“ዘወልድ እና ራያን” የዘከረው ጉማ ትውፊታዊ ቴአትር በባህር ዳር

Wednesday, 25 April 2018 12:20

 

በይርጋ አበበ

ሰባ ወጣቶች መድረክ ላይ ይተውኑበታል፤ ወደ 300 ሺህ ብር የሚሆን ገንዘብ ደግሞ ለቴአትሩ የተመደበለት በጀት ነው “ጉማ ትውፊታዊ ቴአትር” የተሰራው በባህር ዳሩ “ሙሉዓለም የባህል ማዕከል” አማካኝነት ሲሆን ድርሰቱን ደሳለኝ ድረስ እና ንብረት ያለው የተባሉ ወጣቶች ጽፈውት ደሳለኝ ድረስ አዘጋጅቶታል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ቴአትሮች አዲስ አበባ ተወልደው፣ አዲስ አበባ አድገው፣ አዲስ አበባ ሞተው የሚቀበሩበት ዘመን ላይ የደረሱ ሲመስል እነሱም ቢሆኑ አብዛኞቹ ከአስር ሰው በማይበልጥ የሚተወኑ ቴአትሮች ናቸው። የትውፊታዊ ቴአትሮች ህልውና ደግሞ እየከሰመ የመጣ ሲመስል በአዲስ አበባው “ብሔራዊ ቴአትር” ብቻ የሚታዩ ሶስት ትውፊታዊ ቴአትሮች ናቸው ለእይታ እየቀረቡ ያሉት።

ትውፊታዊ ቴአትሮች ከገበያ እየጠፉ ከመጡባቸው ምክንያቶች መካከል በቀዳሚነት ሊጠቀሱ የሚችሉት ምክንያቶች “ሰፊ የሰው ሀይል እና ሰፊ የእውቀት አድማስ እንዲሁም ዳጎስ ያለ ገንዘብ የሚፈልጉ መሆናቸው” እንደሆነ ይነገራል። በዚህ የተነሳም ቴአትር ቤቶች እና አርቲስቶች ወደ ትውፊታዊ ቴአትር ከማዘንበል ይልቅ ወደ ሌሎች ዘውጎች ስለሚያቀኑ አሁን አሁን ለተመልካች የቀረቡለት ብቸኛ የቴአትር ዘውጎች እነሱ ይመስላሉ። ሆኖም ትውፊታዊ ቴአትሮች የአንድን ህዝብ እና ማህበረሰብ ባህል፣ ልምድ እና ዕውቀት ተጠብቆ እንዲቆይ ከማስቻላቸውም በላይ በሌሎች አካባቢዎች እንዲታወቁ በማድረግ በኩልም ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው።

በ2004 ዓ.ም ጥናቱ ተካሂዶ በ2005 እና 2006 ዓ.ም ድርሰቱ ተዘጋጅቶ ለአራት ዓመታት የቆየው “ጉማ ትውፊታዊ ቴአትር” በያዝነው ዓመት አጋማሽ ለመድረክ እንዲበቃ ተደርጓል። በባህር ዳር ሙሉዓለም አዳራሽ ለዕይታ የበቃውን ጉማ ቴአትርን ከእቅድ እስከ ዝግጅት ብሎም መድረክ ላይ ስላለው ተቀባይነት ቴአትሩ ደራሲ እና አዘጋጅ ደሳለኝ ድረስ በስልክ የሰጠንን አስተያየት ከዚህ በታች እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

 

 

ጉማ ስያሜውና ውልደቱ

ጉማ ቴአትር መነሻውም ሆነ መድረሻው የራያ ባህል ሲሆን ትርጓሜው ደግሞ “የደም ካሳ” ማለት ነው። ጉማ ትውፊታዊ ቴአትርም በራያ ባህላዊ የፍርድ እና የጋብቻ ስርዓት ላይ ጥናት ተደርጎ የተሰራ መሆኑን አዘጋጁ ደሳለኝ ድረስ ይናገራል። ሃሳቡን ሲያብራራም “ኢትዮጵያ ውስጥ ቴአትር አለ፤ ኢትዮጵያዊ ቴአትር ግን የለም ይባላል። እንዲህ የተባለበት ምክንያት ደግሞ አብዛኞቹ ቴአትሮች በጥናት ላይ ያልተመሰረቱ በመሆናቸው ነው። ወደ ጉማ ቴአትር ስንመጣ በ2004 ዓ.ም ነው ጥናቱን ያካሄድነው። አካባቢው የራሱ የሆነ የግጭት አፈታት ስርዓት አለው፣ ልዩ የሰርግ ስርዓት እና በርካታ ክዋኔዎች አሉት። ቴአትሩ ከፍተኛ በጀት የሚጠይቅ ከመሆኑ የተነሳ ወደ መድረክ ለመውጣት ረዥም ጊዜ ወስዶበታል” ሲል ተናግሯል። የጉማ ትውፊታዊ ቴአትር ውልደቱ በዚህ መልኩ ሲሆን ቴአትሩን ለማዘጋጀት ወደ 300 ሺህ ብር ገንዘብ እንደተመደበለት አዘጋጁ ጨምሮ ገልጿል።

