አጼ ቴዎድሮስ ዳግማዊ እና የዘመኑ ኪነ ጥበብ

Wednesday, 18 April 2018 13:01

 

በይርጋ አበበ

 

ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ የተሰውበት 150ኛ ዓመት መታሰቢያ በአማራ ክልል በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል፡፡ በስማቸው ተቋማትን እስከመሰየምና ሃውልቶችንም እስከመገንባት የደረሰ መታሰቢያ እየተዘጋጀላቸው ሲሆን ታሪካቸውን የመዘከር ተግባርም በመገናኛ ብዙሃን እና በኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ተዘጋጅቶላቸዋል ተዘግቦላቸዋልም፡፡ እኛም በዚህ እትም የንጉሰ ነገሥቱን ህይወትና ጉዞ በመዝናኛ አምዳችን እንመለከተዋለን፡፡

ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ የጳውሎስ ኞኞ (አጤ ቴዎድሮስ)፣ የአቤ ጉበኛ (አንድ ለእናቱ) እና የተክላፃድቅ መኩሪያ (አጼ ቴዎድሮስ እና የኢትዮጵያ አንድነት) የተሰኙ መጽሃፍትን፤ የጌትነት እንየው (የቴዎድሮስ ራዕይ) የተሰኘውን ቴአትር እንዲሁም ከዘፋኞች ቴዎድሮስ ካሳሁን (ጎንደር)፣ ፋሲል ደመወዝ (አለ ነገር) እና ማዲንጎ አፈወርቅ (ታንጉት) የተሰኙ ዘፈኖችን ሲሆን የባለሙያ አስተያየት የሰጠን ደግሞ ከ120 በላይ የቴሌቪዥን ድራማዎችን በመስራት አንቱታን ያተረፈው አርቲስት በምናቡ ከበደ ነው።

ቴዎድሮስ ሰውየው

ከአጼ ቴዎድሮስ በፊት ጀምሮ እስካሁኑ ዶክተር አብይ ድረስ በዚህች አገር ላይ እየተፈራረቁ የነገሱ ባለጊዜዎች ሁሉም በሚያስብል መልኩ ከሚለያዩበት ይልቅ የሚመሳሰሉበት ባህሪ ይበልጣል። በህዝባቸው ላይ የአገዛዛ ቀንበርን በመጫን የህዝቡን ድህነት አንድ ደረጃ ከፍ በማድረግ ከድህነት አረንቋ የመውጣት ተስፋውን ያጨልሙበታል። ትልቅ እና ሰፊ አገር ሆኖ ህዝቡ ግን በድህነት እንዲኖር ከተደረገባቸው ጎታች ገመዶች አንዱ እና ዋናው የመሪዎቹ ጡንቻ ከህዝቡ ድምጽ በላይ ሆኖ መገኘቱ ነው። በዚህ የተነሳም ኢትዮጵያ በኋላቀርነት ኢትዮጵያዊያን ደግሞ በድህነት መስመር የማለፍ ግዴታ ውስጥ ገብተዋል። አጼ ቴዎድሮስም ቢሆኑ በ13 ዓመታት የአገዛዝ ዘመናቸው ከእሳቸው በፊት እንደነበሩትም ሆኑ ከእሳቸው በኋላ በዚህች አገር ህዝብ ላይ እንደሰለጠኑት ባለጊዜዎች ሁሉ እሳቸውም አምባገነንነታቸው የማይካድ እውነታ ነው።

የመሪዎች ባህሪ አምባገነንነት እንዳለ ሆኖ ያው አምባገነን ገዥ ራዕይ አልባ ከሆነ ደግሞ የችግሩ ስፋት ወሰን አልባ ይሆናል። የቅርብ ዘመናት ገጠመኞቻችን የሚያመለክቱትም ይህንን ነው ራዕይ አልባ ገዥዎች አራት ኪሎ ተቀምጠው ህዝቡ በድህነት እና በችጋር ብሎም በጎጥ ተከፋፍሎ እስከመዋጋት የደረሰበትን ዘመን ልብ ይሏል።

