ ከዕለት ወደዕለት እየከፋ መሄዱ ይታወቃል። መንግስት በቅርቡ ይፋ ባደረገው መረጃ ብቻ እስከ 10 ሚሊዮን የሚገመቱ የዚህች አገር ዜጎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ፈላጊ ናቸው። ይህን ያህል ህዝብ ለዕለት ምግቡ የሰው እጅ አይቶ በሚያድርባት አገር ውስጥ በበዓላት ቀን እንደ ድሮው በግና ዶሮ አርዶ፣ ጠጅ ጥሎ እና ጠላ ጠምቆ፣ ቢራ እና ለስላሳ ደርድሮ በፌሽታ ማሳለፍ ቅንጦት ይመስላል።


ስለዚህ በኢትዮጵያዊነት መልካምነትና በድርጅቶች ማህበራዊ ኃላፊነትን የመወጣት የሞራል ግዴታ መሰረት አንዳንድ ድርጅቶች በጎነትን በተለያየ ደረጃ እና መጠን ሲያበረክቱ ተመልክተናል። ነገር ግን አብላጫውን ቁጥር የሚይዘው በቢራ ፋብሪካዎች የሚደረገው በጎነት ሲሆን አልፎ አልፎ ባንኮች እና የሪል እስቴት አልሚዎች ሲሳተፉ ይታያል።


የበዓል ፕሮግራሞችን ስፖንሰር ማድረግ የንግድ ስምምነት ቢሆንም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ዝግጅቶችን ስፖንሰር ማድረግ የገቢያ ትስስር ሳይሆን በጎነትን የመወጣት ተግባር እስኪመስል ድረስ ስፖንሰር አድራጊ ድርጅቶች በማስታወቂያቸው ላይ የመመጻደቅ ድምጸት ያለው መልዕክት ሲያስተላልፉ ይሰማል።


በዓላት ሲመጡ በኢትዮጵያዊነት መልካምነትና አብሮ የመብላት ስሜት ማሳለፍ ተገቢ ነው። ይህ መልእክት በሀይማኖት መረዎችም ሆነ በፖለቲካ መሪዎች ሲነገር ይሰማል። የበዓል ዝግጅቶችን ማቅረብም የደከመ አካልና አዕምሮን የመንፈስ ምግብ በመስጠት ዘና ለማድረግ ይበጃል። ነገር ግን ሁሉም ፕሮግራሞች ለምን በቢራ ፋበብሪካ ብቻ ተደግፈው (ስፖንሰር ተደርገው) ቀርባሉ? ሌሎቹ ድርጅቶች በዚህ ላይ ያላቸው ተሳትፎ ለምን ቀነሰ? ለሚሉት ጥያቄዎች የሚሰጠው ምላሽ የተለያየ ሊሆን እንደሚችል ቢገመትም ለዚህ ጽሁፍ ግብዓት ሲባል አስተያየታቸውን የሰጡ ሰዎች የሚስማሙበት ሃሳብ ግን ‹‹የቢራ ፋብሪካዎች ከፍተኛ ጥቅም የሚያገኙት በበዓላት በመሆኑ እና ከፍተኛ አምራችና አትራፊም ስለሆኑ፣ በውጭ ምንዛሬ እጥረት የተነሳ አብዛኞቹ አምራች እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላላፉት ሶስት ዓመታት የገቢ መጠናቸው ስለቀነሰ እና በአንዳንድ ታላላቅ ድርጅቶች ደግሞ የማስታወቂያን ጠቀሜታ በግልጽ ስላልተረዱት›› የሚሉት ናቸው።


በዚህም ተባለ በዚያ የ2010 ዓ.ም የፋሲካ (ትንሳዔ) በዓል ከሞላ ጎደል በጥሩ እና አስደሳች በሆነ መልኩ አልፏል። ለቀጣዩ ዓመት ደግሞ በተሻለ ከፍታ እና መልካምነት ያገናኘን በማለት ጽሁፌን እዚህ ላይ እገታለሁ።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
6981 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 155 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us