ቴአትሩ በጽሁፍ መልክ ተዘጋጅቶ ካለቀ በኋላ ዓመታትን ቢያስቆጥርም በጀት የለም በሚል ምክንያት መድረክ ላይ ሳይወጣ ቆይቷል። በመጨረሻም ትኩረት ተሰጥቶት እንዲቀርብ መደረጉን አዘጋጁ ተናግሯል። በዚህ የተነሳም ተዋንያንን እና ድጋፍ ሰጪ አባላትን ጨምሮ 70 ባለሙያዎች የተሳተፉት ትውፊታዊ ቴአትር ለመድረክ እንዲበቃ መደረጉን የገለጸው አዘጋጁ ደሳለኝ፤ ቴአትሩ ከተጻፈ በኋላ ወደ መድረክ ከመውጣቱ በፊትም የማህበረሰቡን ትክክለኛ ባህል እና ማንነት ሳይበርዝ መቅረቡን ለማረጋገጥ ከራያ ምህበረሰብ የተወከሉ ምሁራን፣ የአገር ሽማግሌዎችና የዘርፉ ባለሙያዎች እንዲገመግሙት ከተደረገ በኋላ ማሻሻያ ተደርጎበት ለአደባባይ መብቃቱን ነው የተናገረው። ቴአትሩ የማህበረሰቡን ባህል የሚገልጹ ትወናዎችንና የቃላት ምልልሶችን ብቻ ሳይሆን ሙዚቃዎችን እና ውዝዋዜዎችንም ያካተተ ነው።

 

 

ዘወልድ እና እንበደዲ በጉማ

 

በራያ ቆቦ ማህበረሰብ ዘንድ ከተለመዱ የማህበረሰቡ ነባር ባህሎች መካከል የሽምግልና ባህል ነው። የሽምግልና ስርዓቱ በአካባቢው ህዝብ አመኔታ ያላቸውና ተቀባይነት ያገኙ “ስመ በጎ ሰዎች” ስብስብ ሲሆን ምርጫው የሚካሄደው ፍጹም ታማኝነትና ዴሞክራሲያዊነት በሰፈነበት መልኩ በጊዜ ገደብ የተወሰነ ነው። ይህ የሽምግልና ስርዓት ከተራ ወንጀል እስከ ነፍስ ማጥፋት ደረሱ ከባባድ ወንጀሎችን መርምሮ አጥፊውን የሚያስተምር ተመጣጣኝ ቅጣት መወሰን እና ተበዳይን ደግሞ የሞራልና የህሊና ካሳ እንዲገኝ የሚስችል ውሳኔ ማሳለፍ ነው ስያሜውም ‹‹ዘወልድ›› ይሰኛል።

ዘወልድ ከዘመነ መሳፍንት በፊት ጀምሮ ሲተዳደርበት የነበረ እና አሁንም ድረስ የሚሰራበት የተጻፈ መተዳዳሪያ ህግ ሲኖረው 27 አንቀጾች እንዳሉት የቴአትር ባለሙያው ደሳለኝ ድረስ ይናገራል። “ይህ የሽምግልና ስርዓት ከዘመናዊ ዳኝነቱ በተሻለ መልኩ ደምን በማድረቅ በኩል ፍቱን ስርዓት ነው” ያለው ደሳለኝ ድረስ፤ “የአካባቢው ማህበረሰብ በዘወልድ አምላክ ከተባለ ምንም አይነት እንቅስቃሴ አያደርግም። ዘወልድ የገባበት እርቅ ሙሉ በሙሉ መፍትሔ አለው” ሲል ስለ ዘወልድ ሽምግልና ይናገራል። ሆኖም አንዳንዴ ከማህበረሰቡ ህግም ሆነ ከመንግስታዊ ህግ የሚያፈነግጥ ሰው አይጠፋም። እንደዚህ አይነትን ሰው በተመለከተ ዘወልድ ያስቀመጠው ነገር ምን እንደሆነ ለአርቲስት ደሳለኝ ጥያቄ አቅርበንለት ነበር። አርቲስቱ ሲመልስም “ከዘወልድ ስርዓት አፈነግጣለሁ ያለ “እንበደዲ” ተብሎ ከማህበረሰቡ ይገለላል። ይህን የስነ ልቦና እና ማህበራዊ ቅጣት በመፍራትም የአካባቢው ማህበረሰብ ዘወልድን ያከብራል” ብሏል።