ወደ አጼ ቴዎድሮስ የአገዛዝ ዘመን ስንመጣ ግን አምባገነንነታቸው ሳይካድ ራዕይ እንደነበራቸው ጋዜጠኛ አለማየሁ ገላጋይ ‹‹አጼ ቴዎድሮስ እና አጼ ሙትስሂቶ›› ሲል ጃፓንን እና ኢትዮጵያን በተመሳሳይ ወቅት ስለገዙ ሁለት መሪዎች ያነጻጽራል። በንጽጽሩ ድምዳሜ ላይም የሙትስሂቶ ራዕይ ከቴዎድሮስ ራዕይ በምንም የማይበልጥ ቢሆንም ኢትዮጵያዊያን ግን የቴዎድሮስን ራዕይ መረዳት ባለመቻላችን አሁንም በድህነት ላይ እንገኛለን ይላል። አቤ ጉበኛ አንድ ለእናቱ በሚለው መጽሃፉ ደግሞ ቴዎድሮስ መሪ ብቻ ሳይሆን ራዕይ ያነገበ ታላቅ ንጉስ ነበር ይላል። አርቲስት በምናቡ ከበደ በበኩሉ ‹‹አጼ ቴዎድሮስ የሞቱት ለራዕያቸው ሲሉ ነው›› በማለት ለሰንደቅ ጋዜጣ ይናገራል።

አርቲስት በምናቡ ሃሳቡን ያብራራል ‹‹እኔ እንደሚገባኝ አጼ ቴዎድሮስ የኖሩበትም ሆነ የሞቱበት ምክንያት ለኢትዮጵያ ህዝብ ቴክኖሎጂና የኢንዱስትሪ እድገት ናፋቂ የነበሩ፤ የማህበረሰብ የእጅ ጥበብ ስራ የሚወዱና የሚያፈቅሩ ሰው ናቸው። ይህ ራዕያቸው ደግሞ ያኔ ከጃፓን ጋር እኩል የኢንዱስትሪ አብዮት የተመኙና የጀመሩ ሰው ናቸው። ነገር ግን በዙሪያቸው ያለው የማህበረሰብ የስልጣኔ እድገት አነስተኛ መሆንና በተለይም ለማህበረሰቡ የእጅ ጥበብ ሙያ የነበረው ግንዛቤ ኋላቀር ከመሆኑ ጋር ተደምሮ ለእሳቸው ሞት ምክንያት ሆኗል›› ብሏል። ‹‹ከጀልባ ጀምሮ እስከ ጦር መሳሪያ የደረሰ የቴክኖሎጂ እድገት ናፋቂ እና ታላቅ መሪ ነበሩ›› የሚለው በምናቡ ከበደ፤ ‹‹የማህበረሰብ እደ ጥበብ ስራን በእሳቸው ዘመን ተባብረው ወደፊት ያመጡ እና እንዲያውም ለአድዋ ድል ግብአት የሆኑ እንደ ጋሻ ጎራዴ እና የመሳሰሉት ባህላዊ የጦር መሳሪያዎች የተመረቱት እሳቸው ፈር በቀደዱት መንገድ ሙያቸውን ያሳደጉ ጥበበኞች በሰሯቸው ስራዎች ነው›› በማለት ሃሳቡን በዝርዝር አስቀምጧል።

የቴዎድሮስ ራዕይ ምንድን ነው?