እንበደዲ ወይም በኢብራይስጥ ቋንቋ “የአዛዛል ፍየል” የሚባሉት ማህበረሰባዊ ቅጣቶች የሚፈጸሙት ሰዎች በማህበረሰቡም ሆነ በህሊና ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው ከህዝቡ እንዲገለል የሚጠቀሙበት ቃል ነው። በራያ ቆቦ ማህበረሰብ የዘወልድን ስርዓት ህዝቡ ከተላለፈ “እንበደዲ ወይም የአዛዘል ፍየል ተብሎ ከማህበረሰቡ ተገልሎ እንዳይቅበዘበዝ” ስለሚፈራ ዘወልድን ያከብራል። እንደ አርቲስት ደሳለኝ አነጋገር ከሆነ ዘወልድ ላይ እንበደዲ ሆኖ ያስቸገረው መንግስታዊው የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ነው። የወንጀለኛ መቅጫ ህግ በዘወልድ ላይ በምን መልኩ ሊያምጽ እንደቻለ ላቀረብንለት ጥያቄ ሲመልስም “ጥፋተኛ ተብሎ በዘወልድ የተቀጣ ሰው በማህበረሰቡ ህግ መሰረት ከጥፋት ነጻ ሆኖ ወደ ሰላማዊ ኑሮው እንዲቀላቀል ይደረጋል። ለምሳሌ በደምፍላት ሰው መግደል (ቀይ ደም ያፈሰሰ) ሰው 60 ሺህ ብር እንዲቀጣ ሲደረግ ሆን ብሎ አቅዶ እና አስቦበት ሰው የገደለ (ጥቁር ደም ያፈሰሰ) ደግሞ 80 ሺህ ብር ለሟች ቤተሰብ ይከፍላል። ክፍያው የሚፈጸመው ግን ዝም ብሎ በአንድ ጀምበር ሳይሆን ነፍስ ያጠፋው ሰው ለአንድ ዓመት ከአካባቢው እንዲጠፋ ይደረግና በገዳይና በሟች ቤተሰብ መካከል ቅድመ እርቅ (ረጃት) ተፈጽሞ ከተስማሙ በኋላ ነው። በዚህ መሰረት ቅድመ እርቅ (ረጃት) ከተፈጸመ በኋላ ጥፋተኛው ቅጣቱን ተቀብሎ ደም ላለመቃባት ተማምለው ወደ ሰላማዊ ኑሮው እንዲገባ ይደረጋል። ይህ ከሆነ በኋላ ግን የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ይመጣና እንደገና ጥፋተኛ ብሎ ይከሰዋል። ጥፋተኛ የተባለው ሰውም በአንድ ወንጀል ሁለት ጊዜ ይቀጣል። በዚህ የተነሳ ዘወልድ እንዳይከበር እንቅፋት ሆኖብናል ሲሉ የአገር ሽማግሌዎች ይናገራሉ” በማለት ነበር የገለጸው።

መንግስታዊ ህግ ሲቀረጽ የማህበረሰቡን እምነት፣ ባህል፣ ልምድ እና አኗኗር ታሳቢ ያደረገ መሆን እንዳለበት ይታመናል። ሁለቱ ተጣምረው ለህብረተሰብ ለውጥ እንዲያመጡም ሊፈጸሙ የሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎች አሉ። ይህ ባህል ግን በራያ ቆቦ ማህበረሰብ ዘንድ ተግባራዊ አለመደረጉ የዘወልድ ሽማግሌዎችን እያስከፋ ይገኛል።

 

 