እንኳን የአንድ አገር ለዚያውም እንደ ኢትዮጵያ ላለች ታላቅ አገር መሪ የሆነ ሰው ይቅርና እንደ ስንዝሮ ሰኞ ተወልዶ አርብ ሞተ ለሚባል ማንኛውም የሰው ፍጡር ራዕይ ሊኖረው ይገባል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም ‹‹ራዕይ የሌለው ህዝብ ይገለበጣል›› ሲል ጠቢቡ ሰለሞን በመጽሐፈ ምሳሌ ላይ ገልጾታል። አጼ ቴዎድሮስም እንደ መሪ የነበራቸው ራእይ ምንድን ነው ስንል አርቲስት በምናቡ ከበደን ስንጠይቀው የሰጠን ምላሽ ‹‹አጼ ቴዎድሮስ ለራሳቸው ክብር የሚጨነቁ ሰው አልነበሩም፤ ለራሳቸው ኑሮም የሚጨነቁ አልነበሩም። ሌላው ቀርቶ ከእሳቸው በፊትም ሆነ በኋላ የነበሩ መሪዎች የራሳቸውን አሻራ ለማሳረፍ የሚሰሯቸው ህንጻዎች ነበሩ። እሳቸው ግን በድንኳን ኖረው የኢትዮጵያን ህዝብ አንድ ለማድረግ አንዴ በዚህ ሌላ ጊዜ ደግሞ ወደ ሌላው የአገሪቱ ክፍል በመዘዋወር ሲባክኑ የነበሩ መሪ ናቸው እንጂ ጊዜ አግኝተው ህንጻ በመስራት አሻራቸውን ለማሳረፍ የሚፈልጉ ሰው አልነበሩም። ለዘመናት በመሳፍንት ስርዓት ፈርሶ የነበረውን የአገሪቱን ስርዓት በ13 ዓመታት ወደ አንድነት ለመመለስ የሚወስደው ጉልበት ቀላል አይደለም። ስለዚህ የእሳቸው ራዕይ አንደኛ ኢትዮጵያን አንድ ማድረግ ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ለስልጣኔ ለእውቀት የተዘጋጀ ማህበረሰብ መፍጠር ነበር። ሃሳብ ብቻ ሳይሆን ወደ ተግባር የተለወጠ፤ የሚገዛ ብቻ ሳይሆን የሚያመርት ህዝብ መፍጠር ነበር። ታስታወስ እንደሆነ በዚያ 13 ዓመት ውስጥ ለሚቀልጥ ብረት የሚሆን አፈር አጥንተው ከደንቢያ ጋፋትን ጭምር የመረጡና ያስጠኑ እዚያ ድረስ የሄዱ ታላቅ መሪ ነበሩ›› በማለት የእሳቸውን ራዕይ እና ራዕያቸውን እውን ለማድረግ የሄዱበትን ርቀት ይናገራል።

ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) በበኩሉ ጎንደር በሚለው ዘፈኑ ላይ

‹‹ሳይገላገለው ህልሙን በሆዱ ይዞ፤

ሳይገገገለው ሽሉን በሆዱ ይዞ፤

የሚረዳው አጥቶ ተክዞ ተክዞ፤

ተክዞ ተክዞ ስንቱን በሆዱ ይዞ፤

የወገቡን እሳት አፎቱ ላይ መዞ፤

ጠጥቶላት ሞተ ክንዱን ተንተርሶ።

ካሳ ካሳ

የቋራው አንበሳ›› ሲል የተቀኘላቸው ሲሆን በዚሁ ዜማ ላይ አክሎም፤ ‹‹ዳኘን ዳኘን አንድ ህልም አሳየን›› ሲል አጼ ቴዎድሮስ አንድነትን ሰባኪ መሪ እንደነበሩ ይገልጻቸዋል። ‹‹አምጡት ቆርጣችሁ ከሹርባው ላይ፤ ኪዳን እንሰር እንዳንለያይ›› ሲል የሚቀኘውም በተለይ በዚህ ወቅት የአንድነት ዜማ እጅግ አስፈላጊ ሆኖ እንደተገኘ በማውሳት ነው። ይህን የአንድነት መዝሙር ደግሞ ታላቁ ንጉስ ቀደም ብለው አዚመውት ነበር።

ሌላው የቴዎድሮስ ገጽታ ደግሞ ደፋር እና ጀግና መሆናቸው ነው። ቁመታቸው እስከዚህም ዘለግ ያለ እንዳልነበረ የሚገልጹት እነ ራሳም (እንግሊዛዊው የአጼ ቴዎድሮስ እስረኛ) ቁጡ፣ ደፋር፣ አገራቸውን የሚወዱ እና ፈሪሃ እግዚአብሔር ያላቸው እንደነበሩ ጽፈዋል። የንጉሱን ደፋርነትና ጀግንነት በተመለከተ ድምጻዊ ፋሲል ደመወዝ ‹‹አለ ነገር›› በሚለው ዘፈኑ ላይ ‹‹የጎንደር ወይዛዝርት ካለ የዘር ግንዱ፤ እንደ ቴዲ ያለ ምነው በወለዱ›› ሲል የንጉሰ ነገስቱን ጀግንነት ስቦ ለዚህ ትውልድ ለማውረስ ምኞቱን ይገልጻል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ከፍተኛ አመራር የሆኑት ኮማንደር ዘመነ አመሸ በበኩላቸው ‹‹የሚሊኒየሙ ጀግና፤ ያኔ ገና ሁሉም ነገር በሌለበት ሁሉም ነገር እንዲኖር የተመኘ፣ የሞከረ፣ በከፍተኛ ምኞትና ጉጉት ጥረት ያደረገ፤ የኢትዮጵያን አንድነት በፍላጎት ማምጣት በማይቻልበትና ሁሉም ተከፋፍሎ የየራሱን ጦር ይዞ በጎራው በሚፋለምበት ዘመን የአንድነትን ራዕይ ሰንቆ የታተረ እውን ያደረገ መተኪያ የሌለው የኢትዮጵያ ባለውለታ ጀግና›› ሲሉ ገልጸዋቸዋል።

ኪነ ጥበብ የዘነጋችው ንጉሥ

ኪነት ጉልበቷ ሀያል ነው። ስታነሳም ሆነ ስትጥል ታውቅበታለች። በዚህ በኩል ኢትዮጵያዊውን ንጉስ በተመለከተ ኪነት ምን አስተዋጽኦ አድርጋለች? ለሚለው ጥያቄ መልስ የሰጠው አርቲስት በምናቡ ከበደ ‹‹ታሪካቸው እንደየፀሀፊው ልዩነት ተጽፏል። በፊልም እና በቴአትር በኩል ግን እሳቸውን በትክክል የሚገልጻቸው ሆኖ አላገኘሁትም። በእርግጥ አጼ ቴዎድሮስ አምባገነን እና ጨካኝ መሆናቸው የራሱ ምክንያት እና ጊዜ ሊኖረው ይችላል። ሆኖም ልናነሳላቸው የሚገባው ክፍል ግን ሊነሳላቸው አልቻለም። ይህ የሆነው ደግሞ ስርዓቱ ይህን እንድንሰራ አልደገፈምም አላገዘምም። ምክንያቱም እንደዚህ አይነት ስራዎች በሚነሱበት ጊዜ የግለሰብ ታሪክ እንጂ የአገር ታሪክ አይመስለንም። ይህ ደግሞ ከገዥነት፣ ከጭቆና እና ዘመናዊነትን ከመጻረር ጋር የሚያስብ የፖለቲካ አስተሳሰብ ስለመጣ ስለ አጼ ቴዎድሮስ በስፋት ሊሰራ አልተቻለም። ራዕያቸውን የግል ሀብታችን አድርገን የምንጠቀምባቸው መድረኮች እስከቅርብ ጊዜ ድረስ አልነበረም›› ሲል አጼ ቴዎድሮስ በኪነት ዘርፍ በቂ ትኩረት እንዳይሰጣቸው የተደረገበትን ምክንያት ተናግሯል።

በሌላ በኩል ደግሞ ንጉሰ ነገስቱን የአንድ አካባቢ (ክፍለ ሃገር በአሁኑ አጠራር ክልል) ንጉስ አድርጎ የመውሰድ ነገርም እስካሁን በስፋት ይታይ እንደነበር የሚናገረው አርቲስት በምናቡ፤ ‹‹የእሳቸውን ትክክለኛ ስራ እና ራዕይ የሚገልጹ የጥበብ ስራዎች የሚታዩት ከአካባቢው በተለይም ከጎንደር የወጡ ከያኒያን ብቻ ናቸው። ይህ ግን ፍጹም ትክክል ያልሆነ እና የምንፈልገውን የአገር አንድነት ሊያመጣ የማይችል አካሄድ ነው›› በማለት ኪነት ለአጼ ቴዎድሮስ ንፉግ የሆነችበትን ምክንያት አስቀምጧል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
8282 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 959 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us