ጉማ እና ዱበርቴ

እንደማንኛውም ህዝብ የራያ ህዝብም የራሱ የሆነ የሰርግ ባህል እና ስርዓት አለው። የሰርጉን ስርዓት በተመለከተ በጉማ ትውፊታዊ ቴአትርም የተዳሰሰ ሲሆን እንደ አዘጋጁ ገለጻ የራያ ሰርግ ስርዓት ከመተጫጨቱ ሂደት ጀምሮ በቴአትሩ ተዳሷል። ራያዎች የወደፊት ውሃ አጣጫቸውን የሚመርጡባቸው መንገዶች ብዙ ሲሆኑ ዋና ዋናዎቹ ወላጆቻቸው ሲያጩላቸው እና የሶለል ጨዋታ ይጠቀሳሉ። እጮኞቹ ተፈላልገው ወደ ትዳር ከማምራታቸው በፊት የሚፈጸም የ‹‹ጥፍር መቁረጥ›› ስነ ስርዓት ደግሞ ሌላው ትኩረት ሳቢ ክስተት ነው። ሙሽሮቹ በከብቶች በረት ውስጥ ጥፍራቸውን የሚቆረጡ ሲሆን የጥፍር መቁረጥ ስነ ስርዓቱ የሚከናወነው እግራቸውን ወተት ውስጥ በመንከር ሲሆን ጥፍር የምትቆርጠው ሴት ደግሞ ወይ ገና ትዳር ያልያዘች መሆን አለበለዚያ ደግሞ ትዳር መስርታ ትዳሯ የሰመረላት ልትሆን ይገባል።

በዚህ መልኩ ወደ ጋብቻ የሚመሩ ጉብሎች በዱበርቴዎች ይመረቃሉ። ዱበርቴ ማለት ደግሞ በአካባቢው ማህበረሰብ ተሰሚነት ያላቸው ግብረ መልካም ዕድሜ ጠገብ ሴቶች ሲሆኑ ሙሽሮቹን ‹‹ወረሃቡል›› እያሉ ትዳራቸው እንዲሰምር፣ አዱኛ ከቤታቸው እንዳይርቅ እና ሰላም እንዲበዛላቸው ይመርቃሉ። ምርቃቱ የሚፈጸመው ደግሞ በ‹‹ቆቴ›› ሲሆን ቆቴ ማለት ደግሞ ዱበርቴዎቹ ከእጃቸው የማይለዩት አጭር በትር (በትረ ሙሴ ልንለው እንችላለን) ነው። በጉማ ትውፊታዊ ቴአትር ትኩረት ተሰጥቶት ለዕይታ ከሚቀርቡ የቴአትሩ ክስተቶች መካከል አንዱ ይህ ነው።

በራያዎች የጋብቻ ባህል መሰረት ‹‹ስር ሚዜ›› በከተማ አጠራር (የወንዱ አንደኛ ሚዜ) ሙሽሮቹ ከተጋቡ በኋላ ለአንድ ወር አይለያቸውም። በወጡበት ወጥቶ በገቡበት እየገባ እነሱን ሲያጅብ ይከርማል። ልብሳቸውን የሚያጥበውም እሱ ይሆናል። ምናልባት ከአቅም በላይ የሆነ ስራ ቢያጋጥመው እንኳን ሁነኛ ሰው ወክሎ ይሄዳል እንጂ ሙሽሮቹን እንዲሁ ተለይቶ አይሄድም።

ሌላው ከራያ የጋብቻ ስርዓቶች መካከል ሳይጠቀስ የማያልፈው የ‹‹አበይር›› ተግባር ነው። አንድ ሰው ሰርግ ሲያሰርግ ወጭው ከባድ እንደሚሆን ይጠበቃል። በዚህ የተነሳም ከሰርጉ ማግስት በኢኮኖሚ ቀውስ ጋብቻው ቀውስ ውስጥ እንዳይወድቅ የአካባቢው ማህበረሰብ ለሙሽራው የገንዘብ ወይም የንብረት ድጋፍ ያደርጋሉ ይህም አበይር ይባላል። አበይር ከሌሎች ባህሎች ለየት የሚያደርገው ድጋፍ የሚያደርገው ሰው የሚሰጠውን የገንዘብም ሆነ የንብረት መጠን በስውር ሳይሆን በግልጽ በአደባባይ የሚናገር መሆኑ ነው።

እንደ አርቲስት ደሳለኝ እምነት በዚህ ዘመን ለቴአትር የሚሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆኑን ተከትሎ ዘርፉ እየተዳከመ መሆኑን ተናግሯል። ለዘርፉ ትኩረት ከተሰጠው ግን በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ያሉ ቱባ ባህሎችን ጥናት እያደረጉ ወደ ህዝብ በማቅረብ የኢትዮጵያን ባህል እና ታሪክ ለትውልድ ማስተላለፍ ይቻል ነበር። ለዚህ ደግሞ መንግስት የአንበሳውን ድርሻ ወስዶ የቤት ስራውን ሊሰራ እንደሚገባው መልእክቱን አስተላልፏል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
8216 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1034 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us